September 10, 2010

ዘሪሁን ሙላቱ ወደ ቃሊቲ ወኅኒ ቤት ወረደ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 10/2010፤ ጳጉሜን 5/2002 ዓ.ም):- የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘሪሁን ሙላቱ የግል ተበዳዮች ነን ባሉት በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የቀረቡበትን የሰው ምስክሮች እንዲከላከል በመወሰን ጉዳዩን ለመመልከት ለመስከረም 14 ቀን 2003 ዓ.ም ቀጠረ፡፡ እስከዚያው ድረስ ተጠርጣሪው ማረፊያ እና ምግብ ወደሚያገኝበት ወደ ቃሊቲ ወኅኒ ቤት ተዛውሮ እንዲቆይ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
ዘሪሁን ሙላቱ ለፍርድ ቤቱ፣ “በተከሰስሁበት ጉዳይ አንዳችም ማስረጃ አልቀረበም፤ መንግሥትም ጉዳዩን በውል የሚያውቀው አይመስለኝም፤ የመከላከያ ምስክሮቼን ለማቅረብ ከጎኔ የሚቆምልኝ ሰው የለኝም፤ እኔን ለመጠየቅ ወዳለሁበት ፖሊስ ጣቢያ የሚመጡትን ዘመዶቼን እና ጓደኞቼን መታወቂያቸውን እየተቀበሉ ፎቶ ኮፒ በማድረግ እና አድራሻቸውን በመመዝገብ እያስደነበሯቸው ነው” በማለት ቢያስረዳም ዳኛው መልሰው “ቃሊቲ ሊጠይቁህ የሚመጡ ሰዎችን ስም ዝርዝርም አስቀደምህ አስታውቅ” እንዳሉት ተሰምቷል፡፡ በዚህ መሠረት ተጠርጣሪው ከመጪው ሳምንት የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ማክሰኞ በኋላ እስከ አሁን ከቆየበት ከአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሚዘዋወር ተነግሯል፡፡

ከትናንት በስቲያ ጠዋት የዋስ መብቱ ተጠብቆ እንዲለቀቅ በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በተወሰነለት መሠረት የተጠየቀውን የ2500 ብር ዋስትና ከፍሎ ከሚወጣበት የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በር ላይ በሌላ የፖሊስ ኀይል የተያዘው ዘሪሁን በፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ ተቆጥረው የመሰከሩበት ዲያቆን ዳንኤል ገብረ ሥላሴ፣ መምህር መሐሪ አድማሱ፣ በጋሻው ደሳለኝ እና ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ ናቸው፡፡ ዲያቆን ዳንኤል “ዘሪሁን ሙላቱ ‘የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች’ መጽሐፍን ዲዛይን ሲያሠራ ተመልክቻለሁ›› ብሎ ሲመሰክር መምህር መሐሪ አድማሱ ደግሞ የመጽሐፉ ረቂቅ በዘሪሁን እጅ ተሰጥቶት ለወ/ሮ እጅጋየሁ ማድረሱን እና ለአምስት ሆነው እንዳነበቡት ተናግሯል፡፡ በጋሻው ደሳለኝ በበኩሉ “ዘሪሁን፣ ገንዘብ ስጠኝ፤ አለበለዚያ እጽፍብሃለሁ” በማለት እንደዛተበት ሲናገር ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ ደግሞ ዘሪሁን መጽሐፉን የማሳተሚያ ብር እንዲሰጠው እንደጠየቀው ለችሎቱ እንዳስረዳ ተዘግቧል፡፡

በዚሁ ዕለት የፍርድ ቤቱ ውሎ በኋላ በችሎቱ የነበሩት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና በጋሻው ደሳለኝ “እዚያው እስር ቤት የሚቆይበትን መንገድ እንቅልፍ አጥተን እንደምንም ብለን መፈለግ አለብን፤ ይህ ሰውዬ [ዘሪሁን] በዋስ ከወጣ ከሕዝብም ከመንግሥትም ያጣላናል፤ ከተለቀቀ ያጠፋናል፤ እርሱ እንደው ሕግ አይፈራ!” ሲሉ መደመጣቸው ተመልክቷል፡፡ ይህን ስምምነታቸውን በሚያረጋግጥ አኳኋን ሦስቱ “የግል ተበዳይ ነን” ባዮች ለግለሰባዊ ጉዳያቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን መኪና እና ነዳጅ አላግባብ በመጠቀም እና በማባከን ላይ እንዳሉ ብዙዎች በምሬት ይናገራሉ፡፡ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች እንደሚያስረዱት፣ በተለይም ወይዘሮዋ ዘሪሁን ሙላቱን በወኅኒ ቤት ለማሰንበት በሙሉ ጊዜያቸውን እና አቅማቸው የፈጸሙት ድርጊት ‹‹ገንዘብ ሲናገር ፍትሕ ዝም ይላል›› የሚለውን ብሂል ያስታውሰናል ይላሉ፡፡ ለምስክርነት እና ጉዳዩን ለመመልከት ለ‹‹ጉባኤ›› በሚል ከሄደበት ድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በየቀኑ (እስከ አሁን ድረስ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ተመላልሷል) በአውሮፕላን የደርሶ መልስ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኘው የበጋሻው ደሳለኝ ወጪም ከየት በመሸፈን ላይ እንዳለ ለብዙዎች አጠያያቂ ሆኗል፡፡

የድሬዳዋ ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደሚያስረዱት በጋሻው ደሳለኝ በድሬዳዋ ሰፈረ ገነት ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ገዳም በጠራው ጉባኤ ማንነቱን ዕርቃን በሚያወጣ አኳኋን በካህናት ላይ መረን የለቀቀ ዘለፋ በመናገሩ ካህናት እና ምእመናን በአንድነት ሁኔታውን ለፖሊስ እና ለዐቃቤ ሕግ ማመልከታቸውን፣ የፍትሕ አካሉም ጉዳዩን በማጤን ላይ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ግለሰቡ ሳይገባው በቆመበት ዐውደ ምሕረት ሲያሰማው ያመሸው ዲስኩር፣ ‹‹ቅዳሴው ቢያልቅበት  ቀረርቶ ሞላበት” ይሉት ዓይነት እንደ ነበር በሥፍራው የተገኙ የዐይን ምስክሮች ለደጀ ሰላም አስረድተዋል፡፡

ትናንት ጠዋት ሰፕቴምበር 9/2010፤ ጳጉሜን 4/2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከነበረው የፍርድ ቤት ውሎ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ድሬዳዋ በአየር ተጓጉዞ የተመለሰው በጋሻው በጥቂት ተባባሪዎቹ አማካይነት ምእመናን በሠርኩ ‹ጉባኤ› ላይ እንዲገኙ በከተማው ሲቀሰቅስ ቢውልም የጠበቀውን ያህል ታዳሚ እንዳልመጣለት ተዘግቧል፡፡ በሁኔታው በመበሳጨትም፣ “ፓትርያርኩ በጥብቅ ስለሚፈልጉኝ  ወደ አዲስ'ባ መመለሴ ነው” የሚል ከሀፍረት የመውጫ ሰበብ በተደጋጋሚ በዐውደ ምሕረቱ በመናገር እና በማስነገር ትዝብት አትርፏል፡፡ በጋሻው በከተማው ባካሄደው ቅስቅሳ ጉባኤው ዛሬ እንደሚቀጥል የተነገረ ቢሆንም ትናንት ማምሻውን ከገዳሙ ወጪ ሆኖ በተከፈለ 1500.00 ከሌሎች ሁለት ግለሰቦች ጋራ በሚኒባስ ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ታውቋል፡፡ ገዳሙን ለከፍተኛ ወጪ የዳረገውን ይህንኑ ያልተሳካ ‹‹ጉባኤ›› እንዲካሄድ ትእዛዝ የሰጡት ከፓትርያርኩ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በተላለፈው መመሪያ መሠረት እንጂ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጥሪ እንዳልሆነ ለደጀ ሰላም የደረሰው የማረሚያ አስተያየት ይጠቁማል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)