October 25, 2010

ቅ/ሲኖዶስ 3ኛ ቀን ከሰዓት በፊት፦ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬን ከሥራ አስኪያጅነት ኃላፊነታቸው አነሣ(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 25/2010፤ ጥቅምት 15/2003 ዓ.ም):- ጥቅምት 12 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረውና ዛሬም ቀጥሎ የዋለው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በዛሬው የከሰዓት በፊት ውሎው አወዛጋቢውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬን ከኃላፊነታቸው አስወግዷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ጠዋት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን አስመልክቶ አራት አባላት ባሉት አጣሪ ኮሚቴ ቅዳሜ ዕለት ቀርቦ ባዳመጠው እና የጋለ ውይይት ተካሂዶበታል በተባለው ሪፖርት መነሻነት ነው ሥራ አስኪያጁ ከሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም ጀምሮ ይዘውት ከቆዩት ኃላፊነታቸው እንዲነሡ የወሰነው፡፡
ሪፖርቱ ከንኡሳን ጉዳዮች በቀር የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩትን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ነጻ ያደረገ ሲሆን በዋናነት ተጠያቂ ያደረጋቸው የቀድሞውን እና ዛሬ ከኃላፊነታቸው የተነሡትን ሥራ አስኪያጆች፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን እና በኪራይ ቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ የሚያጸድቁትን የምሕንድስና ባለሞያ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

L.M Fantahun Muchie
29ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በቀረበው የሒሳብ እና ቁጥጥር ሪፖርት ላይ እና ሪፖርቱን ተከትሎ በተደረገው ውይይት ላይ በመመሥረት፣ ‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ ባለማክበር ቅጾችን በአግባቡ ያለመሙላት፣ ፐርሰንት አጠቃሎ አለማስገባት፣ የሁሉም አርኣያ መሆን ሲጠበቅበት በተደጋጋሚ በቂ ባልሆነ ምክንያት በሰበካ ጉባኤ ሁለንተናዊ ተግባር አድባራትን እና ገዳማትን አለመቆጣጠር እና አለማጠናከር ስለሚታይበት የሥራ አያያዙን እንዲያሻሻል፣ በአድባራቱ እና ገዳማቱ ታምኖ በማእከል በተዘጋጁት ቅጾች ተሞልቶ ገቢ ከሆነውም 35 በመቶ ለሀገረ ስብከቱ፣ 65 በመቶ ለመንበረ ፓትርያርኩ ገቢ እንዲያደርግ ጠበቅ ያለ ውሳኔ እና መመሪያ እንዲሰጠው›› ጉባኤው ባወጣው የጋራ የአቅዋም መግለጫ አበክሮ አሳስቦ ነበር፡፡

መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም
በብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እና እርሱን ተከትሎ ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 ቀን 2003 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ተካሂዶ በነበረው ውይይት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በበጀት ዓመቱ ለመንበረ ፓትርያርኩ ማስገባት የነበረበትን የገቢውን 65 በመቶ (ብር 13,667,726.20 ሣንቲም) አለማስገባቱን፣ ከዚህም በላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በተደረገው የዘጠኝ ዓመት የኦዲት ምርመራ ከሀገረ ስብከቱ የመንበረ ፓትርያርኩ ድርሻ የሆነ 65 በመቶ ከብር 42,000,000 በላይ ገቢ ሳይሆን እንደቀረ ተመልክቷል፡፡ በውይይቱ ላይ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም በኦዲት ሪፖርቱ መሠረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዘመኑ ጠቅላላ ገቢ 152,251,740.10 በመሆኑ የመንበረ ፓትርያርኩ ድርሻ የሆነው 65 በመቶ ብር 19,792,726.20 ሣንቲም፣ የሀገረ ስብከቱ 20 በመቶ ድርሻ ደግሞ ብር 30,450,348.02 ሣንቲም መሆኑን አስረድተው ነበር፡፡ በሰበካ ጉባኤው ስታቲስቲክስ ግን የሀገረ ስብከቱ የዘመኑ አጠቃላይ ገቢ 47,115,384.60፣ የሀገረ ስብከቱ 20 በመቶ ገቢ ብር 9,423,076.92፣ ለመንበረ ፓትርያርኩ ፈሰስ ያደረገው ደግሞ 6,125,000.00 ብቻ በመሆኑ በኦዲት ምርመራው ተገኘ ከተባለው ጠቅላላ ገቢ አንጻር ለመንበረ ፓትርያርኩ ገቢ መደረግ ከነበረበት መጠን (ብር 19,792,726.20 ሣንቲም) ከ13 ሚልዮን ብር በላይ ጉድለት እንደተገኘ ተገልጧል፡፡

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ በውይይቱ ወቅት ታይቷል ለተባለው ከፍተኛ ጉድለት ምላሽ ለመስጠት ሞክረው ነበር፡፡ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እና ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በኃላፊነት የነበሩባቸውን ጊዜያት ለሀገረ ስብከቱ የሥራ ላይ ሁኔታዎች አስቸጋሪነት አስረጅ አድርጎ በመማጠን በሰጡት ምላሽ - ሀገረ ስብከቱ ማንኛውንም ገቢውን በሞዴል 30 እንደሚሰበስብ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቁጥጥርም በዚህ ቅጽ ላይ የሰፈሩትን ሁሉንም ገቢዎች ፐርሰንት እንዳሰበባቸው ነገር ግን ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ እና እድሳት፣ ለክሊኒክ እና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ተብሎ በገቢ የሚመዘገቡ ሒሳቦች ፐርሰንት ሊሰበሰብባቸው እንደማይገባ፣ በዚህ ሳቢያ ገቢው ከፍ ተደርጎ መቀመጡ ጎድሏል ለተባለው የተሳሳተ ስሌት ምክንያት መሆኑን፣ ይህም የቁጥጥር ቡድኑ በኦዲት ምርመራው የፈጸመው ቴክኒካል ስሕተት መሆኑን፣ ሀገረ ስብከቱ ግን ከአምናው የመንበረ ፓትርያርኩ ገቢ የብር 424‚987.89 ሣንቲም ብልጫ በማሳየት ካዝናውን አሟጦ ከመቼውም ከስድስት ሚልዮን ብር በላይ ማስገባቱን፣ ይህን ለማረጋገጥ ለውስጥ ይሁን ለውጭ ኦዲተሮች ቢሯቸው ክፍት መሆኑን፣ በርግጥም የተባለውን ፐርሰንት አስቀርተው ከሆነ ‹ፍርድ እንደሚገባቸው›  ተናግረው ነበር፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት በሀገረ ስብከቱ ሒሳብ ላይ ለስድስት ወራት ባካሄደው እና በቀደመ ዓላማው በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ላይ እንከን ለመፈለግ ተነጣጥሮ እንደነበር በተገለጸለት የኦዲት ምርመራ ግኝት ሪፖርት ላይ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ሰበካ ጉባኤ መምሪያ እና ሒሳብ ክፍል አምነውበት ፊርማ እና ማኅተማቸውን እንዳሳረፉበት በመግለጽ ለሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ የመልስ መልስ የሰጡት ደግሞ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ነበሩ፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቃለ ዐዋዲውን ደንብ የጣሰ አካሄድ እየፈጸመ ነው፤›› ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ የሰበካ ጉባኤውን ቃለ ዐዋዲ አንቀጽ 42 ንኡስ አንቀጽ ስድስት በመጥቀስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከተሰበሰበው 20 በመቶ እና ከማናቸውም የሀገረ ስብከቱ ገቢ ላይ ለመንበረ ፓትርያርኩ 65 ከመቶ፣ ለሀገረ ስብከቱ 35 በመቶ ገቢ እንዲያደረግ መታዘዙን አስታውሰዋል፡፡ 

ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ
 የሥራ አስኪያጁ መልስ ደንቡ ከሚያዝዘው አሠራር አኳያ አራምባ እና ቆቦ መሆኑን በአባባል በመተቸት በጉባኤተኛው ያሣቁባቸው ንቡረ እዱ፣ አንድ በጎ አድራጊ በርእስ ለይቶ ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ እና እድሳት ካልሰጠ በቀር ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን እንዳሉት ‹‹ፐርሰንት የማይከፈልበት›› የሚባል ገቢ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅጽ አሞላል እና ለመንበረ ፓትርያርኩ የሚያቀርበው የሒሳብ ሪፖርት ‹‹በሽወዳ/ማታለል የተሞላ›› ነው ያሉት ንቡረ እድ ኤልያስ - የሶማሌ፣ ጋምቤላ እና አሶሳ አህጉረ ስብከት በየዓመቱ ከ10,000 ያላነሰ የገቢ ዕድገት ሲያስመዘግቡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአምስት ዓመት ውስጥ ከ2000 ብር ያልበለጠ የገቢ ዕድገት ብቻ ማሳየቱን፣ የመንበረ ፓትርያርኩ የፐርሰንት ድርሻ ‹‹ቁልቁል እየመታ›› ማሽቆልቆሉን፣ በልማት ስም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ወጪ ተደርጓል የሚባለው ነገር ደግሞ ‹‹ሽቅብ እየወጣ›› መቀጠሉን፣ ከሀገረ ስብከቱ አድባራት እና ገዳማት ውስጥ ዓመቱን ሙሉ ፐርሰንት ያልተጠየቁ፣ የምእመናቸው ቁጥር እና የገቢያቸው መጠን በርግጥ የማይታወቅ ከ20 ያላነሱ አጥቢያዎች መኖራቸውን(በአንዳንዶች ግምት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ፐርሰንት አየር ባየር ይበላል) በአጠቃላይ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሀገረ ስብከቱ ከ42 ሚልዮን ብር በላይ(የዘንድሮውን 13 ሚልዮን ሳይጨምር) የመንበረ ፓትርያርኩን ድርሻ በቅጥፈት ማስቀረቱን አስረድተዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከሚያውቃቸው ሞዴላሞዴሎች ውጭ በሚመዘገቡ ቅጻቅጾች ከፍተኛ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ገቢዎች እንደሚመዘበሩ፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት በሕንጻ አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ የሚቀመጡ የግል ሙዳየ መባዕ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

በሁለቱ ኃላፊዎች ከፍተኛ ትችት የቀረበባቸው እና ‹ግምገማ› የተካሄደባቸው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ከዚያ በኋላ በነበረው የጉባኤው ክፍለ ጊዜ በአዳራሹ አልታዩም፡፡ የሽልማት ኮሚቴው፣ ‹‹የ2001 የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ገቢ ከ2002 ገቢው ጋራ በማነጻጸር የበለጠ ሆኖ በመገኘቱ፣ የአንድነት የስብከተ ወንጌል ጉባኤያትን በማካሄዱ፣ ታላላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓላት በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ በማድረጉ፣ ለጋምቤላ እና ለደቡብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት የበጎ አድራጎት ርዳታዎችን በማሰባሰቡ፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ይዞታ ካርታ ዝግጅት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ለሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያን ድጎማ/ርዳታ እንዲቀጥል በማድረጉ›› ያዘጋጀውን ሽልማትም ቀርበው አልተቀበሉም፡፡

በምትኩ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ትምህርታቸውን ይከታተሉበታል ወደሚባለው ኦስትርያ ማምራታቸው ነው እየተነገረ ያለው፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ በኅዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ ጋብቻ እንደሚፈጽሙ እየተነገረላቸው ያሉት የቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ወደ አገር የመመለሳቸው ሁኔታ አጠራጣሪ ሆኖባቸዋል፡፡ በሌሎች ዘንድ ደግሞ ሰውዬው በኃላፊነታቸው ወቅት ያካበቱትን ሀብት (በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ያሠሩትን ቤት፣ የገዙትን መሬት እና መኪና. . .) እንደዋዛ ጥለው እንደማይቀሩ ነው የሚናገሩት፡፡ አቡነ ጳውሎስ እና ሥራ አስኪያጁ የነበራቸውን ጥብቅ ግንኙነት ታሳቢ ለሚያደርጉት ለእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፣ በአጠቃላዩ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ፓትርያርኩ በተገኙበት የታየው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬን ማእከል ያደረገው ግምገማ አስቀድሞ ስሌት የተሠራበት፣ ‹‹ሥራ አስኪያጁን በወንድ በር ከሕግ ተጠያቂነት ነጻ የማውጣት ድራማ ነው›› ይሉታል፡፡ ለዚህም እንደ አስረጅ የሚያቀርቡት ተናጋሪዎቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የየራሳቸው ችግር ያለባቸው ሁለቱ ኃላፊዎች ብቻ መሆናቸውን እንዲሁም አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በመሆኑ በሚፈጸመው እንከን ሁሉ ፓትርያርኩን የሚመለከት ሆኖ ሳለ የጉባኤው ርእሰ መንበር የነበሩት አቡነ ጳውሎስ ዝምታን መምረጣቸው ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ታሪክ ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ የጥቅም አቀባባዮችን መርበብ በመዘርጋት፣ ከ20,000 - 25,000 ብር እጅ መንሻ በመቀበል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንት እና አባቶች ክብረ ነክ ስድብ በመሳደብ የሚታወሱት የኦስትርያው ፒ.ኤች.ዲ ተማሪ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ከብዙዎች ኀዘን እና ልቅሶ በኋላ ከኃላፊነታቸው ተነሥተዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ግን ከዘርፈ ብዙ የአገልግሎት እና ልማት ተስፋዎቹ ጋራ እየተመዘበረ በውስብስብ ችግሮች ተተብትቦ ይገኛል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በመንፈሳዊ ሕይወቱ፣ በአስተዳደራዊ ክህሎቱ እና በማኅበራዊ ተግባቦቱ የበሰለ ሥራ አስኪያጅ፣ ከቤተ ዘመዳዊ እና ጥቅማዊ አመለካከት የጸዳ ሊቀ ጳጳስ ይሾምለታል ወይስ እንደ አንዳንድ የሥልጣን ጥመኞች ምኞት እንደ ቅርጫ ሥጋ ይከፋፍለዋል? ቆይተን የምናየው ይሆናል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)