September 9, 2010

ማኅበረ ቅዱሳን ‹የአገልግሎት ስልት ለውጥ› እንደሚያስፈልገው አመለከተ

  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 8/2010፤ ጳጉሜን 3/2002 ዓ.ም):- ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ተዋቅሮ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በማበርከት ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ከነሐሴ 22 - 23 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ በ2000 ዓ.ም ያወጣውን የአራት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ሁለተኛ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል::
  ከግምገማው ግኝቶች ክፍተቶቹን ለይቶ እና ድክመቶቹን ዐውቆ በአፈጻጸም አቅሙ ተጠናክሮ በመውጣት ‹‹ከአሕዛብ፣ ከመናፍቃን እና ከዘመነ ሉላዊነት/ግሎባላይዜሽን/ ጋራ ፍጥጫ ገጥሟል›› ያለው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ‹‹የገጠመውን ሥርዐታዊ ችግር/system problem/ በፍጥነት እና ለዘለቄታው ለመፍታት ያስችላል፤ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘመኑን የቀደመ እንዲሆን ያደርጋል፤ የማኅበሩን ሕዝባዊ መሠረት ያሰፋል(ማኅበሩን የሁሉም ያደርጋል)›› ብሎ ያመነበትን የአገልግሎት ስልት ለውጥ ማድረግ አስገዳጅ ሆኖ እንዳገኘው አመልክቷል፤ ከስልቱ በመነሣትም የሚፈጽማቸውን ዝርዝር ተግባራት ለማሳየት በቀረበው ሰነድ ላይ የማሻሻያ ሐሳቦችን በማከል ውሳኔ አሳልፏል፤ የዐሥር ዓመት የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሩንም አስተዋውቋል፡፡

  የማኅበሩን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ከማስፈጸም አኳያ ለጉባኤው በቀረበው ጥናት የአባላትን ቁጥር በመጨመር ለበለጠ አገልግሎት ማብቃት ÷ ተተኪ የአመራር አካላትን በበቂ ሁኔታ ማፍራት፤ የማእከላትን እና ግቢ ጉባኤያትን አቅም በአደረጃጀት፣ በሰው ኀይል፣ በአሠራር እና በሥራ መሣሪያዎች በማጠናከር የመወሰን ድርሻቸውን መወሰን፣ ማኅበሩ ለሐዋርያዊ ተልእኮ÷ ለማኅበራዊ እና ልማት አገልግሎት ያሉትን የገቢ ምንጮች (ወርኀዊ አስተዋፅኦ እና በጎ አድራጎት) አስፍቶ የገንዘብ አቅሙን ማጎልበት፣ የዋናው ማዕከል ሕንጻ አካል ሥራ ያለቀለትን የጽ/ቤት ግንባታ በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ፣ ማእከላት በቀጣና ማእከል እንዲደራጁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ፣ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ የተቀመጠውን የወርኀዊ አስተዋፅኦ መጠን ወጥነት ባለው መልኩ ቢያንስ ወደ ሁለት በመቶ ከፍ ማድረግ፣ እንደ ማእከላት ተጨባጭ ሁኔታ የግቢ ጉባኤያትን አገልግሎት በመደበኛ መምህራን እና ክትትል ማጠናከር የሚሉ እና ሌሎችም ነጥቦች ቀርበው ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
  ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ›› በሚል ርእስ የቀረበው የጥናት ሰነድ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ችግር ፍጥነት እና ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት አኳያ ማኅበሩ በእስከዛሬው ቆይታው የሚሰጠው አገልግሎት ፍጥነት ገና ብዙ የሚቀረው እንደሆነ በማስረዳት፣ ወቅቱ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት የስልት ለውጥ ማድረጉን ግድ ከሚለው ደረጃ ላይ የደረሰበት በመሆኑ፣ ‹‹ብዙ የሚያዩ ዐይኖችን፣ የሚሰሙ ጆሮዎችን፣ የሚያሸቱ አፍንጫዎችን፣ የሚሠሩ እጆችን፣ ጥብቅና የሚቆሙ እና የሚናገሩ አንደበቶችን፣ ለአገልግሎት የሚፈጥኑ እግሮችን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የገባቸው አካላትን ወደ መፍጠር እና ማብዛት  መሸጋገር›› እንደሚገባው ያትታል፡፡

  የቤተ ክርስቲያኒቱን ውስጣዊ እና ውጫዊ ነባራዊ ሁኔታዎች በመዳሰስ ሕገ ማኅበሩን፣ በስትራቴጂያዊ ዕቅዱ ጥናት እና በቀጣይ ግምገማዎች የሚታዩትን የማኅበሩን የአፈጻጸም አቅሞች ከግምት ውስጥ በማስገባት ለወደፊቱ የሚተኮርባቸው የአገልግሎት አቅጣጫዎች፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት የማኅበሩን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ማስፈጸም እንዲችሉ ማብቃት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር በዝግጁነት፣ በስልት፣ በክሂሎት፣ በአሠራር፣ በሰው ኀይል እና በገንዘብ አስተዳደር ማጠናከር፣ የሰንበት ት/ቤቶችን አቅም ማጎልበት፣ የምእመናን በተለይም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ መንፈሳውያን ማኅበራት (የጽዋ፣ የበጎ አድራጎት፣ የአገልግሎት፣ የጉዞ ማኅበራት፣ ሰንበቴ፣ ዝክር. . . ) የጋራ አጀንዳ በመፍጠር በማኅበሩ አገልግሎት ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ፣ በጋራ የማገልገል ባህልን ማጎልበት፤ ስብከተ ወንጌልን እና ሐዋርያዊ ተልእኮን በማስፋፋት መንፈሳዊ ሕይወትን እና የምእመናንን ቁጥር ማሳደግ፣ ቅዱሳት መካናትን እና አብነት ት/ቤቶችን ማጠናከር እና ማቋቋም፣ ምእመኑ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የሚያገኝበትን ሚዲያ መዘርጋት (የሬዲዮ ጣቢያ መክፈት፣ አሁን ያሉትን ሚዲያዎች ወደተለያዩ ቋንቋዎች ማስፋፋት፣ ሕዝብ አሳታፊ ብሎጎችን መክፈት፣ የማኅበሩን ገጸ ድር በመፈተሸ የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ)፤ የውስጥ እና የውጭ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ መቆጣጠር እና መግታት (በማጋለጥ፣ በሕግ አግባብ ለፍትሕ አካላት በማቅረብ) እንደሚሆኑ የማኅበሩን የወደፊት አቅጣጫ የሚያመላክተው እና ለቡድን ውይይት ቀርቦ የዳበረው የጥናት ሰነድ ይጠቁማል፡፡

  ማኅበሩን ቀስ በቀስ ለውጥ ከሚያመጣ የረጅም ጊዜ ጥገናዊ አገልግሎት ይልቅ ወደ መካከለኛና በሂደትም ፍጥነት ያለው ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት ወደሚያስችለው ቀጣይ የአገልግሎት አሰጣጥ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው በታመነባቸው በእኒህ አቅጣጫዎች አፈጻጸም - ከላይ ወደ ታች እና ከታች ወደ ላይ ባሉ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እርከኖች እንደየአግባቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ተከታታይ የቅስቀሳ እና ማደራጀት፣ የተሞክሮ እና ስኬት ማስፋፋት እንዲሁም የአፈጻጸም ሪፖርቶችን የማሰራጨት ሥራዎች ይሠሩባቸዋል፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት ይሳተፋሉ፤ የዐውደ ርእይ፣ የዐውደ ጉባኤ፣ የምርምር እና ተዋስኦ መድረኮች ይዘረጋሉ፡፡

  በቡድን እና በጋራ ውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች በጥናቱ ላይ ውይይት ለማድረግ የተመደበው ጊዜ በቂ የነበረ ባይሆንም የቀረበው ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች በወሳኝ መልኩ ለመፍታት የሚያግዝ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ከዋናው ማእከል ጀምሮ መግባባት የሰፈነበት እና አሳታፊ የሆነ የላቀ ርብርብ መደረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

  ከጠቅላላው ጉባኤው ቀደም ሲል የማኅበሩ ሥራ አመራር እና ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤያት አባላት በተናጠል ባላቸው የመምራት እና የማስፈጸም አቅም ላይ ያተኮረ ጠንካራ ግምገማ መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን በግምገማውም በሁለቱም መዋቅሮች የሚገኙ አባላት ድክመቶች እና ጥንካሬዎች የተለዩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይኸው ግምገማ በዋናነት የማኅበሩን ስልታዊ ዕቅድ ለማስፈጸም ከሚኖር የአመለካከት ዝግጁነት እና የተግባር ክሂል አኳያ በዋናው ማእከል በተዋረድ እና ማእከላቱ በሚገኙባቸው አህጉረ ስብከት በመላ ቀጥሎ እስከ መጪው ጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም ድረስ በማጠናቀቅ ማኅበሩ በተጨባጭ የሚኖረውን የማስፈጸም አቅም እንደሚለይ እና በዚያ ላይ በመመሥረት ጠቅላላ ጉባኤው በአገልግሎቱ ላይ ያደረገውን ስልታዊ ለውጥ ወደ መፈጸም እና በግምገማው ግብአቶች የተሻሻለውን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በቀሪዎቹ ዓመታት ወደሚተገብርበት ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ይጠበቃል፡፡ በመጨረሻም ጠቅላላ ጉባኤው ‹‹ማኅበሩን ከውጤት አልባነት ታድጎ፣ ረጅሙን እና ከባዱን አገልግሎት ለሁሉም ምቹ በማድረግ ዘመኑን ይዋጃል›› ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የአገልግሎት ስልት በበካር አቅሙ እና የካበተ ልምዱ ታግዞ በመምራት እንደሚያስፈጽም ያመነበትን የቀድሞውን የሥራ አመራር ጉባኤ ሰብሳቢ የዲያቆን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያምን የዋና ጸሐፊነት ሹመት አጽቋል፡፡

  በጉባኤው መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ጨምሮ ሰባት ብፁዓን አባቶች ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሰጡት ቃለ ምዕዳን፣ ‹‹በዓለም ላይ ያለው ችግር የሚፈታው በግልጽ ውይይት እና ንግግር ነው፡፡ እናንተም ልጆቻችን የተሸከማችሁት ስም የቅዱሳን አባቶቻችን ስም ነው፡፡ ስማችሁ በተግባር መገለጽ አለበት፡፡. . . የእናንተ መማር፣ ማወቅ መፍትሔ ይሆናል እንጂ ችግር አይሆንም፡፡ የተማረ ሰው ችግር ነው የሚል ካለ አለማወቁን ነው የምረዳው፡፡ ይሁንና በእናንተ ስም በመካከላችሁ የማይሆን ነገር የሚያመጡ ካሉ በጥሞና እንድትወያዩ፣ እንድትመክሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ‹‹. . .ማኅበሩ እንደ ስሙ ቅዱስ ሥራ እየሠራ ነው፤ በክፉዎች ለምን ታማን አትበሉ፤ መታማት የሠራተኝነት ውጤት ነው፤ ያበረታችኋል፤ ያተጋችኋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ በእጃችሁ ነው፤ በእጃችሁ ከገባ በኋላ ጠብቃችሁ ወደፊት መሄድ ነው፡፡ አክሊለ ሦክ ቢከብዳችሁም ወደፊት ማኅበረ ቅዱሳን ለሲኖዶሱ የሚሆን አባት ማውጣት አለበት፡፡ ቢኖር ከእናንተ የወጣውን እንሾምላችሁ ነበር. . .›› በማለት ጉባኤተኛውን አነቃቅተዋል፡፡

  ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በበኩላቸው፣ ‹‹ማኅበሩ በኢትዮጵያዊነት ታንጾ ያደገ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበር ነው፤ ይህን እኔም ሲኖዶሱም እንመሰክራለን፡፡ ፖለቲካ አንዳንድ አገልግሎቱን የማይፈልጉ አካላት የለጠፉበት ነው፤ ማኅበሩ ከሥር ከመሠረቱ የምናውቀው፣ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ለይቶ መስጠትን የሚያውቅ፣ የፖለቲካ ጠባይ የሌለው ዕጣን ዕጣን የሚሸት ማኅበር ነው›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ማኅበሩ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚለውን ስያሜ እንዲይዝ ሐሳብ የሰጡ እንደሆኑ ይታወሳል፡፡ ከተቋቋመ 18 ዓመታትን ያስቆጠረው ማኅበረ ቅዱሳን ከ40‚ 000 በላይ አባላት፣ ከ41 በላይ የአገር ውስጥ እና የውጭ ማዕከላት/በአህጉረ ስብከት/፣ ከ420 በላይ የወረዳ ማእከላት እና ከ210 በላይ ግቢ ጉባኤያት/በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት/ በሥሩ ተደራጅተው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ልማታዊ አገልግሎት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ እሑድ ለሰኞ አጥቢያ በተጠናቀቀው ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የሆኑት 800 አባላት ያህል አባላት ከእኒህ የማኅበሩ የአገልግሎት መዋቅሮች የተውጣጡ ናቸው፡፡
  Post a Comment

  Blog Archive

  የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

  ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)