September 21, 2010

በስብከተ ወንጌል መስፋፋት እና መጠናከር ላይ ያተኮረ ዐውደ ትምህርት ተጀመረ

  • ዐውደ ምሕረቱ በቡድንተኛ፣ ጥቅመኛ እና ፌዘኛ ሰባክያን ተሞልቷል
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 21/2010፤ መስከረም 11/2003 ዓ.ም):-  በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚደረገው ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት እና የማጠናከር ጥረት ዐውደ ምሕረቱ ቀላል ግምት በማይሰጣቸው ቡድንተኛ፣ ለቁሳቁስ እና ለገንዘብ ፍቅር ተላልፈው በተሰጡ እና ለምእመናኑ ዋዛ ፈዛዛ እየተናገሩ ካላሣሣቁ ያስተማሩ በማይመስላቸው ሰባክያን እየተሞላ መምጣቱ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ዛሬ መስከረም 11 ቀን 2003 . ጠዋት በመ//// /ቤት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተከፈተውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዐውደ ትምህርት ላይ ከአንዳንድ የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች በተሰጠው አስተያየት ነው፡፡ አንዳንድ የዐውደ ትምህርቱ ተሳታፊዎች በምሳሌ እየጠቀሱ እንዳመለከቱት በአሁኑ ወቅት በዐውደ ምሕረቱ ለምእመናን እየተሰጡ ባሉ ትምህርቶች በመሠረተ እምነት ትንተና የምስጢር ዳኅፅ (ስሕተት) የሚታይባቸው፣ ስለ ቅዱሳን የተነገሩ ኀይለ ቃሎችን ስለ ክርስቶስ ከሚነገረው ጋራ ወደረኛ እያደረጉ ነገረ ቅዱሳንን ለይስሙላ በማስተማር ፈሊጥ የተጠመዱ ስም ያወጡ ሰባክያን አሉ፡፡ ለምእመኑ በሣቅ እና በስላቅ የተሞሉ ፌዘኛ ትምህርቶችን በማስለመድ እነርሱ ከሌሉ በቀር ጉባኤው እንደማይደምቅ በሰማዕያኑ መካከል በሚፈጥሯቸው ቡድኖች በመቀስቀስ መድረኩን በብቸኝነት አልያም እነርሱ ብቻ በሚያሰማሯቸው ሰባክያን ለመቆጣጠር የሚሹ ቡድንተኛ ሰባክያን እየበረከቱ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት የተገኘውን ወንጌል በጸጋ እና በትሩፋት ለሁሉም ከማስተማር ይልቅ የወንጌል አገልግሎትን ለባለጸጎች የወሰኑ፣ ለቁሳቁስ እና ለገንዘብ ፍቅር ተላልፈው የተሰጡ ሰባክያን ዐውደ ምሕረቱን እየሞሉት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ ሺሕ ብሮችን አውጥታ የምታሠለጥናቸውን ደቀ መዛሙርት በማዕከላዊነት የምታሰማራበት፣ ስምሪታቸውን በወጥነት የምትቆጣጠርበት ጠንካራ አሠራር ስለሚጎድላት የትም ተበትነው እየቀሩ ነው፡፡

ዐውደ ትምህርቱን በጸሎት ያስጀመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹የክርስትና ማእከሉ ፍቅር ነው፤. . ጠላት ከሩቅ አይመጣም፤ ከዚሁ መካከል ነው ያለው፤ በፍቅር እና በመግባባት ይህን ችግራችንን መፍታት ይጠበቅብናል›› ብለዋል፡፡ የዐውደ ትምህርቱ አዘጋጅ የሆነው የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሐላፊ / አባ ኀይለ ማርያም ‹‹ሉላዊነት/ግሎባላይዜሽን/ እና ስብከተ ወንጌል በዘመናችን›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት ፍቅረ ንዋይ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት እና መጠናከር እንደምን ዕንቅፋት ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል፡፡ የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ የሆኑት መምህር ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር ሰባክያነ ወንጌል በዕፅዋት (ብዝኀ ሕይወት) ክብካቤ የሚኖራቸውን ሚና የሚያሳይ በቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ዐውደ ትምህርቱ በነገው ዕለት ቀጥሎ የሚውል ሲሆን ለውይይት ከሚቀርቡት ጥናቶች መካከል ‹‹ሚዲያ እና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር›› የሚል ርእስ ይገኝበታል፡፡ በዐውደ ትምህርቱ ላይ ከአዲስ አበባ እና ከመላው አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ሰባክያነ ወንጌል፣ ዘማርያን እና የትሩፋት አገልጋዮች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)