October 22, 2010

የሀገር ሽማግሌዎች አባቶችን ለማስማማት ሲሞክሩ ቆይተዋል


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 22/2010፤ ጥቅምት 12/2003 ዓ.ም):- የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ዛሬ ሲጀመር አበው በፍቅር እና በሰላም ተወያይተው መልካም ውሳኔ ለመወሰን እንዲችሉ የሚያግባባ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ጥረት ሲያካሂድ መቆየቱ ታውቋል። በአባቶች መካከል ያለው ልዩነት እንዲቀረፍ፣ ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ሲሞክር የቆዩት ሽማግሌዎች ሁሉንም አበው ለማነጋገርና ለማቀራረብ ባይችሉም በቁጥር 16 የሚሆኑትን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥቅምት አራት ቀን በሒልተን ሆቴል አገናኝተው ለማወያየት መቻላቸው ግን ተዘግቧል።

ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፣ ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ፣ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ እና ሌሎች ሦስት ሽማግሌዎችን ያካተተው ባለ ሰባት አባላት  የሽማግሌዎች ቡድን ጀምሮ ሲያደርገው የሰነበተው ሙከራ የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ ከመጀመሩ አስቀድሞ አበው ሰላም እንዲያወርዱ ለማግባባት ነበር። ከመንግሥት ይሁንታ እንዳገኙ የሚታመነው የሽማግሌዎቹ ቡድን ቅዱስነታቸውንና አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ለማነጋገር ችሏል። ለእርቅ እና ለሰላም ፍላጎት እንዳላቸው፣ የበኩላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ከቅዱስነታቸው ቃል የተገባላቸው ሽማግሌዎቹ ብፁዓን አበውንም በግል ለማነጋገር ችለዋል ተብሏል። ይሁን እንጂ ውይይቱን ለመግፋትና ለማጠንከር የመሰብሰቢያ ቦታ ጥያቄያቸው መልስ ሳያገኝ ሲቀር ስብሰባውን በሒልተን ሆቴል እንዳደረጉት ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመጀመሪያ ለውይይቱ መሳካት ቀናነት ካሳዩ በኋላ ለቡድኑ የመሥሪያ ቦታ ካለመፍቀድ ጀምሮ፣ ሽማግሌዎቹን ለማነጋገር ባለመፈለግና በማጉላላት ሙከራውን አለመደገፋቸውን እንዳሳዩ ነገሩን የተከታተሉ ሰዎች አስታውቀዋል።

ጥቅምት አራት ቀን ለመወያየት የተቀመጡት አባቶች በቅዱስነታቸው ላይ ያላቸውን ቅሬታ የገለፁ ሲሆን በተለይም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “በጽኑዕ አገዛዝ ውስጥ ነን ያለነው፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እየተጣሰ መሆኑን ለማረጋገጥ ቦሌ መድኃኔ ዓለም ሒዱና ሐውልቱን ተመልከቱ” ማለታቸው ተሰምቷል። ሌሎቹም አባቶች “ተደብድበን ሳለን መንግሥት ፍትሕ አልሰጠንም” እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን ለዚህ አስተያየት የግል ሐሳባቸውን ከሽማግሌዎቹ አንዱ “መንኮሰ ሞተ አይደለም ወይ? እንኳን መደብደብ ሰማዕትነትስ ብትቀበሉ (ብትሰየፉስ?)?” ሲሉ በመመለስ አባቶች ያላቸውን ከፍ ያለ ኃላፊነት አስታውሰዋቸዋል። 

ይሁን እንጂ ይህ የሽማግሌዎች ቡድን ጥረት ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ለጊዜው ያልታወቀ ሲሆን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በተለይም ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና ቅዱስ ፓትርያርኩን በማቀራረብና በማስታረቅ ጉባዔውን በሰላም እንዲጀምሩ ለማድረግ የቻሉ አይመስሉም።

2 comments:

Kiduse wwek MS said...

ጥረቱ ጥሩ ነበር፡፡ ግን እኮ ለመታረቅም ለማስታረቅም መጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ያስፈልጋል፡፡

Anonymous said...

ምን ይሻላል? እናንተው! በቤተ-መንግሥትም በቤተ-ክህነትም የተቀመጡ ወሮበሎች የሚሠሩትን ግፍ ተሸክሞ በሚኖር ትከሻችን ላይ፤ ያ ያነሰን ይመስል፤ እንደገና ሌላ የድራማ ሸክም የሚጨምሩ "ሽማግሎች" ተሹመው ይጫወቱብናል። የወሮበሎቹንም የሽማግሌ-ተብየዎቹንም ዝና የምታስተጋቡ እናንተም ተፈጠራችኹብን! የት እንድረስ? ? ?

ወዶ አይደለም ነቢዩ ዳዊት እንዲህ ያለው፦

በእግዚአብሔር ተወከልኩ እፎ ትብልዋ ለነፍስየ? አዐይል (ዒሊኑ?)ውስተ-አድባር ከመ-ዖፍ። (ትርጕም፦ በእግዚአብሔር ታምኛለኹ፤ ሰውነቴን ምን በይ ትሏታላችኹ? እንደ ወፍ ብር ብለሽ ጥፊ ትሏታላችኹን?)

በእኛው በትከሻችን ላይ የተዘፈዘፈ ግፍ ተሸክሞ ከመኖር፣ በእኛው በራሳችን የሚቀልድ ድራማ ቊጭ ብሎ ከመመልከት ተላቅቀን የገዛ ኑሯችንን የምንኖረው፣ እውነተኛ ሕይወታችንን የምንመረምረው እንዴት ይኾን? እግዚኦ!!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)