October 5, 2010

በሙስናና ኑፋቄ የሚከሰሱት የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ከሐላፊነታቸው ተነሡ

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 5/2010፤ መስከረም 25/2003 ዓ.ም):- የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ ሥራቸውን በአግባቡ አልተወጡም ባለባቸው ሃይማኖታዊ ችግር የተነሣ ከሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ መምሪያዎች፣ ከማኅበረ ካህናት እና ከማኅበረ ምእመናን ጋራ ተስማምተው መሥራት አልቻሉም፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መካከል መስማማት እንዳይኖር ይጥራሉ፤ የሀገረ ስብከቱን እና የሦስት አድባራትን በርካታ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ያላቸውን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ኀይለ ማርያም ወልደ ሳሙኤልን (ፎቶዎችን ይመልከቱ) ከሐላፊነት አነሣ። የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ በሀገረ ስብከቱ መዋቅሮች ውስጥ ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅነታቸው የዓላማ ቁርኝት ያላቸው እና በሙሰኛነታቸው የጥቅም ተባባሪ የሆኑ ርዝራዦቻቸው ተጣርተው እንዲቀርቡላቸው መመሪያ አውርደዋል፡፡
በቁጥር 2/ጽ/ሀ/44/2003 በቀን 18/01/2003 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ ተፈርሞ በወጣው እና በአድራሻ ለሥራ አስኪያጁ፣ በግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት እና ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተጻፈው ደብዳቤ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ የሥራ አስኪያጁን ችግሮች ለማጣራት በየደረጃው ያደረጋቸውን ጥረቶች ይዘረዝራል፡፡ በዚህ መሠረት በሊቀ ጳጳሱ የሚመራው እና የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሐላፊዎች የሚገኙበት የአስተዳደር ጉባኤ መስከረም 12 እና 17 ቀን 2003 ዓ.ም ከሀገረ ስብከቱ አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ፀሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች እና ቁጥጥሮች ጋራ በተከታታይ በተደረጉ ስብሰባዎች በተወሰዱ ግንዛቤዎች ላይ ተመሥርቶ መወያየቱን አመልክቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መስከረም 17 ቀን 2003 ዓ.ም ከደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ማኅበረ ካህናት ጋራ መምከሩንም ገልጧል፡፡ በውይይቱ እና በምክክሩ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ኀይለ ማርያም ወልደ ሳሙኤል በሥራ አስኪያጅነት ከተመደቡበት ካለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ ሥራቸውን በአግባቡ ሲሠሩ እንዳልቆዩና ራሳቸውም የጤና ችግር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ማመልከታቸውን አሳውቋል፡፡ በመሆኑም ሥራ አስኪያጁ በተወሰደባቸው ርምጃ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ እስኪሰጡበት ድረስ በእጃቸው የሚገኘውን የሀገረ ስብከቱን ንብረት ለሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ እንዲያስረክቡ አዝዟቸዋል፡፡

መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ኀይለ ማርያም በዋልድባ ገዳም ከመጋቢት - ሚያዝያ ወር 1992 ዓ.ም የወፍጮ እህል እየመዘኑ እና አህያ እየጠበቁ በመቆየታቸው ብቻ ማስረጃ የማያቀርቡበትን ምንኩስና ተቀበልኩ ብለው በስሙ ሲጠሩበት ቆይተዋል፡፡ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከሄዱበት እና በምሥራቅ ሐረርጌ - ደደር እና ጉርሱም በዲቁና ማገልገል ከጀመሩበት ከ1986 ዓ.ም አንሥቶ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡ በመጀመሪያ ስማቸው ዲያቆን ካፒታል በኋላ ጌራ እየተባሉ በሚታወቁበት ወቅት በሃይማኖት ሕጸጽ ተጋልጠው በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ከነበሩበት ደብር ተባረዋል፡፡ በዋልድባ ለአንድ ወር ቆይተው ቆብ ደፍተው ተመልሰው በባሌ ሀገረ ስብከት ከቆዩ በኋላ በዋልድባ ገዳም መመንኮሳቸውን ገልጠው ብፁዓን አባቶችን በማሳሳት ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ድሬዳዋ መጥተው የሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን ለሦስት ዓመት ቆይተዋል፡፡

በአስተዳዳሪነት እንደተሾሙ በአጥቢያው ሥር የሚገኘውን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ግቢ ጉባኤን ጽ/ቤት በመዝጋት ከማኅበሩ ጋራ እንደማይሠሩ በዐውደ ምሕረት ላይ ሳይቀር በስድብ በመግለጽ፤ ከሰንበት ት/ቤቶች እና ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሐላፊዎች ጋራም ተጋጩ፡፡ በዚህም ከሀገረ ስብከቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በሚገኝበት የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል አስተዳዳሪ ሆነው በቆዩባቸው ዘጠኝ ወራትም ቀደም ሲል በደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን 20‚000 ብር በመዝረፍ ያካበቱትን ልምድ የካቴድራሉን ሕንፃ በመከራየት ወበራ መድኃኒት ቤትን ከከፈቱት አንድ ምእመን ለካቴድራሉ ገቢ መሆን ያለበትን ሌላ 20‚000 ብር ተቀብለው በግል አካውንታቸው አስገቡ፡፡ በውጭ ከሚኖሩ ምእመን ለሰፈረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ምንዛሬ የተላከውን መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብም ጠልፈው እንዳስቀሩ የደብሩ ልማት ኮሚቴ አባላት ይናገራሉ፡፡ የግለሰቡ ዘራፊነት ከሀገረ ስብከቱ በተላኩ አጣሪዎች የተረጋገጠ ቢሆንም አስተዳዳሪውን ግን በየካቲት ወር 2002 ዓ.ም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከመመደብ አልከለከላቸውም ነበር፡፡

ላለፉት ሰባት ወራት ሥራ አስኪያጁ ቀደም ሲል በጀመሩት አኳኋን በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች እና በሀገረ ስብከቱ መዋቅሮች ውስጥ በውጭ ከሚገኙ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነት እና የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ አካላት ጋራ በመቀናጀት ጭምር የዓላማ እና የግብር አጋሮቻቸውን በማብዛት፣ ማኅበረ ካህናቱን በአደባባይ በማንቋቋሽ፣ የክህነቱን የውስጥ አገልግሎት (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን) በሚያስነቅፍ አኳኋን ያልተገቡ ተግባራትን በመፈጸም፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ቢመጡም ተስማምተው በመሥራት በሚታወቁት የሀገረ ስብከቱ ሐላፊዎች እና ሊቃውንት መካከል ሰላም እንዳይኖር በመሥራት ድብቅ ተልኳቸውን በገሃድ እና በኅቡእ ሲያራምዱ ቆይተዋል፡፡ የሥራ አስኪያጁን ግልጽ የወጡ ስሑት ተግባራት ሲያጋልጡ የቆዩት የአድባራት አስተዳዳሪዎች እና ማኅበረ ምእመናንም ለሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ሌባ እና መናፍቅ ሥራ አስኪያጅን ይዞ በሀገረ ስብከቱ የልማት ሥራ ለመሥራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሳቸውን ያሳውቃሉ፡፡

በአብነት ትምህርቱ በተመሰከረላቸው ሊቃውንት የሚመራው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤም የአድባራት አስተዳዳሪዎቹን ቁርጠኛ ውሳኔ ከራሱ ግምገማዎች ጋራ በመቀመር ለሊቀ ጳጳሱ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ይዋል ይደር ሳይሉ ሥራ አስኪያጁን ከሐላፊነታቸው በማንሣት አዲስ ሥራ አስኪያጅ በቦታው ላይ ተክተዋል፡፡ ውሳኔውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡ አገልጋዮች እንደገለጹት በሥራ አስኪያጁ ላይ የተወሰደው ርምጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መዋቅራዊ መልክ በመያዝ ወሳኝ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ያሰፈሰፉትን የተሐድሶ መናፍቃን ወረራ ለመከላከል ጉልበት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሰውዬው ‹‹ቆሞስ›› እንደተባሉ ሲታይ ደግሞ በመጪው ጥቅምት ወር በወሳኝ መልኩ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የተጨማሪ ጳጳሳትን ሢመት እንደ አጀንዳ በማቅረብ ከወዲሁ ለመሾም በየብፁዓን አባቶች ቤት ደጅ እየጠኑ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሙሰኛ፣ ጠባብ እና በኑፋቄ የሚታሙ ሌሎች ቆሞሳትን ሁኔታ አሳሳቢ እንደሚያደርገው አስተያየት ሰጪዎቹ ያደረባቸውን ስጋት አልሸሸጉም፡፡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ አንድነት መጣር በሚገባበት በአሁኑ ወቅት የከረመውን ልዩነት በሚያሰፋ እና የውስጥ ተቋማዊ ችግሮቿን በሚያባብስ አኳኋን ‹መረቅ እና ፍትፍት› ለሚፈልጉ፣ አገራዊ ይሁን ሃይማኖታዊ አርበኝነታቸው እና ሞያዊ ብቃታቸው ለሚያጠራጥር ሙሰኛ እና መናፍቅ ቆሞሳት ማዕርገ ጵጵስና ለመስጠት ማሰብን የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ‹‹ወቅቱን ያልጠበቀ›› በሚል እንዲያወድቁት አስተያየት ሰጪዎቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቆሞስ ከኤጲስ ቆጶስ በታች ያለ፣ ከቄስ በላይ የሆነ የኤጲስ ቆጶሱ መጋቢ፣ አገልጋይ እና ተለአኪ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተወላጅነት እና በዘረፋ ባካበቱት ብር ጭምር በማግባባት ራሳቸውን ለጵጵስና ያጩ፣ ከባሕር ማዶ ሳይቀር የመጡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ‹‹ቆሞሳት›› ነን ባይ የሹመት ተስፈኞች በተለይ በመዲናይቱ በአዲስ አበባ በርክት ብለው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ 
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)