October 4, 2010

ቤተ ክርስቲያኒቱ አገራዊ ተደማጭነቷ አደጋ ተጋርጦበታል

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 4/2010፤ መስከረም 24/2003 ዓ.ም):-  ከርትዕ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት በማፈግፈግ በአቋራጭ ጥቅም የማግኘት፣ ጉዳይን የመፈጸም እና የመክበር አመለካከት እና ተግባር እየበዛ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልማታዊ አገልግሎት እየተዳከመ፣ በዚህም ላይ የተመሠረተው ሀገራዊ ተደማጭነቷ የመቀነስ አዝማሚያ እየታየበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ መስከረም 11 - 12 ቀን 2003 ዓ.ም ስለ ስብከተ ወንጌል መስፋፋት እና መጠናከር በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተካሂዶ በነበረው የሁለት ቀን ዐውደ ትምህርት ላይ ‹‹ልማት እና ቤተ ክርስቲያን›› በሚል ርእስ የቀረበው ጥናት በሀገር ደረጃ የልማት ፖሊሲዎች ሲቀረጹ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ ባለድርሻ አካል ያላት ተጽዕኖ እና ጠንካራ የፖሊሲ አውጪ ተቋም የመሆን ሚናዋ እያጠያየቀ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ሕዝቡን በግብረ ገብነት የታነጸ መልካም እና ታታሪ ዜጋ እንዲሆን የሚያስችል ጠንካራ የልማት አስተምህሮ እንዳላት ያመለከተው ጥናቱ ከ925 - 1500 ዓ.ም ድረስ ወርቃማ የነበሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ዘመናት ከ15ው መ/ክ/ዘ ጀምሮ በተፈራረቁባት የውስጥ እና የውጭ ችግሮች የተነሣ ወደኋላ የተመለሰበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድቷል፡፡ ጎጂ ልማድን በስብከተ ወንጌል ማበጠር፣ የአብነት መምህራንን እና ተማሪዎችን ጨምሮ የምእመኑን የገጠር-ከተማ ፍልሰት በአጥቢያ ደረጃ በሚዘረጋ የተቀናጀ ተቋማዊ አደረጃጀት እና አደረጃጀቱን በሚያግዙ፣ ቋሚ የገቢ ምንጭ በሚያስገኙ ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶች መከላከል በጥናቱ እንደ መፍትሔ ሐሳብ የቀረቡ ነጥቦች ናቸው፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱ ያሏትንና እንደ እሴት የሚታዩትን ምእመናን ብዛት በቀጣይነት መንከባከብ፣ የእያንዳንዱ አጥቢያ ሀብት በየፈርጁ እና ለልማቱ ያለው ምቹ ሁኔታዎች በጥናት በመለየት መሠረታዊ መዋቅሩ የልማት ማእከል ለማድረግ መትጋት እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

የጥናቱን መቅረብ ተከትሎ ከዐውደ ትምህርቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበዋል፤ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል፡፡ ከእኒህም መካከል በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት ውስጥ ኢፍትሐዊ ቅጥሮች እንደሚካሄዱና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ቅድሚያ ባለመሰጠቱ የሥራ ዐጡ አገልጋይ ቁጥር በርካታ እንደ ሆነ፣ ወደ ሥራ ለመግባትም የሚያደራጃቸው አካል እንደሚያሻ፣ ሌሎች ቤተ እምነቶች ቱጃር መሆንን ቅድሚያ ሰጥተው በመሥራት ውለው አድረው ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን በኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ለመማረክ በቱሪዝሙ ክፍለ ኢኮኖሚ ሳይቀር እየተረባረቡ መሆናቸውን፣ ባለጸጋ ምእመናን የሚሰጧቸው ርዳታዎች እና ድጋፎች የግልጽነት እና ተጠያቂነት አሠራር ባለመኖሩ ምክንያት ከመንገድ እየቀሩ ቤተ ክርስቲያን እየተወቀሰች መሆኗን፣ ለዚህም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማእከላዊ አሠራር ውጪ የሆኑት እና የተቀናጀ አሠራር የሚጎድላቸው 40‚000 ያህል ማኅበራት አስተዋፅኦ እንዳላቸው የሚያወሱ ነጥቦች ይገኙባቸዋል፡፡ መዋቅሩን ያልተከተለውን የማኅበራቱን የተበተነ አሠራር በመጠቀም ‹‹የጽዋ ኮኔክሽን ቸርች›› የተባለ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ቡድን በቅርቡ ተመሥርቶ የቅሰጣ ተግባር ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆኑም ተገልጧል፡፡

የተቀናጀ እና መዋቅሩን የጠበቀ አሠራርን አስፈላጊነት አስመልክቶ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሐላፊ ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ፣ በቁሳዊ አቅሙ የጎለበተ መንፈሰ ጠንካራ፣ ለታሪኩ እና ለባህሉ የሚቆረቆር ወጣት ለማውጣት መዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የ2003 ዓ.ም የመምሪያው ዕቅድ በወጣቶች ላይ አተኩሮ ለመሥራት መዘጋጀቱን የገለጹት ሐላፊው ለዕቅዱ ተፈጻሚነት ከማኅበራቱ መሪዎች ጋራ ምክክር መካሄዱን አሳውቀዋል፡፡ ማኅበራቱን በማእከላዊነት ተቆጣጥሮ ለማሠራት ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ እና ከሰበካ ጉባኤ መምሪያዎች ጋራ በመተባበር በመጪዎቹ ሳምንታት ፓትርያርኩ በተገኙበት የማኅበራቱ ጥምረት እንደሚፈጠር፣ ጥምረቱ የሚመራባቸው ደንቦች እና አሠራሮች እንደሚዘጋጁም አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት ክንፍ በሆነው የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን (DICAC) ውስጥ የተዘረጉት የተቀናጀ የገጠር ልማት ፕሮግራም (Integrated Rural Development Programs) እና የውኃ ልማት ፕሮጀክቶች እየታጠፉ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መታጠፍ - በብቃት እና በሥራ ልምድ ተመዝኖ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሾመ ኮሚሽነር ለኮሚሽኑ አለመመደቡ፣ በምትኩ የፓትርያርኩ ጣልቃ ገብነት መስፈኑ፣ ለረጅም ጊዜ ለፓትርያርኩ በጉዳይ ፈጻሚነት የሚሠሩ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ እና የበታች ሹማምንቶች መኖራቸው፣ የፋይናንስ ሪፖርቶች በወቅቱ ለለጋሽ አካላት አለመቅረባቸው፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የጎደላቸው አሠራሮች መግነናቸው እና በዚህም ባለፈው ዓመት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር እና የአቅም ግንባታ መምሪያ ለአህጉረ ስብከት ሠራተኞች ተዘጋጀ በተባለ ሥልጠና ላይ እስከ 800‚000 ብር ድረስ ለድግስ ወጪ መደረጉ እንደ ምክንያት ተዘርዝረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ባለፈው ዓመት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሾሙት የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለሥራ ሂደት የሚያስፈልጓቸው የቼክ ፊርማ እና የማኅተም ማንቀሳቀስ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳይሟሉ በአቡነ ጳውሎስ ጣልቃ ገብነት በመታገዱ የሥራው ቅልጥፍና እንደተጓተተ፣ ሊቀ ጳጳሱም ሐላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ በተፈጠረባቸው ዕንቅፋት ሳቢያ ተገልለው ያለሥራ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በመጪው ጥቅምት በወሳኝ መልኩ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ጉዳይ፣ የልማት ኮሚሽኑን እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የቁጥጥር መዋቅሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከፍተኛ ውሳኔ በማሳለፍ ለችግሮች መሠረታዊ መፍትሔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡Related Article: http://arefe.wordpress.com/2008/12/08/is-the-orthodox-church-losing-ground/

2 comments:

Anonymous said...

ውድ ደጀ ሰላም እናንተ በምትጽፉአቸው የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች የሚከፉት እና ቅሬታቸውን የሚያሰሙት በዋናነት የእነእጅጋየሁ በየነ እና የእነፋንታሁን ሙጨ ጋሻጃግሬወች ናቸው።የደጀ ሰላም እውነታውን ማጋለጥ እነሱን ምቾት ስለነሳቻቸው ደጀ ሰላምን እንደጠላት መቁተራቸው ለሁላችንም ግልጽ ነው ። ምክንያቱም ደጀ ሰላም ዝም ካለች ሌቦቹ ያለምንም መሸማቀቅ እንደልባቸው መዝረፍ ይመቻቸዋልና ነው።
በሌላ በኩል እነዚህ ዘራፊዎች ምን ያህል ብልጣብልጦች እና ቤተክርስቲያናችን እየጎዱ መሆናቸውን ገና ያልተረዱ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ።ይሁን እንጅ እነሱም ውለው አድረው እውነታውን ስለሚረዱት ማንም ይሁን ማን ቤተ ክርስቲያንን እስከጎዳ ድረስ ለሌሎቻችን ተገቢውን መረጃ አድርሱን ።አንድ ቀን እንፋረዳቸዋለን ።
እግዚአብሄር ሥራችሁን ይባርክ፡፡

Anonymous said...

ውድ ደጀ ሰላም እናንተ በምትጽፉአቸው የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች የሚከፉት እና ቅሬታቸውን የሚያሰሙት በዋናነት የእነእጅጋየሁ በየነ እና የእነፋንታሁን ሙጨ ጋሻጃግሬወች ናቸው።የደጀ ሰላም እውነታውን ማጋለጥ እነሱን ምቾት ስለነሳቻቸው ደጀ ሰላምን እንደጠላት መቁተራቸው ለሁላችንም ግልጽ ነው ። ምክንያቱም ደጀ ሰላም ዝም ካለች ሌቦቹ ያለምንም መሸማቀቅ እንደልባቸው መዝረፍ ይመቻቸዋልና ነው።
በሌላ በኩል እነዚህ ዘራፊዎች ምን ያህል ብልጣብልጦች እና ቤተክርስቲያናችን እየጎዱ መሆናቸውን ገና ያልተረዱ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ።ይሁን እንጅ እነሱም ውለው አድረው እውነታውን ስለሚረዱት ማንም ይሁን ማን ቤተ ክርስቲያንን እስከጎዳ ድረስ ለሌሎቻችን ተገቢውን መረጃ አድርሱን ።አንድ ቀን እንፋረዳቸዋለን ።
እግዚአብሄር ሥራችሁን ይባርክ፡፡

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)