October 2, 2010

መንግሥት የብዙኀን መገናኛዎች በእምነት ተቋማት ውስጥ የተበራከተውን ‹ኪራይ ሰብሳቢነት› እንዲዋጉ ጠየቀ

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 2/2010፤ መስከረም 22/2003 ዓ.ም):-  በሃይማኖት ተቋማት እና በልዩ ልዩ እምነቶች ውስጥ እየተበራከተ እና እየተባባሰ የመጣው የ‹ኪራይ ሰብሳቢነት› አመለካከት እና ተግባር የሀገርን እና የሕዝቡን ሀብት በማባከን፣ ፍትሐዊ ክፍፍል እንዳይኖር መንሥኤ በመሆን እና ግጭቶችን በማነሣሣት ለልማት ዕንቅፋት መፍጠሩን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አመለከተ፤ የብዙኀን መገናኛዎች ተቋማቱን በመቆጣጠር ገዢ አመለካከት እና ተግባር እየሆነ የመጣውን ‹ኪራይ ሰብሳቢነት› እንዲዋጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ (ኪራይ ሰብሳቢነት (rent seeking) ያለነጻ ውድድር እና ፍትሐዊ አሠራር ትርፍን ወይም ገቢን በትውውቅ፣ ጉቦ በመስጠት እና በመሳሰሉት መንገዶች ለማካበት የሚካሄድን እንቅስቃሴ ለመግለጽ የሚያገለግል የኢኮኖሚክስ እና የፖሊቲካዊ ኢኮኖሚ ኀይለ ሐረግ ነው፡፡)
በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሃይማኖት እና የእምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ትናት በሐዋሳ ከተማ የተከፈተው በእምነት ተቋማት እና በተከታዮቻቸው መካከል አክራሪነትን፣ መነቃቀፍን፣ ማግለልን፣ ጥላቻ መነዛዛትን አስወግዶ ሰላምን፣ መከባበርን እና መቻቻልን ለማስፈን አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ በታመነበት የሁለት ቀናት የሚዲያ ባለሞያዎች ዐውደ ጉባኤ ላይ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም እንደተናገሩት ‹‹በአሁኑ ወቅት በሃይማኖት እና እምነት ተቋማት ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢነት ተንሰራፍቷል፡፡ በሃይማኖት ስም የማይገባ ጥቅም የሚያግበሰብሱ አካላት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ኅብረተሰቡ ወደማይፈልገው እሳት እንዲማገድ እያደረጉ ናቸው›› ብለዋል፡፡

የብዙኀን መገናኛዎች በሃይማኖት እምነት ተቋማት ውስጥ ሰላም እና መከባበር እንዲኖር መሥራት አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሚዲያን እንደ መልእክተኛ በመጠቀም በሃይማኖት ተቋማት እና ተከታዮቻቸው ውስጥ አለመተማመን እንዲሰፍን፣ ጥላቻ እንዲፈጠር ለማድረግ በግል እና በቡድን የሚንቀሳቀሱ ወገኖች አሉ› ብለዋል፡፡ የእምነት ነጻነት ሕገ መንግሥታዊ ሽፋን በማግኘቱ ተመልሶ ያደረ ጥያቄ መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትሩ ይህን አስመልክቶ የሚፈጠሩ ችግሮች ለአገር ሰላም፣ ዕድገት እና ልማት ዕንቅፋት ከመሆናቸውም በላይ የሕዝቡን የሥራ ጊዜ እንደሚያባክኑ ገልጸዋል፡፡ የብዙኀን መገናኛዎቹ ‹‹እኔ የምኖረው አንተ ስትጠፋ ነው›› የሚለው የጽንፋዊነት አስተሳሰብ እንዲወገድ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ተጋፍታችኋል፣ የመገናኛ ብዙኀን፣ የመረጃ ነጻነት እና የብሮድካስት ዐዋጁን ጥሳችኋል በሚል ማሳደዱ አግባብ እንዳልሆነ ያመለከቱት ሚኒስትሩ ይሁንና በሂደት ወደ አስተዳደራዊ ርምጃ ከመግባቱ በፊት የሚዲያ ተቋማቱ በራሳቸው ውስጣዊ አሠራር በጋራ አገራዊ ጉዳይ የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ፣ ሐላፊነት የሚሰማው ሥራ እንዲሠሩ፣ የአክራሪዎቹ መጠቀሚያ ከመሆንም እንዲታቀቡ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ ሃይማኖታዊ መልእክቶችን የያዙ ጽሑፎችን በቢሮዎች ውስጥ በመለጠፍ፣ በበራሪ ወረቀቶች በማባዛት እና በማሰራጨት የኅብረተሰቡን ሰላም እና ተከባብሮ የመኖር ባህል የሚያዛቡ ተግባራትን ሁሉም ዜጋ በሐላፊነት ስሜት እንዲከላከለው ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት እና እምነቶች ከተከታዮቻቸው ብዛት እና በውስጣቸው ከያዟቸው ፈርጀ ብዙ ሀብቶች አኳያ ለአገር ሰላም፣ ዕድገት እና ልማት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው በእምነቶቹ ስም እንዲሁም በመንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ መዋቅሮቻቸው ውስጥ በጠባብነት፣ በትውውቅ፣ በሙስና፣ በዘረፋ፣ በድለላ በአጠቃላይ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን በማያሰፍን አኳኋን የሚፈጸመው ‹ኪራይ ሰብሳቢነት› አገርን እና ሕዝብን በእጅጉ እየጎዳ እንደሚገኝ በዐውደ ጉባኤው ላይ ተገልጧል፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱን ወሳኝ እና ከፍተኛ የሥልጣን ዕርከኖች በሕገ ወጥ መንገድ በመያዝ ለኪራይ ሰብሳቢነት እና ጥገኝነት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በአቋራጭ የመክበርን አስተሳሰብ እና ተግባር በማጋለጥ፣ የአገልግሎት እና አስተዳደራዊ መዋቅሮቻቸውን በብቁ የሰው ኀይል እና አደረጃጀት በማጠናከር፣ የምእመኑን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የብዙኀን መገናኛዎቹ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ላዕላዊ እና ታህታዊ የአገልግሎት እና አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ልዩ ልዩ ሹመቶችን፣ የሹመት እና የቅጥር ቦታዎችን፣ ዝውውሮችን፣ የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶችን እና ሕንጻዎችን ኪራይ እና እድሳት፣ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን እና የመቃብር ቦታዎችን. . .በቤተ ዘመዳዊነት፣ በትውውቅ፣ በአገር ልጅነት፣ በጉቦ እና በድለላ በመሸጥ፣ በማከራየት፣ በመስጠት እና በመቀበል የሚገለጽ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እና ተግባር እንደ ሰፈነ፣ የዚህንም ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መሠረት በመናድ ለማስተካከል የማያቋርጥ የውስጥ ትግል በመደረግ ላይ እንዳለ ይታወቃል፡፡

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት እና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በሕገ መንግሥቱ መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን አንቀጽ ባገናዘበ አኳኋን በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የተበራከተውን ሙስና እና ‹ኪራይ ሰብሳቢነት› ለማስወገድ በተከታታይ መድረኮች ቀጣይ ሥራዎችን እንደሚሠራ ተገልጧል፡፡ በዐውደ ጉባኤው ላይ ሃይማኖት (በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ቀኖና በማተኮር) ለልማት እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ያለው አስተዋፅኦ ተብራርቷል፡፡

5 comments:

Anonymous said...

Thank you. But the language smells poletika poletika, as a result I couldn't read it to the end.

By the way - a wonderful calculation from the government. It has long been silent and at some point it encouraged the institutes to be so and now stood up saying, 'let us fight it!!!' That is where the calculation lies - to get the support of the disperated meemenan.' Will it be successful??? As to me - NOOOOOOOOOOOO. Stay by your own my government. Don't come to correct my mother institute which used to correct you accross centuries. Of course our spritual institution should be corrected. And it is not by you but by us.

Anonymous said...

በእውነት መልካም ነገረ ነው ግን ክራይ ሰብሳቢነት ያለው መጀመረያ የኢ.ሬ.ቴ.ድ በ መንገሰት በሜተዳደረው እኮ ነው ለዘህ ማሳያው የድሮውን መጥቀስ ሳያስፈልግ ባለፈው ነሀሴ እና ጻግሜ ወር ያስተላለፈውን መረሀ -ግብረ ማየት በቄ ነወ መለወጥ ከራስ ይጀምረ መልክቴ ነው

Anonymous said...

taበእውነቱ ለመናገር ይክራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአክራሪነት ጉዳይም በጉባኤው ተነስቶ ውይይት ተካሂዶበታል ከዚህም ሌላ በፌዴራሊዝም ኮንሰብት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በአንዳንድ ፌዴራለ መንግስታት ውስጥ ያሉ ክራይ ሰብሳቢዎች ቤተ ክርስቲያንን ከቦታ ይዞታጋር ከግምባታ ፈቃድጋር እና በጥምቀተባህር ቦታዎች ይገባኛል ጉዳይ ላይ አግባብነት የሌለው ስራ እየሰሩ መሆኑ የተገለጠ ሲሆን በተ ለይም ቤተ ክህነቱን በመወከል የሄዱት ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱና የማህበረ ቅዱሳን ስማ ጽድቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ዲያቆን አስራት የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳዮች በማቅረብ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ግንዛቤ እንዲይዝ ያደረጉበት ጥረት የሚደነቅ መሆኑ እጠቅሳለሁ

hailemichael zeaddis said...

ለዚህ ሁሉ ችግር መፈጠር መንስኤዉ መንግስት እራሱ ነው ምክንያቱም ለአቡነ ፓዉሎስ ከለላ እየሰጠ ቤተክርስቲያኒቱ ችግራን በራሳ እንዳትፈታ መሰናክል እየፈጠረ ነውና ስለቤተክርስቲያን ጉዳይ ከመንግስት ምንም ጥሩ ነገር አንጠብቅ ነገሩ የአይጥ ምስክር ድንብጥ እንደምሉት ነው

hailemichael zeaddis said...

ለዚህ ሁሉ ችግር መፈጠር መንስኤዉ መንግስት እራሱ ነው ምክንያቱም ለአቡነ ፓዉሎስ ከለላ እየሰጠ ቤተክርስቲያኒቱ ችግራን በራሳ እንዳትፈታ መሰናክል እየፈጠረ ነውና ስለቤተክርስቲያን ጉዳይ ከመንግስት ምንም ጥሩ ነገር አንጠብቅ ነገሩ የአይጥ ምስክር ድንብጥ እንደምሉት ነው

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)