October 28, 2010

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ" በ20 ቀናት ውስጥ እንዲፈርስ ትእዛዝ ተሰጥቷል፤ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ “አዲስ አበባን አልፈልግም” እያሉ ነው

  • አቡነ ጳውሎስ በውሳኔው ላይ ላለመፈረም እያንገራገሩ ነው፤
  • አቡነ ቀውስጦስ ሐላፊነቱን ለመቀበል መቸገራቸው እየተነገረ ነው፤
  • "ካልሆነ አቡነ ሳሙኤል ወደ ቦታቸው ይመለሱ" (ሌሎች ብፁዓን አባቶች)
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 28/2010፤ ጥቅምት 18/2003 ዓ.ም):- ከተጀመረ ስድስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው የከሰዓት በኋላ ቆይታው ከአንድ ዓመት በላይ በእንጥልጥል በቆየው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጉዳይ ለሹመት ከቀረቡለት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት (የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ የምሥራቅ ሐረርጌ እና ሶማሌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ) መካከል ለብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ 22 የድምፅ ድጋፍ፣ ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል 14 የድምፅ ድጋፍ በመስጠት ምርጫ ማካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከ40 ያላነሱ ሊቃነ ጳጳሳት ከሰጡት ድምፅ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አብላጫ ድምፅ በማግኘታቸው ብዙዎች ደስታቸውን ገልጸውላቸው ነበር፡፡


ይሁንና ዕጩ ሆነው ከመቅረባቸው አንሥቶ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹ የቆዩት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ብዙ ወገኖች በተለያዩ መንገዶች ለማግባባት ቢጥሩም በአቋማቸው እንደ ጸኑ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው ፈቃደኛ ያልሆኑባቸው ምክንያቶች ለጊዜው በዝርዝር ባይታወቁምየተለያዩ መላምቶች ሲሰጡ እየተሰማ ነው፡፡ ሁኔታው ስጋት ያሳደረባቸው ሌሎች ብፁዓን አባቶች ቦታውን ብፁዕነታቸው ቦታውን የማይዙት ከሆነ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እንዲመለሱበት እንደሚሹ መናገራቸውን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና ቅዱስ ሲኖዶሱ ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ ውሎው የአቡነ ጳውሎስ ሐውልት እንዲፈርስ ውሳኔ ያስተላለፈ ቢሆንም ፓትርያርኩ ውሳኔው በሰፈረበት ቃለ ጉባኤ ላይ ላለመፈረም እያንገራገሩ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ለመንበረ ፓትርያርኩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚያስረዱት አቡነ ጳውሎስ "ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እና ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አሠርተዋቸዋል" ያሏቸውን ሐውልቶች እንደ አስረጅ በመጥቀስ በነገው ዕለት ቃለ ጉባኤው ለፊርማ ሲቀርብ ለመሟገት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁኔታውን የታዘቡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች "ፓትርያሪኩ የስብሰባውን የመጨረሻ ቀን በመጠበቅ ሙግቱን ለማንሣት ማሰባቸው ተንኮል እና ፈሊጥ እንዳለበት ያሳያል" ብለዋል፡፡ ይህን የፓትርያርኩን ዝንባሌ የተረዱት ብፁዓን የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሐውልቱን "በኻያ ቀናት ውስጥ እንዲያስፈርሱ ትእዛዝ አስተላልፈዋል" ተብሏል፡፡

በ1991 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ስምንት ንኡስ አንቀጽ ሁለት መሠረት ፓትርያርኩ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ በአንቀጽ 15 ንኡስ አንቀጽ አንድ ላይ እንደተመለከተው ደግሞ ፓትርያርኩ "በተሰጠው ሐላፊነት መሠረት ሃይማኖትን እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፤ ያስጠብቃል" ይላል፡፡ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 16 ንኡስ አንቀጽ 1/ሀ መሠረት ፓትርያርኩ የተቀበለውን ሐላፊነት በመዘንጋት "የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣ ይህም በትክክል ከተረጋገጠ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከሥልጣኑ" እንደሚወርድ ይደነግጋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)