September 26, 2010

ራሳቸው ሳይታመኑ ስለመታመን ለሚያስተምሩ በሙሉ!!

  • ከምእመናን ተሰብስቦ ለባለቤቱ ሳይደርስ የቀረ የዘማሪ ልዑል ሰገድ ዐሥር ሺሕ ብር ተመለሰ
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 26/2010፤ መስከረም 16/2003 ዓ.ም):- በአገልግሎት ላለ ለማንኛውም ሰው በቀዳሚነት የሚነገር መጽሐፋዊ ቃል “በጥቂቱ መታመን እና በብዙው መሾም” ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዘመናችን እንደአሸን ከፈሉት ሰባኪዎቻችን አካባቢ ያጣነው ደግሞ ይኼው ነው።  ለዚህ ማሳይ አንድ ታሪክ እናንሣ። መስከረም አራት ቀን፣ 2003 ዓ.ም ዘማሪ ልዑል ሰገድ ጌታቸው ለቅርብ ባልንጀራው መምህር ዘመድኩን በቀለ በስልክ ደውሎ ያሰማው የምሥራች ‹‹እልል በል! ብሬ ተመለሰ፡፡›› የሚል ቃል ነበር፡፡ በዚህ ቀን ዘማሪው ከአምስት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ታሞ በአልጋ ላይ በዋለበት ወቅት ወደ ባንኮክ ሄዶ ለመታከም እንዲችል ከምእመናን ተለግሶት ነገር ግን በእጁ ሳይደርሰው ከመንገድ ተጠልፎ የቀረበትን አሥር ሺሕ ብር አርማጌዶን ቪሲዲ ላይ “ስሙ ለሰማይ ለምድር የከበደ ሰባኪ” ተብሎ ከተጠቀሰው እና "የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች" ተብለው ከሚጠቀሱት ከነ በጋሻው ደሳለኝና ከያሬድ አደመ የጥብቅ ወዳጅ ከሆነ አንድ ቀሲስ በቼክ ተቀብሏል፡፡ (ዋናው የሰውየው ስም ሳይሆን ታሪኩ በመሆኑ ለጊዜው ስሙን ዘለነዋል)

መስከረም አራት ቀን 2003 ዓ.ም ዘማሪ ልዑል ሰገድ ከሕመሙ በማገገም ላይ በሚገኝበት ሰመኖሪያ ቤቱ የተገኘው የገንዘቡ ወሳጅ ገንዘቡ እስከ ዛሬ ሳይመለስ ለቆየበት ይቅርታ በመጠየቅ፣ ከዚህም በኋላ ዘማሪውን በሚያስፈልገው እንደሚረዳው ቃል በመግባት አብሮት በመጣው ጓደኛው ስም ለንብ ባንክ ዑራኤል ቅርንጫፍ የተጻፈ የዐሥር ሺሕ ብር ቼክ ሰጥቶታል፡፡ ገንዘቡን ወስዶ ያስቀረው ራሱ “ሰባኪው”መሆኑ እየታወቀ ቼኩ ለምን በሌላ ግለሰብ ስም እንደ ተጻፈ ለብዙዎች አጠያያቂ ሆኗል፡፡

ዘማሪ ልዑል ሰገድ ጌታቸው ‹‹ቋንቋዬ ነሽ›› የሚለውን ታዋቂ መዝሙሩን ባወጣበት በ1998 ዓ.ም በጽኑ በታመመበት ወቅት ለባሕር ማዶ ሕክምናው ከ300‚000 ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ከገባሬ ሠናይ ምእመናን ተሰባስቦለት ነበር፡፡ በወቅቱ በዱባይ - ሻርጂያ የሚገኙ ምእመናን ለዘማሪው 10‚000 ብር ለግሰው ነበር፤ ርዳታውን ለሕሙሙ ዘማሪ እንደሚያደርስ ታምኖበት የተላከው ደግሞ በኋላ ጊዜ በአቡዳቢ-ሻርጂያ-ዱባይ የምትገኘዋን አንዲቷን ቤተ ክርስቲያን ከተባባሪዎቹ ጋራ ለሁለት ከፍሎ ሲያበቃ ደገኛ ምእመናንን ከኦርቶዶክሳዊ እምነት፣ ሥርዓት እና ትውፊት ተፃራሪ ለሆኑ ትምህርቶች ተላልፈው እንዲሰጡ ምክንያት የሆነው ሰው ነበር፡፡ 

ይሁንና ሰውየው ርዳታውን ባለማድረስ የምእመናኑን አደራ ይበላል፡፡ ስለ ሁኔታው ለሚጠይቁትም ‹‹እርሱ የዳነ መስሎኝ ገንዘቡን ለሌላ ጉዳይ አውዬዋለሁ›› ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡ ዘማሪው በከፍተኛ ሕክምና እንዲረዳ ላይ ታች ይሉ ከነበሩት በርካታ ወገኖች መካከል አንዱ የነበረው መምህር ዘመድኩን በቀለ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እየተንሰራፉ የመጡትን ለገንዘብ እና ለቁሳቁስ ፍቅር ተላልፈው የተሰጡ አስመሳይ ሰባክያንን ለመቃወም ‹‹አርማጌዴን›› በሚል ርእስ ባወጣው ቪሲዲ የውጭ ገጽ ላይ የሁኔታውን አሳዛኝነት ያመለከተው በዚህ መልክ ነበር - ‹‹እናንተ ስማችሁ ለሰማይ እና ለምድር የከበደ፣ የምስኪኑን ዘማሪ የልዑል ሰገድን ብር መልሱለት፡፡››
ይህ ቪሲዲ በሰፊው ከተሠራጨ በኋላ ገንዘቡን ብሩን ለሕመምተኛው ያላደረሰው ግለሰብ ለባለቤቱ እንዲመልስ ከቤተ ዘመድ፣ ከአባቶች፣ ከባልንጀሮቹ እና ርዳታውን ከለገሱት የኤምሬትስ ምእመናን ከፍ ያለ ግፊት እንደተደረገበት ይታመናል፡፡ ከዚህም ጋር በተለይም ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በኤምሬትስ በምትገኛዋ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው ተከታታይ እና ሰፊ አገልግሎት የፈጠረው መነቃቃት ገንዘብ የወሰደውን ሰው እና ተባባሪዎቹን ክፉኛ አስደንግጦ ሌሎች ድርጊቶቻቸው እንዳይጋለጥባቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ይነገራል፡፡ በቀጣይ ፌዘኛ እና ጥቅመኛ ሰባክያን በሃይማኖታዊ እምነታቸው እና በማኅበራዊ ግንኙነታቸው የፈጸሟቸውን ግልጽ የወጡ ስሑት ተግባራትን በምስል እና ድምፅ መረጃዎች በማስደገፍ እንደሚወጣ የሚጠበቀው እና ዝግጅቱ በገንዘብ ችግር ምክንያት እንደተጓተተ በሚነገረው ‹‹አርማጌዴን ቁጥር 2›› ቪሲዲም ይህን የመሳሰሉ ማጭበርበሮች የትኩረት ነጥብ መሆናቸው ገንዘቡን በወሰደው ሰው እና የእርሱን መሰል ተቀባይነት የሌላቸው ድርጊቶች በፈጸሙ ሌሎች “ስም ያወጡ ሰባክያን” ዘንድም ሳይታሰብ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ በወቅቱ ለዘማሪ ልዑል ሰገድ ርዳታ በማሰባሰብ ሂደት በአዲስ አበባ ኮከብ ሬስቶራንት ከተዘጋጀ ዝግጅት ከ150‚000 ብር በላይ፣ ከአሜሪካም የሰባሰበው ብዙ ገንዘብ ቢሆንም ለዘማሪው ግን በተገቢው አኳኋን እንዳልደረሰው ቀራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)