October 28, 2010

ይድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤ ስለ ብፁዕ አቡነ አብርሃም 2 መግለጫዎች

የሚከተሉት ሁለት ጽሑፎች በዲሲ እና አካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፤ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት እና የምዕመናን ተወካዮች፤ እንዲሁም አንድ ፍቅሩ አበበ የተባሉ ሌላ ምእመን በግላቸው የጻፏቸው ናቸው። እንደታነቡ እንጋብዛለን። በጽሑፎቹ የተገለጹት ሐሳቦች በሙሉ የፀሐፊዎቹ እንጂ የደጀ ሰላም አቋም ሆነ አስተያየት አይደሉም። ደጀ ሰላም ቀደም ባለው “ርእሰ አንቀጿ” መልእክቷን ማስተላለፏ ይታወሳል።
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።
ደጀ ሰላም
             
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት  
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የጸሎታችሁ በረከት ትድረሰን እኛ በዲሲና አካባቢው የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፤ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮችና የምዕመናን ተወካዮች ረቡዕ ጥቅምት 17 ቀን  ባደረግነው አስቸኳይ ስብሰባ ለብፁዓን አባቶቻችን የሚከተለውን ተማጽኖ ስናቀርብ በታላቅ ትህትና ነው፡፡ ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 12 ቀን 2003 .. የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን እያሳለፈ መሆኑን በአንክሮ እየተከታተለን ነው፡፡ ጥቅምት 17 ቀን በጳጳሳት ዝውውር እና ምደባ ላይ በቅዱስ ፓትርያርኩ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም መካተታቸውን በመረዳታችን ይህን የተማጽኖ ደብዳቤ ለብፁዓን አባቶቻችን ለማቅረብ ተገደናል፡፡

ብፁዕ አባታችን አቡነ አብርሃም የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሁነው ከተመደቡበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ ሀገረ ስብከቱን ለማጠናከር ይህ ነው ተብሎ በቃላት ለመግለጽ የማይቻል መስዋዕትነትን ከፍለዋል አሁንም እየከፈሉ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በሀገረ ስብከቱ ተመድበው ለሚመጡ ብፁዓን አበው ማረፊያ ቤት ማለትም መንበረ ጵጵስና ባለመኖሩ ሀገረ ስብከታቸው ከነበረው ከኒውዮርክ ድረስ በህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ እየተመላለሱ  በዲሲና አካባቢው ያሉ ምእመናንን በማስተባበር የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት መነበረ ጵጵስና እንዲኖረው አድርገዋል፡፡

ወደ ዲሲና አካባቢው ከተዘዋወሩም በ=ላ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንን በመትከል በደሲና አካባቢው ያሉ ምእመናንን ትክክለኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና በሚፈቅደው መልኩ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ለህዝበ ክርስቲያኑ ዘወትር እሁድ ትክክለኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን እምነትና ሥርዓት ምን እንደሆነ እያስተማሩ ምእመኑ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ ሥርዓትና እምነት ግንዛቤ እንዲያገኝ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ቀድሞ የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ግዜ እንዲሁም ወደ ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከተዘዋወሩ በ=ላ ከሰሩዋቸው ዓበይት ተግባራት መካከል፤-

  • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የታቀፉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡ የቺካጎ ሚካኤል፤ የኦሀዮ ገብርኤል፤ የሳውዝ ዳኮታ ኪዳነ ምሕረት፤ የአትላንታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፤የኖርፎልክ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ፤የቨርጂንያ ረጉኤል ፤የኖርዝ ካሎራይና በዓታ ለማርያም፤የኬንታኪ ገብርኤልና የሜንፊስ ቅድስት ማርያም ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
  • እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ገለልተኛ የነበሩ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናንንና የቦርድ አስተዳደሮችን ባላቸው የማግባባት ተሰጥኦ ቀርበው እውነታውን ገልጠው በማስታወቅ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲገቡ አድርገዋል እያደረጉም ይገኛሉ ለምሳሌነት ኦክላሆማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ና የኖርዝ ካሮላይና እግዚአብሄር አብ ይጠቀሳሉ፡፡
  • ፈርሶ ሊወድቅ ደርሶ የነበረውን የኒዎርክ ሀገረ ስብከት ሕንጻ ራሳቸው እንደ አንድ ሰራተኛ በመሆን ልዩ አድርገው በማሳደስ፤
  • በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በካህናትና በምእመናን መካከል አለመግባባት ሲፈጠር ፈጥኖ በቦታው በአካል ተግኝተው መፍትሄ በመስጠት፤
  • በሰንበት ት/ቤት አንድነት ጉባኤያት በመገኘት ወጣቱ ለቤተክርስቲያን አንድነት እንዲቆሙ በማድረግ፤
  • በገለልተኝነት ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን በተለያያ ግዜ  ለውይይት በመጋበዝ ወደ መስመሩ እንዲመጡ ጥሪ በማድረግ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፦

በሰሜን አሜሪካ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑ ከእናንተ አባቶቻችን የተሰወረ አይደለም ከዛሬ አራትና አምስት ዓመት በፊት ካለው አሁን ያለው ለውጥ ከፍተኛም ቢሆንም ለዚህ ለውጥ መምጣት ደግሞ ፋና ወጊ የሆኑት ብፁዕ አባታችን አቡነ አብርሃም መሆናቸውን ስንመሰክር በልበ ሙሉነት ነው፡፡ ሥራው ተጀመረ እንጂ አልተገባደደም። ገና ብዙ መስዋዕትነትን ይጠይቃል። በዲሲና አካባቢው ያለን ካህናትና ምዕመናን በብፁዕ አባታችን መሪነት ሀገረ ስብከቱን ለማደራጀት፤ የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት እንዲሁም በአስተዳደር ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለዩትን ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር የሚመጡበትን ሁኔታ በማጠናከር ላይ ሳለን ይህ አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ዜና በመሰማቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የሆነውን ሁሉ አሳዝኖናል፡፡

ስለዚህ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በአርቆ አሳቢነታችሁ ተረድታችሁ ብፁዕ አባታችን የጀመሩትን ሥራ ይፈጽሙ ዘንድ ባሉበት ሀገረ ስብከት እንዲቆዩ በትህትና እናመለክታለን፡፡

ቡራኬያችሁ አይለየን፡፡  

በዲሲና አካባቢው የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፤ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት እና የምዕመናን ተወካዮች
ጥቅምት 17/2003 ዓ.ም

++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

ከግራ ወደ ቀኝ ብፁዓን አበው ኤዎስጣቴዎስ፣ ዘካርያስ እና አብርሃም (ሊቃነ ጳጳሳት ዘአሜሪካ)
ይድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት  

(ፍቅሩ አበበ የተባሉ ደጀ ሰላማዊ እንደጻፉት)                               

ይህን ጽሁፍመጻፍ ያነሳሳኝ በዛሬው ዕለት በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በፓትርያርኩ አቅራቢነት ስለጳጳሳት  የሀገረ ስብከት ዝውውር በተመለከተ በይደር አጀንዳ የተያዘውን የተመለከተ ነው  ነው። ስለጳጳሳት ሲመትና ዝውውር በተመለከተ የቤተ ክርስቲያን ሕግ የሆነው ፍትሐ ነገስት በሚገባ በሥርዓቱ ዝርዝር አድርጎ አስቀምጦታል። አንድ ሊቀ ጳጳስ ለቤተ ክርስቲያን አግልግሎት ሲሾም  ክርስቶስ የሞተላቸውንና ደሙን ያፈሰሰላቸውን በጎች ያለምንደኝነት ጠባይ እንዲጠብቅ ነው። ይህም ክርስቶስ «አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር» እንዲል እርሱም ቸር ጠባቂ መሆን ይጠበቅበታል። ምንደኛና ቅጥረኛ ከሆነ ግን ኃላፊነቱን በሚገባ  አይወጣም።ሞያተኛ ስለሆነ  ለሥጋው ድሎት ፈልጋል። ቦታም ያማርጣል የተሰበሩትን ለመጠገን የባዘኑትን  አይፈልግም። ለእርሱ ተራራውን መውጣት አቀበቱን መውረድ ሞት መስሎ ይታየዋል።ቤተ ክርስቲያን የእንደነዚህ አይነት ምንደኛ  እረኛች እንዳትሆን  ወደቤተ ክርስቲያን  ላይ የሚሰየሙ ኤጲስ ቆጳሳት ላይ ጥንቃቄ መደረግ ነበረበት ያ ሳይሆን ቀረና ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኝ ችግር ላይ ለመውደቅ ችላለች። ይህም የዛሬው የሲኖዶስ ስብሰባ በገሃድ እንዲታይ ካደረጉት ውስጥ፥

የዚህ ዓለም ፓለቲካ ባለሥልጣናት እንኳን የማይታይባቸው ገጽታ  በአባቶች ከዚህ እነሳለሁ አልነሳም ክርክከር አንዱ አሳዛኝ ገጽታ ነው። ይህም ድልድል ፓትርያርኩ አባቶችን ለመከፋፈል የተጠቀሙበት ዓይነተኛ ዘዴ ለመሆኑ ምንን ጥርጥር የለውም።

በአንዱ ሃገረ ስብከት የእረኝነቱን ተግባር በሚገባ  ያለተወጣን አባት ወደ ሌላ ሃገረ ስብከት መመደቡ ሰላማዊ የሆነውን ሃገረ  ስብከት ለችግር መዳረግ አይሆንም?  ለምሳሌ በሃዋሳ የነበረውን ችግር የሃዋሳ ሕዝብ ችግር ብቻ ሳይሆን የድሬደዋም ሕዝብ ችግር ነው ነገ በድሬ ደዋ ላለመፈጸሙ የሃዋሳ ችግር ምን ዋስትና አለው? የአንድ ቤተ ክርስቲያን መታወክ በዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን ችግር መሆኑ ግልጽ ነው። ቤተ ክርስቲያን የአንዱ የክርስቶስ አካል ናትና። ዐይን ሲታመም የሰውነት አካል ሁሉ ይታመማል።

ብፁዕ አቡነ  አብርሃም በውጭ አገር ካሉ አህጉረ ስብከት ውስጥ የዲሲና አካባቢው ሃገረ ስብከትን በላቀ ደረጃ እንዲንቀሳቀስ  ያደረጉ አባት ናቸው። ምንም እንኳን ሃገረ ስብከቱን ከተረከቡ ሁለት አመት ያልሞላው ቢሆንም
በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩት የሥራ እንቅስቃሴ እውነተኛ  የቤተ ክርስቲያንን ልጆች አንገት ቀና ያስደረገ ነው። የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማይፈልጉ በማስጨነቅ ላይ የሚገኝ ነው። በሃገረ ስብከታቸው ስር ባሉ ስቴቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ  ሐዋርያዊና አባታዊ አገልግሎትን በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።  እንድ ሰባኪና አገልጋይ እንኳን የአውሮፕላን ትኬት ሳይቆረጥለት ንቅንቅ በማይልበት በሃገረ አሜሪካ አስቸጋሪ በሆነ የአሜሪካን የክረምት ወቅት ውስጥ ሳይቀር የአውሮፕላን ጉዞ ሲቋረጥ  የዘጠኝ ሰዓት በላይ በመኪና በመጓዝ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን በየስቴቱ  ከፍተዋል። ትምህረተ ወንጌልን ሰጥተዋል። በበዓላት ላይ በመገኘት ከአገሩ እርቆ የሚገኘውን  ሕዝብ  በሐይማኖት እንዲጸና አገር ወዳድ ዜጋ እንዲሆን በማሰተማር የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጡ ይገኛሉ።
 የጥቅማጥቅምና የፓለቲካ አጀነዳዎቻችን ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት የቤተ ክርስቲያኒቱን አቅጣጫ እንደፈለጉ ሲመሩ የነበሩ ሰዎችን ሳይፈሩ  በሐይማኖታዊ አቋማቸው ስለቤተከርስቲያን መስክረዋል።  አንገብጋቢ የሆኑ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በማንሳት ከምእመናን ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ ለሚጠየቁት ጥያቄ በቂና ሙሉ መልስ በመስጠት የማያሳፍር  አባት በመሆን መልስ  ሰጥተዋል ። በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ ሳይወሰኑ የሰንበት ት/ቤ ወጣቶችን ለብቻቸው ሰብስቦ በማስተማር ሐይማኖታቸውን እንዲጠብቁ ቤተ ከርስቲያንን  እንዲያገለግሉ በመምከርና በማበረታታት  አባታዊ ገዴታቸውን ተወጥተዋል። ለህጻናትና በዚህ አገር ለተወለዱ አዳጊ ህጻናት ትኩረት እንዲሰጥ ሁል ጊዜ ከማሳሰብ ወደ ኃላ የማይሉ አባት ናቸው።

ብፁዕ አቡነ አብርሃ በኒዎርክ ሀገረ ስብከት ቀደም ሲል በነበሩበት ጊዜ ተረስቶ የነበረውን ሃገረ ስብከት በማዋቀር በሥሩ የነበሩት አብያት ክርስቲያናት ኅብረት ባማጠናከረና አዳዲስ በመትከል በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት ተግዝቶ በእድሜና በተመላካች እጦት ምክንያት በመፈራረስ የነበረውን  ህንጻ ምእመናንን በማስተባበርና ራሳቸው እንደ አንድ የቀን ሰራተኛ በመሆን በአቦራና በፍርስራሽ ውስጥ ሲሰሩ በመዋል እንጻ ቤ/ ክርስቲያኑ እንዲታደስ አድርገዋል።  በዲሲና አካባቢው ሃገረ ስብከት ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ብዛት ያላቸውን ሥራዎች አከናውነዋል። አሁንም ይህንን በምጽፍበት ጊዜ በዲሲና ኬንታኪ በሚባለው ስቴት ታላላቅ የቤተ ክርሰቲያን ሥራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።  እኔ የማውቀውን ብጠቅስ እንኳን።
         ሃገረ ስብከቱ የራሱ መንበረ ጵጵስና እንዲኖረው አድርገዋል።
         ከእናት ቤተ ከርስቲያን ውጭ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናትን ወደ መዋቅር  ውስጥ አስገብተዋል።
         ለምሳሌ ኖርዝ ካሮላይና እግዚአብሔር አብ
 ኦክልሃማ ገነተ ጽጌ ቅዱስ  ጊዮርጊስ ከገለልተኝነት ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው የገቡት በብፁዕነታቸው ያላሰለሰ ጥረት ነው። አዳዲስ አብያተ  ክርስቲያናትነ  በቻርለት በአታ ለማርያም
                                          በአተላንታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
                                           በኬታኪ  ቅዱስ ገብርኤል
                                           በዲሲ አቡነ ተከለ ሐይማኖት
                                           በዲሲ ዳላስ ራጉኤል ቤተ ከርስቲያን  ለማቋቋም ችለዋል።
ከዚህም ሌላ በሃገረ ስበከቱ ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን  ከካህናት የወጣቶችና የምዕመናንን ተወካዮች በመሰበሰብ ለሃገረ  ስብከቱን በሥራ አስፈጻሚ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲቋቋም አድርገዋል።

የሦስቱንም ሃገረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት  በመንበረ  ጵጵስናቸው በመሰብሰብ በአንድነት እንዲሰሩ ያደረጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና ለቤተ ከርስቲያን አንድነት ፍላጓት ለሌላቸው ራስ ምታት የሆነ ጉዳይ ነበረ።
የሰሜን አሜሪካን ሰንበት ት/ ቤቶች አንድነት ጉባኤ በሥርአት እንዲጓዝ የቅርብ ክትትል ማድረጋቸው የማህበረ  ባለወልድን ማሕበር በቤተ ክርስቲያን ጥላ ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸው በማሕበረ  ቅዱሳን የሥራ እንቅሳቃሴ በጎ ምልከታ ማሳየታቸውና  ማበረታታቸው በዓመታዊው ስብሰባም ላይ እየተገኙ አባታዊ  ምክርን መስጠታቸው በሥደት አገር ላይ ላለው ወጣት እፎይታን ሰጥተውታል። ስለዚህም ነው በወጣቱ ልብ  ውስጥ ገብተው የአንድነትን መንፈስ እንዲቀጣጠል አደረጉት።ስለዚህም በምእመናንና  በወጣቱ ዘንድ መወደድና መከብርን ሊያገኙ ያቻሉት እንዲሁ በስመ ጳጳስ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን  ሥራ ሰርተው የማሰራት ብቃት ያላቸው አባት ሆነው በመገኘታቸው ነው።

ይህ ሁሉ ሥራ የተሰራው በአገር ቤት አባቶች እንደሚከበሩ ተከደረውና  በአለጋ ላይ አልጋ ሆኖላቸው  አይደለም።  በውስጥ ቢጽ ሃሳዊያን ሥራቸውን ለማጨናገፍ ብዙ ጥረዋል። ሕዝቡ እውነቱን እያወቀ ሲመጣ ጥቅማቸው ሊቀርባቸው መቃረቡን የተረዱ ገለለተኛች ነን የሚሉ በየጊዜው እስከ ፓትርያሪኩ ድረስ በመሄድ አሉባልታ ማናፈሳቸውና ለማሰነሳት በተቻላቸው መንገድ ሁሉ ጥረት አድርገዋል። ሕጋዊ ሲኖዶስ ነን ስለሚሉ በልበ ሙሉነት ስተታቸውን መመግለጣቸውና  ሕዝቡም ምንነተቸው እየተረዳው በመምጣቱ የእግር እሳት ሆነውባቸዋል  በውጭና በውስጥ በጥላቻ  የፖለቲካ የተሞሉ ሰዎች  የሚያደርጉትን ጦርነት በመቋቋም ነው። ለሚጠየቁት ጥያቄ ጥበብ የተሞላ መልስ መስጠታቸው። የፖለቲካ ተቃዋሚዋች ችግር ሊፈጥሩቦት ይችላሉ ሲባሉ ወደ ኃላ ሳይሉ በተቃዋሚዎች ሳይደነግጡ  የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም በግልጥ በመመስከራቸውና በተለይም በውይይት የማይፈታ ነገር የለም በሚል የዘወትር አቋማቸው  በመወያየት ብዙ ነፍሳትን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ማርከዋል።   ነገሮችን ሁሉ በውይይት የመፈታት ብቃት ያለው ከውጭ አገር ካለ ባሕሪይ ጋር «ዘጸሐፍኩ ጸሐፍኩ» የሚል ጲላጦሳዊ ግትርንት የሌላቸውና እኔን ብቻ ስሙኝ የማይሉ አባት በመሆናቸው በብዙ ነገር ልቦናው የሻከረባቸውንና ምእመናን ልብ በማለስለስ ወደ እናታቸው ቤተ ክርስቲያን መለሰዋል ።   ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የዲያስፖራ አገልግሎት ጮራ ፈንጣቂ አባትም ለመሆን በቅተዋል።

ታዲያ ይህን ሁሉ ለሰራ አባት ቢያንስ በርታ  ማለት ሲገባ ማዘዋወርን ምን አመጣው? ምንስ  ተልዕኮ  ቢኖረው ነው? «አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ» እንዲሉ  ፓትርያርኩ ለአጥፊዎች ለዘራፊዎች አሜሪካን ላይ ዋሻ ሲያዘጋጁ ምንም ያልሰሩትን  ምን እየሰራችሁ ነው? ብለው ሳይጠይቁ   ሐውልት በቁም ሳሉ ለሰሩልዎት  በአደባባይ ትላንትና ሲሸልሞቸው ዛሬ ምን  እንደተሰማዎ የልብዎን ባውቅ መልካም ነበረ።  ቅዱስ ፓትርያርክ ሆይ የኢትዮጳያ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ሂደት ውስጥ እንደርስዎ ግራ አጋቢ አባት ገጥሟት አያውቅም። አላማዎትን ለማወቅ በጣም ይከብዳል። ሰው የሚወደውን ለምን እንደሚጠሉ  ሁሌ ግራ ይገባኛል። የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑትን ለመስማት ሳይፈልጉ ለምን ሕግና  ሥርዓት አፍራሽ የሆኑትን  የሰማሉ? በእርግጥ ለሰሜን አሜሪካን ችግር መነሻ መሆንዎን የግብር ልጆችዎ < ገለለተኛ ነን >  የተማርነውም  ከአቡነ ጳውሎስ ነው ይላሉ ዛሬም ለእርስዎ ቅርብ ናቸው። ምናልባትም ገለልተኛችን ለመቃወም የሞራል ብቃት ያንስዎት ይሆን?  ሕዝቡን ሲያታልሉት እዚህ የእርሶ ተቃዋሚዎች ናቸው። እርስዎ ጋር ሲመጡ ወዳጅ ናቸው።  እናም ቅዱስነትዎ እባክዎን ዛሬም ጊዜው አለመሸቦትምና ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ ሥራን ሥሩ። ያቀረቡትንም የዝውውር ጉዳይ በጥሞና እንደገና ይዩት።

ብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆናችሁ የወሰናችሁት ውሳኔ በዓለም ያሉ ልጆቻችሁን አስደስታችኃል። ጸጋውን አሁንም ያብዛላችሁ። ኢየሀድገክሙ እጓለ ማውታ ትኩኑ ያለው ዛሬ ተፈጽሞል። የተሰበረ ልባችን ተጠግኖል። እግዚአብሔር እንባችንን አብሶታል። ሁሌም የምንኮራባችሁ ያድርገን።   በዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሏችሁ ፓትርያርኩ ያቀረቡትን የአባቶችን ዝውውር በጥንቃቄ ልታዩት የገባል። በተለይም በብዙ ችግር ውስጥ የምትገኘው የሰሜን አሜሪካን የዲሲና አካባቢው   ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም የነሳሉ መባሉና በእርሳቸው ምትክ ይተካሉ  የተባሉ አባት ከዚህ በፊት ከተመደቡባቸው ቦታዎች አንጻርና  ከሰሯቸው ሥራዎች አንጻር ምን ያህል በዚህ በውጭ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ፈታኝ መሆኑ ለመናገር ነቢይነት የሚያስፈለገው አየመስለኝም። ስለዚህ ብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት  እየተቀጣጠለ ያለው የእናት ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ችቦ እንዳይጠፋ በሃገረ ስብከቱ እየተሰራ ያለው ሥራ  እንዲቀጥለ  ማድረግ የሚቻለውና ሊቀ ጳጳሱ  ከቦታው ላይ ሳይነሱ ሲቀር ብቻ ነው።  ሰለዚህ በአሜሪካን ይህ ሃሳብ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በእናት ቤተ ክርስቲያን ወስጥ ያሉት ምእመናን ወጣቶች የሃዘን ድባብ ውጧቸዋል። የእናንተን የመንፈሳዊ አርበኛች ውጤት በጉጉት እንጠባበቃለን። በረከታችሁ አይለየን።

          
    


Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)