September 15, 2010

መንግሥት ከፓትርያርኩ እና ከጳጳሳቱ ጋር ምሥጢራዊ ስብሰባ አካሄደ፣ ማሳሰቢያም ሰጠ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 15/2010፤ መስከረም 5/2003 ዓ.ም):-  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር እና በየደረጃው በሚገኙ አካላት በየጊዜው የሚፈጸሙ በደሎች እየተባባሱ ሕዝቡን በሚያስቆጡበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውንና ሕዝባዊ ቁጣው እየከፋ ሄዶ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ዕንቅፋት ከመሆኑ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በራሱ ውስጣዊ ተቋማዊ አሠራር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሻ፣ “መንግሥት በቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት  የሚገደደው ሲኖዶሱ በሙሉ ሥልጣኑ እና ኀይሉ    እየወሰነ ስለማይሠራ መሆኑን፤ አባቶች በተለይም ፓትርያርኩ የሚፈጽሟቸው ምእመኑን የሚያስቆጡ ተግባራት ውለው አድረው ለአገሪቱ ሰላም እና ልማት ዕንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ በአስቸኳይ ይቋጭ” ሲል መንግሥት ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር አቶ መረሳ ረዳ በተመራውና ከጳጉሜ 4 - 5 ቀን 2002 ዓ.ም እንዲሁም ዛሬ መስከረም አራት ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ቀጥሎ በዋለው ስብሰባ በተለያየ ዙር ተከፋፍለው የተጠሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ እንዲወያዩ ተደርጓል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተከፋፍለው በተጠሩት እና በሦስት የተለያዩ ዙሮች ለተሰበሰቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ እና የአገር ባለውለታ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ አካላት የሚፈጸሙ ግልጽ የወጡ ስሑት ተግባራት ሕዝቡን እያስከፉ፣ በዚህም ሳቢያ ከሕዝቡ ለመንግሥት የሚቀርቡት አቤቱታዎች እየበረቱ መምጣቸውን፣ እኒህም አቤቱታዎች ውለው ሲያድሩ ለአገሪቱ ዕድገት እና ልማት መሰናክል ለመሆን ከመቻላቸው አኳያ መንግሥትን እያሳሰበው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይም የፓትርያርኩን 18ኛ በዓለ ሢመት አከባበር ምክንያት በማድረግ የተተከለውን የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እና የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከቦታቸው አላግባብ መነሣትን ተከትሎ በሀገረ ስብከቱ ሙስና እና የሰብአዊ መብት ረገጣ መባባሱ እና ውዝግቡም እስከ አሁን ሁሉንም ያስማማ የተረጋገጠ መቋጫ ያላገኘ መሆኑን እንዲሁም በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ከምእመኑ ጋራ የሚፈጠሩ አስተዳደራዊ ውዝግቦችንና ውዝግቦቹ የሚወልዷቸውን ልዩነቶች የዘረዘሩት አቶ መረሳ፣ ሲኖዶሱ እና በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች በሙሉ ሥልጣናቸው እና አቅማቸው ተንቀሳቅሰው በቤተ ክህነቱ ውስጣዊ ተቋማዊ አሠራር መሠረት ለችግሩ አስቸኳይ እልባት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የማይበጁ ግለሰቦች በከፍተኛ አመራሩ ውስጥ ተሰግስገው አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ መሆናቸውን በመጥቀስ በተለይም ፓትርያርኩ ጥቅማቸውን የሚከላከሉላቸውንና ከጀርባቸው ያስጠለሏቸውን ግለሰቦች ማንነት እንዲያጠኑ እና እንዲያጠሩ ጥብቅ ማሳሰቢያ እንደሰጧቸው ተዘግቧል፡፡ በፓትርያርኩ አላስፈላጊ እና ቀኖናዊ ያልሆኑ ተግባራት የተነሣ አንዳንድ ወገኖች በመንግሥት ላይ የሚነዙት ጥላቻ መጠናከሩን በቅሬታ የተናገሩት አቶ መረሳ፣ “የሲኖዶስ ጉባኤ በመጣ ቁጥር መንግሥት መቸገር የለበትም፡፡ መንግሥት ጣልቃ ለመግባት የሚገደደው ሲኖዶሱ powerful ባለመሆኑ ነው፡፡ ሲኖዶሱ powerful መሆን አለበት፤ ሲኖዶሱ powerful ሆኖ በሚወስነው መንግሥትም ይተባበራል” በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚፈጸሙት ዝንፈቶች ላይ በሥልጣን ሊወያይ እና በሙሉ ኀይሉ በመወሰን እርምት ሊሰጥበትና፣ ይህንኑም በየአህጉረ ስብከቱ ተፈጻሚ በማድረግ የአገሪቱን ሰላም መጠበቅ እና ለልማቷም መትጋት እንደሚገባ በመንግሥት ስም ደጋግመው ማሳሰባቸው ተገልጧል፡፡

በየዙሩ ከተካሄዱት ስብሰባዎች በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከብፁዓን አባቶች ጋራ፣ “አባቶች፣ አንለያይ፤ አንድ እንሁን፤ ሰላም እናውርድ” የሚል የተማፅኖ ንግግር ማሰማታቸው ተመልክቷል፡፡ ይሁንና ተሰብሳቢዎቹ ውይይቱ ብፁዓን አባቶች ተለያይተው የተጠሩበት፣ አጀንዳውን በተመለከተም በቅዱስ ሲኖዱሱ ጸሐፊ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ቀድሞ ያልታወቀበት፣ በሹመት ዘመናቸው የባጁ እና ፓትርያርኩን ፊት ለፊት የመገሥጽ ጥብዓት ያላቸው አንጋፋ ሊቃነ ጳጳሳት የተገለሉበት፣ ጥቂቶቹ ጥሪ ቢደረግላቸውም ለመገኘት ፈቃደኛ ያልነበሩበትን መንሥኤ በመጥቀስ አቡነ ጳውሎስን ጠንክረው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ከዚህም ጋራ በተያያዘ የመንግሥት ተወካዩ የፓትርያርኩን ሐውልተ ስምዕ ነቅፈው ለመንግሥትም ሕዝባዊ ጥላቻ ማትረፉን መናገራቸው ድፍረት የጨመረላቸው የሚመስሉ አንዳንድ አባቶች፣ “ሕዝቡ እየተቆጣ ነው፤ ግፊቱ ከአቅምዎ በላይ ከነበረም ስለምን ከሲኖዶሱ ጋራ አልመከሩም፤ ነገሩ ምክክር ቢደረግበት ተገቢ አልነበረም ወይ?“ በማለት አቡነ ጳውሎስን ወቅሰዋል፤ ይህንኑ ወቀሳ ተከትሎም ፓትርያርኩ “ስለ ሐውልቱ እኔ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ነገሩን የተረዳሁት ከቦታው ተገኝቼ ተገልጦ ስመለከት ነው፡፡”  ሲሉ አስገራሚ ነገር ተናግረዋል። 

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ስድስት ቀን 2002 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ “ቤተ ክርስቲያኒቱ የቁልቁሊት እየሄደች ነው፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይከበር፤ ሥርዓተ አበው ይጠበቅ፤ ሙስና እና ቤተሰባዊ አስተዳደር ይወገድ ባልኩኝ ለአንድ ዓመት ጉዳዬ ውሳኔ ሳያገኝ ያለሥራ ተገልዬ መቀመጤ ግፍ አይደለም ወይ?“ በማለት የጠየቁት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የሐውልቱን ሥራ በግልጽ በመቃወም ቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ ላይ መሆኗን እና ከዚህም የተነሣ አባቶች ተባብረው ድምፃቸውን አለማሰማታቸው እንዳሳዘናቸው፣ እርሳቸው ግን ጥቅዐቱን (ውርደቱን) ለመመከት ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረው እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

በሰሞኑ ተከታታይ ዙር ውይይት በፓትርያርኩ ላይ ከፍተኛ መጨነቅ ይታይ እንደ ነበር የተናገሩት የስብሰባው ምንጮች፣ ምናልባትም ጳጳሳቱ በሹመት ዘመን፣ በዕድሜ እና ለፓትርያርኩ ካላቸው የድጋፍ እና የተቃውሞ ዝንባሌ አንጻር ተከፍለው በተለያዩ ዙሮች ለስብሰባው መጠራታቸው ሰላም ወዳድ በመምሰል እንዲህ ያሉትን ትንታግ ተቃውሞዎች ለመቀነስ አልያም ከወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስከፊ መዋቅራዊ ችግር አኳያ በመጪው ጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሊኖር እንደሚችል የተገመተውን የአባቶች አቋም ፈትሾ ለማዳከም እና ከወዲሁ በሐሳብ ለመለያየት ታስቦ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ከሚጠቅሷቸው በርካታ ማሳያዎች መካከል “ተቃውሞ ያስነሣሉ፤ ያሳድማሉ” በሚል ፓትርያርኩ ፊት በሚዛወሯቸው አባቶች ላይ ያላቸው የማይቀየር የሚመስል ስሜት እና ከዚህም ጋራ በተያያዘ ያደርጉታል ተብሎ የሚጠበቀው የሹመት ቦታዎች ለውጥ ነው፡፡ እንደ ምንጮቹ መረጃ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ የምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ እና የኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ከቦታቸው ሊነሡ ይችላሉ፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልም አላግባብ ከተነሡበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውጭ ወደ ሌላ ይዛወራሉ አልያም ከፓትርያርኩ እና ቤተሰቦቻቸው በተፈጠረባቸው ጫና ሳቢያ ለመሥራት እንዳልቻሉ ገልጸው በፈቃዳቸው ወደተዉት የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሐላፊነት ሥልጣን ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተለይም በሃይማኖታዊ አባትነታቸው በመንበረ ጵጵስናቸው ከሚመሯቸው ምእመናን ጋራ በቅርብ ተገኝተው በአንድነት በመሥራታቸው፣ ይልቁንም የወጣቶችን መንፈሳዊ መፍቀድ ተረድተው እና ተደራሽ ሆነው ለጥያቄዎቻቸው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠታቸው፣ በተለያዩ ማኅበራት ተደራጅተው የሚያገለግሉ ወራዙትን አገልግሎት በሚችሉት እየደገፉ - እገዛ በሚያስፈልጓቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ ችሎታው ያሏቸውን እያስተባበሩ የኖላዊነት ሐላፊነታቸውን በአጥጋቢ ሁኔታ በመወጣት ዘመኑን በመዋጀታቸው “የወጣቱ ጳጳስ” ተብለው የሚሞገሱት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከሰሜን አሜሪካው የዋሽንግተን እና አካባቢው ሊቀ ጵጵስና ሐላፊነታቸው ለማዛወር መታሰቡ ወቅቱን ያልጠበቀና ምናልባትም በቤተ ክህነቱ የአገር ውስጥ እና የውጭ መዋቅሮች የተሰገሰጉ ጥቅመኞችን ፍላጎት ለማስጠበቅ የታለመ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮቹ ያስረዳሉ፡፡ ብፁዕነታቸው ባለፈው ዓመት የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር ለማሻሻል እና የፓትርያርኩን ሥልጣን ለመገደብ የተደረገውን ጥረት ለማኮላሸት በብፁዓን አባቶች ላይ የተፈጸመውን አፈና እና ድብደባ ከብፁዕ አቡነ ማቲያስ ጋራ በብዙኀን መገናኛ ቀርበው በቃል እና በጽሑፍ በማውገዝ ግልጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ ዐቢይ ቀኖናዊ ግድፈት መሆኑን በጉባኤ አስተምረዋል፤ በመንበረ ጵጵስናቸው በሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንም ለቀናዒ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሚመች፣ ለይሁዳዊ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች መቅሠፍት ወተግሣጽ የሆነ የአገልግሎት ድባብ ፈጥረዋል፡፡

የመንግሥት ተወካዩ ፓትርያርኩን ጨምሮ ከብፁዓን አባቶች ጋራ እንዳደረጉት ውይይት ሁሉ ከተለያዩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ልዩ ልዩ የመምሪያ ሐላፊዎች ጋራ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ በግሎባል ሆቴል በተካሄደ ስብሰባ በዝግ መምከራቸው ተሰምቷል፡፡ ስብሰባውን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያልተቻለ ቢሆንም ትኩረቱ መንግሥት ለውይይት ከዘረጋው የዕድገት እና ለውጥ ዕቅድ ተፈጻሚነት ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚጠበቅባትን ሚና እና በያዝነው መስከረም ወር መጨረሻ ከሚካሄደው ኢሕአዴግ መራሹ የመንግሥት ምሥረታ ጋራ ተያይዞ አንዳችም የጸጥታ ችግር እንዳይኖር “ምእመኑን በመምከር እና ሕዝቡን የሚያስቆጡ የውስጥ አስተዳደራዊ በደሎችን በመከላከል” ተሰብሳቢዎቹ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ መሰጠቱ ተመልክቷል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)