October 2, 2010

ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የ1.8 ሚልዮን ብር መኪና ተሸለሙ

  • ምእመናን ‹‹ሽልማቱ ለሀገረ ስብከቱ ስድብ ነው›› ይላሉ
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 2/2010፤ መስከረም 22/2003 ዓ.ም):-  ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን እያገለገሉ ለሚገኙት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የ1.8 ሚልዮን ብር ላንድክሩዘር መኪና ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡ ከመኪናው ጠቅላላ ወጪ ገሚሱ የተሸፈነው በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙት የደብረ መንክራት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እና ደብረ ምጥማቅ ጻድቃኔ ማርያም ገዳማት ሲሆን የተቀረው ደግሞ ሀገረ ስብከቱ ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከሚልከው ፈሰስ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ ወጪ ተደርጎ ነው፤ ግዥው የተፈጸመው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ነው፡፡ በዘመን መለወጫ ዋዜማ በመንበረ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ በነበረው የሟሟቀ ድግስ የመኪናውን ቁልፍ ለብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሲሆኑ ለድግሱ ከሀገረ ስብከቱ  በቀሲስ በቀለ ወንድማገኘሁ በኩል 30‚000 ብር ወጪ መደረጉ ተዘግቧል፡፡
ከሀገረ ስብከቱ አዳጋች መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ብፁዕነታቸው ማዕርገ ጵጵስና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሉበት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ከሰጡት የረጅም ዘመን አገልግሎት እና በ2000 ዓ.ም የካቲት ወር ብፁዕነታቸው የጥንታዊቷን የመርሐቤቴ ገረን ማርያም ቤተ ክርስቲያን እድሳት የመሠረት ደንጊያ ጥለው ሲመለሱ ጫጫ ላይ ደርሶባቸው ከነበረው የመኪና አደጋ አኳያ ሽልማቱ ቢያንስ እንጂ እንደማይበዛ አንዳንዶች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በአንጻሩ በሀገረ ስብከቱ አንዳችም አመርቂ የልማት እንቅስቃሴ አለመካሄዱ የእግር እሳት የሆነባቸው ምእመናን እና የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ‹‹ሽልማቱ ለሀገረ ስብከቱ ስድብ ነው›› በማለት ያማርራሉ፡፡ ብፁዕነታቸው ለፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ 18 ዓመት በዓለ ሢመት በተገለጠው ሐውልተ ስምዕ ላይ በመገኘት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በውድ እና በግድ በተዋጣ ከ45‚000 - 85‚000 ብር ለአቡነ ጳውሎስ የተበረከተላቸውን የ3.5 ሚልዮን ብር የ2010 ሞዴል ባለስምንት ሲሊንደር ቶዮታ መኪና ቁልፍ በሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ አስተናባሪነት ለአቡነ ጳውሎስ ሰጥተው እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውሰዋል፡፡

ብፁዕነታቸው አብዛኛውን የሥራ ጊዜያቸውን በጸሎት እና መጻሕፍትን በመመርመር የሚያሳልፉ ‹‹ትሑት እና የዋህ›› አባት ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት የመንበረ ጵጵስናው መቀመጫ በሆነው ደብረ ብርሃን ከተማ የሌሎች እምነት ተቋማት እስከ ሰባት የሚደርሱ ዐጸደ ሕፃናትን ሲከፍቱ፣ ባላገሯ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን የረባ ክሊኒክ ይሁን ዐጸደ ሕፃናት አለመክፈቷ ድክመት ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ እንደ ሆነ ታዛቢዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ሀገረ ስብከቱ በየዓመቱ በሀገር አቀፉ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ሰበካ ጉባኤ ላይ መስፈርቱ በግልጽ በማይታወቀው የደረጃ አሰጣጥ አንደኛ ከሚወጡት ተርታ እየተሰለፈ የሚሸለም መሆኑ ሲታይ ደግሞ ሁኔታውን መሪር እንደሚያደርገው የሀገረ ስብከቱ ምእመናን ይናገራሉ፡፡
አጣዬ፣ ይፋት፣ አንኮበር እና አንጾኪያ የተባሉ የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ጥንተ ክርስትናቸው እየተዳከመ በኢ-ጥሙቃን አማሌቃውያን እየተጥለቀለቁ፣ እንደ አጣዬ ሰንበቴ ቅዱስ ሚካኤል ያሉት አብያተ ክርስቲያን ቅጽሮቻቸው በኢጥሙቃኑ ተጥሶ የመስኮት መስተዋቶቻቸው እየደቀቁ በተለይም ደግሞ ኦርቶዶክሳውያን እኅቶች እምነታቸውን እየቀየሩ ወደ ዐረብ አገሮች እየተላኩ መሆኑን ምእመናኑ በቁጭት ይገልጻሉ፡፡ ጸሎቱም የሚሠምርልን ከተግባር ጋራ ሲተባበር ነው ያሉት ምእመናኑ፣ የሀገረ ስብከቱን የልማት እንቅስቃሴ በተሻለ አቅማቸው መደገፍ የሚችሉት እንደ መንዝ ቅዱስ ሚካኤል፣ ደብረ መንክራት ጻድቃኔ ማርያም ገዳም እና ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ያሉት አብያተ ክርስቲያን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በሰበብ አስባቡ ልማድ እየሆነ ለመጣው ድግስ ቅቤ እና በጦስኝ የደለበ በግ አቅራቢ ሆነው መቅረታቸው እንደሚያንገበግባቸው ከማጋለጥ አልሸሸጉም፡፡ ከዚህ አኳያ ሀገረ ስብከቱ ‹በሥራ አፈጻጸሙ› ከአንደኞች ተርታ የሚሰለፍበት መለኪያ መስፈርት እንደሚያጠራጥራቸው ታዛቢዎቹ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ፋንታሁን ሙጬም ሃያ በሚደርሱ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አስተዳዳሪዎች እና ጸሐፊዎች እንደተዋጣ በተገለጸ 240‚000 ብር የተገዛች ሃችባክ ሞዴል መኪና በፓትርያሪኩ አማካይነት በሽልማት እንደተበረከተላቸው ተሰምቷል፤ የገንዘቡ ምንጭ ባይታወቅም የሥራ አስኪያጁ የራሳቸው እንደሆነና የሽልማት ሥነ ሥርዐቱም ለፈሊጥ የተዘጋጀ መሆኑን የሚናገሩም አሉ፡፡ የሆነው ሆኖ በዘመን መለወጫ ዕለት በመንበረ ፓትርያሪኩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በዝግ ደጅ በተካሄደ ጥብቅ ሥነ ሥርዐት የመኪናዋን ቁልፍ ለሥራ አስኪያጁ ያስረከቡት አቡነ ጳውሎስ እስከዚያ ቀን ድረስ ተናግረው የማያውቁትን ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በወላጅ አባታቸው በኩል አለኝ ያሉትን የትውልድ ቦታ አንድነት መግለጻቸውን ውስጥ ዐዋቂዎች አመልክተዋል፡፡ ሥነ ሥርዐቱን የታዘቡ ተንታኞች እንደሚያስረዱት ሁኔታው የፓትርያሪኩ እና የሥራ አስኪያጁ ያልተቀደሰ የጥቅም ቁርኝት ምን ያህል ሥር እንደ ሰደደና የማይወጡት ኢ - መንፈሳዊ የጥፋት አዙሪት ውስጥ እንደከተታቸው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በአንጻሩም ከሀገረ ስብከቱ እስከ መንበረ ፓትርያሪኩ ድረስ በመዋቅራዊ መልኩ ግዘፍ ነስቶ መልክ አውጥቶ የሚገኘውን በቡድናዊነት፣ በጠባብነት፣ በሙስና፣ በድለላ እና በፍጹም አድርባይነት የመክበርን ተግባር ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን በሚያሰፍን ፍትሐዊ አሠራር ለመቀየር የሚደረገውን ትግል የሞት ሽረት እንደሚያደርገው አመልካች ነው ይላሉ ተንታኞቹ፡፡

መስከረም 15 ቀን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጎፋ ቤዛ ብዙኀን ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እድሳት መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ ለፓትርያርኩ የወርቅ መስቀል፣ ለሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ደግሞ ‹‹ምንነቱ ያልተገለጸ›› ሽልማት (በሥነ ሥርዐቱ አዘጋጆች ተገለጸ እንደተባለው) መሰጠቱ፣ እንዲህ ያሉ ውድ ገጸ በረከቶችም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ደረጃ ባህል እየሆኑ መምጣታቸው ታህታይ መዋቅሩ  ያልተቀደሰ የጥቅም ቁርኝት ከፈጠረው ላዕላይ የቤተ ክህነቱ መዋቅር  ጋራ ጥገኛ በመሆን ተቋማዊ ሥርዓቱን ከላይ እስከ ታች በክሎ ለአጠቃላይ ዝቅጠቱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህላዌ መራዘም ምክንያት እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በመጪው ጥቅምት በወሳኝ መልኩ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የቁጥጥር መዋቅሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከፍተኛ ውሳኔ በማሳለፍ ለችግሩ መሠረታዊ መፍትሔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)