September 14, 2010

መንግሥት “በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም” ተባለ እንጂ ሃይማኖት ላይ ወንጀል ሲፈጸም ዝም ይላል ተባለ እንዴ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 14/2010፤ መስከረም 4/2003 ዓ.ም):- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን “ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነጻ ወጣች” ከተባለ አሥርት ዓመታት እየተቆጠረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ የመንግሥትን ሕጋዊ ከለላ ያጣች ከመሰለችበት ደረጃ ደርሳለች። በዚህች መጦመሪያ መድረካችን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ዓይን ያወጡ ወንጀሎችን ብናትትም፣ ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች የእኛን ጩኸት እየጮኹ ቢገኙም፣ ምእመናንንም አቤቱታተቸውን ቢያሰሙም መንግሥት እና የዜጎች መብት ማስከበሪያ ማሽኑ ሊሰማ አልቻለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ የቤተ ክርስቲያን ባልሆኑ ሰዎች ስትመዘበር እና ስትበረበር፣ ሕግ ሲፈርስ እና አገራዊ ሞራልና ስብዕና ሲናድ መንግሥት ዳር ቆሞ እየተመለከተ ነው ወይም “አበጃችሁ” ባይ ሆኗል።
ከነዚህ መዝባሪዎችና ቀንደኛ ሙሰኞች መካከል ደግሞ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የተባሉ ሴት ዋነኛዋ ናቸው። ሴትዮዋ ከገንዘብ ምዝበራው ባለፈ ብፁዓን አበውን እና ሌሎች አበው መነኮሳትንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በጉልበትና በስድብ ሳይቀር የሚያዋርዱ (ሐራስ የሚያደርጉ) መሆናቸውን በቅጡ የምናውቅ ቢሆንም ሰሞኑን የተከሰተ አንድ ገጠመኝ ደግሞ ጥሩ ማሳያ እማኝ ሆኖ አገኘነው። ይህም ሴትዬይቱ የለመዱትን አበውን የማስፈራራትና የማዋረድ ልማዳቸውን በዲ/ን ዳንኤል ክብረትም ላይ መድገማቸው ነው። ነገሩ እንዲህ ነው።በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ ወይም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር በሕግ የታወቀ እና የተረጋገጠ ተግባር እና ሐላፊነት ሳይኖራቸው ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ በፈጠሩት ልዩ ወዳጅነት እና በየስፍራው ባደራጁት የማፊያ ቡድን አማካይነት ‹‹የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን አስተዳደር አየር በአየር እንደሚመሩ›› የሚነገርላቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ‹‹እጅጋየሁ ኤልዛቤል ናት እያልህ በደጀ ሰላም ላይ ስሜን የምታጠፋው አንተ ነህ፡፡. . . ልንገርህ፣ አንተ ከእኔ ዕድሜ አትደርስም!! ስሜን የሚያጠፉ ደግሞ መጨረሻቸው ወኅኒ እንደ ሆነ ታውቃለህ›› በማለት ለማስፈራራት እና ለማስጠንቀቅ መሞከራቸው ተሰማ፡፡

ትናንት ሰኞ ረፋድ ላይ ዲያቆን ዳንኤል ልዩ ስሙ ጉርድ ሾላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ቢሎስ ኬክ ቤት በረንዳ ላይ ተቀምጦ የቀጠረውን ጓደኛውን በመጠበቅ ላይ ነበር፡፡ ሰዓቱን ለማዳረስ በእጁ የያዘውን የባርባራ ፓዝፐር፣ “THE POWER OF POSITIVE CONFRONTATION: How to handle Confrontations at home, at work place and in Life” መጽሐፍ ያገላብጣል፡፡ በጠቋሚ እንደተመሩ በተገመተ አኳኋን ከኬክ ቤቱ ውስጥ ወጥተው የመጡት ወይዘሮ እጅጋየሁ፣ ‹‹ዳንኤል ክብረት የምትባለው አንተ ነህ ወይ?›› በማለት ጥያቄ ይጀምራሉ፡፡ ተጠያቂውም ‹‹አዎ፣ እርስዎን ማን ልበል?›› ይላል፡፡ ‹‹ለምንድን ነው እጅጋየሁ ኤልዛቤል ናት እያልህ በደጀ ሰላም ላይ ስሜን የምታጠፋው?›› በማለት የመጡበትን ጉዳይ በቀጥታ መጠየቅ ይጀምራሉ፡፡ ዲ.ን ዳንኤልም፣ ‹‹ሲጀመር በደጀ ሰላም ላይ የምጽፈው እኔ አይደለሁም፤ እኔ የራሴን እይታዎች የምገልጽበት ቦታ አለኝ፡፡ በሌላ በኩል ኤልዛቤል ማን ናት ብዬ በራሴ መድረክ የጻፍሁት በዮሐንስ ራእይ ላይ የተገለጸውን መሠረት በማድረግ እንጂ እጅጋየሁ ናት ወይም ዓለማየሁ ነው በሚል አይደለም - ያለዎት መረጃ የተሳሳተ ነው›› በማለት ይመልስላቸዋል፡፡

በአቋማቸው ፍርጥም ያሉት ወይዘሮዋም፣ ‹‹ለመሆኑ እናት የለህም? እኔ በዕድሜ አልበልጥህም? ልንገርህ! አንተ ከእኔ አትደርስም፤ ስሜን በማጥፋት የምትቀጥል ከሆነ ደግሞ ስሜን ያጠፉ መጨረሻቸው ወኅኒ እንደ ሆነ ታወቃለህ›› በማለት ለማስጠንቀቅ እና ለማስፈራራት ይሞክራሉ፡፡ ትዕግሥቱ የተሟጠጠ የሚመስለው ዲያቆን ዳንኤልም፣ ‹‹እንግዲህ በዕድሜም እኔ አልፌዎት ይሆናል፤ ስሜ ጠፍቷል ካሉ በሕግ መጠየቅ ይችላሉ፤ ወደ ወኅኒ የሚወርደውንም ሕግ ይለየዋል፡፡ ይሄ ግን ቦታው ስላልሆነ የማያውቁትን ሰው ከዚህ በላይ እንዲናገሩ አልፈቅድልዎትም›› በማለት ይቃወማቸዋል፡፡ ጠንካራ መከላከል የገጠማቸው ወይዘሮዋም ፊታቸውን አዙረው ወደ መጡበት ይመለሳሉ፤ ዲያቆን ዳንኤልም ምንም እንዳልተፈጠረ ያህል ወደ ንባቡ ያተኩራል - “THE POWER OF POSITIVE CONFRONTATION”.

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ላይ እይታውን የሚያካፍልበት፣ በተለያዩ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ማኅበራዊ ሒስ የሚያቀርብበት በርካቶች የሚከታተሉት መጦመሪያ (http://www.danielkibret.com) መድረክ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ‹‹ኤልዛቤል›› በቅዱስ መጽሐፍ የብሉይ ኪዳን ክፍል የንጉሠ እስራኤል አክአብ ሚስት፣ ንጉሡ ጣዖት እንዲያመልክ፣ በእስራኤል አምልኮ ባዕድ እንዲስፋፋ ያደረገች፣ ነብየ እግዚአብሔር ኤልያስን ያሳደደች፣ ካህናተ በኣልን እና ነበያትን በበተ መንግሥቱ አስቀምጣ የመገበች፣ ‹‹ርስቴን አልሸጥም›› ያለውን የዋህ ሰው ናቡቴን በግፍ አስገድላ የወይን እርሻውን የቀማች በዚህም በከፋ ሁኔታ ተገድላ የከፋ አሟሟት የሞተች፣ አስከሬኗ ያልተገኘ እና ተከታዮቿም በሰይፍ ማለቃቸው ይታወቃል(1ኛ ነገሥ. 21÷ 1-19፤ 2ኛ ነገሥ. 9÷ 30 - 37፤ 10÷ 1 -11)፡፡ በዮሐንስ ራእይ እንደተገለጸው ደግሞ የትያጥሮኗ ኤልዛቤል ክርስቲያን መስላ ገብታ ጳጳሱን ያሳሳተች፣ አምልኮ ጣዖትን እና ዝሙትን ያስፋፋች፣ በዚህም በርካታ ክርስቲያኖችን ያሰናከለች፣ የንስሐ ዕድል ቢሰጣትም በምግባረ ብልሹነቷ የጸናች፣ ባለጸጋ፣ ኀይለኛ እና ዘረኛ እንደነበረች፣ በዚህ ድርጊቷም በቸልታ የሚያያት ጳጳስ ተግሣጽ እንዳገኘው፣ እርሷም ተከታዮቿም ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገልጧል፡፡

ያሰቡትን ሳይፈጽሙ እና የተቃወሟቸውን ልክ ሳያስገቡ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ ገመናቸው እና ኀጢአታቸው ከተጋለጠ በኋላ ጽሑፉን አዘጋጅቷል ያሉትን ‹ሊቀ ትጉሃን› ዘሪሁን ሙላቱን ወደ ቃሊቲ ወኅኒ ቤት ወርዶ ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን እንዲጠብቅ ቢያስደርጉም እፎይ ብለው አልተቀመጡም፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ተባባሪነት የገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎችን እና ጸሐፊዎችን በሀገረ ስብከቱ በመጥራት ‹‹ዘሪሁን ሙላቱን ለማስወገዝ ድጋፍ ለማሰባሰብ›› ቢጥሩም፣ ‹‹ለምን ዛሬ? ከዚህ ቀደም ክርስቶስ ሲሰደብ፣ ቤተ ክርስቲያን ስትነቀፍ፣ ብፁዓን አባቶች ሲዘለፉ የት ነበርን? በተባለው መጽሐፍ የተዘለፉት ግለሰቦች እንጂ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም›› የሚሉ ተቃውሞዎች በመበርከታቸው ሳቢያ የፈለጉት ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

ዋነኛው ጉዳያችን አንዲት ወይዘሮ በዲያቆኑ ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ መፈጸማቸው አይደለም። ይህንን ጉዳይ ለማሳሰብና ለመዘገብ ወይንም በሕግ አግባብ መፍትሔ ለመፈለግ ራሱ ዲ/ን ዳንኤል የሚያንስ ሰው አይደለም። እኛ የፈለግነው ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንዳለው “በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ በደረቀስ እንዴት ይሆን?”  (ሉቃ. 23፣31) ለማለት ነው። ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም ገንዘብና ወርሃዊ መተዳደሪያ የማያገኝ አንድ ግለሰብ ላይ እንዲህ በድፍረት እና በይፋ ያውም በአደባባይ ማስፈራሪያ ለማድረስ የማይፈሩ ሴት ቤተ ክርስቲያንን መጠገቢ አድርገው በሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይማ እንዴት ያደርጉ ይሆን ማለት ነው?
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)