October 31, 2010

አቡነ ጳውሎስ አልፈርምም ብለዋል፤ የሚከተለው ነገር ምንድን ነው?

(ከወልደ  መንክር)፦ በዛሬው እለት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መጠናቀቅን አስመልክቶ በፓትርያርኩ የተሰጠው መግለጫ  ብዙዎቻችን ከምንጠብቀው ውጭ በመሆኑ መገረምና ሀዘን የፈጥሮብናል። አቡነ ጳውሎስ ምን አይነት ሰው እንደሆኑ በቅርበት ለሚያውቃቸው ግን አሁን ያደረጉት የሚጠበቅ ነገር ነው። የሲኖዶሱ አባላት  ፈርመው  ፓትርያርኩ በቃለ ጉባዔው ላይ አልፈርምም  ሲሉ እንደ አካሔድ ታስቦ የነበረው ባይፈርሙም የተጻፈውን ካነበቡት እንደተስማሙበት ማስረጃ ይሆናል የሚል  ስልት ነበር። ነገር ግን ፓትርያርኩ ባላቸው ልምድ የሲኖዶሱን አባላት አስቀምጠው አበው የማይስማሙበትን ያውም አጠቃላይና ግልጽነት በጎደለው መግለጫ ሰጥተዋል። የተጠሩት ጋዜጠኞች በሕጋዊ አካሔዱ ዘግበው ሊያስተላልፉ የሚችሉት በቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ የሚሰጠውን መግለጫ እንጂ የሲኖዶስ አባላትን ስሜት አይሆንምና ሬዲዮውም ቴሌቪዥኑም ያቀረበው የእርሳቸውን ነው። ምክንያቱም ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው መግለጫ የመስጠት ሕጋዊ መብት ስላላቸው እና ጋዜጠኞቹ  ፓትርያርኩን ተላልፈው  ሌላ የሲኖዶስን አባል መግለጫ ለማስተላለፍ የተመቻቹ ሕጋዊ አካሄዶች ስለሌሉ የሆነው ይኼው ሆኗል። ፓትርያርኩ የሰጡትን መግለጫ ሲኖዶሱ አልስማማም ካለ ሌላ ሲኖዶሱን የሚወክል አባት መርጠው ማስቀመጥ አለባቸውና።  የሲኖዶስ አባላት ከመግለጫው በኋላ የተፈጠረውን ችግር አስመልክተው የሲኖዶሱን ( የአባላቱን  ሀሳብ) ለምእመናን መግለጥ ስለሚቻልበት መንገድ ተነጋግሯል። ምናልባትም “የሲኖዶሱ ትክክለኛ ውሳኔ  ይህ ነው”  ለማለት ታስቦ ነው። ይህንን ለማድረግ ግን ቅዱስ ሲኖዶሱ ሀሳብን ከመግለጥ ያለፈ ሌሎች እርምጃዎችን ሊወስድ የሚችሉባቸው ሕጋዊ አካሄዶችን ከዚህ በፊት አላመቻቹም።  ሊኖር የሚችለው አማራጭ የሲኖዶሱ ጸሐፊ ወይም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ወይም በጉባዔው የተመረጠ አባት  ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ማድረግ ነው።  ይህ ግን በመንግስት መገናኛ ብዙኀን ተቀባይነት አግኝቶ ሊተላለፍ ይችላል የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው ።

ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ “ሐውልቱ እንዲፈርስ የማስፈጸም ኃላፊነት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንጂ ለእኔ በስም ተጠቅሶ መሰጠት የለበትም” ማለታቸው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ካለው የአሠራር ልምድ ውስብስብነትና አስቸጋሪነት አንጻር ተነሥተው በመሆኑ ተገቢ ሀሳብ ነው ያቀረቡት። ይህ በፍርሐት ወይም በጉዳዩ አለመስማማት ተደርጎ ሊወሰድባቸው አይገባም እላለሁ። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንደዚህ አይነት ወሳኝ ችግር ሲፈጠር ለምን ለአንድ አባት ኃላፊነት ሰጥተው ለመሄድ ፈለጉ?  በእኔ አመለካከት  የትኛውም የቅ/ሲኖዶስ አባል ውስጥ በጠቅላይ ሥራ አስከያጁ ቦታ ቢቀመጡ በትክክል ይህንን ውሳኔ ያስፈጽማሉ የሚል ግምት የለኝም። ለምን የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሚከተሉት ምክንያቶች በቂ ምላሽ ይሰጣሉ።

1ኛ. የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ ልብ በጋራ መስዋዕትነት ለመክፈል  ዝግጁነት ስለሚቀራቸው፤
አሁን በሚታየው አካሔድ  ያሉት የሲኖዶስ አባላት በሦስት መንገድ የተሰለፉ ናቸው። አንደኛው መሆን አለበት ብለው የተሰለፉ፤ ሌሎች አባቶችን ለማሳመን የሚጥሩ፤ ሁለተኛ ደግሞ ሀሳብ የማይሰጡ፤ ነገር ግን ሌሎችን ተከትለው የሚሔዱ፤ በራሳቸው የማይተማመኑ እና  ሦስተኛዎቹ ደግሞ በአቡነ ጳውሎስ መረብ የተጠመዱና ጥሩ ሀሳብ ያቀረቡ መስለው የውሳኔው አፈጻጸም ከባድ እንደሆነ በመናገርና ገደል ገደሉን በማሳየት አባላቱን ወደ ፍርሐት የሚከቱ ናቸው። ስለዚህ ይህንን የስሜት መለያየት ከማንም የበለጠ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላቱ ስለሚያውቁት እርስ በእርስ የመፈራራት መንፈስ በመኖሩ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን ለሁሉ ነገር ተጠያቂ በማድረግ  የመሄድ ችግር የማይፈታ አመለካከት በመሆኑ አባላቱ ለአንድ ሰው ኃላፊነት ለመስጠት ከማሰብ በጋራ እስከ መጨረሻው ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን  የመደጋገፍ መንፈስ ቢፈጥሩ ይሆናል።

2ኛ. የጠቅላይ ቤተክህነት መዝገብ ቤት በጠቅላይ ሥራ አስኪያጆች ቁጥጥር ሥር አለመሆኑ፤

የጠቅላይ ቤተክህነት መዝገብ ቤት ማኀተም በአቡነ ጳውሎስ ታማኝ በሆኑ ኃላፊ እጅ የወደቀ ነው። እስካሁን  የነበሩት ሥራ አስኪያጆች ተሞክሮ እንደሚያስረዳው የመዝገብ ቤቱ ኃላፊ (ቀሲስ  ዮሐንስ  ዘአድዋ) ያልተስማሙበት ደብዳቤ ጠቅላይ ስራ አስኪያጁ  ቢፈቅዱም ማውጣት እና ማሰራጨት  ያልተቻለበት አጋጣሚዎች  ነበሩ።  የአቡነ ጳውሎስን ስሜት ከመጠበቅ አንጻር የመዝገብ ቤቱ ኃላፊ  ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የበለጠ ሥልጣን አላቸው። ይህንን ጉዳይ የሲኖዶሱ አባላት እያወቁ ጠቅላይ ሥራ እስኪያጁ ያስፈጽሙ ብሎ መወሰኑ አልተናገሩም እንዳይባሉ ወይም ከተጠያቂነት የመሸሽ ምልክት  ካልሆነ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም።

የመጡት ጋዜጠኞች ምን ዘግበው እንደሔዱትና በዜና ሲነገር እንደሰማነውም በቃለ ጉባኤው ላይ አልፈርምም ማለታቸው ድንገት የመጣ ሳይሆን አማራጭ ብለው ካስቀመጧቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ ነው። ይህ መሰናክል ቢታለፍ ኖሮ ደግሞ ሌላ እልክ አስጨራሽ መሰናክል እንሰማ ነበር። 

በእኔ አመለካከት እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ እንኳን ሥራ አስኪያጁ የመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤትም ብቻውም ለማስፈጸም አቅም ያንሰዋል ባይ ነኝ። ጠቅላይ ቤተክህነት ተግባራዊ ያድርግ ከተባለ አፈጻጸሙ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባዔ መምጣቱ አይቀርም። የአስተዳደር ጉባዔ አባላት ውስጥ ደግሞ  አብዛኛው ለሃይማኖትና ለእውነት ያደሩ አይደሉምና ጉዳዩ አንድ ጋትም አይራመድም።  ስለዚህ ሲኖዶሱ ይህንን ተግባራዊ እንዲሆን ከወሰነ  የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ፣  የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ  እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባሉበት ሌሎች ተጨማሪ አባቶች ተመርጠው የመንግሥት ድጋፍ ጠይቀው ለመተግበር  በጋራ መነሳት አለባቸው። የአቡነ ጳውሎስ ሐውልት መፍረስ  የአቡነ ጳውሎስ አምባገነናዊ አሰራር ለማብቃቱ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት በመዝረፍ የግል ጥቅማቸውን  ለሚያስቀድሙ በርካታ ሰዎች “ከእንግዲህ ወዲያ በዚህ የወንጀል ተግባር መቀጠል አትችሉም” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ በመሆኑ ተግባራዊነቱ ወሳኝ ነው።  ስለዚህ አሁን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ገና ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሳይመለሱና ጉባዔው ሳይፈጸም ይህንን ያህል እምቢተኝነታቸውን ማሳየት ከቻሉ  ከተበታተኑ በኋላ ሊያደርጉ የሚችሉትን መገመት ይቻላል። አሁን ባለው አካሔድ አንጻር ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ማድረግ ያለባቸው በአንድነት ሆነው ውሳኔውን በደብዳቤ ለመንግስት መግለጽ መቻል ነው። ምክንያቱም  የጠቅላይ ቤተክህነቱ መዝገብ ቤት እና የቅዱስ ሲኖዶስ መዝገብ ቤት  ማኀተም የተያዙት ለአቡነ ጳውሎስ ታማኝ በሆኑ ሰዎች ስለሆነ በሌላ ደብዳቤ ሐሳቡን መግለጽ አይቻለም። የመንግስት ጸጥታ አስከባሪ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀው ሁሉም ወደ  ሐውልቱ በመሔድ አይናቸው እያየ እንዲፈርስ ማድረግ አለባቸው።

አሁን እንደሚታየው አቡነ ጳውሎስ አልፈርምም በማለታቸው ከጸኑ ሊኖረው የሚችለው ሌላ አማራጭ ከባድ ነው ። የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቀጣዩን አማራጭ የሚደፍሩት ወይም የሚስማሙበት አይመስልም። አሁን እየተደረገ ያለው የተለያዩ አባቶች እየተነሱ በማግባባት ፓትርያርኩ በቃለ ጉባዔው ላይ እንዲፈርሙ መለመን ነው።  ልመናው እስከሚቀበሉት ድረስ ይቀጥልና እንቢ በማለት ከጸኑ፤ የሚኖረው   አማራጭ  ሦስት ነው።

1.       በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እና ሕግ መሰረት ጊዜያዊ ሰብሳቢ መርጠው መሰብሰብና ውሳኔ ማስተላለፍ፤

ይህንን አካሔድ ብዙ የሲኖዶስ አባላት የሚፈሩትና የማይፈልጉት  አማራጭ ነው።  ምክንያቱም ሳብሳቢን መርጦ ውሳኔ ማስተላለፍ አቡነ ጳውሎስን ከሥልጣን የማውረድ ጉዳይን አብሮ ስለሚያስነሳ ነው። ባለፈው ዓመትም ተሞክሮ የነበረ ነገር ግን አባቶች ላይ አካላዊ አደጋ እስከመጣል ያደረሰ ነበር። ከዚህ በፊት አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ሞክሮ በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት ጉዳያቸው ሲታይ ጊዜያዊ ሰብሳቢ ተመርጦ አቡነ ጳውሎስም ከጉባዔው ወጥተው ጉባዔውን ለማካሄድ የሞከረው በአቡነ ጳውሎስ እምቢተኝነትና በሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ተቃውሞ ሳይሳካ ቀርቷል።  ስለዚህ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ በላይ ግፊት እንዳይደረግባቸው የሚፈልጉ ጉዳዩ ቢገፋ በአካሔዱ አንስማማም የሚሉ ሊቃነ ጳጳሳት ስለሚኖሩ፤ ሰብሳቢ ሆኖ ጉዳዩን ለማየት የሚስማሙበት አባት ማግኘት እራሱን የቻለ አጀንዳ በመሆኑ፤ አቡነ ጳውሎስ ከወረዱ ቀጣይ ፓትርያርክ የሚሆነው ማን ነው የሚለው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ስለሚያደርግ እና “ማንን ሥልጣን ላይ ለማውጣት ነው ይህንን ሰማዕትነት የምከፍለው” የሚል የሥነ ልቡና ጫና ስለሚፈጠርባቸው፤ በተጨማሪም መንግሥት በበኩሉ ይስማሙኛል የሚላቸው እንዲመረጡ ለማድረግ  የራሱን ሥራ ስለሚሰራና “አልተዘጋጀሁም” በሚል ስሜት ከተወሰነ ደረጃ በላይ ቅ/ሲኖዶሱ አክርሮ ጉዳዩን እንዲመለከት ስለማይፈልግ፤ ምንም እንኳን ሕገ ቤተክርስቲያን ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ቢያስቀምጥም ወደ ተግባር መተርጎሙ ከባድ ስለሚሆን ይህንን አማራጭ ሲኖዶሱ ሊወስድ ይችላል የሚል ግምቴ ያነሰ ነው።  ነገር ግን እግዚአብሔር የወሰናት ቀን ከሆነ ተፈጽሞ ልናይ እንችላለን ።

2.     የሚያስማማ የውሳኔ ሀሳብ በቃለ ጉባኤው ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ፤

ሐውልቱ ይፍረስ የሚለው ውሳኔ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ የማይቀበሉት ጉዳይ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ ደግሞ ይፍረስ ብሎ በቃል ደረጃ ወስኗል። ከዚህ በኋላ የሚደረገው ስብሰባ የውሳኔ ሀሳቡን የማቅለል አማራጮችን ለማምጣት ነው።  ይህ ደግሞ ውሳኔውን የመሻር ያህል አቅም ይኖረዋል።

3.     ጉዳዩ እንደተንጠለጠለ ጉባዔው መበተን፤
 አሁን ባለው አለመስማማት ነገሮች እየከረሩ ስለሚሔዱ የሚኖረው አማራጭ በቃለ ጉባዔው ላይ የሚስማሙ አባቶች ይፈርሙና (ለታሪክ እንዲሆን) እንደተንጠለጠለ ወደ ሀገረ ስብከታቸው መሄድ ይሆናል። አብዛኛው አባቶች ሊፈርሙ ችለዋል ነገር ግን በአስተዳደራዊ አካሄዱ ውሳኔያቸው አቅም እንዲኖረው ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኔ ነው ብሎ በፊርማው የሚያስተላለፈው  እስካልተገኘ ድረስ ድካሙ ሁሉ ከንቱ ነው:፡ ስለዚህ በቃል ደረጃ እነ እገሌ ፈረሙ ሌሎቹ ግን አንፈርምም አሉ ከማለት ያለፈ ጉዳይ አይሆንም። እዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልገው አቡነ ጳውሎስም በአባቶች  መካከል መለያየት እንዲፈጠርና አንድነቱ እንዲቀዘቅዝ ከወዳጆቻቸው ጋር ሆነው እንደሚሠሩ በመገንዘብ ለእነርሱ ስልት የሚጠቅምና አባቶችን የሚለያይ ሥራ ከመሥራት መታቀብ ነው ።

ስለዚህ አሁን ያለንበት ጊዜ ወሳኝ ስለሆነ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በአንድነት በመቆም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ስለሚገባ  በመላው ዓለም የሚገኙ አባቶች ወንድሞች  እና እህቶች በያሉበት ቦታ ሆነው በጋራ በመወያየት ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተፈጻሚነቱ የሚፈለገውን መስዋዕትናት ሁሉ ለመክፈል መነሳት ጊዜው አሁን ነው ።

የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን ። 


Selam Dejeselam

I tried to post my comment, but it said it is large to process.
I do not know if it is worth to post it in your blog. I tried to express my understanding and feeling
regarding the heroic decision of our fathers.

May God bless you

G/ Michael
Seattle

አሸናፊ እና ተሸናፊ የለም ታሪካዊ ውሳኔ እንጅ

ጎበዝ እንደ እኔ አስተያየት አሁን አቡነ ጳውሎስ አሸነፉ ብየ አላምንም:: ብጹዐን አበው የቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ ወደ ወሳኝ ዕራፍ አድርሰውታል:: ለዚህም ሊበረታቱ ይገባል:: እገሌ አሸንፏል እገሌ ተሸንፏል የሚል መንፈስ ባናራምድ ጥሩ ነው:: የአባቶቻችን ውሳኔ አሸናፊ ነው:: ዋናው ነገር ሁላችንንም ለአገልግሎት የሚበረታታ ውሳኔ ወስነዋል:: ዋናው  ነጥብ ጅምሩ መታየቱ እና ወሳኝ የሆኑ ውሳኔወች መወሰናቸው ነው:: በዚህ ልንበረታታ ይገባናል:: ፓትርያርኩ የሰሩት ስራ እርሳቸውንና አብረዋችው የቆሙትን ሰወች የውርደት ደርጃ የሚያሳይ እንጅ አሸናፊነታቸውን ብፍጹም አያሳይም:: አሁን እኛ ትኩረት ማድረግ ያለብን እና መወያየት ያለብን ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ካልሆነስ ምን ማድረግ አለብን? ይሄንን ውሳኔ የሚያስፈጽሙ አባቶችን እና አካላትን እንዴት እናግዛቸው? የሚሉትና የመሳስሉት  ጥያቄውች እና ሃሳቦች ላይ ነው:: እኔ ሌላ ማለት የምፈልግው አቡነ ጳውሎስ አሸንፉ የምትሉ ሰወች እንዴት ነው ያሸንፉት? እንደ እኔ አረዳድ አቡነ ጳውሎስ በሃሳባቸው ደንድነው ቆዩ መጨርሻ ላይ ደግሞ ሁሌም በማያከብሩት ህዝብ ፊት ዋሹ ነው የምለው:: ምክንያቱም ከቅዱስ ሲኖዶስ የተለየ መግለጫ በመስጠት:: ይሄ ደግሞ አዲስ ነገር አይደለም 18 አመት ሙሉ የለመድነው ነው:: አሁን አዲስ ነገር አልተፈጠረም::አዲሱ ነገር አባቶቻችን የወሰኑዋቸው ቁልፍ ውሳኔወች ናቸው:: ሌላው ነገር ላዘመናት ሲከማች የኖር ችግር አሁን አባቶቻችን በአንድ ስብሰባ ሊፈቱት አይችሉም:: የምፍታቱን ሂድት ግን ጀምረውታል::ስለዚህ ይሄን ጅምር እናበረታታ እንደግፍ እናግዝ:: አሁን ዝም ብለን ተሽነፉ ምናምን እያልን የመሸነፍን እና የማሸንፍን ትርጉም አናበላሽ:: ይሄ የእነ እገሌ እና እነ እግሌ ጉዳይ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ የቀኖና እና የሃይማኖት ጉዳይ ስልሆነ ጉዳዩን በስሜታዊነት እገሌ አሸነፉ ምናምን እያልን ዝቅ ባናደርገው ጥሩ ነው ባይ ነኝ:: አባቶቻችን የወሰናቹት ውሳኔ በጣም ታሪካዊና ቤተክርስቲያናችንን የሚጠቅም የምዕመናንን አንገት ቀና ያደርግ ውሳኔ ነው:: መገግለጫው ምን ተባለ አልተባለ አቡነ ጳውሎስ ፈርሙ አልፈርሙ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም:: አሁንም በርቱ ከጎናችሁ ነን:: ደስ ብሎናል ተስፋ ሰንቀናል::
ለመታዘዝ ተዝጋጅተናል:: እግዚአብሄር እድሜውን እና ጸጋውን አብዝቶ ይስጣችሁ::

አፈጻጸምን በተመለከተ

አባቶቻችን አፈጻጸምን በተመለከተ በየጊዘው ክትትል ብታደርጉ መርጃ ብትሰበስብ በያላችሁበትም ሆናችሁ ቢሆን ለጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ስትመጡም ቢሆን  በትጨማሪ በየሀገረ ስብከቱ ስትመለሱ ለምእመኑ በግልጽ ብታስተምሩ መርጃ ብትሰጡ:: ይሄንን የምለው እናንተ ዝም ብትሉም ምዕመኑ መረጃው ስለሚደርሰው እናንተም ትዝብት ላይ እንዳትወድቁ ነው::

ምእመናን ስለ ውሳኔው ተፈጻሚነት በርትተን እንጸልይ እንጠይቅ መረጃ እንለዋውጥ::ይሄን ካደረግን አስፈጻሚውቹ እንኳን ለማረሳሳት ቢሞክሩ እኛ እንደማንረሳ እንደምንጠይቅ ያሳያል:: መንግስትም ለሰላም እና ለጸጥታ ሲል እንዲፈጸም ግፊት ይፍጥራል::
ደጀ ሰላም ሰሞኑን የሰራችሁት ስራ በጣም ተገቢና ጠቃሚ ስራ ነው:: ለዚህም እግዚአብሄር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ:: ግን በጣም ብዙ ስራ ይቀራል:: በተለይ አፈጻጸሙን በተመለከተ ልክ ሰሞኑን እንዳደረጋችሁት እየተከታተላችሁ ለምእመናን እና ለሚመለከተው መረጃ እንድታድርሱ:; ጠቋሚ ሃሳቦችን እንድታስነብቡ:: ማን ምን እያደርገ እንደሆነ ብትዘግቡ ጉዳዩ እንዳይረሳ እንዲጸለይበት እንዲብላላ በህዝቡም በመንግስትም በመገናኛ ብዙሃንም ትኩርት እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል:: ለሚቀጥለው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባም ለውሳኔ የሚመች በቂ መርጃ ማሰባስብ ይቻላል::

መጨረሻ ላይ

አንዳንዶቻችን የምናንጸባርቀውን ቀቢጸ ተስፋ አቁመን አባቶቻችን ለለፉት ልፋት ተገቢውን ዋጋ ሰጥተን የእኛ ድርሻ ምንድን ነው የሚለውን እያውቅን እና እያደረግን በተጀመረው በጎ እና አበረታች ጅምር እየተበረታታን ወደፊት እንጓዝ:: እግዚአብሄር በቸርነቱ መንገዳችንን ይቅደምልን ወላዲት አምላክ በምልጃዋ ትርዳን::
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)