October 30, 2010

ፓትርያርኩ ቅዱስ ሲኖዶስ በጋራ ካዘጋጀው የተለየ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠታቸው ሳቢያ ጉባኤው በመካረር መንፈስ ተለያየ


  • አቡነ ገሪማ ከአቡነ ናትናኤል ጋር ያዘጋጁትን ዋናውን የቅ/ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ አልሰጡም፤
  • ፓትርያርኩ “አትፈርሙ” የሚለውን የእጅጋየሁን ምክር በተግባር አውለዋል፤
  •  ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በቃለ  ጉባኤው ላይ ፈረመዋል፤ ብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ ዘግይተውም ቢሆን  እንደሚፈርሙ ይጠበቃል፡፡
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 30/2010፤ ጥቅምት 20/2003 ዓ.ም):- ከተጀመረ ስምንተኛ ቀኑን የያዘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጠርቶት በነበረው ጋዜጣዊ ጉባኤ ፓትርያርኩ፣ እርሳቸውም ፈቃደኛ ካልሆኑ ጉባኤው በመረጣቸው ብፁዕ አባት በንባብ የሚሰማ ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅቶ ነበር፡፡  ይሁንና ጋዜጠኞች መግለጫው በሚሰጥበት አዳራሽ ከተገኙ በኋላ ፓትርያርኩ በአቡነ ገሪማ እንደተዘጋጀ የሚነገርለትን በድብቅ መክረውበታል የተባለውን የተድበሰበሰ መግለጫ በንባብ አሰምተዋል፡፡ ሁኔታው በሌሎች ብፁዓን አባቶች ላይ መገረምን እንዳሳደረ መግለጫው በንባብ በሚሰማበት ወቅት ያሳዩዋቸው በነበሩ አካላዊ እንቅስቃሴዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ አቡነ ጳውሎስ የራሳቸውን መግለጫ በንባብ አሰምተው እንደፈጸሙ የሲኖዶሱን መግለጫውን በንባብ እንዲያዘጋጁ በትናንትናው ዕለት በጉባኤው ከተሠየሙት አንዱ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በተሰጣቸው ሐላፊነት መሠረት በንባብ የተሰማው የተዘጋጀው መግለጫ አለመሆኑን መግለጽ ሲጀምሩ አቡነ ጳውሎስ ‹የቀረች ትንሽ ሥራ ስላለች› በሚል ብፁዕነታቸውን አቋርጠዋቸው ጋዜጠኞች እንዲወጡ ይጠይቃሉ፡፡

በመሆኑም የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሐላፊያቸው አቶ ስታሊን ገብረ ሥላሴ የጥያቄ እና መልስ መርሐ ግብር እንደማይኖር በመግለጽ ጋዜጠኞችን አሰናብተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ብፁዓን አባቶች ከፓትርያርኩ ጋራ ወደ ተካረረ የቃላት ልውውጥ ገብተዋል፡፡ በዘወትር ሸፍጠኛቸው አቡነ ገሪማ ታግዘው የልባቸውን የሠሩት ማንአለብኝ ባዩ አቡነ ጳውሎስም ‹‹አባቶቼ ይቅር በሉኝ፤ ይቅርታ አድርጉልኝ››  ቢሉም ብፁዓን አባቶች በእጅጉ በመከፋት እየተራገሙ ስብሰባውን ጥለው ወጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል በቃለ ጉባኤው ላይ ፊርማቸውን ያላኖሩት ሦስቱ ብፁዓን አባቶች በኋላ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በቃለ ጉባኤው ላይ ፊርማቸውን ያላኖሩት ብቸኛው አባት ብፁዕ አቡነ ይሥሐቅ ናቸው፡፡ ዜናው በደጀ ሰላም ይፋ ለሕዝብ እንደተደረገ ይፋ እንደተደረገ ከተለያዩ አቅጣዎች ጫና እየተደረገባቸው እንዳለ የተነገረ ሲሆን ዘግይተውም ቢሆን ይፈርማሉ ተብሎ ይጠብቃል፡፡

ቀደም ባለው የዜና እወጃ እንደገለጽነው በ1991 ዓ.ም ተሻሽሎ የጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሃይማኖት እና ቀኖናን በሚመለከት ከአራቱ ሦስት እጅ አባላት በተገኙበት፣ አስተዳደርን በሚመለከት ከሦስቱ ሁለቱ እጅ በሚገኙበት ሲኖዶስ ማድረግ እንደሚገባ በስብሰባው ሥነ ሥርዐት ላይ ተገልጧል፡፡ በስብሰባ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዐትም አስተዳደርን በሚመለከት ጉዳይ ከሆነ ከተገኙት አባላት መካከል ከግማሽ በላይ በሆነ ድምፅ የተደገፈው ሐሳብ ያልፋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ድምፁ እኩል በእኩል ከሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያልፋል፤ ሃይማኖትን እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ከሆነ ግን በሙሉ ድምፅ እንደሚያልፍ ይደነግጋል፡፡

አሁን አቡነ ጳውሎስ ለሲኖዶሱ ውሳኔ አልገዛም ብለው በልዩነት የቆሙበት አጀንዳ ልዩነቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና በማክበር እና ባለማክበር፣ ሥርዐተ አበውን በመቀበል እና ባለመቀበል መካከል በትይዩ የቆመ ወሳኝ ልዩነት ነው፡፡ አቡነ ጳውሎስ በተሾሙበት ቀን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አበው (ፓትርያርክ) ለመሆን ሉል ጨብጠው አርዌ ብርቱን ይዘው በሥጋ ወደሙ ምለው የፈጸሙትን ቃለ መሐላ፣ በምእመኑ እና በካህናቱ ዘንድ ክርስቶስ ለሞተላት አማናዊት ቤተ ክርስቲያን እረኛ ለመሆን ከሚኖራቸው አመኔታ እና ተቀባይነት አኳያ የሚጠብቃቸውን ፍርድ ለጥፋተኞች እና ለበደለኞች ምሕረት እና ይቅርታ ለመስጠት ሥልጣነ መንፈስ ቅዱስ ከተሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ታላቅ ነውና የእርሱን ጊዜ እንጠብቃለን፡፡
 +++++++++++++
 ምሥጋና፦
ይህንን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያለመታከት በመከታተል አባቶችን በስልክ ሆነ በአካል በማግኘት ላበረታታችሁ፤ የደጀ ሰላም ዜናዎችና ሐተታዎች እንዲዳረሱ ለረዳችሁ ሁላችሁ የቤተ ክርስቲያን አምላክ በረከቱን አብዝቶ ያድላችሁ። አሁን እንደሚታየው ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ወደ አዲስ እና የሁላችንንም ተሳትፎ ወደሚጠይቅ ደረጃ አደገ እንጂ "ቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ አለቀ" ለማለት አንደፍርም።  
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)