September 19, 2010

በሐዋሳ ገብርኤል ሊካሄድ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ምርጫ በሕዝበ ክርስቲያኑ ተቃውሞ ተሰናከለ፤

  . የገዳሙ አጥቢያ ምእመናን ሕገ ወጡን ምርጫ ተቃውመዋል፣ 
  . ሊቀ ጳጳሱ የአጣሪ ኮሚቴውን ተግባር ለማሰናከል እየጣሩ ነው፣

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 19/2010፤ መስከረም 9/2003 ዓ.ም):-  በአገልግሎት ላይ ያለውን የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደንብ(ቃለ ዓዋዲ) እና በገዳሙ የውስጥ አስተዳደር ከተደነገገው ውጭ ከሀገረ ስብከቱ በተላከ ግለሰብ በተጠቆሙ አስመራጮች ዛሬ እሑድ ለማካሄድ ታቀዶ የነበረው ምርጫ በጽኑ ተቃውሞ ገጥሞት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ዝርዝሩን እንዳጠናቀቅን የምናቀርብ ሆኖ ለዚህ ተቃውሞ መንደርደሪያ የነበረውን ጉዳይ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

ባለፈው ሳምንት እሑድ በአቡነ ፋኑኤል በተሰጣቸው ትእዛዝ ከሀገረ ስብከቱ የተላኩት የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ሐላፊ ቀሲስ አማረ በገዳሙ አስተዳደር የማይታወቅ የተድበሰበሰ ሪፖርት በሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር አማካይነት እንዲቀርብ ካስደረጉ በኋላ ራሳቸው በዐውደ ምሕረቱ ቆመው ከምእመኑ መካከል ቀድመው ያዘጋጇቸውን ሦስት ግለሰቦች በድርጅታዊ አሠራር እንዲጠቆሙ በማድረግ አስመራጭ ኮሚቴ ሠይመዋል፡፡ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ስምንት ንኡስ አንቀጽ 1 - 5 እና አንቀጽ ዘጠኝ በተዘረዘረው መሠረት የሰበካውን የምርጫ ሥነ ሥርዐት የሚያስፈጽሙት ከሰበካው ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ቀበሌዎች የተውጣጡ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የሚገኙበት ከአምስት ያላነሱ ከዐሥራ አምስት ያልበለጡ ሆነው በካህናት፣ መነኮሳት እና ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ በመሠየም ነው፡፡ እኒህ የምልዓተ ጉባኤው ሥዩማን የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታቸው የታወቁ፣ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ተመዝግበው የሚገባቸውን አስተዋፅኦ የተወጡ፣ በመንፈሳዊነታቸው፣ በግብረ ገብነታቸው እና በአስተዋይነታቸው የታወቁ እንዲሁም በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን እንደሚኖርባቸው በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ ሦስት እና አራት ላይ ተገልጧል፡፡

ይህን ለማስፈጸም ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በሰበካው ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ወይም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት አማካይነት ለአጥቢያው ካህናት እና ምእመናን ትምህርት እና ቅስቀሳ መደረግ እንደሚኖርበት፣ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤው በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እንደሚመራ፣ ጉባኤውም ሕግንና ሥርዐትን ተከትሎ እርስ በርስ በመፈቃቀር፣ በስምምነት፣ በሰላም እና በጸጥታ መፈጸም እና ማስፈጸም እንደሚያስፈልገው፣ ድምፅ የሚሰጥባቸውን ጉዳዮችንም በድምፅ ብልጫ መወሰን እንደሚገባው በንኡስ አንቀጽ አንድ እና ሁለት ላይ ያዝዛል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ አምስት እና አንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ ሦስት መሠረት አዲስ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ከመካሄዱ ከአንድ ወር በፊት በሥራ ላይ የነበረው የሰበካው አስተዳደር ጉባኤ በአገልግሎት ዘመኑ የፈጸማቸውን እና ያስፈጸማቸውን እንዲሁም በዕቅድ የያዛቸውን ተግባራት አጠቃላይ የሥራ እና የፋይናንስ ሪፖርት ለካህናት እና ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ አንድ መሠረት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ምርጫ የሚያጸደቀው፣ የሚያሻሽለው ወይም የሚሽረው በወረዳ ቤተ ክህነቱ አማካይነት ውጤቱ ከቀረበለት አልያም የምርጫው አፈጻጸም ትክክል ሆኖ ሳያገኘው ሲቀር ጉዳዩን በአስተዳደር ጉባኤ ከተመለከተው በኋላ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት እሑድ በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሆነው እና የታየው ግን ከዚህ የቃለ ዓዋዲው ደንብ ቢያንስ ገሚሱን እንኳን ያሟላ አልነበረም፡፡ አቡነ ፋኑኤል ከእሑዱ የይስሙላ ትዕይንት በፊት የምርጫ አስፈጻሚዎችን በቀጥታ ልከው የነበረ ሲሆን በምእመኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ሕገ ወጥ ተልእኴቸውን ሳያሳኩ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ትምህርት ያልወሰዱት ሊቀ ጳጳሱ የገዳሙ አጥቢያ ካህናት እና ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ ሳይደረግ፣ የምርጫው መካሄድ ታውቆ በቂ ቅስቅሳ እና ትምህርት ሳይሰጥ፣ በሥራ ላይ ያለው ሰበካ ጉባኤ በኀባር የመከረበት የክንውን እና ዕቅድ ሪፖርት ሳይቀርብ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ከተሾሙት የገዳሙ አስተዳዳሪ እና ከሰንበት ት/ቤቱ አመራር ጋራ በተያያዘ የተፈጠሩት ችግሮች ተፈትተው የእርስ በርስ ስምምነት፣ ሰላም እና ጸጥታ መስፈኑ ሳይረጋገጥ የሀገረ ስብከቱን ሰበካ ጉባኤ መምሪያ ልኡክ በድንገት በመስደድ ቀድመው ለአስመራጭነት ልከዋቸው የነበሩትን ሦስት ግለሰቦች በቡድናዊ አሠራር እንዲጠቆሙ፣ የተጠቆሙት ግለሰቦች ከኦርቶዶክሳዊነታቸው፣ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ከመወጣታቸው፣ ከመንፈሳዊነታቸው፣ ግብረ ገባዊነታቸው እና ሞያዊ ብቃታቸው አኳያ የድጋፍ እና ተቃውሞ አስተያየት ሳይደመጥባቸው የቃለ ዓዋዲውን ቃል እና መንፈስ ፈጽሞ በተፃረረ አኳኋን የአስመራጭ ኮሚቴ ተብዬዎች ‹‹ምርጫ›› እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡ ሁኔታውን የበለጠ አሳፋሪ የሚያደርገው ደግሞ በዚህ የአስመራጭ ኮሚቴ ተብዬዎች ‹‹ምርጫ›› የተጠቆሙት ሦስት ግለሰቦች ቀደም ሲል በሊቀ ጳጳሱ ተልከው ምእመኑ የተቃወማቸው መሆናቸው እንደ ሆነ የሰበካው ምእመናን ለደጀ ሰላም አስረድተዋል፡፡ በዕለቱ ለቅዳሴ በገዳሙ የተገኙት ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የአስመራጭ ኮሚቴ ተብዬው ‹‹ምርጫ›› ሂደት ሕጋዊ አለመሆኑን ቢቃወሙም ሰሚ እንዳላገኙ በስፍራው የነበሩ ደጀ ሰላማውያን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እና ምእመናን ኅብረት በሰበካ ጉባኤ እንድትደራጅ የተደረገው በአስተዳደር፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በአገልግሎት እና በምጣኔ ሀብት በኩል በራሷ ሕግ እና ሥርዐት በመመራት እና በመደራጀት እንድትሠራ ለማድረግ መሆኑን ያመለከቱት አንዳንድ የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላት፣ ገዳሙን በሀብታቸው እና በአገልግሎታቸው ለመርዳት ከሚጥሩት ካህናት፣ መነኮሳት እና የሰንበት ት/ቤቱ ወጣቶች አጠቃላይ ጉባኤ ስምምነት ውጭ በአስመራጭ ኮሚቴ ተብዬዎች ሸፍጥ በመጪው እሑድ ለማካሄድ የታሰበውን ‹‹ምርጫ›› በሰላማዊ መንገድ እና በጽናት ለመቃወም እንደተዘጋጁ ለደጀ ሰላም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ችግር ቢፈጠር ተጠያቂነቱ የሊቀ ጳጳሱ እና የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በመሆኑ እኒህ አካላት ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነታቸው እንዲታቀቡ፣ በሥራ ላይ ያለው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአገልግሎት ጊዜ ተጠብቆ በቀጣይ የሚካሄደውም ምርጫ ቃለ ዓዋዲው በሚያዝዘው መሠረት እንዲከናወን አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ይህ ውዝግብ በታላቁ የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሲፈጠር በአዲስ አበባ የተቀመጡት አቡነ ፋኑኤል ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጋራ ቀደም ሲል በሐዋሳ ከተማ ምእመናን ተወካዮች እንዲሁም በገዳሙ ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ አባላት የቀረበባቸውን የአስተዳደራዊ በደል እና ምዝበራ አቤቱታ እንዲያጣራ በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተሠየመውን አጣሪ ኮሚቴ ተግባር የሚያስናክሉበትን መንገድ በመፈለግ ላይ ነበሩ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ የሐዋሳ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አንዳንድ አስተዳዳሪዎች ወደ መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ እንዲመጡ በማዘዝ፣ ‹‹ዕርቅ ፈጥረናል፤ ተስማምተናል፤ አጣሪ ኮሚቴው ይቅር›› ለማሰኘት ሞክረዋል፡፡ ‹‹ዕርቅ ፈጥረናል›› የተባለው ሊቀ ጳጳሱ በክልሉ የአስተዳደር እና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ትእዛዝ በባለሥልጣናቱ ፊት ተንበርክከው የበደሏቸውን የምእመናን እና ካህናት ወገኖች ይቅርታ የጠየቁበትን አጋጣሚ እንደ ሆነ አንዳንድ ደጀ ሰላማውያን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይሁንና ይህ ይቅርታ በአባት እና ልጅ መንፈሳዊ ዝምድና የተደረገ በመሆኑ ያለው ዋጋ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨባጭ የተፈጸመው አስተዳደራዊ በደል ደግሞ በአግባቡ ተጣርቶ ሊታወቅ እንደሚገባ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ሊቀ ጳጳሱ በዘመን መለወጫ ማግሥት ቃሊቲ በሚገኘው ቪላቸው ፓትርያሪኩን ጨምሮ ለቋሚ ሲኖዶስ እና አንዳንድ የአጣሪ ኮሚቴውን አባላት ምሳ መጋበዛቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ የአቡኑ ‹የማግባባት› እና ረብ የለሽ የሕዝብ ግንኙነት ምስነት የማጣራት ሂደቱን እንዳያስተጓጉለው የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴው አባላት ያደረባቸውን ስጋት ተናግረዋል፡፡

5 comments:

Anonymous said...

አባ ፋኑኤል ሆይ አሜሪካን ቅጥ ያጣ አሰራር የለመዱት ለኢትየጵያ አይሰራምና አርፈው ይቀመጡ

selamawi said...

በስመ ስላሴ አሃዱ አምላክ አሜን

እኔ እምለው የኛ የቤተክርስቲያን መሪዎች አምባገነን ካልሆኑ በቃ ባለስልጣን የሆኑ አይመስላቸውም ማለት ነው? አቡነ ፋኑኤል ምን ነካቸው ? በሰለጠነው ዓለም የኖሩ ሰው ናቸው ምነው የአስተዳደር ብቃት አነሳቸው ? አንድ ነገር ትዝ አለኝ አቡነ ጳውሎስ አንድን የቤክርስቲያናችን አባት ምን አሏቸው ይባላል , አባ, ,, ጎሳን ትቀድሳለህ አሉ? አሏቸው እኒያም አባት መልሰው ከርስዎ በተማርኩት ነዋ አሏቸው ይባላል ምን ለማለት ነው ዘመዶችህን ወይም የሃገርህን ሰዎች ትረዳለህ ለማለት ነው መላሹም ሲመልሱ ዘረኝነቱን የተማርኩት ከእርስዎ ነው ነው ያሏቸው ምን ለማለት ነው የፈለኩት አቡነ ፋኑኤልም ቢሆን አምባገነንነቱን ከአቡነ ጳውሎስ ነው የተማርኩት ሳይሉ የሚቀር አይመስለኝም የሆነው ሆኖ ህዝብን በማሳዘን ቤተክርስቲያንን የመናፍቃን መሳለቂያ ስላደረጓት ምንድነው ጥቅማቸው?እኔን የማይገባኝ ይህ ነው ህዝቡን ለምን በአግባቡ አይመሩትም ?ያለስርዓት የሚሄደውን ለምን አይገስጹትም ? ነው ወይስ ያለስርዓት ከሚሄዱት ወገን ናቸው ይቅር ይበለን ,,,, ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን። 2ኛ ተሰ 3፥ 6

Wongel said...

Dears, Thank you for the information. But all your reports are complains we need some thing else. Please try to tell us about Gubae's, Sibkets and new Mezmur's and some positive issues.

We have nothing to contribute on knowing this case. It is one chapel's issue and can be solved by themselves. Now a days, I am not sure if you are reporting appropriately. As to me, if you expect some one is wrong, you want to defame all his graces and his works. I may not be correct.

Please report also positive issues. How many Gubaes do we have all over the Ethiopia, who are preaching the Good New of Jesus? How is the church doing on Gosple? Show us if there are some issues that we can help in the spreading of the Orthodoxawi Gospel to the whole Ethiopians, which is the main purpose of the church.

Otherwise the admin issues are always problematic. Please don't forget also that we have uneducated society.

Anonymous said...

ሊላይ ነኝ። እስኪ እንደልማዴ ጥቂት ላለቃቅስ። የሀገሬ ሰው «ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ» ነው? የሚለው። አዎ!! የኛ ቤተክርስቲያን ጉድ ግን ዓመቱን ሙሉ መሆኑ በመስከረም የነበረውን ብሂል ያፈርሰዋል። እናም ዓመቱን ሙሉ ከሚቀጥለው ችግራችን የመስከረሟን የዋህድ ዕለት ቆንጥሬ ጥቂት ልበል።አንዳንዶች ደረቅ ጽሁፌ ላይጥማቸው ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ የሰውን ጥፋት መዘርዘር ተገቢ ነው ላይሉ ይችላሉ። «ኀዳጌ በቀል፣ ከባቴ አበሳ» መሆንን ከክርስቶስ ተምረነዋል። ለማይገባቸው አጥፊዎችም ተገቢውን የተግባራቸውን ምስ ማቅመሱንም ከእርሱው አግኝተነዋል። እናም አባ ፋኑኤል የተባሉትን ጥቂት ብንነግራቸው ነውራቸውን እስካልደበቁ ድረስ እኛን ዋሾ አያሰኘንም። ቤዛ ዓለም ክርስቶስ የጸሎት ቤት በተባለችው ቤተመቅደስ ይነግዱ ያስነግዱ፣ ይሸጡ ይለውጡ፣ ለነበሩት ካህናት ሌዋውያን፣ ጸሐፍት ፈሪሳውያን የሰጣቸው የእከይ ተግባራቸው ምላሽ ልምምጥ ወይም ማጎብደድ አልነበረም። ማመንዘሪያ ጠረጴዛዎቻቸውን፣ መዘርዘሪያ ዲናራቸውን አይናቸው እያየ ገለበጠ። «የቤትህ ቅናት በላኝ» የተባለውን ይፈጽም ዘንድ በጅራፍ ገርፎ አባረረ። አዎ! የአባቱ ቤት የጸሎት ቤት ትባል ነበር። እነርሱ ግን መሸቀጫ፣ መለወጫ አደረጓት። እናም አለቃ ካህናት ፋኑኤል እየሰሩ ያሉት የጸሀፍቱን ቤመቅደስ ውርስ አደራ ተረክበው መሸቀጥ፣ መለወጥ ነው እየታየ ያለ ተግባራቸው። ዛሬም «የጸሊማን አርጋብ» ማኅበርተኛው አባ ፋኑኤል ጳጳስ ከመባላቸው በፊት አሜሪካ እያሉ ይህችን ቤተክርስቲያን በተቃዋሚ ጎራ ሲዋጉ ከመኖራቸው በላይ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር፣ የትግሬ ቀበሌ መቀሌ፣ሲሉ እንዳልነበር እንደልብስ ሰፊነታቸው ልምድ መርፌ ሆነው ውስጥ ውስጡን እየሾለኩ በመዘርዘር ስራቸው ዶላራቸውን ቤተመቅደሷ ውስጥ ለውጠው የሃበሻ ጵጵስናን ገዝተው ቁጭ አሉና አረፉት። ይሄው እስከዕለተሞታቸው የማይለያቸው የመገለባበጥ አባዜአቸው በአንድ ወቅት የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ መስለው እነ አቡነ ሳሙኤል ለቤተክርስቲያን የሚያደርጉትን ጩኸት የሚደግፉ መስለው አብሬዎት አለሁ ሲሉ እንዳልነበር መሸቀጫ ባህሪያቸው አሸነፋቸውና ቀኝ ኋላ ዙር ብለው ከእነ ወጠጤው በጋሻው ጋር የንግድ ጠረጴዛቸውን ሃዋሳ ላይ ዘረጉ። ሃዋሳን እያመሱ ዋኖስና እርግብ ምዕመናንን በደራ ገበያቸው ይነግዱ ዘንድ ቢጤ ሸቃጫችውን ያሬድ አደመን ፊት አውራሪ አደረጉት። እናም ጴጥሮስ በአንድ ወቅት የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማ ብሎ ጌታ በገሰጸው እውነተኛ ቃል « አንተ ሰይጣን፣ ወደኋላዬ ሂድ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና»ማር8፣33 እንዳለው የክርስቶስ የቤቱ ቅናት ቢበላኝና እኚህን የቤተክርስቲያን ሳይሆን የዴማስ ዓለማቸውን የሚቀጩትን አባ ፋኑኤልን ብናገር ተወቃሹ እኔ ሳልሆን የሚተካከለው የለም እንጂ የቃሉ ባለቤት ክርስቶስ በሆነ ነበር። ስለሆነም ከጌታ ቃል ተውሼ እሳቸውን ሳይሆን አመለካከታቸውን« አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አትሰማም»እላቸዋለሁ።

Anonymous said...

Abet yan ken betam yigermal behiwote be betekirstian wuistendeza ayle kewuiti tekawumo abatoch demo yihenen tekawuimo wodegon sitewu yasifera neber.....field behedikubet neber yayehut...Aba yibikawot betekiristian yalemimenana min waga alewu.!!!!!!!!!!!!!!!!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)