October 31, 2010

“ሰውየውን” ታዲያ ማን እንበላቸው?

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 31/2010፤ ጥቅምት 21/2003 ዓ.ም):- አስተያየት የሰጣችሁ ብዙ አንባብያን ከሰጣችሁት በመነሣት ይህንን አጭር ሐሳብ እናቀርባለን። አሁን ከገባንበት ንዴት፣ ሐዘን፣ ቁጭት እና አንዳንዴም ቀቢጸ ተስፋ አንጻር ብዙ ነገር ልንናገር እንችላለን። ምናልባትም “ዳን” የተባሉ ደጀ ሰላማዊ እንዳሉት “ስማቸውን አንስማ፣ ፎቷቸውን አንይ” ልንል እንችላለን። ያ ግን መልስ አይደለም። አንድ አንባቢ “ብፁዕ ወቅዱስ አትበሏቸው” ብለዋል። በዚሁ አጋጣሚ ስለዚህም መናገር ይገባናል።
በቤተ ክርስቲያናችን “ብፅዕና እና ቅድስና” ሁለት መልክ አለው። በገድል በትሩፋታቸው፣ በጽድቅ ሥራቸው ሀገር አውቆላቸው፣ ፀሐይ ሞቆላቸው፣ ጸጋ በረከታቸው ከሰውነታቸው ተርፎ ለልብሳቸው፣ ለምድራቸው፣ ለገዳማቸው የተረፈላቸው አበው እና እመው “ብፅዕና እና ቅድስና ይገባቸዋል” ና ብፁዓን ቅዱሳን እንላቸዋለን።

ሁለተኛው የዚህ አገባብ መጠቀሚያ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ለምትሾማቸው የበጎቿ እረኞች የምትሰጠው “የክብር ስም” ነው። እነዚህም ኤጲስ ቆጶሳት ናቸው። እነርሱንም “ብፁዕ አቡነ” ለአንድ ሰው፤ “ብፁዓን አበዊነ ሊቃነ ጳጳሳት” (ለብዙ) ብለን እንጠራቸዋለን። ከነዚህ “ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት” መካከል አንዱን የእነርሱ አለቃ (ፓትርያርክ) ስንለው ለእርሱም “ብፁዕ ወቅዱስ” በሚል ስያሜ እንጠራዋለን። “ብፅዕናውም ሆነ ቅድስናው” የሚሰጠው ወይም “ብፁዕ ወቅዱስ የሚባለው” ስለያዘው ሥልጣንና የአገልግሎት ወንበር እንጂ ስለሠራው ገድል እና ትሩፋት አይደለም።

በአጭር አነጋገር ለምሳሌ አቡነ ፋኑኤልን “ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል” ወይም አቡነ ጳውሎስን ደግሞ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ” የምንላቸው ስለ እነርሱ ማንነትና ሕይወት ሳይሆን ስለተቀበሉት መንፈሳዊ ሥልጣን ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን በሚሠሩት ሥራ ቤተ ክርስቲያንን እየጎዱ መሆናቸውን ብናውቅምና በአደባባይ ብንቃወማቸውም  ሌላ ጥፋትና ስሕተት እንዳይሆን አንዳንዶች እንደሚሉት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን “አባ መላኩ”፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ደግሞ “አባ ገ/መድን” አንላቸውም። ፀያፍ ነው። ኦርቶዶክሳዊም አይደለም።

ይሁን እንጂ አንድ ቀን ቅ/ሲኖዶሱ በሁለት እግሩ ቆሞ፣ በራሱ ሕግ መሠረት ቅዱስ ፓትርያርኩን በተመለከተ ውሳኔ ቢያሳልፍ እና “ብፁዕ ወቅዱስ ሊባሉ አይገባም” ቢል ያን ጊዜ እኛም “አባ ገ/መድኅን” እንላቸዋለን። እስከዚያው ግን እየተቃወምናቸው ነገር ግን ““ብፁዕ ወቅዱስ” ማለታችን ይቀጥላል። አንድ ጥሩ ለመሥራት ተነሥተን ሌላ ጥሩ ነገር ማጥፋት የለብንም። “ወደ ገነት ለመሔድ ወደ ሲዖል ጎራ ማለት” እንዳይሆንብን። ጥሩ ለመሥራት ዘዴውም ጥሩ መሆን አለበት። አለበለዚያ ሃይማኖት መሆኑ ይቀርና “የሀገራችን የመበላላት ፖለቲካ” ይሆንብናል።

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን    
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)