October 28, 2010

ርእሰ አንቀጽ፦ የሀ/ስብከት ምደባ አጀንዳ አባቶች የምትለያዩበት/ የምትከፋፈሉበት “የመሪባ ውሃ” እንዳይሆን (ዘጸ. 17)

  • ዘዴው “በጎሽ ቆዳ ተደብቆ ጎሽን መውጋት” የሚለው ያረጀ ዘዴ፤ አባቶችን "በሀ/ስብከት ምደባ ሰበብ" መከፋፈልና እርስበርሳቸው ማጋጨት ነው
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 27/2010፤ ጥቅምት 17/2003 ዓ.ም):- የሰሞኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አባቶች የወሰዱት አቋምና በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰኑ ውሳኔዎች የምእመናኑን ልብ በተስፋ የሞላ፣ አንገቱን ቀና እንዲያደርግና በአባቶች ላይ ያሳደረውን ቅሬታ እንዲያነሳ በር የከፈተ ነው። ቅ/ሲኖዶስ አጀንዳዎቹ ላይ በሕቡር ልብ እና በሕቡር ቃል አንድ ሆኖ እየተወያየ መጥቶ ስብሰባውን ለማጠናቀቅ ትንሽ አጀንዳ ፈሪ፣ ምናልባትም የአንድ ቀን ስብሰባ ብቻ ነው የቀረው። ይሁን እንጂ ዛሬ ረቡዕ በነበረው “የጳጳሳት ምደባና ዝውውር” አጀንዳ ውይይት ወቅት የአባቶች አንድነት እንዲፈታ ጥሩ መንገድ የተገኘ ይመስላል። በስብሰባው ወቅት “በአርምሞ” የቆየው አካል በተግባሩ ወቅት “ከንዋመ አርምሞ”ው ነቅቶ በተግባር ውሳኔዎቹን እንዳይቀለብሳቸው እያስፈራን ነው። አበው እንደሚሉት “ዓይጥ ወልዳ ወልዳ …” እንዳይሆን አስግቶናል። ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች ለማቅረብ ወደድን።

በዛሬው ዕለት በቅዱስ ፓትርያርኩ በቀረበው በጳጳሳት ዝውውርና ምደባ ላይ እንደቀደሙት አጀንዳዎች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በአንክሮ አጢነው ሊወያዩባቸው ይገባል። በቅዱስ ፓትርያርኩ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ አንዳንድ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን። ከሀገረ ስብከታቸው ምዕመናን ጋር እጅና ጓንት ሆነው እየሰሩ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወሩ ሰላምን ለማደፍረስ ካልሆነ ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም። ለአብነት ያህል በሀገረ ስብከታቸው አመርቂ የሥራ ውጤት እያስመዘገቡ ካሉት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ አብርሃምን መጥቀስ ይቻላል። ይህ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሳይቀር የታወቀ ነው። በሀገረ ስብከቱ ካሉ  ካህናትና ምእመናን የይነሱልን ጥያቄ ሳይቀርብ የአዋሳ ምእመናን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላይ ላቀረቡትና ላሰሙት አቤቱታ አጫፋሪ በማድረግ ከሀገረ ስብከታቸው ምእመናን ጋር በጥሩ መንፈስና በመግባባት እየሠሩ ያሉትን ሊቃነ ጳጳሳት ለማዘዋወር መፈለግ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ይበጃል ከሚል መንፈስ የቀረበ ስላልሆነ ብፁዓን አበው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በጽሙና ልታስቡበት ይገባል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም
በተለይ የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከትን ለማጠናከር ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ በመሆናቸው፣ ሀገረ ስብከቱ በሁለት እግሩ ቆሟል ለማለት ስለሚያስቸግር፣ የራሱ መንበረ ጵጵስና የተገዛ ቢሆንም ዕዳው ገና ተከፍሎ ያላለቀ በመሆኑ፣ የመንበረ ጵጵስናው ቤተ ክርስቲያን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሌሎችን ቤተ አምልኮ ለተወሰነ ሰዓት በመከራየት አገልግሎት ሲሰጥ በመቆየቱ፣ አሁን በቅርብ ቀን ሊዝ የተደረገው (የተከራየው) ወርሃዊ ክፍያው ከፍተኛ በመሆኑ፤ በአጠቃላይ ሀገረ ስብከቱ በወር ከአስር ሺህ ዶላር በላይ ወጪ ስለሚጠብቀው፤ ይህ ሁሉ ወጪ የሚሸፈነው ደግሞ በምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት (መንበረ ጵጵስና) ቤተ ክርስቲያን አባላት በመሆኑ፣ እነዚህ ምእመናን በብፁዕ አቡነ አብርሃም የሥራ መሪነት በአካባቢው ያለውን ፈተና ተቋቁመው በመንፈሳዊ ትጋት እየሠሩ እያለና ለወደፊት ሀገረ ስብከቱ የራሱ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖረው እየተፋጠኑ ባለበት በዚህ ሁኔታ ላይ ሠርተው እያሠሩ ያሉትን አባት ማንሣት የተጀመረውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ከማኮላሸት፣ ሀገረ ስብከቱንም ከመግደል ውጪ ምንም ጥቅም አይኖረውም።  

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
የብፁዕ አቡነ አብርሃምን ሀ/ስብከት ለአብነት ጠቀስን እንጂ በሌሎቹም ቦታዎች ብዙ ተመሳሳይ ጉዳዮች ይኖራሉ። ለምሳሌ በሥራቸው መልካም እመርታ አሳይተው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ወደ ሀ/ስብከታቸው የማይመለሱበት ምንም አጥጋቢ ምክንያት አልቀረበም። በደፈናው “ጳጳሳትን የመበወዝ አበዜ” በተለይ ቅዱስነታቸው በዘመነ ፕትርክናቸው ከሚወቀሱበትና ከሥርዓተ አበው ፈቀቅ ለማለታቸው ከሚከሰሱባቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ወደቀደመው ሥርዓት መመለስ ካለብን ወደፊት ቅ/ሲኖዶሱ ሊያስብባቸው ከሚገቡት ነገሮች አንዱ ይኸው  የሊቃነ ጳጳሳቱና የሀ/ስብከታቸው ጉዳይ ነው። አንድ ሊቀ ጳጳስ ሀ/ስብከቱ እንደ ሕጋዊ ሚስቱ ናት። በየጊዜው ሚስት እየፈቱ ሌላ ማግባት እንደሌለ ሁሉ አባቶችን በየዓመቱ ከሀ/ስብከታቸው እያፋቱ ለሌላ የመዳሩ ዘመን አመጣሽ አሠራር ሕግ ሊበጅለት ይገባል። “ብፁዕ አቡነ እገሌ ዘ…” ምን እንበል? ዛሬ አንዱ ጋር ናቸው፤ ነገ ደግሞ ሌላ። ለስም አጠራርም የማይመች ነው። ለጊዜው ይህንን ሐሳብ በዚህ እንግታ።

ቅ/ሲኖዶሱ ሌላው ሊያስብበት የሚገባው አምና የተጀመረው የሥራ አስፈጻሚው ጉዳይ ነው። ሰሞኑን የተወሰኑት ዕንቍ ዕንቍ ውሳኔዎች ከጥቅም ላይ ካልዋሉ “የወረቀት ላይ ነብር” ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም። ሥራ አስፈጻሚውን የመሰለ ይህንን ተግባራዊ የሚያደርግ አካል ማቋቋም ካልቻላችሁ ነገሩ ዞሮ ዞሮ “ዓይጥ ወልዳ ወልዳ” ይሆናል።

በመጨረሻ ማንሣት የምንፈልገው ነገር ቅዱስነታቸው ባላቸው ሰፊ የከፋፍለህ ግዛ ዘዴ ቅ/ሲኖዶሱን የሚከፋፍሉበትና አቅም የሚያሳጡበት ዘዴያቸው ይኸው የቦታ ጥያቄ ነው። በዛሬው ውሎ እንኳን 3 ቡድን ተፈጥሯል። አንዱ እኔ ከሀ/ስብከቴ ካልተነሣሁ ምን ቸገረኝ ባይ፤ ሁለተኛው እንደምንም የምፈልገውን ላግኝ ባይ፤ ሦስተኛው በዚህ ተሠላችቶ ጉባዔውን ሳይፈጽም ወደመጣበት ለመመለስ የቸኮለው ናቸው። ይኼ ሁሉ ዞሮ ዞሮ የሚጠቅመው የቅ/ሲኖዶስ መጠናከርን ለማይፈልገው ክፍል ነው። አባቶች አደራችሁን። አስደስታችሁን ስታበቁ በመጨረሻ ጉድ ሆናችሁ፣ ጉድ እንዳትሠሩን፣ ቤተ ክርስቲያንንም ጉድ እንዳትሠሯት። በየሀ/ስብከታችሁ ስትመለሱ የጀግና አቀባበል ሊያደርግላችሁ በልቡ እየተዘጋጀ ያለውን ምእመን አንገት እንዳታስደፉት። ውይይቱ ወደ ጭቅጭቅ ተለውጦ ጉባዔው ሳይታሰር እንዳይበተን፤ ይህ አጀንዳ የመሪባ ውኃ ታሪክ እንዳይሆን (ዘጸ. 17፤ ዘኊ. 20፡24፤ ዘኊ. 27፡14፤ ዘዳ.32፡51 እና ዘዳ. 33፡8)። አደራ!!!!
ቸር ወሬ ያሰማን፤አሜን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)