October 19, 2010

29ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እየተካሄደ ነው(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 18/2010፤ ጥቅምት 8/2003 ዓ.ም):- ከጥቅምት 6-11/2003 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቀው ዓመታዊው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ዓመታዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ስለዚሁ ዓመታዊ ጉባዔ ሪፖርተሮቻችን ያጠናቀሩትን ዘገባ እና ሒሳዊ ሪፖርታዥ እንደሚከተለው እናቀርባለን። 

ዋና ዋና ሐሳቦች ጨመቅ (በአጭሩ)፦
  • ‹‹ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ሰበካ ጉባኤን ማጠናከር፣ ምእመናንን በማብዛት እና በጥራት በመመዝገብ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎትን ማሟላት ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡›› (የሰ/ጉ/መምሪያው ሐላፊዎች መልእክት)
  • ‹‹ከተመሠረተ 37 ዓመታትን ያስቆጠረው ሰበካ ጉባኤ ከፍጹምነት ደረጃ ደርሶ አለመታየቱ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡›› (ለጉባኤው ከቀረበው የአህጉረ ስብከት ሪፖርት)
  • ‹‹የመወሻሸት እና የድብብቆሽ ሥራ እንዳያውክ፣ የምእመናንን መተማመን  እንዳይፈታተን የሐናንያ እና የሰጲራ ጠባይ እንዲጠፋ ማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ፍቅር እና መተማመን የመላበት፣ ከዓለማዊ አስተዳደር የተለየ እና የሚያስቀና መልካም አስተዳደር ማስፈን እስከ መጨረሻው ሊዘመትባቸው ይገባል፡፡›› (ሊቀ ካህናት ዘሩባቤል ገብረ መድኅን)      
  • ከ47 አህጉረ ስብከት ከ26 ያላነሱት በገቢያቸው ወጪያቸውን መሸፈን አልቻሉም፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከገቢ ዕቅዱ ከ13 ሚ. ብር በላይ ባለማስገባቱ የበጀት ዓመቱን ጠቅላላ ገቢ ቀንሶታል፤ ገንዘቡም የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ በሰሜን ሸዋ እና ምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ከሦስት ሚልዮን ብር በላይ ሳይወራረድ በተንጠልጣይ ሰነድ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ከሁለት ሚልዮን ብር በላይ በጉድለት ተገኝቷል፡፡ ሙስና የተንሰራፋበት የሕፃናት እና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ከገቢው ከሦስት መቶ ሺሕ ብር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ወረቀት እና የኅትመት መሣሪያዎች ከውጭ አገር በርዳታም ሆነ በብድር ለማግኘት አልቻለም፡፡ ሥራው እና የምርት ውጤቱ የቀነሰው የጎፋ ጥበበ እድ ማሠልጠኛ ድርጅታዊ ህልውና አስጊ ሆኗል፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ቋሚ የሥራ ማስኬጃ በጀት የለውም፤ የኮሌጅ ደቀ መዛሙርት የደመወዝ ስኬል አይጠበቅም፤ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በጠረፋማ አህጉረ ስብከት ተመድበው የሄዱ ደቀ መዛሙርት የሉም፡፡
  • የሰበካ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲ ይሻሻላል፤ የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ ክፍያ ከ24 ብር ወደ 48 ብር ከፍ የሚያደርግ መመሪያ ይወጣል፡፡ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያን በባለሞያ እና በበጀት በማጠናከር በሁሉም አህጉረ ስብከት የተጠናከረ የሒሳብ ምርመራ ለማድረግ፣   ቤተ ክርስቲያን በልማት ራሷን ችላ ከተረጂነት እንድትወጣ፣ ለአህጉረ ስብከት እና ለወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት ታቅዷል፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሥራ ይጀመራል፡፡ የመጽሐፈ ኄኖክን እና መጽሐፈ ቄርሎስን አንድምታ ትርጓሜ ለማሳተም ታቅዷል፡፡
 ዝርዝር ሪፖርታዥ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደር እና በፍትሕ መንፈሳዊ በራሷ ሕግ እንድትመራ፣ በምጣኔ ሀብት የአገልጋዮቿን ካህናት ኑሮ ለማሻሻል እና ለምእመናን የሚሰጠውን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማሟላት ትችል ዘንድ በካህናት እና ምእመናን ኅብረት እንድትደራጅ ታስቦ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በትእዛዝ ዐዋጅ ቁጥር 83/65 ተፈቅዶ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ በጥቅምት ወር 1965 ዓ.ም በቃለ ዓዋዲው ደንብ ተመሥርቶ 37 ዓመታትን ያስቆጠረው የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን፣ በወረዳ እና በሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ እነሆ በዘንድሮው ዓመት 29 ዙር ላይ የደረሰው ይኸው ሀገር አቀፍ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጉባኤ ጥቅምት ስድስት ቀን 2003 ዓ.ም ረፋድ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሌሎች የተመዘገቡ ጉባኤተኞች በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ባደረሱት ጸሎተ ወንጌል ተከፍቷል፡፡

‹‹ሰበካ ጉባኤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ሁሉ ተጠቃለው የሚፈጸሙበት ዐቢይ መዋቅር ነው፡፡ የዘመናችን ገባሬ ተአምር የሆነው ሰበካ ጉባኤ እንዲቋቋም የቃለ ዓዋዲውን ደንብ በሩቅ አስበው፣ በኀይለ እግዚአብሔር ተመርተው ያወጡ ሙሉአነ አእምሮ መገብት ነበሩን፤ ደንቡም በሥራ ላይ እንዲውል ከጊዜው ሁናቴ ጋራ አስማምተው ይህ ነው የማይባል መሥዋዕትነት እና ብርታት በተዋሐደው ትዕግሥት ለፍሬ በረከት ያበቁ ቅዱሳን አበው እና ልጆቻቸው በዚሁ ሥራቸው የማንነታቸው ልዕልና ተለይቶ ይታወቃል ይላል ስብሰባውን አስመልክቶ በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የወጣው የልዩ ዕትም መጽሔት መግለጫ፡፡

የጉባኤው መጀመር እና መሰናዶው
በልዩ ዕትሙ ላይ ለጉባኤው መልእክታቸውን ያስተላለፉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹የቅዱሳን ሐዋርያትን ፈለግ ተከትለን የቤተ ክርስቲያናችን ዕድገት የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም በቀሩትም ሥራዎች ላይ ተመካክረን ለመሥራት እና ያለውን ሁኔታ ለመረዳት በዚህ መሰብሰባችን እጅግ የሚያስደስት ነው፡፡ ሰበካ ጉባኤ ሲመሠረት የነበሩት አባቶቻችን ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለው አልፈዋል፤ እኛም ተከታዮቻቸው የሰበካ ጉባኤን እንቅስቃሴ በቸልተኝነት ልንመለከተው አይገባም፡፡ ሌላው የዘወትር አገልግሎታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ቀዳሚ ትኩረትን ከሚሹ ሥራዎቻችን ሁሉ ለሰበካ ጉባኤ መጠናከር ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ምእመናንን በትምህርተ ወንጌል ለማብዛት፣ ለመጠበቅ፣ በጥራት ለመመዝገብ እና ለሚፈልጉት ሁሉ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡ ፓትርያርኩ ጉባኤው አጽንኦት ሰጥቶ በመምከር ‹‹ለቀጣዩ ሥራ የተሟላ ፕሮጀክት ሊያዘጋጅላቸው ይገባል›› ካሏቸው ተግባራት መካከል - ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ የሰበካ ጉባኤን የአሠራር ሂደት ማጠናከር፣ የምእመናን ምዝገባ እና አጠባበቅ፣ ስለ ልማት ሥራ እና ገቢን ማሳደግ፣ ስለ ዐሥራት በኲራት ክፍያ አፈጻጸም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሀብት እና ንብረት አጠባበቅ፣ ስለ ድህነት ቅነሳ እና ስለ ካህናት ኑሮ መሻሻል የሚመለከቱ ነጥቦች ይገኙባቸዋል፡፡

‹‹ስብከተ ወንጌል ለሰበካ ጉባኤ መስፋፋት መሠረት ነው›› በሚል ኀይለ ቃል የተነሡት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሉባቦር እና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ 2003 ዓ.ም ሰባክያነ ወንጌል እና ካህናት ስብከተ ወንጌልን ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት በማስፋፋት የምእመናንን እምነት አጽንቶ እና ሥነ ምግባራቸውን አጎልብቶ ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት በሚጥል አኳኋን በሰበካ ጉባኤ እንዲደራጁ፣ ከቤተ ክርስቲያናቸው እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው ጋራ ያላቸውን ግንኙነት በመመርመር እና በመከታተል አባልነታቸውን አጠንክረው እንዲይዙ፣ ዐሥራት በኲራት እንዲያወጡ ተግተን የምንሠራበት ጊዜ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ወንጌልን በማስተማራችን የምንጠቀመው ሰማያዊ ክብር ለመውረስ ብቻ ሳይሆን ከወንጌል አዝመራ[ምእመናን] በሰበካ ጉባኤ አባልነት ክፍያ አማካይነት አስፈላጊውን የኑሮ ድጋፍ የምናገኝ መሆኑን ባለመዘንጋት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት እና በማጠናከር፣ ሰበካ ጉባኤን በማደራጀት እና በማጠናከር የሚገባትን አገልግሎት ካከናወነች ማሳው በሰብል መረቡ በዓሣ ይሞላል፤ ምእመናን በሃይማኖታቸው ጽኑዓን ይሆናሉ፣ የካህናትም ኑሮ ይሻሻላል ያሉት ብፁዕነታቸው በአሁኑ ጊዜ የአብነት መምህራን፣ በየኮሌጁ የተመረቁ ሊቃውንት፣ የሰንበት ት/ቤቶች እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እንዲሁም በድምፀ ቃና የሚዘምሩ ዘማርያን በአንድ ላይ ተጣምረው ትምህርተ ወንጌልን በስፋት በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ፣ ይህም የበለጠ ንቃትን እና ቅልጥፍናን በማዋሐድ ከዘመኑ ጋራ እኩል መሮጥ እና መቅደም የሚያስችለንን አቅም እንደሚገነባልን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ሀገረ አቀፍ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጉባኤ ላይ የሚቀርበውን ዓመታዊ ሪፖርት በሚገባ ገምግሞ ተገቢውን አቅጣጫ መቀየስ እንደሚያስፈልግ በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ እና ሶማሌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ መልእክት ላይም ተገልጧል፡፡ ብዙ ያልተወጣነው ድርሻ እንዳለ ይታወቃል ያሉት የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ያልተሳካውን ለማሳካት የሚያበቃ ዕቅድ ጉባኤው እንዲያቅድ አስገንዝበዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በሰው ኀይል እና በበጀት እንዲጠናከር ባለፈው ዓመት ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት የሚያስፈልገው በጀት ተጠንቶ መቅረቡን ያስረዱት ደግሞ የመምሪያው ሐላፊ ሊቀ ካህናት ዘሩባቤል ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ ቀድሞ በነገሥታት ችሮታ መተዳደሪያ ተብሎ የተሰጠው የመሬት ሥሪት በሥርዐተ መንግሥት ለውጥ ምክንያት እንደማይቀጥል ሲታወቅ የሰበካ ጉባኤ ማቋቋሚያ እና ማጠናከሪያ ደንብ ቃለ ዓዋዲ መደንገጉን፣ በድንጋጌው መሠረት ካህናት እና ምእመናን አንድነት ፈጥረው በሰበካ ጉባኤ መደራጀታቸው በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸው እና በሀብታቸው ቤተ ክርስቲያንን በተሟላ መልካም አስተዳደር እንዲያስተዳድሩ ታስቦ መሆኑን ሊቀ ካህናት ዘሩባቤል አስታውሰዋል፡፡

ሰበካ ጉባኤ ከተቋቋመ ወዲህ ሊቃውንት እና ካህናት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲተጉ፣ ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚያስፈልገውን እንዲያስቡ፣ ወርኀዊ እና ዓመታዊ አስተዋፅኦ እንዲለመድ በተጓዳኝም በየደረጃው ባለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የገቢ ምንጭ እንዲፈጠር እና የልማት ሥራ እንዲሠራ በተደረገው ጥረት የማይናቅ ዕድገት ተገኝቷል፡፡ ካህናትን በደመወዝ ማስተዳደር መቻሉ፣ መተዳደሪያ ለሌላቸው ገዳማት፣ ለአብነት መምህራን እና ደቀ መዛሙርት የድጎማ በጀት መበጀቱ፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ አህጉረ ስብከትን በማስፋፋት መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቱ ጎልቶ መቀጠሉ፣ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት መታነጻቸው፣ መንፈሳውያን ኮሌጆች መከፈታቸው፣ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች እና ክሊኒኮች መቋቋማቸው፣ የገቢ ምንጭ የሚሆኑ ሕንጻዎች መገንባታቸው የዕድገቱ ምልክቶች ናቸው - እንደ ሊቀ ካህናት ዘሩባቤል መልእክት፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ እና ንብረት በአስተማማኝ ሁኔታ እየመዘገቡ በጥንቃቄ እንዲጠበቅ፣ የድብብቆሽ እና የመወሻሸት ሥራ እንዳያውክ፣ የምእመናንን መተማመን እንዳይፈታተን የሐናንያ እና ሰጲራ ጠባይ እንዲጠፋ ማድረግ፣ ፍቅር እና መተማመን ያልተለየው፣ ከዓለማዊ አስተዳደር የተለየ እና የሚያስቀና መልካም አስተዳደር ማስፈን እስከ መጨረሻው ሊዘመትበት እንደሚገባ፣ ሀገር አቀፍ አጠቃላይ ጉባኤው እስከ አሁን የተደረሰበትን የሥራ ውጤት በሚገባ ገምግሞ እና መክሮበት ለበለጠ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሚያበቃ መመሪያ እንዲያወጣ ሐላፊው አሳስበዋል፡፡

በአዘቦታዊ ድባብ የቀጠለው ጉባኤ
ከአቡነ ጳውሎስ ቃለ በረከት እስከ መምሪያው ሐላፊ ማሳሰቢያ ድረስ ከአህጉረ ስብከት እስከ መንበረ ፓትርያርኩ ባሉት የአፈጻጸም ሪፖርቶች ላይ ግምገማ እና ምክክር ማካሄድ፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችን መቀየስ እና ‹‹የቤተ ክርስቲያንን ልማት ለማስቀጠል የሚያበቃ ዕቅድ ማውጣት›› የሚሉት መመሪያዎች እንደ አዝማች መነገራቸው ይስተዋላል፡፡ ይሁንና 29ው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ባለፉት ዓመታት እንደተለመደው ሁሉ ያለአንዳች ውይይት ይሁን ግምገማ በዋናነት በሞዴላሞዴል ገቢዎች(ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለደመወዝ እና ሥራ ማስኬጃ ለአህጉረ ስብከት በሚመድበውና አህጉረ ስብከት በበጀት ዓመቱ ለመንበረ ፓትርያርኩ በሚልኩት የ35 ከመቶ ገቢ) ላይ ባተኮሩ፣ እንደ ሞኝ ዘፈን የአምናው ለዘንድሮ ግልባጭ እየተደረጉ በሚደጋገሙ፣ እውነታቸው በአመዛኙ አጠራጣሪ በሆኑ ስልቹ የሪፖርት አቀራረቦች ገና ከጠዋቱ እያንቀላፋ፣ ለየት ባለው የጭብጨባ ዘይቤው እና ጫን ባለው የሻይ ዕረፍት እና የራት ላይ ግብዣዎች ደግሞ ‹እየተነቃቃ› እነሆ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡

በጉባኤው ለረጅም ጊዜ የመሳተፍ ልምድ ያላቸው አንድ ተሰብሳቢ ለደጀ ሰላም እንደገለጹት፣ በየጊዜው እያጸጸ እንደመጣው አሳሳቢ የምእመናን ቁጥር (በመንግሥት ስታቲስቲክስ መሠረት)፣ ለአብነት መምህራን እና ተማሪዎች ቀለብ አለመኖር እንዳስከተለው ፍልሰት፣ በካህናት እና መባዕ ዕጦት እንደተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት እና ከድጡ ወደ ማጡ እንደሆነው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮች የመሳሰሉት አንገብጋቢ አጀንዳዎች በስብሰባው ላይ እንዲነሡ፣ ተሳታፊዎች በነጻነት ሐሳባቸውን እንዲያንሸራሸሩ ፈጽሞ አይፈለግም፡፡ ከዚህ ይልቅ አህጉረ ስብከት በሥራ አስኪያጆቻቸው አማካይነት በሚያቀርቡት ‹ሪፖርት› በሊቃነ ጳጳሳቱ በኩል ለፓትርያርኩ በቼክ በሚሰጧት የፐርሰንት አበርክቶ ላይ እንዲያተኩሩ፣ ሌላውን የሪፖርቱን ክፍል እንዲያሳጥሩ ይዋከባሉ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ለስብሰባው የተሠራጨውን የመርሐ ግብር ዝርዝር መመልከት ብቻ እንደሚበቃ ተሳታፊው አመልክተዋል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በ47 አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ በመምሪያዎች እና ድርጅቶች ሐላፊዎች ሪፖርት በተጨናነቀው መርሐ ግብር ውስጥ ‹‹ውይይት›› የሚለው ቃል ለመሐላ የሰፈረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው - እርሱም ‹‹የውሳኔ እና የጋራ መግለጫ ረቂቅ አዘጋጅ ኮሚቴ›› በጉባኤው መጀመሪያ ላይ የተሠየመበትን እና በጉባኤው መጨረሻ ላይ በሚያቀርበው በይዘቱ ብዙም በማይለዋወጠው፣ ከተኣምሩ መቅድሙ በሚበዛው ‹‹ቃለ ጉባኤ እና የጋራ መግለጫ ረቂቅ›› ላይ የሚደረግ ነው፡፡ ለእያንዳንዳቸው 30፣ 30 ደቂቃ የተሰጣቸው የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ የሕጻናት እና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የሪፖርት ማቅረቢያ እና የውይይት ጊዜያት ቢኖሩም በራሳቸው ውጤታማ አይሆኑም፤ ከዋናው የስብሰባው አጀንዳ ጋራም ግንኙነት አይኖራቸውም፡፡

ቤተ ክርስቲያን በብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ ተወካዮቿ ደረጃ ‹‹ከእግር እስከ ርእስ›› በአንድ አዳራሽ በተሰበሰበችበት፣ ከጥቅምት 6 - 11 ቀን 2003 ዓ.ም ለስድስት ቀናት በሪፖርቶች ናዳ ሲጨናነቅ ለሚቆይ ጉባኤ በስድስተኛው ቀን ከቀኑም ለ20 ደቂቃ የሚካሄድ ‹ውይይት› ይበቃዋል ቢባል ነገሩ እንዴት ነው አያሰኝምን? የሪፖርቱ ዶፍ እውን እንደሚባለው የአህጉረ ስብከቱን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እና ሞራላቸውን ለመጠበቅ ወይስ በነገር ብዛት ለማደንዘዝ? ለወጉ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 50 ንኡስ አንቀጽ ሰባት እንደተመለከተው የመንበረ ፓትርያርኩ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) ለስብሰባው የሚሆኑ የመነጋገሪያ ርእሶችን (አጀንዳዎችን) የማዘጋጀት ሥልጣን እና ተግባር ተሰጥቶት ነበር፡፡

አስተያየት ሰጪው አያይዘው እንደሚያስረዱት ይኸው የስብሰባው አካሄድ ጥቂት ለማይባሉት የጉባኤው ተሳታፊዎች አያስጨንቃቸውም፡፡ እንዲያውም አዘጋጆቹ ጉባኤተኞቹ ስብሰባውን በቀጣይነት ስለ መሳተፋቸው በስም ዝርዝር እና በፊርማ ስለማይቆጣጠሩ፣ የጉባኤው ውሎ እና አመራሩም ስለሚያሰለች በስብሰባው ሰዓት መርካቶ ወጥተው ሸቀጥ ሲሸምቱ የሚዉሉቱ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡ ከዚህ የባሰው ግን እኒህ የእግረ መንገድ ጉባኤተኛ ‹ሸማቾች› ከየሀገረ ስብከታቸው ለስድስት ቀን ወጥቶ ሊከፈላቸው የሚገባውን አበል እስከ ዐሥራ ስድስት ቀን ድረስ እያስመዘገቡ ለመውሰድ የመድፈራቸው የጠራራ ፀሐይ ዘረፋ ነው፡፡ በአናቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ የአህጉረ ስብከት ተወካዮች በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 46 ንኡስ አንቀጽ አንድ/ሀ ስለ መንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አመሠራረት እና አቅዋም ከተደነገገው ውጭ ለአበል ሲባል በወዳጅነት ተጠራርተው የሚገኙ ናቸው፡፡

በቃለ ዓዋዲው መሠረት ሀገር አቀፉን ስብሰባ መካፈል የሚችሉት ፓትርያርኩ፣ በየአህጉረ ስብከቱ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የተመደቡት ሊቃነ ጳጳሳት፣ በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ከመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት የኮሚሽን፣ የመምሪያ እና የድርጅት ሐላፊዎች፣ ከየመንበረ ጵጵስናው ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ተመርጠው የተወከሉ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በአንድነት ናቸው፡፡ በልማዱ ግን ከተብሳቢዎቹ ውስጥ የአህጉረ ስብከት ሠራተኞች እና ካህናት ይበዙበታል፤ ከእኒህም ብዙዎቹ ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም እና መዝገብ ቤቶች ናቸው፤ በሚያሳዝን ሁኔታ በስብሰባው ላይ በመገኘት ቤተ ክርስቲያናቸው ያለችበትን ቁመና በቁጭት ለመረዳትም ለማስረዳትም አጋዥ ሚና ያላቸው የስብከተ ወንጌል፣ የምእመናን ተወካዮች እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የመሳተፍ ዕድሉ የላቸውም፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በመልእክታቸው እንዳሉት ሰበካ ጉባኤ በአደረጃጀቱ በምእመናን የላቀ ተሳትፎ ተጠናክሮ ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት ለመጣል ሊሠራ ከሆነ፣ ይህን የተሳታፊዎች ውክልና አግባብነት ጉዳይ በመንበረ ፓትርያርኩ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሚተላለፉትን ውሳኔዎች የማስፈጸም ሐላፊነት ያለባቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሰበካ ጉባኤ መምሪያ እና የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤያት በጥብቅ ሊከታተሉት ይገባል፡፡ በአጭሩ ተጨምቆ በልዩ ዕትሙ ላይ በቀረበው የአህጉረ ስብከት ሪፖርት ማጠቃለያም የቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ በአግባቡ አለመከበር እና እንዲከበርም ጥረት አለማድረግ እንደ ቀዳሚ ችግር ተጠቅሷል፡፡

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ባቀረቡት ሪፖርት የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ አጠቃላይ ሪፖርት ላይ አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮች አጋጥመዋል፤ ትችቶችም መሰንዘራቸው አልቀረም፡፡ የአዲስ ሀገረ ስብከት በሁለት ቦታዎች ስሙ በአጉል መነሣቱ አልቀረም፡፡ የአህጉረ ስብከትን ሒሳብን በተመለከተ በቀረበው የተጨመቀ ሪፖርት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በበጀት ዓመቱ ሊገባ ከሚገባው ወደ 13‚667‚726.20 ብር በመቀነሱ በመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላላ ገቢ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ሀገረ ስብከቱ በ2001 ዓ.ም የበጀት ዓመት 5‚700‚012.11 ብር የጠቅላላ ገቢውን 35 በመቶ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ያስገባ ሲሆን በ2002 ዓ.ም 47‚115‚384.60 ጠቅላላ ገቢ አግኝቶ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈሰስ ያደረገው 6‚125‚000 ብር ነው፡፡ የ2002ቱ ከ2001ዱ የ424‚987.89 ብር ብልጫ ቢኖረውም ሀገረ ስብከቱ በዘንድሮው ዓመት በገቢው ወጪውን ስለመሸፈኑም ይሁን የፐርሰንት ዕድገት ስለማሳየቱ በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ስታቲስቲክስ ላይ የተመለከተ ነገር የለም፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ከልማት ተቋማት በሙሉ ፐርሰንቱን በቅጽ ሞልተው አለማሳየታቸው እና በቅጽ የታየውም የሀገረ ስብከት እና የመንበረ ፓትርያርክ ድርሻ ተጠቃልሎ አለመግባትን ባጋጠሙ ችግሮች ዝርዝር ውስጥ የተመለከተ ሲሆን በተለይም ይህ ድክመት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ ጎልቶ እንደሚታይ ተገልጧል፡፡ ከ13 ሚልዮን ብር በላይ የገቢ ዕቅድ ጉድለት የታየበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሁሉም ሀገረ ስብከት ማእከል እና አርኣያ በመሆኑ ሰበካ ጉባኤያትን በማጠናከር ረገድ በመልካም ምሳሌነት እንደ ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ከፍ ብሎ መታየት እንደማይገባው መምሪያው በማጠቃለያ ሪፖርቱ ላይ አሳስቧል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ከጽ/ቤቱ እስከ መንበረ ፓትርያርኩ ድረስ ለሹመት፣ ለሽልማት፣ ቅጥር እና ዝውውር፣ ኪራይ እና እድሳት የተዘረጋ የጥቅም ትስስር መኖሩ ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ገቢ ይሆናል ተብሎ በሌላ ዕቅድ ከተያዘ ብር 3‚504‚790.05 ውስጥ የቁሉቢ ንዋየ ቅድሳት ማደራጃ ሒሳብ በዋናነት እንደሚገኝበት ተገልጧል፡፡

የ26 የሥራ ክፍሎችን ሒሳብ መመርመሩን የገለጸው የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ የብር 2‚405‚779.44 ሣንቲም ጉድለት ማግኘቱንና ከዚህም ውስጥ አብዛኛው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ (ወሊሶ) ሀገረ ስብከት የአዳዲ ቅድስት ማርያም መሆኑን ገልጧል፡፡ በመምሪያው ምርመራ ብር 3‚369‚561.33 ሣንቲም ሳይወራረድ በሰነድ የተገኘ ሲሆን ከዚህም ውስጥ አብዛኛው የምሥራቅ ጎጃም እና የሰሜን ሸዋ አህጉረ ስብከት እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ቀደም ሲል አስተያየታቸውን የጠቀስንላቸው የጉባኤው ተሳታፊ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሕግ አውጪ፣ በሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና የአስተዳደር ጉባኤው (ሥራ አስፈጻሚው) ሰብሳቢ በመሆን ሕግ አስፈጻሚ፣ በቋሚ ሲኖዶስ አባልነታቸው እንደ ሕግ ተርጓሚ በመሆን በአስተዳደር ሞያ እና በሌሎች መስኮች ባለሞያዎች ላይ በዐምባገነንነት የሠለጠኑበትን ሁኔታ የፈጠረው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙበት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በ2001 እና በ2002 ዓ.ም ባሳየው የ35 በመቶ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ መካከል የተጋነነ ልዩነት አላሳየም፡፡ በርግጥ በሀገረ ስብከቱ ይታያል ከሚባለው ደካማ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ይህ ብዙም ባይገርምም በተንጠልጣይ ሳይወራረድ በሰነድ ይገኛል የሚባለው ሒሳብ ግን አስደንጋጭ ነው።

የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት እና የሕጻናት እና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ከገቢያቸው በላይ ወጪ ማድረጋቸው በዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡ መጻሕፍትን በማሳተም እና በማሠራጨት ላይ የሚሠራው የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት 2‚735‚801.07 ብር ገቢ አድርጎ ብር 3‚523‚019.22 ሣንቲም ወጪ አድርጓል፡፡ ወጪው ከገቢው የበለጠበት ምክንያት ‹‹በክሬዲት የታተሙ መጻሕፍት ዕዳ ስለተከፈለ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ትእዛዝ በበጀት ያልተያዘ ብር 230‚000.00 ወጪ ሆኖ በመከፈሉ ነው›› ተብሏል፡፡ ይሁንና መጻሕፍት በሰነድ ከሚታወቁበት ቅጂ በላይ እንዲታተሙ እየተደረገ በደንበኛው አሠራር ከማተሚያ ቤቱ ወጥተው ወደ አከፋፋዮች እጅ ሳይገቡ ሐላፊዎቹ በድብቅ አውጥተው ቀድመው እየሸጡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጥቅሟን የምታጣበት አሠራር ለጉድለቱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የድርጅቱ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በአንጻሩ በሥሩ የሚገኘው የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት በከፍተኛ የማቴሪያል ችግር ላይ እንዳለ ተመልክቷል፤ ወረቀት እና የኅትመት መሣሪያዎች ከውጭ ሀገር በርዳታ ይሁን በብድር አለመገኘቱ፣ ለማሽኖች በቂ ጥገና አለመደረጉ ማተሚያ ቤቱን ያጋጠሙት ችግሮች ናቸው፡፡

ረቡዕ ሪፖርት እንዲቀርብ ፕሮግራም የተያዘለት የሕጻናት እና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅትም ብር 34‚365‚617.97 በገቢ መዝግቦ 34‚ 715‚423.79 ብር ወጪ ማሳየቱ ታውቋል። ከቤተሰብ እና ኅብረተሰብ ጋራ ለሚኖሩ ሕጻናት፣ ከኤች.አይ.ቪ ጋራ ለሚኖሩ ተረጂዎች የትምህርት፣ የምግብ፣ የአልባሳት እና የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅቱ በዕውን በሌሉ ሕጻናት ስም በቀጣይነት የሚመጣ አገልግሎት ለግል ጥቅም እንደሚውልበት፣ ለርዳታ የመጣ መኪና ታርጋው እየተቀየረ ኮንቴይነር ሳይቀር የሚሸጥበት በዚህም መኖርያ ቤታቸውን በማይታመን ሁኔታ ያሣመሩ የድርጅቱ ሐላፊዎች የሚገኙበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ራሱን በባለሞያ እና በበጀት በማጠናከር በሁሉም አህጉረ ስብከት የሒሳብ ምርመራ ለማድረግ ያቀደው የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ እኒህን መሰል ድርጅቶችንም እልምት ውስጥ አስገብቶ በብርቱ በመፈተሽ እያጋለጠ ሙስና የሚያፍርባቸው ተቋማት ሊያደርጋቸው ይገባል፡፡ አልያ ውጤቱ የጎፋ ጥበበ እድ ማሠልጠኛ ገጥሞታል እንደተባለው የህልውና ስጋት ከመሆን ላያልፍ ይችላል፡፡

በሪፖርቱ እንደተመለከተው የጎፋ ጥበበ እድ ማሠልጠኛ ምርቱ እና የምርት ውጤቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ገቢው ቀንሷል፤ ለባለሞያዎች በቂ ደመወዝ መክፈል አልቻለም፤ ሠራተኞቹም የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ ማሠልጠኛውን በመልቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ችግሩ መፍትሔ ካልተሰጠው ለወደፊቱ ችግሩ ለቤተ ክርስቲያን ከባድ ሸክም ይሆናል፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት ላይ ተጠቅሰው ትችት ካስከተሉት ነጥቦች መካከል በ10‚670 አብያተ ክርስቲያን ውስጥ ከ2‚706‚253 በላይ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በውስጡ በመያዝ ‹‹ወጥ መዝሙሮችን እንዲዘምሩ፣ በክብረ በዓላት ሐላፊነታቸውን እንዲወጡ›› እያደረገ የሚገኘው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበራትን ለመከታተል የሚያስችል ወጥ የሆነ መመሪያ አለማውጣቱ፣ ቋሚ የሥራ ማስኬጃ እና የኅትመት በጀት እንደሌለው መነገሩ ይገኙበታል፡፡ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የተሰባሰቡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች አስተዋፅኦዋቸው የወቅት በመሆኑና ተገቢውን ቦታ ባለማግኘታቸው፣ የመምሪያውም ሠራተኞች ክብረ በዓል ካልመጣ በቀር ሥራ ፈተው በመዋላቸው የሚያማርሩ ሲሆን በአንጻሩ ሐላፊው በአሜሪካዊ ዜግነታቸው እና በአሜሪካ ባቋቋሙት ‹‹የግል ቤተ ክርስቲያን› ‹ቆሞስ› እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ራሳቸውን ‹‹የመንበረ ፓትርያርኩ ሕጋዊ ወኪል›› ብለው ከሚጠሩት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ጋራ በመምሪያው ያላቸውን ሐላፊነት ተጠቅመው ‹‹የቅን ልቦና ተሐድሶ መጥምቃውያን ኅብረት›› በተሰኘ እንቅስቅሴ ወጣቱን ለመበከል የተጻጻፉት ደብዳቤ እዚሁ መጦመሪያ መድረክ ላይ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በመጪው የጥቅምቱ ሲኖዶስ ለማዕርገ ጵጵስና ወረፋ ይዘዋል ከተባሉት ቆሞሳት መካከል አንዱ እንደሆኑ እየተነገረላቸው ነው፡፡ በቀጣይም የሰንበት ት/ቤቶች ማ/ መምሪያ በጀት በማስደብ የፈለገ ጥበብ መጽሔት እና የወርኃዊ ጋዜጣ ዝግጅትን ለማስቀጠል፣ የግእዝ እና አማርኛ መዝሙራትን በቪዲዮ፣ ቪሲዲ እና ዲቪዲ በማዘጋጀት ለማከፋፈል ዕቅድ ይዟል፡፡

በዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ከተገለፁት ነጥቦች መካከል ቤተ ክርስቲያኒኦቱ ካሏት ከሦስቱ ኮሌጆች በዲግሪ እና በዲፕሎማ የተመረቁ 75 ደቀ መዛሙርት በሥራ እንደተመደቡ መገለጹም ከተቋማቱ ወጥተው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ በሚሠሩ ምሩቃን ላይ ግርምት ፈጥሯል፡፡ እንደ እነርሱ አባባል ምደባው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅሮች ውስጥ የተደረገውን የሚመለከት ከሆነ ብዛታቸው ከዐሥር ብዙም እንደማይበልጥ በየመምሪያው ውስጥ ያሉ ጓደኞቻቸውን በመጥራት ይቆጥራሉ፡፡ እነርሱም ቢሆኑ የትምህርት ደረጃቸውን ያህል የሚመጥን ቦታ አለማግኘታቸውን ያስረዳሉ፡፡ በነገረ መለኮት ዲፕሎማ እና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በግላቸው ሌሎች ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን የሚናገሩት እኒህ ሠራተኞች የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆኑት መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ እንዳሉት ተቋማቱ ‹‹አስተምረው የበተኗቸው ወጣቶች ጡረተኞች›› መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ 15 መምሪያዎች ውስጥ በዋና እና በምክትል የሐላፊነት ቦታ ላይ ካሉት ውስጥ በሁለቱ ብቻ (በቅርቡ በሦስቱ የተደረገውን ለውጥ ሳይጨምር) በዘመናዊ ትምህርታቸው የገፉ ሐላፊዎች መኖራቸው ትምህርት ተገቢውን ዋጋ ያልተሰጠው መሆኑን፣ መማር ማለት ከደረጃ ዝቅ የማለት የበታች-ሠራተኝነት-ተዘምዶ እንደተሰጠው ያስመስላል ይላሉ፡፡ ከሐላፊነት ደረጃዎች ውጭ “ኢየዓርግ ወኢይወርድ” (የማይወጣ፣ የማይወርድ)፣ እንደ ዶግማ የማይለወጠው የደመወዝ ስኬል ሌላው መገለጫ መሆኑን ምሩቃኑ ይናገራሉ፡፡

አንድ በነገረ መለኮት እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊታዊ ትምህርት ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ፣ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ከአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ የተመረቀ ደቀ መዝሙር በዲፕሎማ እና በዲግሪ ተመርቆ ሲመደብ መነሻውም መጨረሻውም 347.00 የኢትዮጵያ ብር እና 600.00 የኢትዮጵያ ብር ደመወዝ እንደቅደም ተከተላቸው ይከፈለዋል፡፡ ከዚህም ላይ የሥራ ግብር፣ የጡረታ እና ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ እና ማጠናከሪያ ተብሎ ይቆረጣል፡፡ ክፋቱ መቆረጡ ሳይሆን ለዓመታት ሌላው ቀርቶ በየጊዜው የሚደረገው 32 ብር የዕርከን ጭማሪ እንኳ የማያውቀው መሆኑ ነው፡፡ መንግሥት ከመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ለሚወጡ መምህራን ከቤት አበል ጋራ 836 ብር፣ በድጋፍ ሰጪዎች ደረጃ የሚከፈለውን የደመወዝ መነሻ ወለል ከ400 ብር በላይ ባደረገበት፣ ራሱ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በጥበቃ፣ ጽዳት እና ተላላኪ የሚቀጥራቸውን ሠራተኞች መነሻ ደመወዝ ብር 400 እንዲሆን በወሰነበት ሁኔታ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ከ3 - 4 ዓመታት የተማረ ደቀ መዝሙር ደመወዝ ከ347.00 የኢትዮጵያ ብር በላይ የማያድግበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ሁኔታው ደቀ መዛሙርቱ ከተመደቡባቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅሮች እየወጡ በሌሎች ቤተ እምነቶች ተጽዕኖ ሥር በሚገኙ ድርጅቶች ከመቀጠር ጀምሮ ሴኲሪቲ ጋርድ፣ ፖሊስ፣ በንግድ እና በጉዳይ አስፈጻሚነት እንዲሠማሩ እንዳስገደዳቸው ተዘግቧል፡፡ በዚሁ ደመወዝ ለመኖር ከሚጣጣሩቱም መካከል በጀታቸው በወቅቱ ተጠቃሎ ባለመግባቱ እና ታመው በቂ ሕክምና የሚያገኙበት አቅም በማጣታቸው ሳቢያ በጠበል ስፍራዎች ያለረዳት ወድቀው ሕይወታቸው ያለፉ፣ ሲከፋም የእጅ አመል የሚታይባቸው እንዳሉ በኀዘን ያስታውሳሉ፡፡ በዋና ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ላይ ከየአህጉረ ስብከቱ ለሚዛወሩ ሠራተኞች፣ ከየኮሌጆች ለሚመረቁ ደቀ መዛሙርት፣ አዲስ ለሚቀጠሩ ሌሎች ሠራተኞች የሚከፈለው ገንዘብ፣ ከየአህጉረ ስብከት የፐርሰንት ገቢ ተጠቃሎ አለመግባቱ፣ የኮሌጆች የተጨማሪ በጀት ጥያቄ፣ የደመወዝ ስኬል አለመጠበቅ በወጪ ላይ ጫና መፍጠሩ በበጀት እና ሒሳብ የሥራ ክንውኖች ሥር ተገልጧል፡፡

በአንጻሩ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ከኮሌጆቹ ተመርቀው ወደ መተከል እና ጠረፋማ አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ደቀ መዛሙርት ከቦታው አለመሄዳቸው ባጋጠሙ ችግሮች ዝርዝር ውስጥ ተመልክቷል፡፡ በመስከረም ወር በተካሄደው የሰባክያነ ወንጌል የሁለት ቀን ዐውደ ትምህርት ላይ እንደ ሁመራ፣ አፋር፣ ሽሬ፣ ዋግ ኽምራ፣ ኢሉአባቦራ፣ ማይጨው ያሉት አህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሐላፊዎች ይህንኑ ሪፖርት አቅርበው ነበር፡፡ በሪፖርታቸው ላይ እንደጠቀሱት የደቀ መዛሙርቱ ችግር የደመወዝ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ባህል እና ቋንቋ አለማወቅ እና በዚህ የተቃኘ ትምህርት ለመስጠት አለመቻል ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተለይም በሽሬ የቃለ እግዚአብሔር ጥማት ያለባቸው በርካታ የኤርትራ ስደተኞች ሰፊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ያሠሩ ቢሆንም በበጀት እጥረት ሳቢያ እነርሱን የሚያረካ ሰባኬ ወንጌል ለማግኘት አለመቻሉ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከጥበቃ ሠራተኝነት ተነሥተው አንዳች የትምህርት ዝግጅት እና አግባብነት ያለው ሞያዊ ልምድ ሳይኖራቸው የሠራተኛ አስተዳደር ሐላፊ እና የአስተዳደር ጸሐፊ ሆነው እስከ 1200 ብር የሚከፈላቸው ግለሰቦች መኖራቸው ተመልክቷል፡፡ በረጅም ጊዜ ቆይታ እና በመቀራረብ ብቻ ከሐላፊነት ደረጃ የሚደርሱት እነዚህ ግለሰቦች ይህ ነው የሚባል ሙያም ሆነ ሥራ የሌላቸው መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹የወለደው ልጁ ከቤተ ክህነቱ በጡረታ ተገልሎ አባትየው ግና ሥልጣኑን ጨምድደው 'በሥራ' ላይ ናቸው ቢባል ምን ይልሻል?›› ይላል ዘመን በተሻገረው ተቋም ውስጥ ሽምግልና ከወጣትነት ግብግብ መግጠማቸውን ሲናገር ፈገግታውን መደበቅ የሚሳነው አንድ የቤተ ክህነቱ ሠራተኛ፡፡ የሆነው ሆኖ አዲሱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመዋቅራዊ ጥናታቸው ይህን ውጥንቅጥ መልክ ያስይዙት ይሆን?

በሪፖርቱ ላይ በአስተዳደር ዘርፉ የተፈጸመውን በተመለከተ ከ340 የቤተ ክህነቱ ሠራተኞች መካከል 109ኙ ናቸው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ያላቸው ሴቶች በበረከቱበት ዘመን በቤተ ክህነቱ ከጸሐፊነት የዘለለ ሐላፊነት እምብዛም የላቸውም፡፡ ከእነርሱም በዘመድ አዝማድ የገቡ፣ ለተመደቡበት መጠነኛ ሐላፊነት እንኳ ብቃት የሚያንሳቸው  እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ከተመሠረተ 37 ዓመታትን ያስቆጠረው ሰበካ ጉባኤ ወደ ፍጹምነት ደረጃ ደርሶ አለመታየቱ ከፍተኛ ችግር በመሆኑ አጠቃላይ ጉባኤው ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል - ጉዳዩ በጉባኤው አጀንዳ እንደማይሆን ቢታወቅም፡፡ ምናልባት በቀጣይ የሰበካ ጉባኤውን ቃለ ዓዋዲ ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ መቅረቡ፣ ለዚህም በሕግ አገልግሎት መምሪያው በኩል የማማከር ሥራ መሠራቱ መገለጹ ተስፋ ይሆናል፡፡ የቅዱስ ያሬድ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅን ግንባታ ማስጀመር፣ ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በዓልን ለማክበር፣ በአስተዳዳሪዎች ምደባ እና ዝውውር የካህናት አስተዳደር መምሪያ ድርሻ እንዲኖረው መታሰቡ፣ ለአህጉረ ስብከት እና ለወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱ ከሪፖርቱ መድበል የተገኙ ሌሎች የመሻሻል ተስፋዎች ናቸው፡፡ ሁሉም ተስፋዎች ግን የሰሞኑን ሦስት እና የመጪዎችን 12 ሹመኞች ሞያዊ በረከት ይጠብቃሉ።

ጉባኤው አሁንም የቀጠለ ሲሆን የተያዘለት የስብሰባ ጊዜ ሲጠናቀቅ ቀሪ ሂደቶችንና ተያያዥ ጉዳዮች መሠረት አድርገን እንመለስበታለን።  

10 comments:

Anonymous said...

+++
የተወደዳችሁ ደጀ ሰላሞች ፥
ስለ ሪፖርቱ እግዚአብሔር ይሰጥልን። ብዙ የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታወችን እያወቅን ነው።
ብዙ የሚሰራ ሥራም እነዳለ ማንም የሚረዳው ጉዳይ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያ ጉዳይ ለሚያሳስበው ሁሉ።
አሁን በአቀረባችሁት ሪፖርት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማ.መምሪያ ሃላፊን ጉዳይ ዳስሳቺሁታል።
እኒህ ሰው በእነደዚህ ያለ ሁኔታ እያሉ ጵጵስና ቢሾሙ ጥፋቱ የማን ነው ትላላቺሁ!!!
በእውነት ለቤተ ክርስቲያን የሚገደን ከሆነ አስቅድሞ ደምጽ ማሰማት አይገባም ወይ?!
እባከቺሁ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፥ ለፓትርያርኩ ድምጻቺንን አሰሙልን ባላቺሁ መንገድ ሁሉ!!!
ቤተ ክርስቲያን መፋረጃ የሚያደርጉ “የግል ቤተክርስቲያን” የከፈቱ ፥ የአሜሪካ ዜጎቸ ፥ እንዲሁም በቀኖናዋ እና በዶግማዋ እምነት የሌላቸው ሰዎችን እየሾሙ ቤተ ክርስቲያንን አይፈታተኗት!!!
የተወደዳቺሁ ደጀ ሰላሞች እና የደጀ ሰላም ተጠቃሚች እባካችሁ ሁል ጊዜ ነገር ከሆነ በኋላ ብዙ ከምንል ዛሬ ለተሿሚ ጳጳሳት ትኩረት እንዲሰጥ በነዚህ አጪር ቀናት ባለን አጋጣሚ የድርሻችንን እንወጣ!!!
አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርሰቲያንን ይጠብቅልን !!!

Anonymous said...

thankyou dejeselam for updating us.
but u know the administration complexity of our church needs a great research study to solve.

if possible let u open a discussion forum on how to be the administrational organizational structure of our church .meaning everybody will givehis vision on how the church administration will be

Anonymous said...

መቼ ይሆን አባቶች ስለገንዘብ ማውራት ትተው ስለመንጋው መበተን፤ ቤተክርስቲያኒቷን እያስነቀፈ ስላለው የአስተዳደር ብልሹነትና እና ቀኖና ቤተ-ክርስቲያን ጥሰት የሚወያየው? ዙሪያ ጥምጥም መሄዱ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም።

"...ትንሣኤሽን ያሳየን.."

Anonymous said...

ድጀሴላሞች እግዚአብሔር ይስጣችሁ፡፡ ስለ ቤተክርስቲያን እንድናስብ ታደርጉናላችሁና፡፡

የሚሰማ ከተገኘና የማሰሚያው መንገድ ካለ፣ ለአባቶቻችን አንዲት መልዕክት አድርሱልኝ፡፡ እርሷም ታላቅና አስፈላጊ የቤተክርስቲያንን ህልውና የምትመለከት ጥያቄ በመሆኗ አጀንዳቸው አድርገው ቢወያዩባት ከጥፋት ለመዳን አንድ አስትዋፅኦ ታደርጋለችና፡፡ እርሷም እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡-
በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ ትምህርት በየገጠር ቀበለው እየተስፋፋ ይገኛል፣ በአንፃሩ የቤተክርስቲያን ትምህርትና የአብነት መምህራን የኖሮ ሁኔታ እይተሸረሸረ፣ ወላጆች ከቤተክርስቲያን ትምህርት ልጆቻቸውን እያራቁ ላይ ናቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የከተማው ወጣት ከትምህርት ቤትና ከቴሌቪዥን ጋር ያለው ዝምድና ከእግዚአብሔርና ከወላጆቹ ጋር ካለው እጅግ እየበለጠ ሄዷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉቱ እግዚአብሔር የለሽ ሴኩላርና ወይንም ፅንፈኛ እስላሞች በመሆን ክርስትናን የሚሸረሽሩ ሕጎችን፣ የአኗኗር ዘይቤዎችን፣ የትምህርት ይዘቶችን በመቅረፅ ለስም በሀይማኖት ጣልቃ አንገባም እያሉ በተግባር አማኝ በማጥፋት ይተጋሉ፡፡

ከእነዚህ ከላይ ካመለከትኳቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ቅዱስ ሲኖዶስ ምን አዲስ ስልት እየቀየሰ ይገኛለ?

awudemihret said...

ደሰ እግዚአብሄር ይስጥልን፤፤ስንት ዘመን ተደብቆ የቆየን ሚስጥር ይፋ አደረጋችሁልን፤፤በርቱ በስራችሁ ጠንክሩ፤፤
ቤታችን የምትጸዳበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤፤

Tamiru said...

እግዚአብሔር አምላካችን ይህንን መንፈሳዊ ጉባኤ
አባቶቻችንን ለቤተክርስቲያን የሚበጀውን አስበው ቤተክርስቲያንን የሚታደጉበት
አጥፊዎችን የሚገስፁበት
ለቤተክርስቲያን ህልውና የሚጨነቁበት ያድርግልን፡፡

Anonymous said...

Dejeselam

I pray for God to give you strength and power to continue in your job. I was how as you coordiante and organize all this news throught the world, I mean time, money and skill. Let our lord bless your job Amen.
I am helping you only by reading and praying

Anonymous said...

Dear Dejeselams or Your Holliness members of the Synod

I have read the ajenda to be discussed on. We have read in the news that in southern part of the country some Orthodox christians were endangered and their houses were set on fire. Is this not an issue for discussion? Is getting legal solution for that politics? We know that St Paul, when illegally imprisoned,as a Roman citizen, exercised his legal right to appeal to the Emperor of Rome.

123... said...

ደጀ ሰላሞች በርቱ የ አዚህ አይነት መንገድ አመላካች ፅሁፍ አጅግ ጠቃሚ ነው።
አሁን ጥያቄው ይሄ ሁሉ ችግር አንዴት ይፈታ ? የሚለው ነው ።በተለይ በገንዘብ ጉዳይ አንዴ መዥገር የተታበቁት አካላት በ ንግግር በ መመርያ ይለቃሉ የሚል አምነት የለኝም ።
በ አሁኑ የ ጥቅምቱ ጉባኤ ላይ ምንም አይነት አይነተኛ ለውጥ ካልታየ አና ነገሮችን አድበስብሶ የማለፍ ሂደት ከታየ ትህትና የሚባል ነገር ገደቡን ያጣል ። ለምን የ አዋሳ ምመናን አይነት የ አዲስ አበባ ህዝብም ሆ ! ብሎ ቤተክህነቱ ውስጥ ያሉት መዝገሮች አስክያባረሩ አንደሚጠበቅ አልገባኝም ።

Unknown said...

㜎㜎‹‹የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም፡፡›› 1ኛ ቆሮ 15፣50
የእግዚአብሔርን መንግስት በምድር ለመመስረት በመንግስቱ አምሳያ በተመሰረተችው ቤተክርስቲያን አባላት የሆንን የሁላችን ጌታ፣የስማችን መጠሪያ እና በደሙ የመሰረታት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች እንደ አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለሁላችን ይሁን፡፡ አሜን፡፡
የአንድ ነገር ቅርጽ እና ማንነት በመበስበስ ይጠፋል፡፡ ማንነት ክብር መገለጫ እና የመሳሰሉት በመበስበስ ለብክነት እና ውርደት ይጋለጣሉ፡፡ የሰው አካልና ክብር በመበስበስ መጥፋትን ገንዘቡ ያደረገው በራሱ አልታዘዝም ባይነት ነው፡፡የዚህ ክስተት መገለጫው ቅርጽን እና ማንነትን ማጣት ብቻ ሰይሆን መጥፎ ጠረንም ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ ተቃራኒው ደግሞ አለመበስበስ ነው፡፡ የመበስበስ መነሻውም መድረሻውም አልታዘዝም ባይነት መሆኑን ስንገነዘብ በህይወታችን የሚታዩ የማንነትና የህይወት መበስበሶችን ለይተን በማወቅ ህይወታችንን ከንቅዘት መጠበቅ እንጀምራለን፡፡
ቤተክርስቲያን በጥላዋ ያሉ ምእመናንን ጌታን በማመን በሚበሰብስ አካል በማገልገል በማይበሰብሰው አካል ዳግም እንዲኖሩ የምታደርግ ሰማያዊ ተቋም ናት፡፡ በጥላዋ የሚኖሩ እና አለምን ከክፋትዋ ጋር ድል ያደረጉ ምእመናን ሞትን ድል አድርገው የድልና የድህነት ዝማሬን በብርጭቆው ባህር ላይ በድል ይዘምራሉ፡፡ራዕ 15፣23
ለሰው ልጅ ጌታ በተፈጥሮ ያጎናጸፈውን ክብርን ማጣት ምክንያት እምቢተኛነትና አልታዘዝም ባይነት ሲሆን ይህ በሽታው ዛሬም በቤተክርስቲያናችን ከምንጊዜውም በላይ ገዝፎና በዝቶ ይታያል፡፡ ሁሉም ይህን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ መበስበስ ዳር ቆሞ በመተቸትና በማማት ማስተካከል የሚቻል ይመስለዋል፡፡ የችግሩ ባለቤቶችም እራሳቸውን ከመመርመር ይልቅ እንደቀድሞዎቹ ወላጆቻችን ሌሎችን ተጠያቂ ለማድረግ ይሯሯጣሉ፡፡ አዳም ሄዋንን ሄዋን ደግሞ እባብን መጠቆም፡፡ የሚገርመው ግን ሁሉም በሰበሱ፡፡ ጠላታችን አፈር ልሶ ሲነሳ ሁላችንም ግን ወደ መጣንበት አፈር ምድር መመለስን መበስበስን ገንዘብ አደረግን፡፡ ዛሬም ቅድስና ገንዘቧ በሆነ ለሀገራችን ክብር መሆን በቻለች አሁንም እድሉ ባላት ቤተክርስቲያን ተጠልለን የሰው ዘር ሁሉ ለመበስበስ ተላልፈን በተሰጠንበት የመካሰስ ህይወት ውስጥ ዛሬም እንገኛለን፡፡ የሚገርመው አብዛኛው ችግሮቻችን መነሻቸው ከእያንዳንዳችን ማንነት ጀምሮ ነው፡፡ ሁላችንም የየራሳችንን እና የየማህበራችንን እና የየቡድኖቻችንን የመበስበስ ማንነት ለማስተካከል ለደቂቃዎች እንኳን ብንጥር ለውጥ ያኔ ይጀምራል፡፡ በሚበሰብስ ማንነት መበስበስ የሌለበትን መንግስት መውረስ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ አዎን አይቻልም፡፡ አሜን፡፡kerlos2010@gmail.com

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)