October 31, 2010

ይድረስ ለቅዱስነትዎ

ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከዓመታት በፊት በአውሮፓ አንድ የኦርቶዶክሶች ኔትወርክ አባል ሆኜ የሁለት ቀናት “በጎ አመራር” ላይ ያተኮረ ውይይት ለማድረግ ተሰባስበን ነበር። የቡድን ውይይት ወቅት ሁለት ሁለት ሆነን ተመደብንና የምንወያይበት ርዕስ ተሰጠን። አቀማመጣችን ጀርባ ለጀርባ ተነካክተን መቀመጥ ሲሆን። “ለጥፈው” (Post-It) ከብዕር ጋር ተሰጥቶናል። በሕይወታችን የምንኮራበትና አርአያ የምናደርገው በጎ መሪ (በመንፈሳዊው ዓለምም ሆነ ከዛም ውጪ) ከተቀመጥንበት ሆነን በየግላችን ማሰብ እና የተሰጠን “ለጥፈው” ላይ ስሙን መጻፍ። ከዛ ስሙን ለይተን እንደጻፍን መጨረሳችንን  ከተናገርን በኋላ ፊት ለፊት እየተያየን እያንዳንዳችን የመረጥነው በጎ መሪ ማንነትና ምንነት እና ለምን በጎ ብለን እንደመረጥነው መወያያት። ከዛም ሁለታችን የተወያየንበትን የበጎ መሪ መገለጫዎች ለቤቱ በየተራ ማቅረብ። አንዱ የመረጠውን ከነመገለጫው የሚያቀርበው አብሮት የተመደበው ተወያይ ነበር።

በዚህ መሠረት እኔም በዕድሜ ከኔ እጅግ ከምታንስ በውጭ አገር ተወልዳ ካደገች ግብጻዊት ኦርቶዶክሳዊት ብላቴና ጋር ተመደብኩ። ጀርባ ለጀርባ ተቀመጥን። አሰበች። አሰብኩ። ለኔ ከባድ ነበር። “ማን ነው አርአያ የማደርገው በጎ መሪ?” …… ከመንፈሳዊውም ዓለም ውጪ ቢሆን” ተብሏል።  አማራጮቹን ለማስፋት ነበርና ሳቡ ደግ  ነበር።  ነገር ግን “ከመንፈሳዊውም ሆነ ከመንፈሳዊው ዓለም ውጪ ማንን ነው እንደ በጎ መሪ የማየው? ለምን የሚለውንስ እንዴት ነው ቅር ሳይለኝ የማብራርው?” የሚለው ሀሳብ አናወዘኝ። አሰብኩት። ከባድ ፈተና።  በተቃራኒው በኋላ እሷ ስትናገር እንደተረዳሁት ለግብጻዊቷ ብላቴና ጥያቄው ቀላል ነበር። መልሱ አብሯት የሚውልና የሚያድር፤ ስታስበው ደስ ብሏት፤ ስትናገረው ደስ ብሏት፤ ስትጽፈው ደስ የሚላት መልስ ነበራት።

ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ
“ጨረስክ?” አለችኝ። የሞት ሞቴን “አዎ” አልኩኝ። በተሰጠኝ ጊዜ መልሱ ማግኘት ከከበደኝ አዲስ በጎ መሪ በዛ ቅጽበት አልፈጥርምና ነው “አዎ ማለቴ እንጂ ፍጹም መልስ ይዤ አልነበረም። ፊታችን አዙረን ፊት ለፊት እየተያየን በየመልሳችን ዙሪያ ማውራት ጀመርን። ቅድሚያውን እኔ ወሰድኩ። በጎ መሪ የምለው ሰው የሙያ መስክ አቻዬ በልምድ አንዳች የሚያህል ስብዕና ያለው እገሌ የተባለ ኢትዮጵያዊ የኬሚካል መሐንዲስ እንደ በጎ መሪ የማየው መሆኔን ያየሁበትም  መገለጫዎች ትጋቱ፤ ብቃቱ፤ አሳታፊነቱ፤ ቅንነቱ ወዘተነቱ መሆናቸውን አስረዳሁ ወይም ለማስረዳት ሞከርኩ (በበጎም ቢሆን ስሙን እዚህ መጥቀስ አልፈለግኩም ግን አንድ የመመረቂያ ጽሑፌ መታሰቢያነቱ ለእሱና ለአያቴ ያደረግኩት ስለሆነ ስሙ ከዛ ይገኛል)። ውይይታችን መንፈሳዊ ነክ እንደመሆኑ መጠን መንፈሳዊ መሪ ብጠቅስ ምንኛ ደስ ይለኝ ነበር።

ወደሷ መልስ ገባን… የእሷ በጎ መሪ ማንነት ለመግለጥ ገና ስታስብ ሰውነቷ ውስጥ ሌላ ብርሃን የተለኮሰ እስኪመስል ድረሰ ገ ሁሉ አበራ። በጣም ጣፍጧት የበላቸውና አሁን ድረስ ጣዕሙ ከምላሷ አልወጣ ያላት ግሩም ምግብ ስም ለመናገር የምትንሰፈሰፍ ነበር የምትመስለው። ጉጉቷ የራሴን የበጎ መሪ ጉድለት አስረስቶኝ የበጎ መሪዋን ስም ምላሷ ጥርሷና ከንፈሯ  መሐከላቸው አስቀምጠው እንዴት ብለንና በምን ቅላጼ እናውጣው እያሉ ሲወያዩ ያየሁ እስኪመስለኝ ድረስ ስሙን ከመከላቸው የመፈለግ ያህል አፍ አፏን እያየሁ ሳለ “አቡነ ሺኖዳ” የሚሉት ሁለት ቃላ ገና ከመሰማታቸው  ተሸማቅቃ የቆየችው ነፍሴ  ወዲያው ከመቅጽበት “I knew it” ስትል የሌላ ሰው ነፍስ እስክትመስለኝ ድረስ በኃይል ነበር። 

ብላቴናይቱ ስለ አቡነ ሺኖዳ በጎ መሪነት ማብራራት ያዘች። እኔ እና ነፍሴ ደግሞ ከላይ እስከታች ከሞላ ጎደል ጆሮ ብቻ ሆነን ማዳመጥ ያዝን። በመሐል እኔ እና ነፍሴ በብላቴናይቱ የአቡነ ሺኖዳ ድርብ-ሰረዝ ጠገብ የበጎ መሪነት ማብራሪያ ጣፋጭነት ምራቃችንን እየዋጥን አዳመጥን አዳመጥን አዳመጥን።  እሷ አውሮፓ ተወልዳ አድጋ በደረሰችበት መንፈሳዊም ሆነ ከዛ ውጪ ባለው ዓለም የማያወላዳ የበጎ መሪ መገለጫ መስፈርቶቿን ጢቅ አድገው ያሟሉላት የሚልዮኖች ምእመናን አባት የሆኑት አቡነ ሺኖዳ ሆኑ። እኔ ደግሞ በደረስኩበት መንፈሳዊም ሆነ ከዛ ውጪ ባለው ዓለም ልጠቅሰው የቻልኩት በጎ መሪ ከሁለት መቶ የማይበልጡ አባላት ያሉት የሙያ ማኅበርን ሲመራ ያየሁት አንድ ኬሚካል መሐንዲስ ሆነ። አዬ ርቀት! አዬ ልዩነት!

ይሄ ከሆነ ከዓመታት በኋላም ያ ውይይት እንደገና ዛሬ ይህን ጽሑፍ በኮምፒዩተር ሰሌዳ በምከትበት ጊዜም ቢሆን ቢደገም የእሷም መልስ የኔም መልስ የመቀየር ዕድሉ ኢምንት መሆኑን ሳስብ ምስኪንነቴን ያጎላብኛል።

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ሆይ!
ያ ውይይት በሚደረግበት ወቅት በእናት ቤተ ክርስቲያኔ የአቡነ ሺኖዳ አቻ ቦታ የያዙት ቅዱስነትዎ ነበሩ። ዛሬም በዛው ቦታ የሚገኙት ቅድስነትዎ ነዎት። ታዲያ ያኔም ዛሬም ለምን የቅዱስነትዎ ስም አልመጣልኝም? አዎ ከዓመታት በኋላ ዛሬም መልሴን ሊቀይር የሚችል ነገር መጥፋቱ ያማል (“ማ”ን ጠበቅ)። ከሰሞኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አንጻር ነገ ተነገወዲያ እግዚአብሔር ቢፈቅድ ለበጎ መሪ ጥያቄ የሚኖረኝ መልስ ሊቀይር የሚችለውን ነገር ምን እንደሆነ ሳስበው ከቅዱስነትዎ የሚከተሉት ፫ት ነገሮች በሚታይ በሚዳሰስና ብሎም በሚሰማና በሚጨበጥ መጠን እጠብቃለሁ - እንደ ምእመን፡

፩ኛ) እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ደስ በሚያሰኝ በሚያከብር አካሄድ መቃኘት
ለምሳሌ- ለእግዚአብሔር ቤት የሚተጉትን አገልጋዮችን ምክር በመስማት፤ መንፈሳዊነት በቤተ ክህነት ሞልቶ ለቤተ ሕዝብና ለቤተ መንግሥት እንዲተርፍ ወሳኝ ሚና በመጫወት ሊገለጽ የሚችል፤

፪ኛ) “አባቶቼ” እያሉ የሚጠቸውን ብዓን አባቶችን የማክበርና የመስማት አሠራር መተግበር
ለምሳሌ - በአስተዳደርና በፋይናንስ በሀገረ ስብከት ጉዳዮች ላይ ያሉትንና በማናቸውም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች አካሄድና አፈጸጻም ላይ በሚጫወቱት በጎ ሚና ሊገለጽ የሚችል፤

፫ኛ) የምእመናን መንፈስ የሚያረካና የሚያስደስት ድባብ መፍጠር
ለምሳሌ-  ምእመናንን ወደ መንፈሳዊነት የሚያስፈነጥርና በሕይወት የሚገለጽ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፋት፤ ከፍቅረ ንዋይና ከሥጋዊ እንቶ ፈንቶ የጸዳ ተናፋቂና “ባየሁት፤ በሰማሁት፤ በነካሁት” የሚያሰኝ የአባትነት መንፈስ በመፍጠር ሊገለጽ የሚችል

የሰሞኑ የሲኖዶስ ውሳኔዎች ላይ ቅዱስነትዎ ተጫወቱት የተባለው ሚና እና በመጨረሻም ከመግለጫው ጋር ተያይዞ እየሆነ ያለው ነገር ሲታይ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሦስት ነጥቦች በቅዱስነትዎ በኩል የተዘነጉ ለመሆናቸው አስረጂዎች ናቸው።
ከኔ በፊት የነበረው ትውልድ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄድም ነበር ብቻ ሳይሆን አያምንም ነበርና ትውልዱና ቤተ ክርስቲያን ተራርቀው ቆይተው ነበር። ዛሬ ደግሞ የኔ ትውልድ በየመሰለውና በቻለው መንገድ  ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርቦ እየታየ ነው። ይሁንና ዛሬ በግዘፍ ቤተ ክርስቲያንን የምትወክሉ አበው ለዚህ ትውልድ ፍላጎትና ጥረት የምትመጥኑ አልሆናችሁምና ዛሬም እንደትንቱ ለቤተ ክርስቲያንና ለትውልዱ የመራራቅ ምክንያቱ እንጂ ርቀቱ አልተለወጠምና  ነፍስን እጅግ ያሸማቅቃል።

ለዚህ ሁሉ መስተካከል በእግዚአብሔር ፈቃድ በመንበሩ ያሉት ቅዱስነትዎ ወሳኝና አይተኬ የሆነ በጎ ሚና ሳይዘገዩ መጫወት ከቻሉ ጌታችን በወንጌሉ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነችእንዳለው በአሁኑ ሰዓት የበርካታ ምእመናንን ነፍስ እጅግ እያሳዘነ ያለውን ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ቸርነት መቀልበስ ይቻላል። 
ይህ ሆኖ የበጎ መሪ መልሴ የተቀየረ ዕለት….. “ለማለት የፈለግሁት ቅዱስ ፓትርያርኩን ነበር” ብዬ ለማረም…… ያቺን ብላቴና  ፍለጋ ሩቅ እጓዝ ይሆናል።

 ከደጀ ሰላም

 ዶ/ር ጌታቸው ካናዳ በሚገኘው በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካልጋሪ ተባባሪ ፕሮፌሰርና ቼይር ናቸው።ይድረስ ለደጀ ሰላም ጸሐፊዎች አስተያየት ሰጪዎች

ዶር ጌታቸው አሰፋ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)
በዚህ መጦመሪያ ሰሌዳ የሚወጡት አንዳንድ ጽሑፎችና አስተያየቶች ይዘት መንፈሳዊ ባልሆነ መንገድ መንፈሳዊ ነገርን ለመሥራት የመሞከር ያህል እግዚአብሔር ደስ የማይሰኝባቸው ነገሮች ናቸውና ቢታረሙ መልካም ነው። አለበለዚያ እንዲሆን የምንፈልገውና እንዲሆን የምንሠራለት ነገር እንዳይለያይ ያስፈራል - በእግዚአብሔር ዓይን ሲታይ። ይሰውረን! አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)