September 15, 2010

የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ባለ ሥልጣን አቡነ ፋኑኤልን አስጠነቀቁ፤ ያሬድ አደመ ከማንኛውም የመድረክ አገልግሎት ታገደ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 15/2010፤ መስከረም 5/2003 ዓ.ም):- ነሐሴ 21 ቀን ማምሻውን በሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል፣ “ምእመናን ሁላችሁ በዚህ ጉባኤ ተሳተፉ፤ ባትሳተፉ. . . !” በሚል ማሳሰቢያ ተጀምሮ ከነሐሴ 22 - 23 ቀን 2002 ዓ.ም በሐዋሳ መስቀል አደባባይ ከተካሄደው የእነ በጋሻው ደሳለኝ ስብሰባ በኋላ ያሉት የሳምንቱ ዕለታት ለቡድኑ የተመቹ አይመስሉም፤ እንዲያውም “እኛ የፈቀድነው ካልሆነ በቀር የደቡብን ምድር የሚረግጣት ሰባኪ እና ዘማሪ አይኖርም” በሚል የነዟት ውርድ ወደ ራሳቸው መልሳ ያስተጋባችበት እና ክፉኛ የተቀለበሰችበት አሳፋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል። በአቡነ ፋኑኤል አገላለጽ “ጥንቃቄ የጎደለው” የቡድኑ ቀንደኛ መሪዎች ጠባይዕ በቀቢጸ ተስፋ ፈጦ እና ገጦ እየወጣ መመለሻ ወደሌለው አዘቅት ይዟቸው እየነጎደ ይመስላል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አንሥቶ በሐዋሳ ምእመናን ተወክለው በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና ሥራ አስኪያጅ የሚፈጸመውን አስተዳደራዊ በደል ለፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ለክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት አካላት በልዩ ልዩ መንገድ ሲያሰሙ የቆዩት የፍትሕ እና የልማት ኮሚቴ አባላት ተቃውሟቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ በሐዋሳ መስቀል አደባባይ ከተካሄደው ስብሰባ በፊት ሊቀ ጳጳሱ፣ የኮሚቴው አባላት በየትኛውም አጥቢያ እንዳይሰበሰቡ ለፖሊስ አመለክተዋል፤ የገዳሙ ጥበቃ አባላትም ለስብሰባ የሚመጡ የኮሚቴው አባላት ቢኖሩ እንዲደበድቡ ጥብቅ መመሪያ ከማውረዳቸውም በላይ ትእዛዙን የማይፈጽሙትን ጥበቃዎች ከሥራቸው እንደሚያባርሩ አስጠንቅቀዋል ተብሏል፡፡ በዚህ ሳቢያ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የክልሉ አስተዳደር ችግሩ በቤተ ክህነቱ የውስጥ አሠራር ካልተፈታ ለክልሉ ጸጥታ መጠበቅ ሲባል ጣልቃ ለመግባት እንደሚገደድ ቀደም ሲል በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ሊቀ ጳጳሱን፣ የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤን፣ በምእመናን የተወከሉትን የፍትሕ እና ልማት ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም በመስቀል አደባባይ “ጉባኤ” ያደረገውን ኮሚቴ በአንድነት እንዲቀርቡ ያዝዛል፡፡


የክልሉ አስተዳደር ሹም በተነሣው ውዝግብ ሳቢያ የክልሉ ሰላም እየደፈረሰ መረጋጋት ሊጠፋ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል በመጥቀስ፣ “ለዚህ ሁሉ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት እርስዎ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ነዎት፤ ለዚህም ማሳያው በምርጫው ሰሞን በሀገረ ስብከትዎ ሆነው ሕዝቡን በማረጋጋት ፈንታ በሕክምና ሰበብ ወደ አሜሪካ ሄደዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ድብቅ ተልእኮ እንዳለዎት ያሳያል. . .” እያሉ ስለ ሁኔታው በመግለጽ ላይ ሳሉ ያሬድ አደመ “አካሄድ፣ አካሄድ” በማለት እጁን ያወጣል፡፡ በሁኔታው ክፉኛ ያዘኑት የክልሉ ባለሥልጣን፣ “እንዲያውም ሕዝቡን ለሁከት በማነሣሣት እና ቡድን በማደራጀት ለሰላም መደፍረስ ግንባር ቀደም ሆነህ የምትንቀሳቀሰው አንተ ነህ፤ ከዚህ በኋላ በማንኛውም መድረክ ላይ ብትቆም ርምጃ እንወስዳለን” የሚል ቀጭን መመሪያም ይሰጣሉ፡፡ ሀገረ ስብከቱ በያሬድ አደመ ላይ ያለውን አቋም ለመንግሥት እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ሁሉ በአስቸኳይ በጽሑፍ እንዲያሳውቅ በማሳሰብ ውይይቱን ይቋጫሉ፡፡

ወዲያውም የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤ በቀድሞው ሕጋዊው የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ ዋሕድ ወልደ ሳሙኤል ምትክ ያለአግባብ በተሾሙት አስተዳዳሪ አማካይነት አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጦ ያሬድ አደመ ከእንግዲህ በገዳሙ ዐውደ ምሕረት ላይ እንዳይቆም መወሰናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለሀገረ ስብከቱ ይጽፋሉ፤ ሀገረ ስብከቱም የገዳሙን ደብዳቤ መነሻ በማድረግ “ላእከ ወንጌል” የሚል ማዕርግ የተለጠፈለት ያሬድ አደመ በማንኛውም የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት እና የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንዳይቆም በአስተዳደር ጉባኤ ተወያይቶ መወሰኑን በሊቀ ጳጳሱ ፊርማ የወጣውን ደብዳቤ ለግለሰቡ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በማብረር አሳውቋል፡፡

የእግዱ ደብዳቤ መውጣቱ እንደ ተሰማ እነበጋሻው ደሳለኝ ገስግሰው ሊቀ ጳጳሱ ፊት ይቀርባሉ፡፡ “ምነው ብፁዕ አባታችን፣ ያኔ ቃል ገብተውልን አልነበረም ወይ?” በማለት አቡኑ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ገብርኤል ጀርባ በሚገኘው ቪላቸው የተገባቡትን መሐላ ያዘክሯቸዋል፡፡ ያኔ - አቡነ ፋኑኤል በዚያ መኖርያቸው ውስጥ ከወራት በፊት የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን የፈጸመውን ዘማሪ ትዝታው ሳሙኤልን መልስ ጠርተው፣ “ልጆቼ፣ ደቡብ የእናንተ ነው፤ ማንም አይገባባችሁም፤ ያሻችሁን አድርጉ” በማለት ቃል ገብተወላቸው ኖሯል፡፡ “ቀን ሲደርስ ዐምባ ይፈርስ” እንዲሉ የገቡት ቃላቸው ሳያገብራቸው ቀኝ ኋላ የዞሩት አቡነ ፋኑኤል “ልጆቼ እስከማይገባኝ ድረስ ወርጄ አብሬያችሁ ቆምሁ፤ ወጣሁ ወረድሁ፤ ልጁም [ላእከ ወንጌል ያሬድ አደመ] አልጠነቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ቀድሞን ሄዷል፤ ሰዉም ታገለን፤ መንግሥትም ሁሉን ነገር ዐውቆታል፤. . . ከዚህ በኋላ ራሴን ለመጠበቅ ግድ ይለኛል፤ ከአሁን በኋላ ልረዳችሁ ስለማልችል በዚህ ጉዳይ አትምጡብኝ!!” ሲሉ ቁርጡን ይነግሯቸዋል፡፡

በብዙዎቹ የአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎች ውስጥ አንድ አገር ያወቀው ጥቅስ ይነበባል - “ሟች ከመሞቱ በፊት ይንቀዠቀዥ ነበር” የሚል፡፡ “ያሬድ አደመስ?“ ቢሉ ያሬድ አደመማ ከፈነጨበት ዐውደ ምሕረት እና የሕዝብ አደባባይ ወርዶ የመድረክ ሞት ከመሞቱ በፊት መላእክትን ተመስለው በትጋሃ ሌሊት (በሰዓታት እና በማሕሌት) ስብሐተ እግዚአብሔር የሚያደርሱትን፣ ማልደው ለኪዳን እና ከዚያም ለቅዳሴ የሚፋጠኑትን አበው ካህናትን ሲዘልፍ ነበር እንላለን፡፡ ሙሉ ቃሉም እንዲህ ይላል፤ የተሰማበት ስፍራም የሐዋሳ መስቀል አደባባይ ነው - “ምእመናን፣ እንደ ደከማችሁ ዐውቃለሁ፤ ይኹንና የእናንተ ድካም ሌሊት ሰዓታት እና ማሕሌት ቆመው አድረው ጠዋት ቀድሰው ወጥተው በነፍስም በሥጋም እንደማይጠቀሙት እና እንደማይጠቅሙት ካህናት አይደለም፤ እናንተ በነፍሳችሁ ትጠቀማለችሁና፡፡”
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)