September 26, 2010

ስለ ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን የወጣው መመሪያ ግልጽነት እንደሚጎድለው እና በእኩልነት እንደማይተገበር ተመለከተ

  •  የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የሰባክያንን እና ዘማርያንን ስምሪ ለመቆጣጠር ተስኖታል
  •  የሰባክያን ድልድል፣ የደመወዛቸው አለመሻሻል እና ስብከተ ወንጌልን እንደ ዋነኛ አገልግሎት አለመቁጠር ጉልሕ ችግሮች ሆነዋል
  • ‹‹ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት ታዋቂ ሳይሆን ዐዋቂ ሰባኪ ነው፤ በታዋቂ ሰባክያን ምእመኑ አድናቂ እንጂ ተነሳሒ አልሆነም››  (የሰሜን ወሎ ተወካይ)
  • ‹‹በዚህ ዘመን ወንጌል የእንጀራ ልጅ ሆኗል፤ ሰባኪው ከፍቅረ ንዋይ ጋራ ከተቆራኘ መጻጉዕ ይሆናል፤ ሰባኪው እና እግዚአብሔር ሳይገናኙ እሰብካለሁ ማለት መንጋውን  ማደናበር ራስንም ግራ ማጋባት ነው፤ ሰባኪው እና እግዚአብሔር ከተገናኙ ግን ባሕሩም መረቡም ዓሣውን ይሰጣሉ፤ የዓሣውም ብዛት መረቡን አይቀደውም›› (ብፁዕ አቡነ ማርቆስ)
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 25/2010፤ መስከረም 15/2003 ዓ.ም):-  ሕጋውያን ያልሆኑ ሰባክያንን እና ዘማርያንን ስለመቆጣጠር በቅዱስ ሲኖዶስ ተደንግጎ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ለመላው አህጉረ ስብከት የተላለው መመሪያ ሕጋዊ እና ሕገ ወጥ የሆኑ ሰባክያንን እና ዘማርያንን ከመለየት አኳያ ግልጽነት የሚጎድለው፣ በሁሉም አህጉረ ስብከት በተመሳሳይ መልኩ ሊተገበር ያልቻለ፣ በምትኩ ቲፎዞ እና ተቀናቃኝ የሚለይበት እንዲያውም መመሪያውን የሚያስፈጽሙ አካላትን ከሕዝቡ ጋራ በማጋጨት የልዩነት መንሥኤ እንደ ሆነ Yአህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎች አመለከቱ፡፡

የሰባክያኑን እና ዘማርያኑን ስምሪት ለመቆጣጠር አዳጋች እንደሆነበት የገለጸው የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በበኩሉ፣ በዐውደ ምሕረት እና በኅትመት ውጤቶች ውስጥ እየጎሉ የመጡትን የነገረ ሃይማኖት (ዶክትሪን) ሕጸጾችን የሚከላከሉ እንዲሁም መዋቅሩን ያልጠበቀውን የሰባክያኑን እና የዘማርያኑን አገልግሎት መልክ የሚያሲዙ ደንቦችን እና አሠራሮችን እንደሚያዘጋጅ አሳውቋል፤ ደንቦቹ እና አሠራሮቹም በአህጉረ ስብከት እና በአጥቢያ ደረጃ ካሉት ሁኔታዎች ጋራ ተጣጥመው ተፈጻሚ እንዲሆኑ አሳስቧል፡፡

ስብከተ ወንጌልን ስለ ማስፋፋት እና ማጠናከር አስመልክቶ ከመስከረም 11 - 12 ቀን 2003 ዓ.ም በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት በተካሄደው ዐውደ ትምህርት ላይ የአህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎች እንዳመለከቱት፣ በጥቅምት ወር 2001 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ የተላለፈው መመሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ከመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ጋራ በመተባበር መቆጣጠር እንደሚገባ ያዝዛል፡፡ ይሁንና በአንዱ ሀገረ ስብከት የተከለከለ የአገልግሎት ፈቃድ የሌለው ሰባኪ እና ዘማሪ በሌላው ሀገረ ስብከት እንደሚፈቀድለት የተመለከቱ ምእመናን ሁኔታውን እንደግለሰባዊ ቅንዓት እና ምቀኝነት በመቁጠር ከሀገረ ስብከቱ ሐላፊዎች ጋራ ተደጋጋሚ ንትርክ ውስጥ እንደሚገቡ ተገልጧል፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያኑ እና ዘማርያኑ በቡድን የተደራጁ፣ በየአህጉረ ስብከቱ በዓላማ እና በጥቅም በተሳሰሯቸው ጥቂት አባቶች እና ‹‹አበ ልጆች›› ተመክተው በእነርሱ ስም እንደሚንቀሳቀሱ በዐውደ ትምህርቱ ላይ የቀረበው የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎቹ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ሕገ ወጥ ሰባክያኑ እና ዘማርያኑ በአህጉረ ስብከት እና የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት ውስጥ በተሰገሰጉ የዓላማ እና የጥቅም ተባባሪዎቻቸው አስተባባሪነት ምስሎቻቸውን በፖስተሮች እያወጡ፣ “ታዋቂ” የሚል ቅጽል እየለጠፉ ምእመኑን በመቀስቀስ በሚያዘጋጇቸው መርሐ ግብሮች በክፍያ እንደሚደራደሩ፣ በድርድሩም በአንድ ጉባኤ ብቻ ከ10,000 - 15,000 ብር እንደሚከፈላቸው፣ ይህ ዓይነቱ አካሄድም በታላላቅ ከተሞች በነጋዴዎች እንደሚመራ እና የጉባኤያት ዝግጅት ራሱን የቻለ የቢዝነስ ስልት እየሆነ እንደመጣ ተብራርቷል፡፡ ሕገ ወጦቹ አገልጋዩ እና የአገልግሎቱ ቅደም ተከተል ማን እና ምን መሆን እንዳለበት እና እንደሌለበት በመፍቀድ እና በመከልከል ጠብ እና ክርክር ያስነሣሉ፤ ሲሻቸውም ጉባኤያቱን ያጥፋሉ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዶግማዋ እና በቀኖናዋ የማይመስላትን ከአባቶች እርሻ ያልተቃረመ ትምህርት ይሰጣሉ፤ ትውፊቷን ይቃወማሉ፤ በአካባቢው ሕዝብ ባህል ተቃኝቶ በፈሊጥ ያልታሸ ‹‹እልል በሉ፤ አሜን በሉ›› በሚሉ ወቅታቸውን ያልጠበቁ አባባሎች ሰማዕያንን ያደናቁራሉ፤ ማኅበራዊ ግጭቶችን የሚያባብሱ ትንኮሳዎችን ያዘወትራሉ፤ ምእመናንን ከንስሐ አባቶቻቸው ጋራ የሚያገናኝ ሳይሆን አበጣብጦ የሚያለያይ፣ ካህናቱን እና አገልግሎታቸውን የሚያንኳስስ እንክርዳድ ይዘራሉ፤ በስብከት ዘዴዎቻቸውም ‹‹መምህር ወመገሥጽ›› ሳይሆኑ ልቅ እና ግለኛ የሆነ የጥራዝ ነጠቅ ሊበራሊዝም እና የዘመናዊነት መንፈስ የተጠናወታቸው የሉተራውያንን ሐሳብ የሚያንጸባርቁ ናቸው ተብሏል፡፡

መምሪያው ከላይ ለተገለጹት ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሔ ከመሻት አኳያ በአጎራባች አህጉረ ስብከት መካከል የሰባክያን መተጋገዝ እና የጋራ መድረክ እንዳይኖር ጭምር ዕንቅፋት መፍጠሩ ተመልክቷል፡፡ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ከተለመደው በተቃራኒ በሰሜኑ የኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት በጋራ ጉባኤያት መምህራንን መለዋወጥ እንደ መነጣጠቅ እንደሚታይ ተነግሯል፡፡ በመሆኑም መመሪያው ሕገ ወጥ የሆኑ እና ያልሆኑ ሰባክያንን እና ዘማርያንን ለመለየት በሚያስችል አኳኋን በግልጽ እንዲቀመጥ፣ ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊው ትምህርት እንኳ አሥረኛ እና አሥራ ሁለተኛ ክፍልን በአግባቡ ማጠናቀቅ የተሳናቸው ሰነፎች ማጠራቀሚያ ሳትሆን በአብነት ትምህርቱ እና/ወይም ከሦስት የነገረ መለኮት ኮሌጆች በአንዱ ሠልጥነው ወጥተው ምልዕት መሆኗን የሚያሳውቋት፣ ማእከላዊ አሠራሯን ጠብቀው በበሯ የሚወጡ እና የሚገቡ፣ በቲፎዞ ያይደለ በብቃት፣ በብልጣብልጥነት ያይደለ በፀጋ መንፈስ ቅዱስ፣ በጥቅም ያይደለ ምእመናንን ከማዳን (ከማጽናት) አኳያ እስከ ገጠር ቀበሌዎች እና ኢጥሙቃን (ይልተጠመቁ) በሚበዙባቸው አካባቢዎች ድረስ ዘልቀው እንደ ቋንቋው፣ እንደ ባህሉ የማገልገል ቁርጠኝነት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ የዐውደ ትምህርቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይም ‹‹የአገልጋዮች ኅብረት ማኅበር›› የተባለው እና ለዐውደ ትምህርቱ (ሴሚናሩ) ዝግጅት የክብር ስፖንሰር የሆነው አካል በውስጡ ያቀፋቸው ዘማርያን እና ሰባክያን የሞያቸው አግባብነት በሚመለከተው አካል ከወጥ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ አንጻር እየተረጋገጠ መዋቅሩን ጠብቀው የሚያገለግሉበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ተጠይቋል፡፡

ማእከላዊ አሠራር ያስፈለገው ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው ሁሉም በየፊናው እንዳይፋንን እና ሕገ ወጥነትን ለመቆጣጠር መሆኑን የተናገሩት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሐላፊ ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ፣ መመሪያው የተላለፈው የቅዱስ ሲኖዶስን ሕግ ለማስጠበቅ፣ ሰባክያኑን እና ዘማርያኑን በተለይም መደበኛ ሥልጠና ያላገኙ የትሩፋት አገልጋዮችን በአግባቡ ለማስተናገድ ታስቦ መሆኑን ገልጸው በመመሪያው አፈጻጸም ረገድ በአህጉረ ስብከት የሚያዘው ጥብቅ አቋም የግጭት መንሥኤ ሊሆን እንደማይገባ መክረዋል፡፡ የትሩፋት አገልጋዮች የማገልገል ፈቃድ የሚሰጣቸው አድራሻቸው፣ መንፈሳዊ ትምህርት የተማሩባቸው ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የአገልግሎታቸው ዓይነት እና ያገለገሉበት ዘመን በትክክለኛው ቅጽ ተመዝግቦ ለሚያከናውኑት ተግባር ተጠያቂነት እና ሐላፊነት ሲኖራቸው መሆኑን ሐላፊው አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ሐዋርያት ሳይጠሩ አልመጡም፤ ሳይላኩ አልሄዱም፡፡ የተጠሩበት እና የተመረጡበት ዋና ዓላማ ለቃሉ እውነተኛ ምስክሮች እንዲሆኑ ነው፤. . . ክርስቶስ ሲያስተምር ጊዜውን፣ አጋጣሚውን፣ ሁኔታውን፣ እየተከተለ ስለነበር ሁኔታው ሁሉ ለሕዝቡ ይታወቅ፣ ትምህርቱም ይረዳ ነበር›› በማለት ስብከተ ወንጌል አምላካዊ ትእዛዝ በመሆኑ በማንም የማይገታ ቢሆንም ሥርዓት እንዳለው ግን አስረድተዋል፡፡

ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) የሰዎችን አመለካከት እና የመኖር ትርጓሜ በሊበራሊዝም (ነጻ የንግድ እና የሰዎች እንቅስቃሴ)፣ በሞደርኒዝም (በዝማኔ እና ምዕራባዊነት) እና ኮስሞፖሊታኒዝም (በዓለምአቀፋዊ ዜግነት) መንፈስ እና ስሜት ወደ አሐዳዊነት በማምጣት በሀገራዊ ብሔረተኝነት፣ በታሪክ እና ትውፊት ፍቅር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የገለጹት ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም አገልጋዩ የሥጋንና የመንፈስን ተግባራት በመለየት የአኗኗር ሁኔታውን በጥበብ ሊያራምድ፣ የጊዜውን ቴክኖሎጂ በመማር እና በማስተማር እንደ አግባቡ ሊጠቀም፣ በኦርቶዶክሳዊ ክርስትና እሴቶች ላይ የተመሠረተ የክርስትና ግሎባላይዜሽንን ለማስፋፋት መጣር እንደሚገባው መክረዋል፡፡

ሊቃውንት እና አገልጋዮች እርስ በርስ የሚቀራረቡባቸው እና የሚተዋወቁባቸው የጋራ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያትን በመላው አህጉረ ስብከት የማዘጋጀት ልምድ መጠናከር እንደሚኖርበት የተናገሩት ሐላፊው፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሀብቶቻችንን በማጣመር፣ በአብነት እና በዘመናዊ ትምህርቱ መካከል ድልድይ በመፍጠር፣ ቡድናዊ እና ጎሳዊ (አካባቢያዊ) ስሜትን በመሻገር፣ በማቴሪያላዊ አቅም ራሳቸውን አደርጅተው እየተፈታተኑን ያሉትን አማሌቃውያንን ተቋቁመን ለልማት እና ለአገልግሎት በአንድነት መነሣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‹‹የዘመኑን ፈተና በማዜም ብቻ አንወጣውም፤ ከጸናጽሉ እና ከመቋሚያው ጋራ ወንጌሉም አብሮ መሄድ አለበት፡፡. . . . የእኛ ሊቃውንት ከድጓው እና ከቅኔው ጋራ ቁንጫ ሲበላቸው አንዷ ዘማሪ ነኝ ብላ መጥታ ገንዘብ እየዘረፈች ሄደች›› በማለት የገሠጹት ደግሞ የመምሪያው የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ናቸው፡፡ ‹‹ዕውቀት ንብ አይደለም፤ ዝም ብሎ ወደሰው ቀፎ አይገባም›› ያሉት ብፁዕነታቸው ለመንፈሳዊ አገልግሎት መከራ ስላለበት መንፈሳዊ ጉልበት እንደሚያስፈልግ፤ አገልጋዩ ፍቅረ ንዋይን እርም ብሎ በምልዓት ከሚሰጠው ቃለ እግዚአብሔር እየቀዳ ለምእመኑ ለማዳረስ ይችል ዘንድ ባልትና (የትምህርት ዝግጅት) እንደሚያሻው መክረዋል፡፡

በሌላ በኩል በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሠልጥነው የሚወጡት ምሩቃን በዕጣ በሚደለደሉባቸው ምድብ ቦታዎች ላይ ቆይተው እንደማያገለግሉ፣ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ለሰባክያን የተወሰነላቸው የደመወዝ መጠን ዝቅተኛ እና ከኑሮው ውድነት ጋራ የማይሻሻል መሆኑ፣ ጥቂት በማይባሉ አህጉረ ስብከት ለስብከተ ወንጌል የሚመደበው በጀት ውስን እና አገልግሎቱም እንደ ዋነኛ መንፈሳዊ ተግባር ባለመታየቱ ምክንያት እንደ ሆነ በዐውደ ትምህርቱ ተሳታፊዎች ተገልጧል፡፡ ይህም ሰባክያነ ወንጌል ሊሳተፉባቸው በሚገቡ የሥልጠና እና የውይይት መድረኮች ላይ ለአበል ሲባል ጉዳዩ የማይመለከታቸው የሀገረ ስብከት ሐላፊዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እስከመላክ እንደሚደረስ ተመልክቷል፡፡ ለዚህ የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎቹ አቤቱታ ከመምሪያ ሐላፊዎች የተሰጠ ግልጽ እና ቀጥተኛ ምላሽ ይሁን ተስፋ የለም፡፡

በምትኩ የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎቹ የበጎ ፈቃድ (የትሩፋት) አገልጋዮች እየተባሉ በአንድ ጉባኤ ከ10000 እስከ 15,000 ብር የሚያፍሱትን ‹‹የአገልጋዮች ኅብረት›› አንዳንድ አመራሮችን እና አባላትን በግልጽ ወቅሰዋል፡፡ የኅብረቱ ብዙዎቹ አባላት በስብከት እና በዝማሬ አገልግሎታቸው የሚደክሙ ናቸው፡፡ ይሁንና ስም ያወጡ እና የአመራር ሚና የሚጫወቱት አንዳንድ ግለሰቦች የሌሎችን የሥራ ፍሬ የራሳቸው አስመስለው በማቅረብ፣ ‹‹የገጠር አብያተ ክርስቲያንን፣ ዕጓለ ሙታንን እንረዳለን፤ እናሳድጋለን፤ እናስተምራለን. . .›› በሚል ከባለጸጎች እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምእመናን በሚሰበስቡት ገንዘብ ራሳቸውን ያበለጸጉ፣ ከመንበረ ፓትርያርኩ በሚያገኙት የድጋፍ ደብዳቤ ቪዛ እያስመቱ ከአገር ከወጡ በኋላ ‹‹ገለልተኛ ነን›› እያሉ በማምታታት፣ የምእመናንን አንድነት የሚከፋፍሉ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓለም አቀፋዊ አንድነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ የሚያባብሱ፣ ‹‹የተነቃቀፍንበት ዘመን ይበቃል›› ቢሉም ካህናቱን እና ትጉሃን አገልጋዮችን የሚያናንቁ፣ ከፓትርያርኩ እና በዙሪያቸው ከተሰለፉ ማፊያዎች ጋራ በፈጠሩት ልዩ ግንኙነት ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልዩ ልዩ መምሪያዎች በላይ ሆነው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ተገልጧል፡፡ እነርሱን የተመለከቱ የእገዳ እና ሌሎች ርምጃዎችን የሚገልጹ የበላይ አካል ደብዳቤዎችም በመሳቢያ ውስጥ እንደሚቆለፍባቸው ታውቋል፡፡ ከዚህ አኳያ በኅብረቱ ተዘጋጅቶ በሴሚናሩ ማጠናቀቂያ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት ላልተሳተፉት ጭምር በጅምላ የተሰጠው የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ግለሰቦቹ ‹‹ቤተ ክህነቱ ያውቀናል›› በሚል ለጥቅመኛ እንቅስቃሴያቸው ሕጋዊ ልባስ ለማስገኘት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አንዳንድ የሴሚናሩ ተሳታፊዎች ያደረባቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡ ዐውደ ትምህርቱን የራጉኤል ጎልማሶች ጉባኤ በ20,000 ብር፣ ማኅበረ ቅዱሳን በ10,000 ብር፣ የአገልጋዮች ኅብረት (በዲ/ን ዘላለም ወንድሙ በኩል) 43,000 ብር ስፖንሰር እንዳደረጉት ተገልጧል፡፡

3 comments:

Anonymous said...

sile higewet sebakiyan sinnager higawiyan sebakiwoch yetebalus min iyaderegu newu bilo tinish comment bitsexu minale.bete kihinet yezerawun newu iyesebesebe yalewu mikiniyatum meriyeleleu awura hunawal ina yalewu meri katolik,adventist, ere sintuun bealem lalewu betkiristyan meri degimo yeselam predent ketwedet yeselam aleqa yetebalewu "only God" min yideregal "laaqiin lukaan baqatan cinaachaan keessa ciisu jedhama mitiiree" ?

ጉድ ፈላ ዘሚኒሶታ GUD FELA ZE-MINNESOTA said...

ለሁሉም ጊዜ አለው።

በትንቢተ ሐጌ በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? ተብሎ የተጻፈው ቃል የደረሰ ይመስላል። በእጃቸው ያለውን ወርቅ ከመዳብ ቆጥረውት የፕሮቴስታንቱ ዝማሬና ስብከት ከያሬዳዊ ዜማና ከሊቃውንቱ ስብከት የበለጠ ነው በማለት የተነሡት ጥቂት ግለሰቦች የዘረጉት መረብ ብዙኻኑን አጥምዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች እንድትመዘበር ከሆነች ዓመታት አልፈዋል። ስብከት እንደ ኪነት ተቆጥሮ ገንዘብ እየተከፈለበት ሲገባ ለብዙ ዓመታት ዝም ተብሎ በመታየቱ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ የሚባለው ተረት እውን ሆኖ ሁሉም በየፊናው አውደ ምሕረቱን ገንዘብ መሰብሰቢያ አድርጎት ቆየ። ገበያው በሰው በተጨናነቀበት ስፍራ ላይ በጠራራ ፀሐይ ባትሪ እያበራ ሰው በመፈለግ ላይ ነኝ ያለው ፈላስፋ በልጅነታችን ሲነገረን አስቆን ብናልፈውም ዛሬ ግን ስናስተውለው እውነትም ከሰው መኻል ሰው ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነገር መሆኑን ልብ እንድንል አድርጎናል። ዘንድሮ ሰባኪ ወንጌል በዓይነት በዓይነቱ በየቦታው ቢገኝም ዛሬም እንደ ትናንቱ ፈላስፋ ባትሪ ይዞ ከሰባክያን መካከል ሰባኪ ለማግኘት መነሣት ግድ ይላል። ለሰው ቀና የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን ሞት ነው በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን ያስተላለፈልን መልእክት ለብዙዎች የተከፈተ በር ያገኙ ቢመስላቸውም ፍጻሜው ግን መጋለጥ እና በአደባባይ መውጣት እየሆነ ሲመጣ ስናየው እግዚአብሔር እውነትን ያያል ግን ይቆያል በማለት የተናገረውን ጸሐፊ ሊዎ ቶልስቶይን እንድናሰበው ያደርገናል። በመዝሙር የተማረው ሕዝብ እና ገንዘብ ከፍሎ ገብቶ ከመጽሐፍ ላይ የተጠቀሰለት ጥቅስ በውስጡ ቤት ሠርቶ የሰባክያኑን አካሄድ በውል ተረድቶ የሐሰት ስብከታቸውን ማጋለጥ የጀመረበት ወቅት ላይ መድረስ ችለናልና ዛሬም እንደ ትናንት ብዝበዛ እንዳይቸኩል በዚሁ ይበቃል ብለን ለማስቆም ሁላችን አብረን መሥራት ይኖርብናል። በዚህ በአሜሪካ ሰባኪው ለአንድነት ከመስበክ ይልቅ ለመለያየት መስበክን ገንዘቡ አድርጎታል። እውነትን የሚሰብኩ ሰባክያን የሉም እያልኩኝ ሳይሆን ከእውነት መንገድ የወጡ እና የምእመናኑን ገንዘብ ብቻ ከመብላት ባሻገር አንዳችም ግብር የሌላቸው ሰባክያን መኖራቸውን ለመናገር ነው። ወደ አዳራሽ የወጣው ሕዝብ መቼ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚመለስ እግዚአብሔር ያውቃል። አንዱ ይጀምራል አንዱ ይከተላል። ፖለቲካን መጠቀሚያ በማድረግ እኔ የገለልተኛ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ እደግፋለሁ በማለት በውጭው ዓለም ያለውን ሕዝብ በቃል በመደለል በእግዚአብሔር ስም ሰዎችን ማጥፋት የተጀመረበት ሰዓት ስለሆነ ወንጌል ብርሃንነቱ ብቻ የሚሰበክበት መንገድ እንዲዘጋጅ የተጀመረው እንቅስቃሴ መክኖ እንዳይቀር በአባቶቻችን ላይ ያደረው መንፈስ ከፍጻሜ ይድረስልን በማለት ምኞቴን አቀርባለሁ።
ሰውን የገነቡ መስሏቸው እያፈራረሱት እነርሱ ግን በተሸለሙ ቤቶቻቸው ለመኖር ኪሳቸውን በገንዘብ ለመሙላት ለተነሡት ሰባክያን በሙሉ በዚያው በትንቢተ ሐጌ የተጻፈው ቃል እንደሚፈጸምባቸው ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ ነኝ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። በማለት የተጻፈው መልእክትም እውን ይሆናል። በመሳቀቅ ከመኖር ወንጌልን በነፃነት ሰብኮ በነፃነት መኖር ከሁሉ ይበልጣል። እግዚአብሔር ይርዳን፤ የተጀመረውም እንቅስቃሴ ከታሰበበት ይድረስ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

GUD FELA ZE MINNESOTA said...

ለሁሉም ጊዜ አለው

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)