September 1, 2010

ሐውልቱን በመቃወም የተጠረጠሩት የቦሌ መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ጸሐፊ ከቦታቸው ተነሡ

  • አ.አ የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊዎች ዝውውር ተበራክቷል
  • ጸሐፊዎች በመቶ የአንድ ሺሕ ብር ጉቦ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 1/2001፤ ነሐሴ 26/2002 ዓ.ም):- የቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ጸሐፊ ሆነው ሲሠሩ የቆዩት መምህር የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ወደ ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተዘዋወሩ - የዝውውሩ መንሥኤ በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ ሳቢያ በስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት እና በካቴድራሉ የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ የሆነው ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ፣ ‹‹ለረጅም ጊዜ በሥራው ላይ እንደማይገኝ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሪፖርት አላቀረብኽም›› በሚል እንደ ሆነ ተመልክቷል፡፡ ይኹንና አንዳንድ የዜናው ምንጮች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በጸሐፊነት ደርበው የሚሠሩት መምህር የማነ ከካቴድራሉ ጸሐፊነታቸው የተነሡበት ዐቢይ ምክንያት በካቴድራሉ ደጃፍ የቆመው የአቡነ ጳውሎስ ‹‹ሐውልተ - ስም›› ተቃዋሚ በመሆናቸውም ጭምር ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ጸሐፊው 18ኛውን የፓትርያሪኩን በዓለ ሢመት ሰበብ በማድረግ ሐምሌ አራት ቀን 2002 ዓ.ም ያለሰበካ ጉባኤው ዕውቅና በካቴድራሉ የተካሄደውን ‹‹የስብከተ ወንጌል ጉባኤ›› እና የሐውልቱ መገለጥ ሥነ ሥርዐት በመቃወም ከሰበካ ጉባኤ ሐላፊነታቸው የለቀቁትን የምእመናን ተወካዮች አቋም ውስጥ ለውስጥ እንደሚጋሩ ይነገርላቸዋል፡፡

በመምህር የማነ ቦታ የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ደብር ሰበካ ጉባኤ ዋና ጸሐፊ የሆኑት መምህር ሰሎሞን በቀለ እንዲተኩ ተወስኗል፡፡ መምህር ሰሎሞን ባለፈው ዓመት በነበረው የሲኖዶሱ ውዝግብ የሌሊት ወፏን ገጸ ባሕርይ በመላበስ መተወናቸው ይነገርላቸዋል - ‹‹በብርሃን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደራዊ ለውጥ እና መሻሻል ከሚፈልጉት ወገኖች ጋራ ግንባር ቀደም ሆነው ይውላሉ፤ በጨለማ ደግሞ ለውጡን ከሚያደናቅፉት ወ/ሮ እጅጋየሁ ጋራ ይመክራሉ፡፡›› በአሁኑ ወቅትም በ‹ሊቀ ትጉሃን› ዘሪሁን ተጽፏል በሚባለው ‹መጽሐፍ› ሳቢያ ታውከው ባለጉዳይ አብዝተው የሀገረ ስብከቱን ሥራ እስከ ማስተጓጎል የደረሱትን ሊቀ ማእምራ ፋንታሁን ሙጬን እና ወ/ሮ እጅጋየሁን በምክር እየረዱ እንደ ሆነ ከመሰማቱም በላይ የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ ከሆኑት ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ እና ሌሎችም ጋራ በ‹ሊቀ ትጉሃን› ዘሪሁን ላይ ለመመስከር መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡ የጉዳዩ ታዛቢዎች እንደሚያስረዱት መምህር ሰሎሞን የቦሌ መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ ሆነው መዛወራቸው፣ ‹‹ስለውለታቸው የተበረከተላቸው ገጸ በረከት ነው፡፡››

በሌላ ዜና በሌሎች አድባራት እየተካሄደ ከሚገኘው የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊዎች ዝውውር እና ምደባ ጋራ በተያያዘ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በተዘረጉ የጥቅም መቀባበያ መረቦች አማካይነት ሙስና መጧጧፉን፣ በዚህም ሳቢያ አገልግሎት እየተበደለ ባለጉዳዮችም እየተጉላሉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የዝውውሮቹ ዋነኛ መንሥኤ ከጥቅም ትስስር እና በቀል ጋራ የተያያዘ እንደሆነም ይነገራል፡፡ በጠየቁት አጥቢያ ለጸሐፊነት ለመመደብ የሚፈልጉቱ በመቶ ብር ደመ ወዝ የአንድ ሺሕ ብር ጉቦ እንዲሰጡ አልያም የተወሰኑ ወራት ደመ ወዛቸውን አስቀድመው እንዲለቁ የሚጠየቁ ሲሆን ይህም እጅ መንሻ በጥቅም አቀባባዮቹ ‹‹ሥራ ማስኬጃ›› የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል፡፡

እስከ አሁን ድረስ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና በ‹‹አዲሱ›› ሚካኤል መካከል ከአንዱ ወደ ሌላው የጸሐፊዎች ዝውውር ተደርጓል፡፡ የደብረ ኀይል ቅዱስ ራጉኤል እና የአስኮ ቅዱስ ገብርኤል ሰበካ ጉባኤያት ጸሐፊ ያልተመደበባቸው ሲሆን ይህን በተመለከተ በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረቡ ለሚገኙት የአጥቢያው ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ‹‹ለቦታው የሚመጥን ሰው ባለማግኘታችን ነው፤›› የሚል ምክንያት ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንደ መረጃ ምንጮቹ አስረጅነት ግን ሐቁ፣ ‹‹በቦታው ለመመደብ ከጠየቁ ጸሐፊዎች ጋራ የጥቅም አቀባባዮቹ በጎን የሚያደርጉት ድርድር ባለመቋጨቱ ነው፡፡›› በዚህ የጥቅም ትስስር መረብ(ኔት ወርክ) ውስጥ ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሐላፊዎች ስም ዝርዝር ለደጀ ሰላም ተያይዞ የደረሰ ቢሆንም መረጃውን በሌሎች መንገዶች እስክናጣራ ድረስ ዝርዝሩን ለመያዝ ወደናል፡፡ ‹‹ኔት ወርኪንግ›› በአገር ዓቀፍ ደረጃም ከፍተኛ የሙስና መፈጸሚያ እና መጠቃቀሚያ መንገድ በመሆን ሕዝብ የተቸገረበት ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)