October 5, 2010

ሰበር ዜና፦ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዳይመለሱ የሚጠይቅ የአድማ ፊርማ እየተሰበሰበ ነው

  • አድማውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እያስተባበረ ነው
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 4/2010፤ መስከረም 24/2003 ዓ.ም):-  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በመጪው ጥቅምት ወር በወሳኝ መልኩ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ምልዓተ ጉባኤ በሕገ ወጥ መንገድ ወደተነሡበት አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዳይመለሱ የሚያሳድም ፊርማ እየተሰበሰበ መሆኑን ከሀገረ ስብከቱ የውስጥ ምንጮች ለደጀ ሰላም የደረሰው ጥቆማ አጋለጠ፡፡ 

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለጾመ ፍልሰታ ሱባኤ ቆይታ ካደረጉባት ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ተከትሎ እየተሰባሰበ ነው የተባለውን የአድማ ፊርማ የሚያስተባብረው ሐምሌ ስድስት ቀን 2002 ዓ.ም በተደረገው የሲኖዶሱ ስብሰባ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅነታቸው በመጪው ጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም እስከሚካሄደው የቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ምልዓተ ጉባኤ ድረስ በተራዘመላቸው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ በሚመራው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ግንቦት 6 - 13 ቀን 2001 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ምልዓተ ጉባኤ በፓትርያርኩ እየተፈጸሙ ናቸው የሚሏቸውን ሙስና፣ ቤተ ዘመዳዊ አሠራር፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን የሚጥሱ ሹመቶች፣ ዝውውሮች፣ የገንዘብ አወጣጦች. . . ወዘተ በተደራጀ የአጀንዳ አቀራረብ በጽናት ተቃውመዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ባልታየ አኳኋን የተቀመረ የተቃውሞ ሐሳብ በብፁዕነታቸው በቀረበበት በዚሁ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚታየውን አስተዳደራዊ ችግር በጥልቀት እና በስፋት አጥንቶ መፍትሔ እንዲሰጥ፣ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ ፣ የሥራ ዘመኑ አንድ ዓመት የሆነ ሰባት ብፁዓን አባቶች የሚገኙበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተቋቋሟል፡፡ 

ብፁዕነታቸው በሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ተደግፎ የተቋቋመው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጸሐፊ በመሆን ሰኔ አንድ ቀን 2001 ዓ.ም ፓትርያርኩ ያለሲኖዶሱ እና ያለኮሚቴው ዕውቅና የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀዳሚ የልማት ክንፍ ለሆነው የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ለመሾም ያደረጉት ሙከራ እንዲቆም የሚያሳስብ ደብዳቤ ከኮሚቴው አባላት ጋራ በመመካከር ጽፈዋል፡፡ 

በዚያው ሰሞን ፓትርያርኩ ወደ ጣልያን አድርገውት ለነበረው ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን እና የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚተላለፍ ጉዞ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ከኮሚቴው አባላት ጋራ በመሆን ጽፈው ነበር፡፡ ከዚሁ ጋራ ተያይዞ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚያደርጋቸው የሥራ ዝውውሮች ሲኖዶሱ ያልወሰነባቸው እና አቤቱታ እየጎረፈባቸው በመሆኑ እንዲቆሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ ከመጻፋቸውም በላይ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች እና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ችግሮችን በመጠቆም፣ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ የሚጠይቅ ማስታወቂያ ከኮሚቴው አባሎች ጋራ በመሆን አውጥተዋል፡፡

 (ፎቶ፦ ቅዱስ ፓትርያርኩ ባለፉት ዓመታት በየአብያተ ክርስቲያናቱ ካሰቀሏቸው ፖስተሮች መካከል አንዱ፤ "ስለ ዓለም ሰላም ሲፀልዩ" የሚያሳይ)
በነባራዊው አሠራር ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣኑን በብቸኝነት ተቆጣጥረው ለቆዩት ፓትርያርክ እና በዙሪያቸው ለተሰለፉት ቡድኖች እኒህ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ፋታ የማይሰጡ ተከታታይ ርምጃዎች ግልጽ መፈተኛዎች ነበሩ፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጸሐፊነታቸው የኮሚቴው አባላት ከሆኑ ሌሎች ብፁዓን አባቶች ጋራ የፓትርያርኩን ያልተገደበ ሥልጣን እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደራዊ ችግር ለማስተካከል ከመጣራቸው ቀደም ብሎም ፓትርያርኩ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት በቀጥታ የሚያደርጉትን ያልተገባ ግንኙነት እና ጣልቃ ገብነት ለማስቆም፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣባቸውንና በልማድ የሚፈጸሙትን እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር ያደረጓቸው ጥረቶች እንደ ተግዳሮት ተወስዶባቸዋል፡፡

በዕሥራ ምእቱ በዓል አከባበር ሰበብ የፓትርያርኩ ምስል በየአጥቢያው እንዲሰቀል የተደረገውን ተግባር፣ ፓትርያርኩ ቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ሳይመክርበት ‹‹ሰማዕት ዘእንበለ ደም፣ የሚሌኒየሙ አባት›› የተባሉባቸውን የግርግር መርሐ ግብሮች በግልጽ ተቃውመዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን አገልግሎት ‹‹ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ›› በሚል ሀገረ ስብከቱን ለአምስት ለመክፈል በአቡነ ጳውሎስ ቀርቦ የነበረው ሐሳብ በቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ጉባኤ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡

የሁኔታው ጠቅላላ አዝማሚያ ያላማራቸው አቡነ ጳውሎስ በሰኔ ወር 2001 ዓ.ም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን እና አባላቱን አገዱ፡፡ በቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖ የተቋቋመውና የመተዳደሪያ ደንቡን እያዘጋጀ ሥራውን በማከናወን ለሐምሌ 2001 ዓ.ም ቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ጉባኤ እየተዘጋጀ የነበረው ኮሚቴ የከፈተው ጽ/ቤት፣ ‹‹በቤተ ክርስቲያኒቱ የማይታወቅ እና ፈቃድም ያልተሰጠው ነው›› በሚል በአስቸኳይ እንዲዘጋ ‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትን እና አድባራትን ይወክላሉ›› በተባሉ ተሰብሳቢዎች ተወሰነ፡፡ ሕገ ወጥነቱ በዚህ ሳያበራ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጸሐፊ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ከሐላፊነታቸው ታገዱ፡፡ እግዱን የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት በጥብቅ ተቃወሙት፤ የሲኖዶሱን የዕለት ከዕለት ሥራ በሚመራው ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ም አልተደገፈም፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በፓትርያርኩ ለተጻፈው የእግድ ደብዳቤ በሰጡት መልስ እግዱ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚጥስ እና ‹‹ባልተሰጠዎት ሥልጣን›› የተላለፈ ስለሆነ የተበተነው ደብዳቤ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ ሲሉ ጠይቀው ነበር፡፡ ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም ጠዋት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የመኪናቸው ቁልፍ ባልታወቁ ሰዎች ከሹፌራቸው ተነጥቆ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ ታግተው ከመቆየታቸውም በላይ የኮሌጁ ቅጽርም በፌዴራል ፖሊስ ይጠበቅ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ እገታው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን መታገድ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ሊቀ ጳጳስ መነሣት፣ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነርን ሹመት፣ በብፁዕነታቸው ላይ የተጻፈውን ስም አጥፊ መጽሐፍ፣ ፓትርያርኩ በሕገ ወጥ መንገድ በጠሩት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች እና የአስተዳደር ጉባኤ ስብሰባ አስመልክቶ እንደሚወያይ በሚጠበቀው በውጥረት የተሞላ ጉባኤ ላይ እንዳይገኙ ለመከላከል የታሰበ ነበር፡፡

በስብሰባው ክራሞት ለሕገ ቤተ ክርስቲያን መከበር እና ለታሰበው በጎ የአሠራር ለውጥ አዎንታዊ አቋም የነበራቸውን ብፁዓን አባቶች መኖርያ ቤት በር በመስበር እና በማንገላታት አሳዛኝ ፍጻሜ በታየበት የሲኖዶሱ አስቸኳይ ጉባኤ ፓትርያርኩ ከማንኛውም አስተዳደራዊ ሥልጣን ለቀው በአባታዊ አገልግሎት እንዲወሰኑ በቀረበው ሐሳብ ላይ ገሚሶች ለዘብተኛ አቋም ሲይዙ፤ የተቀሩትም በተከታዮቹ ቀናት በቀጠለው ስብሰባ ሳይገኙ በየቤታቸው መዘጋታቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ በኋላ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት እና ምክር በተዳከመ ሁኔታ በተካሄደ ስብሰባ ስለተፈጠረው ችግር አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲቆዩ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ኮሚቴውም የደረሰበትን ሳያሳውቅ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልም በማንአለብኝነት በቀጠለው የአቡነ ጳውሎስ ጣልቃ ገብነት የተነሣ በኮሚሽኑ የተሰጣቸውን ሐላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንዳልቻሉ በመግለጽ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄዱ ችለዋል፡፡

ሐምሌ ስድስት ቀን 2002 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ቅዱስ ሲኖዶስ  ጉባኤ ብፁዕነታቸው የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ለሠየመው ቅዱስ ሲኖዶስ  የማይቀርብበትን እና ሥራቸውን የማይቀጥሉበትን ምክንያት በተመለከተ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ለጥያቄያቸው ፓትርያርኩ የሰጡት ምላሽ የአጣሪ ኮሚቴውን ሪፖርት በቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ  ለማየት ታስቦ የነበረ ቢሆንም ኮሚቴው ሪፖርቱን በወቅቱ ማድረስ እንዳልቻለ፣ ብፁዕነታቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በአግባቡ እንዳላስረከቡ እና ወደ ውጭ ሄደው መቆየታቸውን ያጣቀሰ ነበር፡፡ የሀገረ ስብከቱን ርክክብ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በፓትርያርኩ የተሰጠው ምክንያት ትክክል እንዳልሆነና በራሳቸው እጅ ተገቢውን ሰነድ ሰጥተዋቸው እንደነበር አስተውሰዋቸዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በበኩላቸው የአጣሪ ኮሚቴው አባላት በጥቅም ከመደለል ጀምሮ ሪፖርቱ ስለምን ለሲኖዶሱ ሳይቀርብ እንደቀረ ዝርዝር መረጃ እንዳላቸው፣ እርሳቸውን ለመጉዳት 24 ገጾች ያሉት የሐሰት ውንጀላ ለመንግሥት ከማቅረብ አንሥቶ በፓትርያርኩ እና በተባባሪዎቻቸው ምን እየተፈጸመ እንዳለ እንደሚያውቁ፣ ይሁንና ፓትርያርኩ እንደሚያስቡት አንዳችም ጉዳት ሊያገኛቸው እንደማይችል፣ ይልቁንም የትመጣቸው የማይታወቁ መንደርተኞች በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከትመው ሕገ ቤተ ክርስቲያን እየተጣሰ፣ ሥርዓተ አበው እየፈረሰ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የቁልቁሊት እየሄደች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ብፁዓን አባቶች ከመተባበር ይልቅ በሌሎች አጀንዳዎች መጠመዳቸው እንደሚያሳዝናቸው፣ እርሳቸው ግን ተጋድሏቸውን አጠናክረው እንደሚጥሉ በግልጽ አሳውቀው ነበር፡፡

 በሐምሌው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ዋዜማ ለ18ኛው በዓለ ሢመት ሐውልተ ስምዕ አሠርተው በማስመረቅ ሽር ጉድ ያሉት በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ (ፎቶውን ይመልከቱ) የሚመራ ቡድን ስብሰባው በታየው መልክ ያለውጤት እንዲጠናቀቅ አንዳንድ አባቶችን በጥቅም የማግባባት ሥራ ሠርቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በሐምሌ ወር መጨረሻ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በመሄድ የሱባኤውን ወቅት፣ የዘመን መለወጫን እና የመስቀል በዓላትን በዚያው ውለው ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ቢሆንም አካሄዳቸው በውጭ ለመቅረት፣ አልያም በውጭ የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደሆነ የቤተ ክህነቱ የማፊያ ቡድን አሉባልታ ሲነዛ ከርሟል፡፡ ለብፁዕነታቸው ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደሚያስረዱት ግን አቡነ ሳሙኤል እርሳቸውን የሚቀርቡ የሀገረ ስብከቱ እና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሐላፊዎች እና አገልጋዮች የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ በመረዳት እንዲሁም ከደኅንነታቸው አኳያ የሱባኤውን ወቅት በፍጹም ጽሞና ወደሚያሳልፉበት ኢየሩሳሌም እንደሄዱና አሁንም ቢሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸመ ላለው በደል መፍትሔ ለመሻት እየተጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በመስቀል ደመራ ክብረ በዓል ላይ ቁጥራቸው ያልተገለጹ ሰዎችን ዝርዝር ፊርማ ያረፈበትን የአድማ ወረቀት የያዙ ሁለት ጥቅመኛ ግለሰቦች የአጥቢያ አስተዳዳሪዎችን፣ የሰበካ ጉባኤያት ጸሐፊዎችን እና ካህናትን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዲመለሱ ሊተላለፍ የሚችልን ውሳኔ በመቃወም ዙሪያ የማግባባት ሥራ ሲሠሩ መታየታቸው ተዘግቧል፡፡ ሁኔታው ከሀገረ ስብከቱ እስከ መንበረ ፓትርያርኩ ድረስ የተዘረጋውን የመጠቃቀሚያ ሰንሰለት በማስቀጠል ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዐበይት የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የቁጥጥር ችግሮች ሁነኛ መፍትሔዎችን እንደሚሰጥ የሚጠበቀውን የጥቅምቱን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከወዲሁ ለማሽመድመድ የሚደረጉ የቀቢጸ ተስፋ ሙከራዎች ዓይነተኛ መገለጫ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)