September 29, 2010

የመስቀል ደመራ በዓል መርሐ ግብር ሪፖርታዥ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 28/2010፤ መስከረም 18/2003 ዓ.ም):-  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሥጋውን የቆረሰበት፣ ደሙን ያፈሰሰበት እና ነፍሱን የካሰበት ቅዱስ መስቀል የፍቅር ፍጻሜ፣ የሰላም ማረጋገጫ እና የአንድነት ዙፋን ነው፡፡ ክርስቶስ በደሙ ለዋጀው ሕዝብ ቀዋሚ ዓርማ በሆነው ቅዱስ መስቀል ሰማያውያን እና ምድራውያን ታርቀዋል፡፡ መስቀል ለመላእክት እና ለሐዋርያት የስብከታቸው ማእከል፣ ለእኛ ለምናምንበትም ኀይል እና ጽንዕ ነው፡፡ ከአበው እንደ ወረስነው መስቀል በደረታችን ላይ፣ መስቀል በጣታችን ላይ፣ መስቀል በየልብሳችን ላይ፣ መስቀል በአብያተ ክርስቲያን ጉልላት፣ በር እና መስኮት ላይ፤ መስቀል በንዋያተ ቅድሳት ላይ፣ መስቀል በካህናት እጅ ላይ፣ የመስቀሉ ባለቤት እግዚኣ ሕያዋን ወሙታን ነውና መስቀል በሙታን መቃብር ላይ ሳይቀር ይገኛል - በዚህም ዘወትር እንሳለመዋለን፤ እንባረክበታለን፤ በረከት እና ረድኤትም እናገኝበታለን (ማቴ.10÷38)፡፡

ደመራ - ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል በማያምኑበት አይሁድ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል እንዳይገኝ ተደርጎ ከተቀበረ በኋላ በዕሌኒ ንግሥት ፍለጋ በደመራው የዕጣን ጢስ ስግደት የተደበቀበት ስፍራ ተለይቶ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን ከተቀበረበት ወጥቷል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ተቀምጦ መስከረም 16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፤ ስለሆነም ደመራ ዕንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡

በአገራችን በተደጋጋሚ ያስቸገረውን ረኀብ እና በሽታ ለማስወገድ ዐፄ ዳዊት በራእይ ተገልጾላቸው የክርስቶስን ግማደ መስቀል ካስመጡ (መስከረም 10 ቀን) በኋላ ‹‹መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ›› በሚለው ትእዛዝ መሠረት ግማደ መስቀሉ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት አፈጻጸም የቅዱስ መስቀል በዓል በዓመት አራት ጊዜ ማለትም መስከረም 10 - ዐፄ መስቀል፤ መስከረም 16/17 – 25 (ተቀጸል ጽጌ)፤ መጋቢት 10 ይከበራል፡፡ በአገራችን የመስቀል በዓል አከባበር ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባሻገር ባህላዊ ገጽታም እንዳለው ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ መስከረም 16 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ተከብሮ በዋለው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባሰሙት ቃል ‹‹በአገራችን የመስቀል በዓል ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን አከባበሩ ሳይቋርጥ ተጠብቆ ከዚህ ዘመን መድረሱ ቀደምት ወላጆቻችን በዘመናት ውስጥ የገጠማቸውን መልካሙን ነገር የሚያሰናክል ደባ በተአምኖ እግዚአብሔር የተቋቋሙበትን ጥልቅ እና ልባዊ ብርታት ይመሰክርልናል›› ብለዋል፡፡ ‹‹በዓለ መስቀል ታሪካዊ ሀብታችን እና መንፈሳዊ ጸጋችን ነው›› ያሉት ቅዱስነታቸው የበዓሉ ታላቅነት የእኛን ሐላፊነት ከባድ ስለሚያደርገው በታሪክ ሠሪ ወላጆቻችን ፍኖት ጉዟችንን ለመቀጠል መጻሕፍትን ማወቅ፣ ሊቃውንትን መጠየቅ፣ የሚገጥሙንን ማናቸውንም ችግሮች በትዕግሥት፣ በአኰቴት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በስምምነት፣ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝ እና በመቻቻል መቋቋም እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ‹‹የክርስቶስ መስቀል በባሕርዩ ጥላቻን የሚጋብዝ ሳይሆን በትዕግሥት ተቻችለን የምንኖርበት ትልቁ አምላካዊ ዓርማችን›› መሆኑን በማስረዳት ወላጆቻችን በእምነት ከእነርሱ ልዩ የነበሩ ወገኖች በስደት ሲመጡ በእንግድነት አክብረው ተቀብለው ያስተናገዱ እንጂ ጥላቻ እንዳልነበራቸው፣ ቤተ ክርስቲያን በመንግሥት አስተዳደር የታወጀው የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ተካትቶ የሚገኝባት የኅብረተሰብ አንድነት ምልክት መሆኗን እና የቤተ ክርስቲያን ልጅ ለመሆን ልበ ሰፊ መሆን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

አቡነ ጳውሎስ ሕዝቡ ማንም ሳይወተውተው በእግዚአብሔር ላይ ያለው ጽኑዕ እምነቱ ቀስቅሶት እና ታሪካዊ ግዴታው ተሰምቶት በአደባባዩ በበርካታ ቁጥር መሰብሰቡ ራሱን ለእግዚአብሔር ያስገዛ ትውልድ መሆኑን እንደሚያሳይ ይናገሩ እንጂ በቀጣይ ትውልዱ ከወላጆቹ የወረሰውን ሰፊ እና መንፈሳዊ ታሪክ በመገንዘብ በአባቶቹ መንገድ እንደሚጓዝ የገለጹበት ዘይቤ አንድም በወጣቱ አእምሯዊ ሁኔታ ላይ ያላቸውን የጥርጣሬ ግዕዘ ኅሊና የሚያሳብቅ አልያም ፓትርያርኩ በእምነት አደባባይ ለፖሊቲካ ዲፕሎማሲ ያላቸውን ጽነት የሚያሳይ እንደሆነ ንግግራቸውን የተከታተሉ አንዳንድ ተቺዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል - ‹‹አሁን ያለው ትውልድ ከጥንት አባቶቹ የወረሰውን ሰፊ እና መንፈሳዊ ታሪክ ከግንዛቤ በማስገባት በአባቶቹ መንገድ እንዲጓዝ ያስፈልጋል፤ እየተጓዘም ነው ብዬ ለመናገር እሞክራለሁ፡፡››

ተቺዎቹ አያይዘው እንደተናገሩት፣ ፓትርያርኩ አሁን በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በአክራሪ ሙስሊሞች የሚፈጸመውን ማኅበራዊ ሰላምን የሚያናጋ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና የሚፈታተን ድርጊት በሚቃወም መንፈስ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የነበራቸውን እንግዳ ተቀባይነት (Civility) እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት (ኲላዊት) መሆኗን ማስታወሳቸው መልካም ነው፡፡ ይሁንና በአገላለጻቸው ብዙዎች በትርጉም የሚወዛገቡባቸውን ፖሊቲካዊ ሐረጎች መጠቀማቸው አነጋገራቸውን ጥያቄ ላይ ይጥለዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ብሔር›› እና ‹‹ብሔረሰብ›› የሚባሉት ቃላት ያላቸው ግእዛዊ ፍቺ ፖሊቲከኞቹ ከሚጠቀሙበት አገባብ እና ትንተና በመሠረቱ ይለያል፡፡ እንደ ፓትርያርኩ ገለጻ ‹‹የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አካላት›› በቤተ ክርስቲያናችን መኖራቸው እውነት ቢሆንም በመሐል ይሁን በዳር አገር በስብከተ ወንጌል ሽፋን፣ በአገልጋይ ካህናት ምደባ፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም የሚደረግላቸው መንፈሳዊ ክትትል ለግለሰቦች በጎ ፈቃድ የተተወ፣ በታሪክ ውስጥ ያመለጠን ዕድል ተመልሶ እንዲደገም የሚያደርግ አይደለም ወይ? ተሳትፏቸው እና የተሳትፏቸው እኩልነትስ እስከምን ድረስ ነው? በሃይማኖታዊ እምነት መቻቻል ሲባል እንዴት ነው? ልበ ሰፊ መሆንስ ማለት ምን ማለት ነው? ሃይማኖታዊ እምነት በጎሰኝነት እና በጥላቻ መንፈስ በተበረዘበት፤ ሃይማኖት ግላዊ፣ ፖሊቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማራመድ ሽፋን በሆነበት፣ መቻቻል በተግባር የአንድ ወገን አጀንዳ ብቻ በመሰለበት በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ያሉት ገለጻዎች ከአደባባይ ቃለ ነቢብ (rhetoric) ባሻገር ግርታን (ambiguity) በማይፈጠር አኳኋን ከክርስትና አስተምህሮ ጋራ ተጣጥመው መብራራት እንደሚገባቸው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

አገራችን እንደ መስቀል ደመራ ብርሃን ‹‹የዕድገት ጮራ መፈንጠቅ መጀመሯን›› በክብረ በዓሉ ላይ ያመለከቱት የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የአቶ ከፍያለው አዘዘ ንግግርም ከዚሁ አንጻር መታየት የሚገባው ነው፡፡ ምክትል ከንቲባው እንዳሳሰቡት በርግጥም ‹‹ጊዜው በሃይማኖት ሽፋን የሚታየውን የአክራሪነት ዝንባሌ ለዘመናት ባዳበርነው የመቻቻል ባህል ቦታ አሳጥተን ተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ተላብሰን ራሳችንን በሥነ ምግባር አንጸን መጓዝን ይጠይቀናል፡፡›› ሕገ መንግሥቱ መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ መግለጹ አንዱ በሌላው ጣልቃ ሳይገባ ሁሉም የየራሱን ሥራ እንዲፈጽም የሚያደርግ እንጂ መንግሥት እና ሃይማኖት በጋራ አገራዊ አጀንዳ ላይ በአንድነት አይሰለፉም ማለት ከቶ እንዳልሆነ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

አቶ ከፍያለው፣ የመስቀል ደመራውን ብርሃን ተምሳሌታዊ ፋይዳ የዕድገት እና ለውጥ ዕቅዱን በአንድ መንፈስ ተነሣሥተን በመተግበር ድህነትን እና ተመጽዋችነትን እስከወዲያኛው በማስወገድ የሁላችንም መመኪያ የሆነች የበለጸገች አገር እና ከተማ ለመፍጠር እንድናረጋግጥበት ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የከንቲባው ንግግር እውን ሊሆን የሚችለው በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው ቤተ ክርስቲያኒቷ ተቋማዊ ነጻነቷ ተረጋግጦ፣ ታሪካዊ አስተዋፅኦዋ ተገቢውን ዕውቅና አግኝቶ፣ በገጠር ይሁን በከተማ ሥሪቷና ይዞታዎቿ ተከብረው፣ ልጆቿ በመላው አገሪቱ በእምነታቸው እና በትውልዳቸው ሳቢያ አድልዎ ሳይደረግባቸው “የራስዋን ችግር በራሷ” ለመፍታት ስትበቃ፣ ውስጣዊ አቅሟን ለማጠናከር እና ለማንቀሳቀስ ስትችል እንደሆነ ርግጥ ነው፡፡

ከምክትል ከንቲባው ንግግር በመከተል የዓለም አብያተ ክርስቲያን ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር ሁሉ ጥንተ ክርስቲያን እና የአማናዊው ክርስትና እምነት ባለአደራ የሆነች ቅድስት አገር መሆኗን መስክረዋል፡፡ በ1948 ዓ.ም የዓለም አብያተ ክርስቲያን ምክር ቤትን ካቋቋሙ መሥራች አገሮች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ዋና ጸሐፊው፣ በዓሉ የመስቀሉ የምሥራች ለብዙዎች የሚደርስበት ሁነኛ ገጽታ በመሆኑ በመስቀል ደመራው በዓል ላይ ለመገኘት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

የደመራው ዝግጅትን ቅንብር በተመለከተ
ተናጋሪዎቹን በማስተናበር እና የዕለቱን መርሐ ግብር በማስተዋወቅ መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ናቸው፡፡ በአደባባዩ በተገኙት የክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች እና መርሐ ግብሩን በቀጥታ ስርጭት በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን በተከታተሉቱ ዘንድ ሥራ አስኪያጁ መድረኩን የመሩበት መንገድ ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል፡፡ ይኸውም ቤተ ክርስቲያኒቱ በብዙኀን መድረኮቿ ወቅታዊ መልእክቷን ውጤታማ በሆነ አኳኋን በማስተላለፍ ያመኑትን ለማጽናት፣ ከእርሷ በአፍዓ ያሉትን ስቦ በማቅረብ አማናዊት መሆኗን ለማረጋገጥ ያላት ዕድል አደጋ እንደተጋረጠበት፣ ከዚህም በላይ ብቃት ያላቸው ‹ጋኖች› ሊቃውንቷ አልቀው (ተሰደው) ሩቅ እና ቅርቡን፣ ወንዱን እና ሴቱን፣ ነጠላ እና ብዙውን በማይለዩ ነገር ግን በተለያየ አጋጣሚ ለመድረክ በበቁ ሰዎች የተሞላች መዘባበቻ እንዳያደርጋት ስጋት የሚፈጥር እንደ ሆነ ተመልክቷል፡፡

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ የቆሙበት መድረክ የአማርኛም ይሁን የልሳነ - እንግልጣር (እንግሊዝኛ) ቋንቋዎች ዕውቀታቸውን በጽሕፈት እና በቃለ ስብከት ለረጅም ዓመታት በማሳየት፣ ታሪክን አቃንቶ፣ አስፋፍቶ እና አስረግጦ የሚናገር አርትዖተ ልሳን ባለቤት የሆኑት መልአከ ሰላም ዳኛቸው ካሳሁን የቆሙበት እንደ ነበር ነው እናስታውሳለን፡፡ ከመልአከ ሰላም ዳኛቸው ጋራ በልሳነ ዐረቢ (በዐረብኛ) በመጻፍ እና በመናገር፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሳይቀር ቋንቋውን በማስተማር የሚታወቁት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ እና በልሳነ ግሪክ ደግሞ መምህር ገብረ ሚካኤል ድፈር ትዝ ይሉናል፡፡ ከእኒህ ብዙዎቹ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከነበራቸው ሐላፊነት ለቀው በውጭ አገር በስደት ለመኖር ሲገደዱ በጡረታ የተገለሉም አሉ፡፡ ከእነርሱም በፊት ዛሬ በቁመተ ሥጋ ባይኖሩም በመጽሔት እና በጋዜጣ ከሚያወጧቸው አሳማኝ ጽሑፎች በተጨማሪ በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ያስተላልፉት በነበረው ጣዕመ ትምህርታቸው የሚዘከሩት እነ አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ክርስቶስ፣ እነ አለቃ ነቢየ ልዑል ዮሐንስ፣ እነ መልአከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈ፣ እነ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ወዘተ. . .የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በርግጥ የመስቀል ደመራው መርሐ ግብር ዝርዝር ክዋኔዎች በተያዘላቸው ሰዓት ተጀምረው ያልተከናወኑ በመሆናቸው በመድረኩ አመራር ላይ የራሱ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለተረኞቹ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ሊቃውንት እና የሰንበት ት/ቤቱ አባላት (Picture) ‹‹አረጋዊ አንግሀገይሰ›› የሚለውን ጣዕመ ዝማሬ ሲያቀርቡ በጣም ከመቆየታቸውም በላይ የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ዝማሬ ሳያልቅ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ይህም ሆኖ በቀጥታ ስርጭት በሚተላለፍ ትዕይንት ላይ መሠረታዊ (101) የሚባሉ የቁጥር መስማማቶችን፣ የቃላት ንባብ ስልቶችን እና ደንበኛ አገባባቸውን ሊታገሡት ከሚችሉት በላይ ለመጠንቀቅ አለመቻል ግን ብዙዎችን በሀፍረት መድረሻ ያሳጣ እና አንገት ያስደፋ ነበር፡፡ ስሕተቱ እና ግድፈቱ ለሥራ አስኪያጁ ሁለተኛ ቋንቋ በሆነው በእንግሊዝኛው ብቻ ሳይሆን በአማርኛው ላይ ጭምር መታየቱ ደግሞ ብዙዎችን አስደንግጦ እርስ በርሳቸው እንዲተያዩ አድርጓል፡፡

ባለፈው ዓመት የጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ቃለ ምልልስ የፒ.ኤች.ዲ ተማሪ መሆናቸውን የነገሩን ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ሊቀ ማእምራን›› የሚለውን ማዕርግ እንዲያብራሩ ሲጠየቁ ፕሮፌሰር ማለት እንደሆነ አስረድተው ነበር፡፡ ‹‹ካልታረደ አይታይ ስባቱ፣ ካልተናገረ አይታይ ብልሃቱ›› ነውና እነሆ ምክትል ከንቲባውን ሲጠሩ ‹‹ዘ ቫይስ ማየር››፣ መስማት የተሳናቸው ወጣቶች ያቀረቡበትን የምልክት ቋንቋ (sign language) በእርሳቸው ቋንቋ ‹‹symbolical language››፣ ጥቂት ፕሮግራሞች - ‹‹small programs››፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች - ‹‹Sunday school youth children›› . . .ሲሉ ሰማናቸው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ደመራውን ‹‹በማይኩ እንደሚባርኩ››ም ነገሩን፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ማእከላት ከነሐሴ 20 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ሲሠለጥኑ የቆዩት ከ128 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የተውጣጡ ቁጥራቸው ከ3700 በላይ የሆኑ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሲደክሙበት የቆዩትን ልዩ ልዩ መልእክት ያላቸውን ዐውደ ትርኢቶች እና ያሬዳዊ መዝሙሮች በቅጡ ለማቅረብ ካለመቻላቸውም በላይ እንደ አንዳንዶቹ አገላለጽ ከዚህ በፊት ተነግሮ በማያውቅ መልኩ በሰልፍ ብቻ እንዲያልፉ ታዝዘዋል - ‹‹መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣልና ሕዝቡ እና ቅዱስ አባታችን ወደ ቤታቸው ሳይሄዱ ቶሎ ቶሎ እለፉ!›› ተብለዋል በሥራ አስኪያጁ፡፡ 

በአጠቃላይ ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሰ ብር ወጪ እንደተደረገበት የተገመተው የወጣቶቹ ዝግጅት ለፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ የተሰጠውን ያህል ጊዜ እንኳን ትዕግሥት ተደርጎለት ባለመታየቱ የተበሳጩ አንዳንድ ወጣቶች ለትርኢቱ የለበሷቸውን ሻሾች እና የያዟቸውን ፊኛዎች በብስጭት ወደ ሕዝቡ ሲወረውሩ ታይተዋል፡፡ የጋሞ ብሔረሰብ ሽማግሌዎች እና ወጣቶች፣ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ መስማት የተሳናቸው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የገጠማቸው ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡

ዘወትር በጉጉት የሚጠበቁት የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ያደረጉበት የመስቀሉን መገኘት የሚያዘክር አጭር የመድረክ ትርኢት እንደቀድሞው የደመቀላቸው አልሆነም፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ምክትል ሐላፊ መምህር ዕንቁባሕርይ ተከሥተ በመድረክ መሪው ተጠርተው በአቡነ ጳውሎስ የተገሠጹ ሲሆን እርሳቸውም በፈንታቸው ከወጣቶቹ አስተባባሪዎች ተደጋጋሚ ጭቅጭቅ ውስጥ ገብተው ታይተዋል፡፡ የሰሜን ክፍለ ከተማ ወጣቶች ያቀረቡት የአብነት ት/ቤቶች የመማር ማስተማር (ቤተ ጉባኤ) ስልት በልምምዱ ወቅት በሥራ አስኪያጁ ሳይቀር በአዲስ አቀራረቡ ተደንቋል፡፡

በሥልጠናው ወቅት የወጣቶቹ የትራንስፖርት አበል በመጡባቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የተሸፈነ ሲሆን ለዐውደ ትርኢቱ የሚያገለግሉት የድጅታል አርት ጽሑፎች ደግሞ በሀገረ ስብከቱ የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ለሥልጠናው የሚጠበቅባቸውን በጀት እና የሰው ኀይል ለመመደብ ማንገራገራቸው (በቀን ለአንድ ሰው 10 ብር ለመመደብም የሚደራደሩ አሉ) በአደባባዩ ከታየው ወከባ ጋራ ተደምሮ የክፍለ ከተማ አስተባባሪዎቹን እና የወጣቶቹን የአገልግሎት ሞራል መንካቱ ተዘግቧል፡፡ ‹‹እኛ የምንፈለገው መስቀል እና ጥምቀት ሲመጣ እየዘመርን በዓል እንድናደምቅ፣ አባ እገሌ እንዲሾሙ ቲፎዞ/አጃቢ እንድንሆን ነው፤. . .በቤተ ክርስቲያን ከዚህ ያለፈ ትርጉም ያለው አገልግሎት የምንሰጥበት ቦታ የለንም›› ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የወጣቱ አስተዋፅኦ ሲያዩት እንደሚያምረው፣ በኋላ ግን ተረጋግጦ እንደሚጣለው የበዓል ቄጤማ መሆኑ እንዲያበቃ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በአጠቃላይ የመስቀል ደመራው በዓል በተለመደው መልኩ በሥነ ሥርዓትና በሰላማዊ መልኩ መጠናቀቁ እንደተጠበቀ ሆኖ ከተሠራው አንጻር የጎደለውን ማሳየቱን የዚህ መልእክት ዓላማ ያደረግነው “ምንም መልካም ነገር መናገር የማንችል ጨለምተኛ” መምህራን ስለሆንን ሳይሆን በሚቀጥሉት ዓመታት ጉድለቶች እንዲስተካከሉ ካለን ጸኑዕ ፍላጎት ነው። የመድረኩን አስተናባሪ ስም የጠቀስነውም በትምህርት አደባባይ የዋሉ፣ መተቸትን ከውርደት ከሚቆጥሩ አንዳንድ ስመ ምሁራን የተሻሉ ናቸው ብለን ስለምናምን ነው። ስማቸው በመጠቀሱ እንደደመኛቸው እንደማያዩን ተስፋ አለን። በዚህ ዝግጅት የተሳተፉ ሌሎች ሰዎችም ጭምር እንዲያው እንደሚያደርጉ እምነታችን ነው።

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)