October 1, 2010

የመስቀለኛው ተራራ መስቀላዊ ተልእኮ

ከዚህ በታች ያለውን ጽሑፍ ያደረሱን አንድ ደጀ ሰላማዊ ናቸው። ዘወትር ከምንዘግበው እና ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በስብከተ ወንጌል አካባቢ እየተካሄደ ካለው ኢ-ኦርቶዶክሳዊ እንቅስቃሴ አንጻር ለእናንተ ለደጀ ሰላማውያን የሚያበረክተው አንድ ቁም ነገር አለው ብለን ስላመንን እንድትመለከቱት አቅርበነዋል። ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።
ደጀ ሰላም
+++
(ታዛቢ፤ ከአዲስ አበባ)፦ አንድ ዓመት ወደ ኋላ - መስከረም 20 ቀን 2003 ዓ.ም፤ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ዐምባሰል ወረዳ በምትገኘው በግሼን ደብረ ከርቤ መካነ መስቀሉ ለክርስቶስ ገዳም ታቦተ ሕጉ በሚወጣበት እና ወደ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ በተጣለው የማኅበረ ወይንዬ ድንኳን ውስጥ ብፅዓታቸውን ለመፈጸም እና ከበረከተ መስቀሉ ለመሳተፍ ከሩቅም ከቅርብም የመጡ ተሳላሚ ምእመናን ተሰብስበዋል፤ የነገር ሰው በጋሻው ደሳለኝም በመካከላቸው ነበር፡፡

ጉባኤተኞቹ በመርሐ ግብሩ መሪ አስተናባሪነት የተለያዩ መዝሙሮችን በጋራ ሲዘምሩ ከቆዩ በኋላ ተጨማሪ የመዝሙር ምርጫ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ አንድ ምእመን ይነሡና ጉባኤው ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የሚያወሱ አራት መዝሙራት ሲዘምር የቆየ በመሆኑ አሁን ደግሞ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያዘክር መዝሙር እንዲመርጥ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ሐሳባቸውን በቅንነት ላቀረቡት ለእኒህ ምእመን የተሰጣቸው ምላሽ ግን የጉዞው አስተባባሪ የሆነውን አካል ነውረኛነት እና የግብረ በላዎቹን መናፍቅነት የሚያጋልጥ ነበር፡፡

አስተባባሪው ግለሰብ ምእመኑ ስለ ፍቅረ ድንግል ላቀረቡት ጥያቄ፣ ‹‹ይህን አንተ አታዝዘንም፤›› የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው በቅርቡ አባ ሰይፈ ሥላሴ ዘደብረ ሊባኖስ የተባሉ አባት ባሳተሙት መጽሐፍ ‹‹የማይበሉ ፍሬዎች›› እና ‹‹ቢዝነስ ግሩፕ A›› ከሚሏቸው ራሳቸውን በዝነኛ እና ታዋቂ ሰባኪነት ሾመው በካህናተ እግዚአብሔር ላይ ከሚያንገራብዱት መካከል ቀንደኛው በጋሻው ደሳለኝ ከአስተባባሪው ብሶ፣ ‹‹አስወጡት! እናንተም አታጉረምርሙ፤ እዚህ የመጣነው መስቀሉ ወደዚህ ተራራ የገባበትን 570 ዓመት ለማሰብ ነው፤ ወደዳችሁም ጠላችሁም በዚህ ተራራ ላይ የነገሠው ጌታ ኢየሱስ ነው፤ በዚህ ተራራ ላይ ከበሮ የሚመታው ለጌታ እንጂ ለማርያም አይደለም፤ ተራራው የጌታ ስለሆነ. . .›› በማለት ያንቧትራል፡፡ ለወጉ በጋሻው በመስቀለኛው እና ግማደ መስቀሉ ባረፈበት ተራራ ላይ በተጣለ ድንኳን ውስጥ የተገኘው ‹መምህር› ተብሎ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አንዲት እማሆይ ተነሥተው ምእመኑ ከድንኳን የሚያስባርር ምንም ጥፋት አለመሥራታቸውን፣ ሐሳብ ማቅረብም መብታቸው መሆኑን በመናገር ይቃወሟቸዋል፤ ምእመኑም እማሆይዋን ተከትለው እመቤታችን መድኅን ዓለም ክርስቶስን ወልዳ ያስገኘች፣ አዝላ የተሰደደች፣ በዚያ በመከራው ቀንም በእግረ መስቀሉ የተገኘችና በማዳን ሥራው ሁሉ ያልተለየች መሆኗን በመገንዘብ ያቀረቡት ሐሳብ እንጂ ለበጋሻው ስድብ ምክንያት ለመሆን እንዳይደለ ከይቅርታ ጋራ ቢገልጹም ከድንኳኑ ያስወጧቸዋል፤ ጥቂቶችም ምእመኑን ተከትለው ጉባኤውን ጥለው ወጡ፡፡

ወደ ግሼን በሄደባቸው ጊዜያት ሁሉ በክብረ በዓሉ ቀን እንኳ እንደ ሌሎቹ ዲያቆናት በውስጥ አገልግሎት መራዳት ይቅርና እንደ ምእመን ቆሞ ባለማስቀደስ እንዲያውም ተኝቶ በማሳለፍ፣ ረቡዕ ዓርብ ሳይል - ሰዓት ሳይወስን - በቃለ ወንጌል እመክረዋለሁ የሚለውን ምእመን ፊት ሳያፍር በየማዕድ ቤቱ ደጃፍ በመታየት የሚታወቀው በጋሻውም ማንቧተሩን ቀጥሎ ከ45 ደቂቃ በኋላ ይጨርሳል፡፡ ጉባኤው እንደተበተነ አንዲት ምእመንት ወደ በጋሻው ቀርባ እመቤታችን እርሷ በምጥ ፃዕር ተይዛ ሳለ በቃል ኪዳኗ ተማፅና ያደረገችላትን በመመስከር ንግግሩ ግርታ እንደፈጠረባት እና ግልጽ እንዲያደርግላት ወጥራ ትይዘዋለች፡፡ ይህች የዋሂት ግን በጋሻው እና የመንፈስ አባቱ እንደ ሆነ የሚነገርለት አሸናፊ ገብረ ማርያም ‹‹አሪፍ ግጥም እና ዜማ እንሰጣችኋለን፤ ዱባይ እንልካችኋለን፤...›› እያሉ ከሚያማልሏቸው ‹የቢዝነስ ግሩፕ A› አባላት አንዷ የነበረችውን ዘርፌ ከበደን ያለፈውን ዓመት የፍልሰታ ሱባኤ በደብረ ምጥማቅ ጻድቃኔ ማርያም ገዳም ሰንብታ በመምጣቷ፣ ‹‹ምን ልሠሪ ትሄጃለሽና ነው ዐሥሬ ጻድቃኔ ጻድቃኔ የምትይው!›› እንዳላት ብትሰማ ግርምቷ ይቀንስ ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ የማይኖረውን ወንጌል እሰብካለሁ የሚለው በጋሻው ለሴቲቱ የመለሰላት መልስ እንዲህ የሚል ነበር፤ ‹‹እኔ የተቀባሁ ነኝ፤ አንቺ ልትናገሪኝ አትችይም፡፡›› በምላሹ ከቁጥጥር ውጭ የሆነችው እንስት የምእመንነት ቅናት ይዟት ጫማዋን ብትር አድርጋ ‹መምህሩን› መቋቋም ስትጀምር ሁኔታቸውን የተከታተሉ ሌሎች ምእመናን ግልግል ይገባሉ፡፡

ሀፍረተ ቢሱ በጋሻው ከዚህ ድርጊቱ በኋላም በሌሎች ድንኳኖች ለማስተማር ሞክሯል፡፡ ዜናው እንደ ሰደድ እሳት ተዛመተና የድንኳን አስተባባሪዎቹ ምእመናን በጽሑፍ በሚልኩላቸው እና በተባበረ ድምፅ በሚያሰሟቸው አስተያየቶች ይጨናነቃሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ለከት የሌለው ትዕቢቱ እና የእናቲቱ ወኔ ዘልቆ የተሰማቸው ወጣቶች ለበጋሻው አስተማሪ ቅጣት ለመስጠት ተንቀሳቅሰው እንደ ነበር ተዘግቧል፡፡ ባለቀ ሰዓት ዕድሉ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም መናፍቅነቱን ባጋለጡበት ምእመናን ፊት የማስተማር ወኔ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ያም ሆነ ይህ በግሼን ተራራ የተፈጸመው የሴቲቱ ገድል እና የነደደው የወጣቶቹ ቁጣ መሀል አዲስ አበባ ድረስ ያስተጋባና የቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን መምህራንን መንፈስ ይቀሰቅሰዋል፡፡

መምህራኑ በጋሻው ከጓደኞቹ ጋራ በተገኘበት ምክክር ላይ ስሕተቱን ተረድቶ እንዲያርም ጥረት ቢያደርጉም የማፊያው መናጆዎች፣ ‹‹እንደ በጋሻው የበራለት የለም፤ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ከበሮ ስንደበድብላት ነው የኖርነው፤ ማርያም አማራ አይደለችም፣ ውዳሴ ከንቱ አትፈልግም፤›› በማለት አንገታቸውን ያደነድናሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ከበጋሻው ጋራ ያላቸውን ግንኙነት ፈጽሞ ያቆሙት መምህራኑ በአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በቆሙባቸው የሠርክ ጉባኤያት ሁሉ በዚህ ዓመት ወደ ግሼን የሄዱ ተሳላሚዎችን እየጠየቁ በማስነሣት በጋሻው የፈጸመውን ድፈረት እንዲመሰክሩ በማድረግ ያጋልጡት ገቡ፡፡ የቤተ ክርስቲያን እና የእመቤታችን መደፈር ያቃጠለው ምእመንም ወደ በጋሻው ስልክ እየደወለ ተግሣጹን እና ማንነቱ መጋለጡን ያንጎደጉድበት ገባ፤ በተመሳሳይ መድረኮች የስድብ አፉን በመክፈት መምህራኑን በዓይነት ለመበቀል የፈለገው በጋሻውም የጠየቃቸው መድረኮች በስብከተ ወንጌል ሐላፊዎቹ ቅትልት ስለተነፈገው በዚህ የማጋለጥ ቅስቀሳ ውስጥ አሉ የሚላቸውን መምህራን እየደወለ ‹‹በጩቤ አስወጋሃለሁ፤ እዘከዝክሃለሁ›› በማለት መዛቱን ለጉዳዩ ማስረጃ እንዳላቸው የሚመሰክሩ መምህራን ያስረዳሉ፡፡ ማስፈራራቱ ያልያዘለት በጋሻው ሽማግሌ በመላክ ዕርቅ ቢሞክርም ልዩነቱ ሃይማኖታዊ ነውና ነገሩን ሁሉ የ‹‹አርማጌዴን ቁጥር - 1›› ቪሲዲ ደርሶ ማኅተሙን አሳረፈበት፡፡ ማጋለጡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንደ ዘገየ በሚነገረው የመምህር ዘመድኩን በቀለ ‹‹አርማጌዴን ቁጥር - 2›› ቪሲዲ የሚቀጥል ሲሆን አሁን በቅርቡ ደግሞ አባ ሰይፈ ሥላሴ ዘደብረ ሊባኖስ የተባሉ አባት ‹‹የማይበሉ ፍሬዎች›› በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ በጋሻውን በትምህርቱ፣ በእርሳቸው አገላለጽ ‹‹የቤተ ክርስቲያን በር ግንባሩን ባልገጨው›› ገንዘብ አምላኪ ማንነቱ ሞግተውታል፡፡

በሌላ በኩል በጋሻው እና የማፊያ ቡድኑ በየዓመቱ በግሼን ተራራ ያሰሙት ፀረ ማርያማዊ ዲስኩር ያስቆጣቸው ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ሰባክያነ ወንጌል እና ዘማርያን ዘንድሮ ከየጉዞ ማኅበራቱ ጋራ በመቀናጀት ከመስከረም 17 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ በግሼን ደብረ ከርቤ ተራራ ላይ ከትተዋል። ግሼናውያንም (ግሼኖችም) ለተሽከርካሪ እና ለእግረኛ የሚያገለግሉ ዋና እና አማራጭ መንገዶችን በመጥረግ እና በማስፋት፣ የቤት ኪራይ ወጪዎችን ጨምሮ ሌሎች መስተንግዶዎችን ምቹ በማድረግ አገልጋዮቹን እና ተሳላሚ ምእመናኑን ተቀብለዋቸዋል፡፡ እስከ አሁን በደረሰን መረጃ ከደሴ 80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የክረምቱ ዝናም ከጎዳው አስቸጋሪ የመኪና መንገድ ጉዞ በኋላ በምትገኘው ግሸን ደብረ ከርቤ መካነ መስቀሉ ለክርስቶስ ገዳም ዙሪያ የሚገኘው መናኸሪያ፣ ተሳላሚዎችን ያጓጓዙትን 1052 ያህል የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ለማስተናገድ ተስኖታል፡፡ ለክብረ በዓሉ ወደ ስፍራው የተጓዙት ምእመናን ከመላዋ አገሪቱ እና ከኢትዮጵያም ውጭ የመጡ ሲሆኑ ጉዟቸውን በማስተባበር በርካታ መንፈሳውያን ማኅበራት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በማኅበረ ጽዮን ዘግሼን ማርያም የጉዞ ማኅበር ሥር ተሳላሚው በስድስት አውቶቡሶች የተጓጓዘ ሲሆን በማኅበሩ ለነዳያን አልባሳት፣ ለአበው መነኮሳት የሚያገለግል ወይባ፣ መርፌ፣ ክር፣ ጨው፣ ስኳር፤ ለተዘጉ አብያተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት፣ አልባሳት፣ ጧፍ፣ ዕጣን፣ ዘቢብ. . .መባዕ እንደሚበረከትም ተገልጧል፡፡ ለግማደ መስቀሉ ማረፊያነት ከመመረጧ በፊት የቀድሞው ነገሥታት ልጆች የሚጠበቁባት ወኅኒ ዓምባ የነበረችው የመስቀለኛዋ ግሼን ምሥራቃዊ በር ወደ ዓምባዋ የሚያስወጣ 153 ደረጃዎች አሏት፡፡ በመሀል ግማደ መስቀሉ የሚገኝበት የእግዚአብሔር አብ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በምዕራብ አፍዛዣ የቅዱስ ሚካኤል፣ በሰሜን የቅዱስ ገብርኤል እና በጅምር ላይ ያለው የቅዱስ ዑራኤል አብያተ ክርስቲያን፣ በደቡብ የተለያዩ መንፈሳውያን ማኅበራት ያሠሯቸው መኖሪያ ቤቶች ይገኙባታል፡፡

የማኅበረ ኢያቄም ወሐና፣ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም እና ሌሎችም የጉዞ ማኅበራት ከትላንት ዐሥር ሰዓት ጀምሮ በየአቅጣጫው በተጣሉ ድንኳኖች እና በዐውደ ምሕረቱ እየተሰጡ ያሉትን ትምህርታዊ ጉባኤያት በማስተባበር ሁነኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡ ዛሬ ዘጠኝ ሰዓት ቀጥሎ እስከ ዋለው ጉባኤ ድረስ ትምህርተ ንስሐ፣ ትምህርተ ቁርባን፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እና ምላሹ ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች በአባ ኢያሱ፣ በመምህር ዘመድኩን በቀለ፣ በመምህር በላይ ወርቁ፣ በመምህር ዳንኤል ግርማ፣ በመምህር ምሕረተ አብ አሰፋ፣ በመምህር ተስፋዬ ተሾመ፣ በመምህር ሐዲስ ዓለማየሁ፣ በመምህር ዘማሪ ኤርሚያስ አሰፋ ተሰጥቷል፤ ከዘማርያኑም ዘማሪ ምንዳዬ ብርሃኑ፣ ዘማሪ ኤፍሬም አሰፋ፣ ዘማሪት ማርታ ኀይለ ሥላሴ፣ ዘማሪት ሕይወት ተፈሪ፣ ዘማሪት ለምለም ከበደ፣ ዘማሪ በኃይሉ፣ ዘማሪ አስናቀ፣ ዘማሪ ዘውዱ፣ ዘማሪ ኤልያስ(ዋሽንት)፣ ዘማሪ ዘውዱ(ክራር) የመዝሙር አገልግሎታቸውን አቅርበዋል፡፡

በትምህርታዊ ጉባኤያቱ ወቅት የገዳሙ ስብከተ ወንጌል ሐላፊ መሪጌታ ይትባረክ፣ ‹‹ተራራው በአምሳለ መስቀል የሚገኝ ነው፡፡ ተራራው ግማደ መስቀሉ ያረፈበት ነው፡፡ መስቀል ላይ ቆሞ ስለ እመቤታችን የማይናገር ሰባኪ እርሱ ጉንፋናም ነው፡፡ ምእመናን ልትከታተሉት የሚገባው እንዲህ ያለውን ትምህርት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚመጡ እንዳሉ ሁሉ የአምልኮት መልክ ያላቸውን ኀይሉን ግን የካዱትን ተጠንቀቋቸው፤›› በማለት ጉባኤተኞቹን መክረዋል፡፡ ስለ ጉባኤው ይዘት አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ ምእመናንም፣ ‹‹ስለ እመቤታችን አትናገሩ እየተባለ እስከ ዛሬ ከተቸገርንባቸው ጉባኤያት ይልቅ የዘንድሮው ለየት ያለ ነው፤ ለውጦናል፤›› በማለት በአገልጋዮቹ የተቀናጀ እና ኦርቶዶክሳዊ ማንነትን በሚያጠናክረው አገልግሎት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በአንጻሩ እንደተለመደው በማኅበረ ወይንዬ እና በአንድ ሆቴል የሠራተኞች ጉባኤ አማካይነት ወደ ስፍራው የተጓዘው በጋሻው ደሳለኝ ከግብር ምስያዎቹ ጋራ የዛሬ ዓመት በረበሸበት አንድ ድንኳን ብቻ ተወስኖ ለአላፊ አግዳሚው አገኝ አጣውን እየተናገረ፣ የጨከነበትን የምእመኑን ልብ የሚያራራባቸውን የማስመሰያ ድርጊቶች እየፈጸመ፣ አምና በተሰነዘረበት የወጣቶቹ ዛቻ ሳቢያ በስጋት ተውጦ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡ ዋናው ክብረ በዓል በነገው ዕለት ከዋለ በኋላ በመውጫ በሩ እና በአካባቢው መጨናነቅ ምክንያት ተመላሾቹ የጉዞ ማኅበራት እስከ መስከረም 23 ቀን 2003 ዓ.ም በስፍራው ሊቆዩ እንደሚችሉ ተዘግቧል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)