September 18, 2010

መንግሥት ከጳጳሳቱ ጋራ የሚያደርገው ውይይት እንደቀጠለ ነው

  • የጥቅምቱ ሲኖዶስ የመንግሥት እና ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ግንኙነ ከመወሰን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ከመፍታት አኳያ ወሳኝ ጉባኤ መሆን እንደሚገባው ተገለጸ
  • ‹‹እኛ ይህን መንበር ከያዝን በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላም አጣች፤ ተደፈረች›› (ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ)
  •  ‹‹የብፁዓን አባቶችን መኖሪያ ቤት የሰበሩ እና ብፁዓን አባቶችን የደበደቡ ለምን ለፍርድ አልቀረቡም?›› (ብፁዕ አቡነ ሚካኤል)
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 18/2010፤ መስከረም 8/2003 ዓ.ም):-:- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፕትርክና ራሷን ከቻለችበት ጊዜ አንሥቶ ያሉት ኀምሳ ዓመታት ሰላሟን ያጣችበት እንደ ሆነ፣ በተለይም አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሥልጣን የቆዩባቸው ያለፉት 18 ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቱ ክብሯ የተደፈረበት እና በእጅጉ የተዋረደችበት ወቅት መሆኑን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ተወካይ ጋራ ውይይት የተቀመጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተናገሩ፡፡ ጳጉሜን አራት ቀን 2002 ዓ.ም ተጀምሮ መስከረም ስድስት ቀን 2003 ዓ.ም ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ቀጥሎ በዋለው አራተኛ ዙር ስብሰባ ቀደም ሲል በነበሩት ውይይቶች ያልተገኙ፣ በአመዛኙ የተቃውሞ አቋም እንዳላቸው የሚታመኑ እና ለጊዜው በአዲስ አበባ የቆዩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ መረሳ ረዳ ጋራ ኀይለ ቃል እና ተግሣጽ የበዛባቸው የሐሳብ ልውውጦችን አድርገዋል፡፡
የሊቃነ ጳጳሳቱ ሐሳብ በዋናነት ያተኮረው - ቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳችም በይፋ የታወቀ ሥልጣን፣ ተግባር እና ሐላፊነት ያልሰጠቻቸው የውጭ አካላት ክርስቲያን መስለው ገብተው በቤተ ክህነቱ አሠራር ውስጥ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት፣ ባለፈው ዓመት የርክበ ካህናት እና የሐምሌ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያት ወቅት ፓትርያሪኩ ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ተገዥ እንዲሆኑ፤ ቤተሰባዊ አስተዳደር፣ ብኩንነት እና ሙስና እንዲወገድ፤ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ሥራ ተረክቦ በበላይነት እንዲመራ እና የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች ተፈጻሚነት እንዲከታተል በምልዓተ ጉባኤው የተደረሰበት ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን በታገሉት አባቶች ላይ የተደረገውን እገታ፣ የመኖሪያ ቤታቸውን በመስበር የተቃጣውን የግድያ ሙከራ፣ ሌሎቹንም ከመኖሪያ ቤታቸው አውጥቶ በመውሰድ የተፈጸመባቸውን ወከባ እና እንግልት በማውሳት በወቅቱ ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ድርጊቱን እንደፈጸሙ በታመነባቸው ሰዎች ላይ ስለተወሰደው ርምጃ የሚሞግት ነበር፡፡ የመንግሥት ተወካዩ እኒህን አቤቱታዎች በጥሞና ከማዳመጥ በቀር መንግሥት በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ስለ ወሰደው ርምጃም ይሁን በወንጀሉ ተጠያቂ ሊሆን ስለሚችለው አካል አንዳችም ቃል አለመተንፈሳቸው ታውቋል፡፡ የመንግሥትን ፍትሕ በትዕግሥት ቢጠብቁም መልሱ ዝምታ መሆኑን አሰምተው የተናገሩ አንድ ብፁዕ አባት ‹‹ቤቴ ጠርቼ ስንት ነገር ነግሬህ ነበር፤ አንዳችም ያስፈጸምከው ነገር የለም፡፡ ዛሬ ከወንበሬ ተነሥቼ ሰላምታ ያልሰጠሁህም ለዚህ ነው›› ብለው ምሬታቸውን መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡ ይህን ምሬታቸውን እንደ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ያሉ አባቶች ተጋርተዋቸዋል፡፡


የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሐላፊ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ‹‹ምነው እነ ወይዘሮን ሃይ ብትሏቸው?›› በማለት ለቤተ ክርስቲያኒቷ በማይበጁ ግለሰቦች የሚደረገውን ጣልቃ ገብነት ተቃውመዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በፓትርያርኩ እና በብፁዕ አቡነ ገብርኤል መካከል ያለው ግንኙነት ክፉኛ እንደሻከረ እና እስከ መጎሻሸም ደርሶ እንደ ነበር የተገለጸ ሲሆን መንሥኤውም ብፁዕነታቸው ፓትርያርኩ በየሰበቡ በሚያደርጉት ጉዞ እንዲያጅቧቸው በተደጋጋሚ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ባለመቀበላቸው እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በበኩላቸው ሌሎች የእምነት ተቋማት በአስተዳደራቸው ጎልቶ የሚሰማባቸው የውስጥ አስተዳደራዊ ቀውስ እንደሌለባቸው አስታውሰው ‹‹ምነው እኛ ብቻ እንታመሳለን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አያይዘውም በተለይም አቡነ ጳውሎስ ወደ መንበረ ፕትርክናው ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር የሚጋፉ - ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትዋረድባቸው፣ በሐሳብ ድዉይ እና ቀኖናዊ ያልሆኑ ድርጊቶች መበራከታቸውን በመዘርዘር የመንግሥቱም ተወካይ የሚተጉት ለፖሊቲካቸው በማሰብ እንጂ ለቤተ ክርስቲያኒቱ በመጨነቅ እንዳልሆነ በኀይለ ቃል መናገራቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡


ለሊቃነ ጳጳሳቱ አቤቱታ ቀጥተኛ መልስ ያልሰጡት አቶ መረሳ ‹‹መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላም እንድትሆን ይሻል፤ በጉባኤዎቻችሁ በሐሳብ ተከራከሩ እንጂ አትበጣበጡ›› በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ለገጠማት መዝረክረክ ትኩረት በመስጠት ከኋላ ቀር አሠራር የምትወጣበትን መንገድ ሲኖዶሱ እንዲቀይስ አሳስበዋል፡፡ የመንግሥት የአስተዳደር እና ፍትሕ አካላት እንዲሁም በርካታ የብዙኀን መገናኛዎች በቤተ ክህነቱ ውስጥ በየደረጃው የሚፈጸሙ ክሦችን እና አቤቱታዎችን በማየት እና በማራገብ መጨናነቃቸውን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም የዘንድሮውን በአብዛኛው ቤተ ክህነቱ ተረቺ የሆነባቸውን የፍርድ ቤት ማኅደሮች ማገላበጥ እና ሚዲያዎቹ በተለያዩ ውዝግቦች ላይ የሰጧቸውን ሽፋን መለስ ብሎ ማየት ብቻ እንደሚበቃ አመልክተዋል፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ የተቋሟን ውስጣዊ አሠራር መሠረት አድርጎ እና እውነትን ተመርኮዞ የማያዳግም ውሳኔ እንዲሰጠው፣ ከዚህ አኳያ መጪውን የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ወሳኝነት በዛሬው ዕለት ከተጠናቀቀው የኢሕአዴግ ስምንተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ‹‹ወሳኝነት›› ጋራ ያነጻጸሩት አቶ መረሳ በአጠቃላይ ሥር ከመስደዱ የተነሣ ከቤተ ክህነቱ አልፎ ሕዝባዊ የሆነው ችግር ለአገር ልማትም ጠንቅ በመሆኑ የሲኖዶሱ አባላት ችግሩን ቁጭ ብለው በውይይት መፍታት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ የሲኖዶሱ አባላት ይህን ማድረግ ባልቻሉበት ሁኔታ ግን ‹‹አብረን ለመጓዝ ይቸግረናል›› በማለት ማስጠንቀቃቸው ታውቋል፡፡


እስከ አሁን በደረሰን መረጃ ከ28 የማያንሱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በተለያየ ዙር ተከፋፍለው መጠራታቸው ‹‹ለውይይት እንዲመች ነው›› የሚል ምላሽ የተሰጠበት ይኸው ስብሰባ ለጊዜው ለመሳተፍ ባልቻሉትና በየሀገረ ስብከታቸው የሚገኙት አባቶች ባሉበት ወደፊትም እንደሚቀጥል ተገልጧል፡፡ የውይይቱ አስፈላጊነት ዋና ጥንስስ የሚጀምረው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከ2002ቱ ምርጫ በኋላ ባካሄደው ግምገማ (በተለይ በአዲስ አበባ ያገኘው የምርጫ ውጤት) ምልከታዎች ጋራ በተያያዘ እንደ ሆነ አስተያየታቸውን የሰጡ ደጀ ሰላማውያን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በመነሣት መንግሥት ለዚህ የዝግ በር ውይይት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በፊት ጀምሮ መትጋት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ሊቃነ ጳጳሳቱ ቀደም ሲል ለመንግሥት ተወካዩ አቅርበዋቸው በነበሩት ምላሽ ሳያገኙ በቀሩት ጥያቄዎቻቸው ሳቢያ በአቶ መረሳ የማስፈጸም አቅም ላይ እምነት በማጣታቸው ወዲያውም ደግሞ የፍልሰታ መታሰቢያ ሱባኤ በመግባቱ እስከ ዓመቱ ማገባደጃ ድረስ ሊዘገይ እንደ ቻለ ተዘግቧል፡፡


አሁን ባለው የሁኔታዎች ግምገማ ፓትርያርኩ እና እርሳቸውን መጠለያ (safe heaven) ያደረጉ የማፊያ ቡድኖች (በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አገላለጽ “መንደርተኞች”) በቤተ ክህነቱ የውስጥ መዋቅር ተበራክተው ለወቅቱ የመንግሥት እና ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት (political theology) ጠንቅ እና ጦስ (liability) የሚሆኑበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዓባይ ፀሐየ አንሥቶ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በመመላለስ አቡነ ጳውሎስን እንዲመክሩ አስገድዷቸዋል፡፡ ይሁንና ለመንግሥት የወዳጅነት ምክር “ኦሆ” ባይ ከመሆን በቀር በተግባር ለመፈጸም የተሳናቸውን አቡነ ጳውሎስን ሰሞኑን በተያዘው መንገድ የሚቀራረቧቸውን እና የሚገዳደሯቸውን አባቶች ለያይቶ በመጥራት ተጽዕኖ ለመፍጠር አንድም ለመዋዕለ ሢመታቸው ፍጻሜ ሊሆኑ የሚችሉ የመጨረሻ ምልክቶችን በመስጠት አማራጭ የእርምት መንገዶች ማበጀት የተሻለ ሆኖ የተወሰደ እንደሚመስል ታዛቢዎች ይናገራሉ - የላላውን መወጠር፣ የጠጠረውን ማላላት፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)