October 12, 2010

በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር እና ፋይናንስ መዋቅሮች የሐላፊዎች ሹም ሽር ተደረገ  •  ለውጡ ‹‹የጨለማው ሲኖዶስ›› ቡድን አባላትን ከዋና ዋና የሐላፊነት ቦታዎች እንዲገለሉ አድርጓል
  •  ከቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት ግንኙነት እንዲሁም ለጥቅምቱ  ሲኖዶስ ከሚደረገው ዝግጅት አኳያ ጥያቄዎችን አስነሥቷል 
  •  ሹም ሽሩ በሌሎች 12 መምሪያዎችም እንደሚቀጥል ይጠበቃል
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 12/2010፤ ጥቅምት 2/2003 ዓ.ም):- በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ እና በልዩ ልዩ መምሪያዎች ሐላፊዎች ላይ የተግባር ሽግሽግ፣ ሹም ሽር እና ዝውውር ተደረገ፡፡ በከፍተኛ ምስጢር ተይዞ ዝግጅት ሲደረግበት በቆየው እና ‹‹የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አቅም በባለሞያዎች በመገንባት መልካም አስተዳደርን ያሰፍናል›› የተባለለት ይኸው የተግባር ሽግሽግ፣ ሹም ሽር እና ዝውውር የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መዋቅሮች በቤተ ዘመዳዊ አሠራር በመቆጣጠር አስተዳደራዊ በደሎችን እና ግፎችን የፈጸሙት እና በውስጥ ስማቸው ‹‹የጨለማው ሲኖዶስ›› የሚባለው ቡድን አንዳንድ አባላት ያለ አንዳች የትምህርት ዝግጅት እና ሞያዊ ብቃት ከያዟቸው ወሳኝ የሐላፊነት ቦታዎች እንዲገለሉ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ለውጡ ለቡድኑ አባላት የበጋ መብረቅ እንደሆነባቸው የተዘገበ ቢሆንም ብዙዎች ዘላቂነቱን ይጠራጠራሉ፤ በምትኩ በወሳኝ መልኩ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ሊነሡ የሚችሉ ጥያቄዎችን ከወዲሁ በመላ ለማዳከም የታሰበ የይስሙላ ጥረት አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ሌሎች የጉዳዩ ተከታታዮች ደግሞ፣ ‹‹መንግሥት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ውስጥ የሚታዩትን እና እንደ ዕንቅፋት የሚቆጥራቸውን ተቋማዊ ድክመቶች ምክንያት አድርጎ ከፍተኛ አመራሩን በራሱ ሰዎች በመቆጣጠር ለወቅቱ የዕድገት እና መዋቅራዊ ለውጥ ዕቅድ አፈጻጸም ምቹ መደላድል ለመፍጠር እንዲሁም ሌሎች ፖሊቲካዊ አጀንዳዎቹን ለማስፈጸም ያለውን ፍላጎት እንደሚያሳይ ያስረዳል›› ይላሉ፡፡

ከጥቅምት አንድ ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው እና በአድራሻ ለተሸሚዎቹ በግልባጭ ለልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ብቻ ግልባጭ ተደርጎ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተፈርመው ወጡት ደብዳቤዎች እንደሚያመለክቱት
  1. አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ - የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ
  2. አቶ ደሳለኝ መኰንን - የአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያ ሐላፊ
  3. ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ - የሒሳብ እና በጀት መምሪያ ሐላፊ
በመሆን የተሾሙ ሲሆን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ባልጠበቁት የመጀመሪያው ውሳኔ ግራ ተጋብተው የነበረ ቢሆንም ዘግይቶ በደረሳቸው ደብዳቤ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ደረጃ ከማኔጅመንታዊ ተግባራት ርቀው መንፈሳዊ ጉዳዮችን በመከታተል ተወስነው እንዲሠሩ ታዝዘዋል፡፡

የአስተዳደር እና አቅም ግንባታ መምሪያ ሐላፊ የነበሩት የፓትርያሪኩ የእኅት ልጅ ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደው እና የሒሳብ እና በጀት መምሪያ ሐላፊ የነበሩት በኲረ ትጉሃን ገብረ መስቀል ድራር ወደፊት በልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ውስጥ በሚገኘው ክፍት ቦታ ተመድበው እንደሚሠሩ የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች ከቀድሞው ሐላፊነታቸው ጋራ የሚመጥን ይሁን የሚዛመድ አንዳችም የትምህርት ዝግጅት ይሁን ሞያዊ ብቃት እንደሌላቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡ ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደው ባለፈው ዓመት ሳይገባቸው ከያዙት ሐላፊነታቸው የመነሣታቸውን መርዶ የሰሙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩን አጅብው በሚገኙበት ዐድዋ እንዳ አባ ገሪማ ገዳም ሲሆን መርዶውን እንደ ሰሙ ከአቡነ ጳውሎስ መለየታቸው ተዘግቧል፡፡ በቀጣይ የቤተ ክርስቲያኒቱን የኪራይ ቤቶች በሚያስተዳድረው መምሪያ በሐላፊነት ለመመደብ እንደሚሹ መግለጻቸው የተነገረላቸው ሊቀ ኅሩያን ያሬድ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መራር የጥቅም እና የባለሟልነት ፍልሚያ የገጠሟቸው ወደረኛቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጥቅም ከሚያጋብሱባቸው የቤተ ክርስቲያኒቷ ኪራይ ቤቶች ሊያባርሯቸው እንደ ዛቱ ተገልጧል፡፡

ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር መሻሻል እና አቅም ግንባታ የተጉት በካሩ የሥራ አመራር ባለሞያ እና ምሁር አቶ በድሉ አሰፋ ተመርረው እንዲወጡ በማድረግ ሁነኛ ሚና እንደ ተጫወቱ የሚነገርላቸው በኲረ ትጉሃን ገብረ መስቀል በበኩላቸው ያልደከሙበትን ዲፕሎማ በሸመታ ለማግኘት እያጠያየቁ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ዛሬ ከቀትር በኋላ በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት ከመላው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች ጋራ አዲሶቹን ተሽዋሚዎቹን የማስተዋወቅ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የማሳረጊያ ንግግር ያደረጉት አቡነ ጳውሎስ በመንግሥት ተደረገ የተባለውን ‹‹የመተካካት መርሕ›› አርኣያነት በመከተል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ብቁ ባለሞያነትን እና ርቱዕ እምነትን ማዕከል በማድረግ በተካሄደው እና በቀጣይም በሚካሄደው ለውጥ ማንም አኩራፊ ሊሆን እንደማይገባ መክረዋል፡፡ በመዋቅራዊ ለውጥ እና በዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ ተግባራት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ በሁለተኛነት ከተሾሙት አዲሱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በተጨማሪ ‹‹ልማትን በተመለከተ ሌላ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንደሚሾም››ም ፍንጭ ሰጥተዋል - ፓትርያኩ፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ((picture) በኩላቸው ብዙ ጊዜ ፍግ እየተደረገላት ፍሬ ያላፈራችውን በለስ ምሳሌ በማድረግ ‹‹ቤቱ የነገር እንጂ የሥራ ቤት አልሆነም›› ብለው በመገሠጽ ሁሉም ወደ ሥራው እንዲያተኩር አሳስበዋል፡፡ እንግዶቹ ተሽዋሚዎች ራሳቸውን፣ ትምህርታቸውን እና ሲሠሩባቸው የቆዩ ተቋሞችን በየተራ ያስተዋወቁ ሲሆን ከተሰብሳቢው ሞቅ ያለ የጭብጨባ ድጋፍ ተለግሷቸዋል፡፡ እንደ ቤተ ክህነቱ የውስጥ ምንጮች ገለጻ ሹም ሽሩ ‹‹የብሔር ተዋፅኦን›› መሠረት አድርጎ በሌሎች 12 መምሪያዎች ላይም እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል ከተገለጹት መምሪያዎች በተጨማሪ እስከ አሁን ዝውውር የተፈጸመባቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተ ጉባኤያት እና ሌሎች ትምህርታዊ ሥልጠናዎች ላይ አተኩሮ የሚሠራው የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ አንዱ ነው፡፡ የዚህ መምሪያ ሐላፊ የነበሩት መጋቤ ሥርዐት ዳንኤል ወልደ ገሪማ ወደ ቁልቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ ተዘዋውረዋል፡፡ እኚህ ‹‹የጨለማው ሲኖዶስ›› ተብሎ የሚታወቀው ቡድን አባል የሆኑ ሰው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ረጅም ዓመታትን ከማስቆጠር በቀር በቤተ ክርስቲያኒቱም ይሁን በዘመናዊ ትምህርት የደከሙበት የዕውቀት መስክ እንደሌለ በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ በዝውውሩ የተመደቡበት መዋቅር በአቡነ ጳውሎስ ቀጥተኛ ትእዛዝ የሚንቀሳቀስ እና ከፍተኛ ዘረፋ የሚፈጸምበት መምሪያ በመሆኑ ሐላፊነቱን ‹‹በደስታ መቀበላቸው›› ይነገርላቸዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም የታየውን የቤተ ክህነቱን አስተዳደር የማሻሻል ጥረት ከእ ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደው ጋራ እጅ እና ጓንት በመሆን ካመከኑት አንዱና የዋና ሥራ አስኪያጁ ጸሐፊ የሆኑት ቀሲስ በላይ ጸጋዬ በትምህርት እና ማሠልጠኛው መምሪያ በሐላፊነት ተዛውረዋል፡፡ በቀሲስ በላይ ጸጋዬ የዋና ሥራ አስኪያጁ ጸሐፊነት ቦታ ደግሞ አባ ኪዳነ ማርያም የፓትርያኩ የቅርብ ሰው ተተክተዋል፡፡

ቤተ ክህነቱ ውጭ የመጡት አዲሶቹ ተሿሚዎች ከሳይኮሎጂ፣ ማኔጅመንት እና ፋይናንስ ሞያዎች ጋራ የተያያዙ የመጀመሪያ እና ተጨማሪ ዲግሪዎች ባለቤቶች ከመሆናቸውም በላይ በአዲስ አበባ ኒቨርሲቲ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በመስኩ በመሥራት ከዐሥር ዓመት ያላነሰ ልምድ ያካበቱ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ ለሦስት ዓመት ያህል የሚቆይ ውል ልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ጋራ የፈረሙት አዲሶቹ ሹመኞች ከ4000 - 8000 ብር ወርኀዊ ደመ ወዝ እና ከ500 - 1000 ብር አበል ተቆርጦላቸዋል፤ የገንዘቡ ምንጭ ኮሚሽኑ ከዓለም አቀፉ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን በጎ አድራጊዎች (IOCC) ያገኘው ፈንድ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች እንደሚያስረዱት አዲሶቹ ባለሞያ ሹመኞች ዶ/ር አግደው ረዴ፣ በኮሚሽኑ የአማካሪ ቦርድ አባል ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ፣ አቶ መኩሪያ ታደለ (ከአቡነ ጳውሎስ እና የስደተኞች እና ሕፃናት ጉዳይ መምሪያ ሐላፊ አቶ አዋሽ ገብሩ ጋራ በመሆን) የተመለመሉበት መንገድ እና የተመዘኑበት መስፈርት ይፋዊ ውድድር የሌለበት እና ግልጽነት የሚጎድለው ነው፡፡ የኮሚሽኑ የቦርድ አባል ሆነው ሳለ ያለቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሆኑት ዶ/ር አግደው ረዴ (Picture above) አሿሿም ራሱ ሕግን ያልተከተለ መሆኑ እየተነገረ ነው። 

ለአብነት ያህል የቀድሞው ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ሹመት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተከናወነ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በተለይም ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከሚፈቅደው ጊዜ በላይ በአማካሪነት ስም የኮሚሽኑን ቦርድ አባልነት እና አማካሪነት ርስት ያደረጉት ግለሰቦች ሃይማኖታዊ ዝንባሌያቸው እና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ያላቸው ግንዛቤ ሲታይ የመለመሏቸው ተሿሚዎች ከአስተዳደራዊ ሪፎርም ባሻገር በሚኖራቸው ሚና እና ውጤታማነት ላይ ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሡ አስገድዷቸዋል፡፡

3 comments:

ሽታው /ከቀጨኔ/ said...

እኔ የምለው "በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ"ነው የሚባለው ለመሆኑ ልማት ኮሚሽን ውስጥ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ አለ እንዴ? የሹመኞቹን የእውቀት ደረጃ ብቻ ወይንስ የሀይማኖት ጥንካሬም ማየት አለብን ነው ወይስ እንደ ወንጌሉ መድረክ ቤተ ክህነቱንም አስረክበን እንሟገት ይህን የምለው ዝም ብዬ አይደም ከመልማዮቹ እስከ ተሿሚዎቹ የማውቀው ስላለኝ ነው በቀጣይ እመለስበታለሁ ግን የሚገርመኝ ከሲኖዶሱ አባላት አንዱ አባት ይህንን ዜና ደጀ ሰላም ላይ እንዳዩት ለእኔ መንገራቸው ነው እንግዲህ የቤተ ክርስቲያኒቷ/የቤተ ክህነቱ/ባለቤት ማን ነው? እነ አቶ እና ከነአቶ የማይሻሉት...ጳውሎስ ብቻ???????? ግዴለም!!!

Anonymous said...

egio amlk hoy ere ebakh yebete chrstiann wudket temelket !!!

Dirsha said...

I believ this is the same with the previous B/c if it was realy to the church it could be proposed to the Holy Synod and then asigned. It is to mislide and change people attention. The guys proposed may be the other face of the previous once b/c the are smiply selected by "the patriaric" as usual.I believe the 'patriaric' will not asign true orthodox chiristians since it is not good for his misbehaviors.So still I am frastrated and the government may interfer as usual being on side of the Mafiya group lead by the "patriaric". Lets pray and do what we can. Nothing will be there with the "patriaric"

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)