October 11, 2010

ክርስትናን በኦርቶዶክስ ዐውደ ምሕረት ስንማረው ነገር ግን በፕሮቴስታንት መንገድ ስንረዳው

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 11/2010፤ ጥቅምት 1/2003 ዓ.ም):- ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳን አንድ ዐቢይ ምክንያት አለ። ነገሩ ከዚህቹ የጡመራ መድረካችን ጋር የተገናኘ ነው። የተለያዩ ዜናዎችን፣ አስተያየቶችንና ሐተታዎችን “በጠነከረ መልኩ” (ሐርድ ቶክ እንዲሉ ፈረንጆቹ) ማቅረብ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ የአንባብያንና የተመልካቾቻችን/ ደጀ ሰላማውያን አቀባበል፣ አረዳድና አመላለስ እንዲሁም አመለካከት እንደ የኔ-ቢጤ የልመና ምግብ ምስቅልቅል ያለ ነው። በዝግጅታችን ተደስቶ ካለማወቅ ወደማወቅ በመምጣት ወደ መቆጨት ብሎም አንድ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የሚዘጋጀውን ጨምሮ “እንዲህ ዓይነቱን ነገር እያነሣችሁ ለምን ትበጠብጡናላችሁ፣ ለምን የሚያንጽ ነገር አታስተምሩንም፣ ለምን ሁል ጊዜ አፍራሽ ዜና ብቻ ትዘግባላችሁ?” እስከሚለው ድረስ ብዙ ዓይነት አንባቢ ነው ያለን። ይህንን በተመለከተ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተፈጸመ ስላለው ጥፋት የምንጽፍበት ምክንያት” በሚል ርእስ መልስ መስጠታችን ይታወሳል።

በቁጭት ለተግባር የተዘጋጀውን ትተን “ምንም መጥፎ ነገር አልይ፣ አልስማ” የሚለውን ክፍል ለምን ወደዚህ አስተሳሰብ ሊመጣ ቻለ የሚለውን ለመረዳት የራሳችንን መጠነኛ ፍተሻ ለማድረግ ስንሞክር ቆይተናል። ለጊዜው የተረዳነው የሚከተለውን ነው። እነዚህ ሰዎች ክርስትና ሃይማኖትን በኦርቶዶከስ ዐውደ ምሕረት/ ዐውድ የተማሩ ቢሆኑም አረዳዳቸው ግን ኢ-ኦርቶዶክሳዊ (እቅጩን ተናገሩ ከተባለ ደግሞ ፕሮቴስታንታዊ) ነው ለማለት ደፈርን። ለምን ይህንን እንዳልን እንድናብራራ ይፈቀድልን። የተቃወማችሁንን በጅምላ “ፕሮቴስታንት ናችሁ፣ ኦርቶዶክስ አይደላችሁም” ለማለት እንዳልፈለግንም ከወዲሁ በማስገንዘብ እንጀምር።

የኦርቶዶክስ ትምህርትና አስተምህሮ ከተግባራዊነት ጋር የተያያዘ ነው። ለምሳሌ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ብንመለከት “በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ፀጋ እግዚአብሔር” የምንቀበልበት/ የሚሰጥበት መሆኑን ሊቃውንቱ ያስተምራሉ። በፕሮቴስታንቱ ዓለም ከምግባር ይልቅ “እምነት ብቻ ነው የሚያድንህ፣ በጸጋ ድነሃል” የሚለው ነቢባዊ ጽንሰ ሐሳብ ሲራመድ በኦርቶዶክሳዊው ዓለም ግን “እምነት ያለ ምግባር የሞተ ነው” የሚለው አጽንዖት ይሰጠዋል። ፕሮቴስታንቱ “ኃጢአትህን በቀጥታ ለጌታ ንገረው” ሲል፤ ኦርቶዶክሳዊው ግን “ራስህን ለካህን አሳይ” ብሎ የሚያዝ፣ የሚጨበጥ ያደርገዋል። ፕሮቴስታንቱ “ወደ ሆድ የገባ አያረክስም”፤ “ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ” ብሎ ወደ አስረሽ ምቺው ሲገባ ኦርቶዶክሱ ግን “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅምም” ብሎ ወደ መታቀብ፣ ራስን ወደ መግዛት ያደላል። ፕሮቴስታንቱ አገራችን በሰማይ ነው ብሎ ለሀገር መቆርቆርንና መታገልን ብሎም መሞትን ሲያጣጥል ኦርቶዶክሱ ግን ታቦቱን ይዞ እስከ ዐውደ ጦርነት እየገባ ሞቶ የሀገሩን ዳር ድንበር ያስከብራል። ወዘተ ወዘተ

ይህንን ሁሉ ለማለት የፈለግነው በኦርቶዶክሱ እና በሌላው ዘንድ የክርስትና ትምህርት እና ይትበሃል እንዲሁም ትውፊት ልዩነት መኖሩን ለማሳየት ነው። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በኦርቶዶክስ አደባባይ የሚሰጡ ትምህርቶች እና አረዳዳቸው ከኦርቶዶክሳዊቱ ርትዕት ቤተ ክርትስቲያን እያፈነገጠ የመጣ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። በተለይም ወጣቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የመትመሙን ያህል አንዳንድ አረዳዱ ግን ፕሮቴስታንታዊ የሚመስልበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ለምሳሌ ያህል “ኢየሱስ ብቻ” የሚለው ፕሮቴስታንታዊው ትምህርት ከመሰልጠኑ የተነሣ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል” የሚለው ሐዋርያዊ ቃል እንዲሁም “ነገረ ቅዱሳን” እና በክርስቲያናዊ ባህላችን ለዘመናት የነበረው ኢትዮጵያዊነት የማይስማማቸው ብቹዎች መኖራቸውን እንመለከታለን (ኤፌ. 2፡20)። ሰባኪ የሚባሉት ሳይቀሩ “ማርያም ማርያም ማለት በዛ፤ ኢየሱስ የሚለው አነሰ” እስከማለት ደርሰዋል። ይህ የነገረ ድኅነትን ትምህርት፣ ምሉዕ የሆነውን ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሃይማኖት ካለመረዳት የሚመጣ ነው።

በሌላም በኩል በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሀገር፣ በቤተሰብም ሆነ በአካባቢ ለሚፈጠር እና የእነርሱን ሱታፌ ለሚፈልግ ነገር ጀርባቸውን እየሰጡ “ጌታ ይፍታው” የሚለው አካሄድ ኦርቶዶክሳዊ ነው ለማለት ይከብዳል። የማርያም እና የማርታ ወንድም የሆነው አልአዛር በሞተ ጊዜ የነበረውን ታሪክ እዚህ ላይ ማንሳት ያስፈልጋል። ጌታ ወደነማርታ ቤት ሲመጣ የአልአዛርን መሞት ነገሩት፤ እርሱም በአምላክነቱ ሁሉን የሚያውቅ ቢሆንም ወዴት ቀበራችሁት ብሎ ጠየቃቸው፣ እነርሱም ወደተቀበረበት ቦታ ወሰዱት፣ እርሱም ከመቃብሩ ላይ የተጫነውን ድንጋይ እንዲያነሱት አዘዛቸው፤ ከዚያም ከሞት ሸለብታ፣ ከመቃብር አልጋ በቃሉ “አልአዛር አልአዛር” ብሎ ቀሰቀሰው (ዮሐ. 11፡38-44)።

በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ቁምነገሮችን እናገኛለን። በዋነኝነት ግን የሰውን ድርሻ እና የአምላክን ድርሻ ለይተን እንድንገነዘብ ያስተምረናል (ዮሐ. )። የሰው ድርሻ ድንጋዩን መገልበጥ ሲሆን የአምላክ ድርሻ ደግሞ የሞተውን ሕይወት ሰጥቶ መቀስቀስ ነው። እንዲህ ዓይነቱ እምነትን እና ምግባርን ያዋሐደ ሕይወት ነው ኦርቶዶክሳዊነት። በጅምላ ድንጋዩን ሳይፈነቅሉ “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ” ማለትን ግን ኢ-ኦርቶዶክሳዊ/ ፕሮቴስታንታዊ እንለዋለን። በተጨማሪ አንድ ባህላዊ አፈ ታሪክ እንጥቀስ።

አንድ የወሎ ሙስሊም ናቸው አሉ። በግ ጠፍቷቸው ፍለጋ ሲጓዙ አንድ ሌላ ሰው ያገኛሉ። ምን እንደሚፈልጉ፣ ወዴት እንደሚሄዱ ይጥይቃቸዋል። እርሳቸውም “በግ ጠፍቶኝ እየፈለግኹ ነው” ይሉታል። ያ መንገደኛም ጅላጅል አማኝ መሳይ ሰነፍ ሰው ኖሮ “አላህን እመን፣ እርሱ ይጠብቃቸዋል፣ አንተ ምን አስለፋህ” ይላቸዋል። እርሳቸውም ሲመልሱ “አላህንም አምናለኹ፣ በጎቼንም እጠብቃለኹ” አሉት ይባላል። የዛሬ አማኝ መሳይ ሰነፎች ሕይታዋችን ከእኒህ አዛውንት ሙስሊም አባባል እንኳን ያነሰ ሆኖ እናገኘዋለን።

ስለ ቤተ ክርስቲያን ችግር፣ መከራ እና ስለ አበው ስቃይ፣ ስለ እናታችን ቤተ ክርስቲያን ንብረት ውድመት ሲነገራቸው “እግዚአብሔር ያውቃል፣ እኛ ምንም ማድረግ የለብንም፣ ዋናው መጸለይ ብቻ ነው” የሚሉ አማኝ መሳይ ሰነፎች ብዙ ናቸው። መጸለይ ይገባል። ጸሎት የክርስቲያን ዋና መሣሪያ ነው። ነገር ግን “ጸሎት ላይ ነኝ” እያሉ በጊዜ ማድረግ ያለበትን ሳያደርግ የሚቀር ግን ጥፋተኛ ነው እንጂ ሙያተኛ አይደለም። “በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው” እንዲል ቅዱስ ያዕቆብ መልካሙን ነገር እያወቅን፣ እየተረዳን ነገር ግን አለመሥራት ኃጢአት ነው (ያዕ. 4፡17)። እንኳን በዓለም ያለን እኛ በገዳም በዱር በገደል፣ በጥሻው በፍርክታው ውስጥ ያለ ባህታዊ እንኳን “ጸሎት ላይ ነኝ፣ ምግቤን እግዚአብሔር ያምጣልኝ” አይልም። ጸሎቱን ሲጸልይ ቆይቶ ቅጠሉንም፣ ፍሬውንም ለመለቃቀም የሚወጣበት ጊዜ አለው። ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት እና ኑሮ ይህ ነው። የዘመናችን አንዳንድ ሰባክያን ያደነዘዙት ብዙ ሕዝብ “ፍቅር፣ የሰውን ኃጢአት መሸፈን፣ እግዚአብሔር ያውቃል” በሚሉ ቃላት ሥር ተደብቆ ቤተ ክርስቲያኑ ስትጎዳ ዝም ብሎ ይመለከታል። ይህንን በርግጥም የኦርቶዶክስ ሕይወት የገባው ነው ለማለት ይከብደናል።

ለሚጠይቁን መልሳችን ይህ ነው።
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን


+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 2/2010፤ መስከረም 22/2003 ዓ.ም):- ለምንድን ነው ስለ ቤተ ክርስቲያን ገመና የምታወጡት? ለምን የሚያንጽ ሌላ ነገር አትጽፉም? ከባቴ አበሳ ለምን አትሆኑም? የሰውን ኃጢአት ብቻ ለምን ታወጣላችሁ?” ወዘተ ወዘተ የሚለው የአንዳንድ ደጀ ሰላማውያን አስተያየት እና ጥያቄ ነው። መልሳችን እና አመክንዮዋችን እነሆ።
ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች ናት። ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ስለ ቤተ ክርስቲያኑ ያገባዋል። ከምእመኑ እስከ ሐጻዌ ኆኅቱ፣ ከዲያቆኑ እስከ ሊቀ ጳጳሱ፣ አገልግሎታቸው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ድርሻ አለው። በዚህ ዘመን የድርሻ መመሰቃቀል፣ የቦታ መለዋወጥ፣ የአቅጣጫ መቀያየር ስለተፈጠረ ለምን ብለን እንጠይቃለን።
ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት የተፈጠሩባት ውሳጣዊም አፍአፈዊም ችግሮች ቢኖሩባትም አሁን የተከሰተውና የገነነው ግን በዓይነቱ እና በዘላቂነቱ ወደር አልተገኘለትም። ይህም የቤተ ክህነቱ ሞራላዊ ድቀት (Moral Decadence) ነው- በአጭሩ ለማስቀመጥ።
ቤተ ክህነት፣ በየትም ሀገር ያለው ቢሆን ትልቁ ለሀገር የሚሰጠው ጥቅም ሞራላዊ ልዕልና እና የበላይነት ነው። ቤተ ክህነት ከቤተ መንግሥት የበለጠ የሚፈራውና የሚከበረው የሚያዘው ጦር ስላለው፤ እሰርልኝ፣ ጣልልኝ፣ ግረፍልኝ፣ ቀፍድድልኝ ስለሚል አይደለም። ለዚያማ ጉልበቱም፣ ጦሩም፣ ዝናሩም ያለው ከቤተ መንግሥት ነው። ነገር ግን በየትኛውም ዘመን አብያተ መንግሥቱ ካላቸው ድምጽ የበለጠ የሚሰማው ቤተ ክህነቱ የሆነበት ምክንያት በዚሁ ባላት የሞራል ልዕልና ነው። ቤተ መንግሥቱ ሥጋችን ቢቆጣጠርም ነፍሶቻችን ግን የቤተ ክህነቱ ናቸው ማለት ይቻላል። አሁን ግን ይህ ሐሳብ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ሞራላዊ ልዕልና ማለት ምናልባት በአጭሩ ለመበየን (ዲፋይን ለማድረግ) ቤተ ክህነቲቱ ከእግዚአብሔር በተሰጣት ጸጋ እና ሥልጣን የመንፈስ ልጆቿ ቢያጠፉ ቀጥታ አስቀጥታ፣ ጸልያ አማልዳ የምታስምር ከመሆኗ እና ከእግዚአብሔር ጋር ባላት ግንኙነት ያገኘችው ነው። የቤተ ክህነት የሥልጣን ምን እግዚአብሔር ነው። ቤተ ክህነቱን የሚመሩት አካላት ከእግዚአብሔር ዓላማ ሲወጡ እና ሞራላዊ ልዕልናቸው ሲጓደል፤ ሊመሩት የቆሙለት ሕዝብ ከእነርሱ ተሽሎ ሲገኝ ያን ጊዜ ቤተ ክህነት ቁልፏን ትነጠቃለች ማለት ነው። በፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና የሆነው ይህ ነው። ነገር ግን ይህ በእኛ ቤተ ክህነት የተጀመረ ሳይሆን ቀድሞም በሌሎች ታይቶ የነበረ ነው። ለምሳሌ በቫቲካንና በእስክንድርያ።
1. ቫቲካን

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቫቲካን ከፍተኛ ሞራላዊ ድቀት ውስጥ ገባችበት ዘመን እንደነበር የአደባባይ ምሥጢር ነው። መሪዎቿ በሥጋዊ ፈቃድ ተይዘው አምላካዊውን ሕግ እየተላለፉ የራሳቸው ደንብና መመሪያ አውጥተው ይገዙ የነበረበት ዘመን ነበር። የየራሳቸው ኢ-ክርስቲያናዊ አካሄድ ሳያንሳቸው የኃጢአት ማስተስረያ ቲኬት እየሸጡ፣ ክርስቲያኑ ሕዝብ በገንዘቡ ብዛት ከበደሉ እንደሚጸዳ፣ የሞቱ የጥንት ዘመዶቹም አሁን እርሱ በሚገዛው ቲኬት እንደሚማሩ እያስተማሩ በበደላቸው ደነደኑ። ይህንን የሚቃወማቸውን ሁሉ ከፍ ብለው አንገቱን ዝቅ ብለው ባቱን እያስቆረጡ በክፋታቸው ጸኑ። ይህ ግፍ እና መከራ ተጠራቅሞ ጉድ ወለደባቸው። ይህ ማርቲን ሉተር ነው።፡ ሉተር ካቶሊክን ሰንጥቆ አዲስ እምነት ፈጠረባቸው።
2. እስክንድርያአቡነ ዮሳብ ከፓትርያርክ ቄርሎስ 6ኛ ቀድመው የነበሩ ፓትርያርክ ሲሆኑ ገነዘ በመቀበል ሥልጣነ ክህነትን ይሰጣሉ እስከመባል የደረሱ፤ በዚህም ምክንያት በሕዝብ ግፊት ከመንበረ ሥልጣናቸው ወርደው በገዳም የተጋዙ፤ በዘመነ ፕትርክናቸው የብዙ ኮፕት ክርስቲያኖችን አንገት ያስደፉና በዚህም ምክንያት በአማኙ ሕዝብ መካከል ሰፊ መከፋፈልና ብጥብጥ ተፈጥሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላም እንዳታገኝ ያደረጉ ፖፕ ነበሩ። ቤተ ክህነታችን አሁን የሚገኝበት ደረጃ እና ሁኔታ በአቡነ ዮሳብ ዘመን የነበረችውን የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን ያስታውሰናል።
ቫቲካን በዚያ የበደል ተግባሯ ሉተርን የመሰለ መቅሰፍት የላከባትን ያህል እስክንድርያን ግን በምሕረቱ ተመልክቷት ቅዱሱን አባት አቡነ ቄርሎስን አስነስቶላታል። እርሳቸውም በሐዘን ልቡ የደማውን ምእመን በፀጋቸው እያጽናኑ እና እያከሙ በመፈወስ የሐዘን ማስረሻ፣ የአዲስ የትንሣኤ ዘመን ብሥራት ሆነዋል።
3. ኢትዮጵያቤተ ክህነታችን የገባችበት ዝቅጠት ቫቲካንና ዘመነ ዮሳብ እስክንድርያ የገቡበትን ይመስላል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ነቢዩ እንዳለው “አክሊል ከራሳችን ወድቋል” (ሰቆቃወ ኤርምያስ 5፤16)። እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ምድር አሸዋ በበዙት ቅዱሳን አበው እና ቅዱሳት እመው ጸሎት በቫቲካን የደረሰው ዓይነት መከራ እና ቅጣት፣ በእስክንድርያ የነበረው ዓይነት መከፋፈልና ጥፋት እንደማይመጣባት እናምናለን።
አጥፊውና ጥፋቱ
ከላይ ከፍ ብለን እንደተመለከትነው የሞራል ልዕልና መናጋት አማኙን የሚያምነው ነገር ላይ ያለውን ናት ጥያቄ ውስጥ ስለሚጥለው ለማንኛው ቤተ እምነት ከባድ ፈተና ነው። ቤተ ክርስቲያናችን የዮዲት ጉዲት እሳትም ሆነ የግራኝ ሰይፍ አላንበረከካትም እንበል እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ከውስጥ የሚመጣ ፈተና ግን ቀላል ነው ማለት አንችልም። አንድን ሰው ሊያስፈራው የሚችለው የመጨረሻው ከባድ ፈተና ሞት ቢሆንም ለክርስቲያን ግን ስለ ሃይማኖቱ የሚከፍለው ዋጋ ሰማዕትነት ስለሚሆንለት በታላቅ ክብር ይቀበለዋል። የውስጥ ፈተናዎች እንዲህ ዓይነቱን ሰማዕትነት ዋጋ የሚያሳጡ ስለሚሆኑ ከባድነታቸው ከግራኝ ሰይፍ እና ከዮዲት እሳት ይከፋል።
አንዳንድ የዋህ የደጀ ሰላም አንባቢዎች ዜናዎቻችንን እና ሐተታዎቻችንን እየተመለከቱ ከመሳቀቅ ተነሣ “ለምን የሰው ገመና ታወጣላች?” ይላሉ። በየትኛው ዜናችንም ሆነ ሐተታችን የአንድን ሰው የግል ሕይወት ተከታትለን ያንን ግለሰብ ለማሳጣት ሙከራ አላደረግንም። ከንስሐ አባቱ ጋር ሊጨርሰው የሚችለውን ጉዳይ ወደ አደባባይ አውጥተን “ገመናውን” አልገለጥንም። ጉዳያችን ከግለሰቦቹ አልፎ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ሲሆንና ይህም በተደራጀ የማፊያ መንገድ ሲፈጸም ፤ በዚህም ለሚቀጥለው ትውልድም መጥፎ አርአያ ትቶ በሚያልፍ መልኩ ሲከናወን ነው።
ለምሳሌ በወ/ሮ እጅጋየሁ እና በግበረ አበሮቻቸው የሚፈጸመውን ዝርፊያ እና ቅ/ሲኖዶሱንና በጠቅላላውም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን በመውረስ የወንበዴዎች ዋሻ የማድረጉን ዘመቻ እንመልከት። በዚህ ጉዳይ ውስጥ ስለሴትዬዋ የግል ሕይወት ምንም ብለን አናውቅም። ያ የግል ሕይወታቸው ነው። እኛ የምንጠይቀው “እጆ ከቤ ክርስቲያናችን ላይ ያንሱ፤ ኤልዛቤል አይሁኑ” ነው።በሌላ ምሳሌ በቅዱስ ፓትርያርኩ ዘመድ አዝማድ፣ አምቻ ጋብቻ የሚሿሿሙትን፤ የሚዘርፉትን፤ በሽልማት ስም ለመንደላቀቂያ የሚሰጣጡትን የመኪና እና የቁሳቁስ ጋጋታ እናንሳ። ይህ ሁሉ የሚደረገው በግል ገንዘባቸው ቢሆን ምን ገዶን። የምንናገረው ይህ ሁሉ አስረሽ ምቺው የሚፈጸመው ከድሃው ምእመን በሚሰበሰበው ሳንቲም መሆኑ ነው። ለብፁዕ አቡነ ኤፍሬም መኪና መገዛቱ ምና ያሳዝነናል? መቸም እርሳቸውን የሚያክል አባት በእግሩ ይሂድ አይባልም። ቄያችን ለምን የ1.8 ሚሊዮን ብር መኪና የሚል ነው? ብሩ ከየት መጣ? ማን ፈቀደው? በርግጥስ ለአንድ አረጋዊ አባት እንዲህ ያለ የቅንጦት መኪና አስፈልጓቸው ነው ወይስ በእርሳቸው ስም የሚጠቀሙ አሉ?
ለአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ ለሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ መኪና ቢሰጣቸው አንቃወምም። ገንዘቡ የሀ/ስብከቱ አጥቢያዎች ሰበካ ጉባዔያት ሳያውቁት በተወሰኑ መነኮሳት እመሰገን ባይነት እየተመዠረጠ የተገዛ መሆኑ ግን ጉዳዩን የእኛም ጉዳይ ያደርገዋል። ይህንን አልን እንጂ ስለ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን የግል ሕይወት ምንም አልተናገርንም፤ አንናገርምም። ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያላቸው እንቅስቃሴ ግን የግላቸው ሳይሆን የጋራችን ነውና ያገባናል።ከሁሉ የገረመንን አንድ ጉዳይ እናንሣ። በጋሻው ደሳለኝ የተባለ ሰው በግሸን ማርያም የእመቤታችንን ክብር የሚያሳንስ ቃል ያውም በአደባባይ መናገሩን እያስነበብን አንዳንድ ምእመናን “ለምን ትነኩታላችሁ፣ ለብቻው ለምን አትነግሩትም?” ሲሉ አደመጥናቸው። እንዲህ ያለው ሰው በርግጥም ኦርቶዶክስ ነው ለማለት ይከብደናል። በአደባባይ የተነገረ ኑፋቄና ድፍረት በጓዳ የሚስተካከለው ከመቼ ወዲህ ነው? አንድን ግለሰብ መውደድና መከተል ሌላ፤ ሃይማኖትን ማስቀደም ሌላ። ዛሬ ስለ እመቤታችን ክብር ለመናገር ካፈርን ነገ ምን ይመጣ ይሆን? ይህኛው የነበጋሻው ቡድንና መስመሩ ከላይ ከጠቀስነው የሞራል ልእልና ዝቅጠት የሚመደብ ቢሆንም ከገንዝቡና ጥቅማ ጥቅሙ አልፈው ወደ እምነቱም ሽርሸራ ስለተሻገሩ በሌላ ጊዜ እንመለስባቸዋለን።
በጠቅላላው ቤተ ክህነታችን በዚህ ዓይነት የሞራል ስብራት ላይ ይገኛል። አስተዳደሩ በመንፈሳዊ ሕግ የሚመራ ካለመሆኑ ጋር መንግሥትም በሀገሪቱ ሕግ ለመዳኘት እንኳን ዝግጁ የሆነ አይመስልም። ይህንን የምንለው በጭፍን ጥላቻ ወይም በፖለቲካው ስሌት ከተመለከትነው ፀረ-ኢሕአዴግ ስለሆንን ሳይሆን ራሱ የመንግሥት የፍትሕ አካሉ ቤተ ክህነቱ ከጥፋት ወደ ጥፋት እንዲሸጋገር ሽፋን እየሰጠው ስለሆነ ነው።

  • አምና በዚህ ሰሞን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በሮቻቸው በማፊያዎች (የመንግሥት ሰዎች ናቸወ የሚሉም አሉ) ተሰባብሮ አረጋውያን አባቶች አደጋ ላይ ሲወድቁ መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ አላደረገም፤ ከዚያም ወዲህ ቢሆን የጥፋቱን ፈጻሚዎች ተከታትሎ ለፍርድ አላቀረበም፤ ጉዳዩን አንድም ጊዜ በይፋ አልተናገረም።
  • ቤተ ክህነቱን “ያልመተሾመች ፓትርያርክ” የሆነች እስኪመስል ድረስ የምታሽከረክር አንዲት ሕገ ወጥ ሴት መሆኗን ሚዲያዎች በሙሉ ደጋግመው እየጻፉና ሕዝቡም ስሞታውን እያሰማ መንግሥት ለሕዝብ ወገንተኝነቱን የሚያሳይ ምንም እንቅስቃሴ አላሳየም፤ ይህም ለወንጀሎኞቹ ከለላ ሆኗል የሚለውን ጥርጣሬ አጠናክሮታል፤
  • ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ የወጣ ተግባር እንደሚፈጽሙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባሉበት ሳይቀር እየተነገረ መንግሥት ግን አሁንም ለፓትርያርኩ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ድጋፍ እየሰጠ ነው።
  • ከዚህ አንጻር ሰሞኑን በአዋሳው የሚዲያ ዐውደ ጉባዔ ላይ ሙስና በቤተ ክህነቱ እንደተንሰራፋ፣ ይህንንም መንግሥት እንደተገነዘበው ለማስረዳት የተደረገው ሙከራ መልካም ጅምር ቢሆንም በቂ ላለመሆኑ ግን ራሱ መንግሥትም ያውቀዋል። መንግሥት ከእንቅልፉ እስኪነቃ እና ሕግ በተሠራበት ሀገር ያለ ሕግ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚዘርፉ እና የሚያዋርዱ እስኪስተካከሉ እኛም እንጽፋለን።


እንግዲህ ይኼው ነው። በቂ ምክንያት ነው ብለን እናምናለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፣


አሜን

4 comments:

123... said...

ፕሮቴስታንታዊ ሀሳብማ ውጤቱ በ አፍሪካ ተሞከረ ። ደዝሞን ቱቱ አንዳሉት
''ፈረንጆቹ ሲመጡ መሬቱ የ አኛ መፅሐፉ የነሱ ነበር አጎንብሳችሁ ፀልዩ አሉን አጎነበስን ቀና ስንል መሬቱ የ አነሱ መፅሐፉ ለ አኛ ሆነ '' ያሉትን ልብ ይሏል ።
ዛሬ ፕሮቴስታንት የ አፍሪካውያንን ስነ ልቦና ሰልቦ ለ አጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ዳርጎአቸዋል ። አኛ ከ አባቶቻችን አንበልጥም ብለን ስናስብ ሁሉ ይከሰትልናል ። አንዳላችሁት ለምን ? ብሎ የማይጠይቅ ለ መፍትሄውም የማይነሳሳ በ አራሱ ምውት ነው ።
አዚህ ላይ አንድ አባት የተናገሩት ምሳሌ ልጥቀስ ። አንድ ወጣት ልጅ ወደ መምህረ ንስሃው ይቀርብና አባቴ ለምንድነው ፕሮቴስታንት ውስጥ ሹክቻቸው ብዙ አይሰማም ውስጥ ለውስጥ ነው የ አኛ ኦርቶዶክስ ግን በ አደባባይ ይሰማል? ብሎ ይጠይቃል።አባትም ቀጥታ ከ ቤተክርስትያን ጉአሮ ወዳለው የ መቃብር ቦታ ወሰዱት አና '' ልጄ አዚህ ምን ይሰማሃል አሉት?'' ምንም አይሰማኝም ብሎ መለሰ ። ቀጥለው ወደ ቤተክርስትያን ቅፅር ግቢ ወስደው አዝህስ ምን ትሰማለህ? አሉት ማህሌት ይሰማኛል የሰዎች ድምጽ ይሰማል አላቸው። አየህ አሉ አኛ አባት ሙታን መንደር ድምፅ የለም ሕያዋን መንደር ግን ድምፅ አለ። ሰይጣን ያለው ደሞ ህያዋንን ልዋጋ ነው አንጂ ሙታንን አደለም አሉት።ልጁም ተገርሞ ወደ ቤቱ ሄደ ።አና አናውራ ካልን ፕሮቴስታንታዊ ትምርት ብዙ ጉድ አለው ።

Anonymous said...

እጅግ እጅግ ትክክል ናችሁ፡፡ እውነት መናገር የድኅነት መንገድ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ቅዱስ ጊዮርጊስና ዱዲያኖስን ምን ያጣላቸው ነበር? ሰማኝታትስ እንዴት ይፈጠራሉ?
እባካችሁ በርቱና እውነትን መናገር ቀጥሉበት፡፡ ይእፉኚት ልጆችን የእርግብ ልጆች አትበሉአቸው፡፡ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክፉ ወሬ የሚናገር ሆኖ አይደለም አይሁድን በግብራቸው እናንት የነፍሰገዳይ ልጆች ብሎ የጠራቸው፡፡ ይልቁንም እውነት ስለሆነ ነው፡፡

tesfaye said...

ፕሮቴስታንታዊ ሀሳብማ ውጤቱ በ አፍሪካ ተሞከረ ። ደዝሞን ቱቱ አንዳሉት
''ፈረንጆቹ ሲመጡ መሬቱ የ አኛ መፅሐፉ የነሱ ነበር አጎንብሳችሁ ፀልዩ አሉን አጎነበስን ቀና ስንል መሬቱ የ አነሱ መፅሐፉ ለ አኛ ሆነ '' ያሉትን ልብ ይሏል ።
ዛሬ ፕሮቴስታንት የ አፍሪካውያንን ስነ ልቦና ሰልቦ ለ አጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ዳርጎአቸዋል ። አኛ ከ አባቶቻችን አንበልጥም ብለን ስናስብ ሁሉ ይከሰትልናል ። አንዳላችሁት ለምን ? ብሎ የማይጠይቅ ለ መፍትሄውም የማይነሳሳ በ አራሱ ምውት ነው ።
አዚህ ላይ አንድ አባት የተናገሩት ምሳሌ ልጥቀስ ። አንድ ወጣት ልጅ ወደ መምህረ ንስሃው ይቀርብና አባቴ ለምንድነው ፕሮቴስታንት ውስጥ ሹክቻቸው ብዙ አይሰማም ውስጥ ለውስጥ ነው የ አኛ ኦርቶዶክስ ግን በ አደባባይ ይሰማል? ብሎ ይጠይቃል።አባትም ቀጥታ ከ ቤተክርስትያን ጉአሮ ወዳለው የ መቃብር ቦታ ወሰዱት አና '' ልጄ አዚህ ምን ይሰማሃል አሉት?'' ምንም አይሰማኝም ብሎ መለሰ ። ቀጥለው ወደ ቤተክርስትያን ቅፅር ግቢ ወስደው አዝህስ ምን ትሰማለህ? አሉት ማህሌት ይሰማኛል የሰዎች ድምጽ ይሰማል አላቸው። አየህ አሉ አኛ አባት ሙታን መንደር ድምፅ የለም ሕያዋን መንደር ግን ድምፅ አለ። ሰይጣን ያለው ደሞ ህያዋንን ልዋጋ ነው አንጂ ሙታንን አደለም አሉት።ልጁም ተገርሞ ወደ ቤቱ ሄደ ።አና አናውራ ካልን ፕሮቴስታንታዊ ትምርት ብዙ ጉድ አለው ።

October 11, 2010
Anonymous Anonymous said...

እጅግ እጅግ ትክክል ናችሁ፡፡ እውነት መናገር የድኅነት መንገድ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ቅዱስ ጊዮርጊስና ዱዲያኖስን ምን ያጣላቸው ነበር? ሰማኝታትስ እንዴት ይፈጠራሉ?
እባካችሁ በርቱና እውነትን መናገር ቀጥሉበት፡፡ ይእፉኚት ልጆችን የእርግብ ልጆች አትበሉአቸው፡፡ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክፉ ወሬ የሚናገር ሆኖ አይደለም አይሁድን በግብራቸው እናንት የነፍሰገዳይ ልጆች ብሎ የጠራቸው፡፡ ይልቁንም እውነት ስለሆነ ነው፡፡

October 12, 2010

Anonymous said...

ኦርቶዶክሳዊ ለሀገሩ ህልውና የሚዋጋ ነው አልከው? ለመሆኑ የቤተ ክህነት ሰው ነህ የጻፍከው? አረ በጣም ያሳፍራል። ለሀገሩ ህልውና የሚዋጋው ኢቲዮጵያዊ እንጂ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም። በመጀመሪያ ደርጃ ጭንቅላትን ሰፋ ማድረግ ያስፈልጋል። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አለም አቀፋዊት እንጂ አገር አቀፋዊት ብቻ አይደለችም። የግብጽ ኦርቶዶክሶች ለኢትዮጵያ ካልተዋጉ ኦርቶዶክስ አይደሉም ልትል የቃጣህ ተመስላለህ። ጥቅሶችን ደግሞ ማን እንዳቀበለህ እግዚአብሄር ይወቀው። ከጽሁፍቅ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርትንና መጻህፍቶችዋን ብዙም እንደማታውቃቸው ያስታውቃል። አዎ ልክ ነህ አምነት ከምግባር ጋር አይለያዩም። ግን በስራዬ እጸድቃለሁ ብለህ የምታስብ ከሆነ good luck! በትክክል የሚያምን ሁሉ ፍሬ ያፈራል። ያ ምግባር ይባላል እሽ? አባቶቻችን ወደገዳም የገቡት ለመጽደቅ ብለው ይመስልሀል? አይደለም ያዳናቸውን አምላካቸውን ለማመስገንና ክርሱ ጋር በጸጥታና በጸሎት ለመኖር ነው። አይ መሸወድ! አባክህ በጻህፍትን በጥሞና መርምር። ደሞ ቤተክርስቲያናችንን አታሳፍር። ለሊቃውንቱ ተውላቸው እንዲህ አይነቱን ነገር።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)