September 9, 2010

ሁለቱ ማኅበራት:- "የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር" እና "የአገልጋዮች ኅብረት"

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 9/2010፤ ጳጉሜን 4/2002 ዓ.ም):- ነሐሴ 23 ቀን 2002 ዓ.ም ‹‹የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር›› ከኮሌጁ ደቀ መዛሙርት እና ከኮሌጁ አስተዳደር ጋራ በመተባበር ሲደክሙበት የቆዩትን የስብከተ ወንጌል ጉባኤ እንዲሁም በጥሬው እና በቃል ኪዳን ከመቶ ሺሕ ብር በላይ የተገኘበት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በማካሄድ የተግባር አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡
በኮሌጁ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የኮሌጁን የመማሪያ ክፍሎች ለማስፋፋት፣ ከአገልግሎት ብዛት ከጥቅም ውጭ የሆኑትን የደቀ መዛሙርት መገልገያ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች እና ኋይት ቦርዶች በአዲስ ለመተካት፣ የቤተ መጻሕፍቱን የውስጥ ቁሳቁሶች ለማሟላት፣ ተቋሙን የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የ12 ኮምፒዩተሮች ግዥ ለማካሄድ ታቅዶ የተደረገ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ሳይታሰብ በድንገት ከአራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ማሰብ የስጦታ መጀመሪያ ነው፤ ብዙዎች ከዚህ ቤት ወጥተዋል፤ ለቤቱ በማሰብ ደረጃ የምናያቸው ልጆቻችን ግን እኒህ በፊታችን የምናያቸው ናቸው፤›› በማለት 50‚000 ብር እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል፡፡ በማቴሪያል ደረጃ 210 ያህል ወንበሮችን በግዥ ለማበርከት፣ 10‚000 ብር በጥሬ ለማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን 30‚000 ብር የቃል ኪዳን ሰነድ በማስሞላት፣ 60‚000 ብር ያህል ደግሞ ከትኬት ሽያጭ ለማግኘት መቻሉ በፕሮግራሙ ላይ ተገልጧል፡፡ መርሐ ግብሩ በመምህር ውድነህ የኔ ዓለም እና በመምህር ታዴዎስ ግርማ የተመራ ሲሆን መምህር ዳንኤል ግርማ የዕለቱን ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ደጆሽ አይዘጉ›› ማኅበር፣ ‹‹ማኅበረ ወይንዬ››፣ ‹‹ማኅበረ ጽዮን ዘግሸን ማርያም የጉዞ ማኅበር››፣ ‹‹ማኅበረ ጻድቁ አቡነ ሐራ››፣ ‹‹ኢያቄም ወሐና የጉዞ ማኅበር›› በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር በጥር ወር 2002 ዓ.ም በቤንሻጉል ጉምዝ ክልል /አሶሳ/ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ በተገኙበት ከ4000 ያላነሱ ወገኖችን በኦርቶዶካሳዊት ተዋሕዶ እምነት አስተምሮ በማስጠመቅ፣ 30 የአካባቢውን ተወላጆች ለሦስት ወራት ያህል ወጪያቸውን ችሎ በማሠልጠን እና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት በማስመረቅ ተመልሰው በቋንቋቸው ወገኖቻቸውን እንዲያስተምሩ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡

ይሁንና አንዳንድ ስም ያወጡ ሰባክያን ይህን የማኅበሩን (‹‹የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር››) ጥረትና ያስጠመቃቸውን ኢ-አማንያን ቁጥር የራሳቸው በማስመሰል ባቀነባበሩት የቪዲዮ ፊልም በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲ.ሲ ያሰባሰቡትን ከ43‚000 ዶላር በላይ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን አጥብቀው እንደሚቃወሙ አስተያየታቸውን ለደጀ ሰላም የሰጡ የማኅበሩ አባላት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ተግባር የሚኮንኑት አንድ ሰባኪ በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚገኙ የጥቅም አጋሮቹ ጋራ በማበር ለሌላው ወንድሙ ለገጠር አብያተ ክርስቲያን መርጃ እያለ በሚሰበስበው ብር የጉዞ ወኪል ድርጅት በመክፈት እና ሦስት ኤክስካቫተር ተሸከርካሪዎችን ገዝቶ እንዲያከራይ በማድረግ ማበልጸጉ ሳያንስ በቅርቡ ራሱ ኮድ 3 - መለያ ቁጥሩ ? ? ? ? (ለጊዜው መግለጽ አልፈቀድንም) - አ.አ የሆነ ላንድ ክሩዘር ፒክ አፕ መኪና ባለቤት ለመሆን መቻሉን በምሬት ገልጸው ምእመኑ እንዲህ ካሉት እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል፡፡ የማኅበሩ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤ በየዓመቱ በጥቅምት ወር በመንበረ ፓትርያርኩ ከሚደረገው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማግሥት ተያይዞ ይካሄዳል፡፡

በአንጻሩ ‹‹የአገልጋዮች ኅብረት›› በመባል የሚታወቀው እና ሰባክያነ ወንጌልን እንዲሁም ዘማርያንን ያሰባሰበው አካል በዘገየው የማኅበሩ ዕውቅና የማግኘት እና ለአባላቱ የመታወቂያ ወረቀት በመስጠት ጉዳይ ለመምከር ተሰብስቦ ያለአንዳች ስምምነት የተጠናቀቀ ቢሆንም በአገልጋዮች ላይና በአገልጋዮች መካከል የሚታዩትን ጉልሕ ችግሮች (እንከኖች) በራሳቸው በአገልጋዮቹ ታምኖበት በገዛ አንደበታቸው ፊት ለፊት እንዲወጣ ከማድረግ አኳያ ጠቃሚ ሊባል የሚችል አስተዋጽዖ ያበረከተ ነበር፡፡

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተካሄደው ይኸው ስብሰባ በማኅበሩ ሰብሳቢ በመምህር ፋንታ ገላው የተመራ ሲሆን በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም ደሳለኝ የተገኙበት ነበር፡፡ በዘማሪ ብዙዓየሁ ተመስገን የቀረበው ሪፖርት ማኅበሩ ባለፈው ዓመት ‹‹በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት›› ከአባላቱ ጋራ የነበረው ግንኙነት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን ያስረዳል፡፡ የማኅበሩ ሰብሳቢ የዕለቱ አጀንዳ ‹‹በስብስቡ ዕውቅና የማግኘት ጉዳይ›› ላይ አባላት አስተያየት እንዲሰጡበት መሆኑን ካስተዋወቁ በኋላ ግን በቤቱ የተቃውሞ እና የምሬት አስተያየቶች ተስተናግደውበታል፡፡

በዕለቱ ከተሰጡት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ሊቀ ዘማርያን ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ፦
‹‹ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣው፣
 አንድ እምነት ነው፣
 ጽኑ ሃይማኖት ነው›› ብለው በመዘመር አስተያየት ለመስጠት ወደ መድረክ የወጡት ሊቀ ዘማርያን ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ የሚከተለውን በእንባ የታጀበ አጭር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በሥጋ አመንዝራነት ሁላችንም ወድቀን ይሆናል፤ የሃይማኖት አመንዝራነት በመካከላችን ሲታይ ግን በጣም ያሳዝናል›› በማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ስልት እየጎላ የመጣው መናፍቅነት እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል፡፡

ዘማሪ ዘውዱ ጌታቸው፦ ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቷ ራሷ በመዋቅሩ መሠረት እየሠራች በሌለበት ሁኔታ ዕውቅና ቢገኝ ባይገኝ ጥቅሙ ምንድን ነው?›› በማለት የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ አሠራር በግለሰቦች የዘፈቀደ አሠራር እንደተጠለፈ እና አገልጋዮችም መዋቅሩን ጠብቀው እንደማያገልግሉ ተችተዋል፡፡ አያይዘውም መዋቅሩ በዚህ ሁኔታ በሚገኝበት ደረጃ የአገልግሎት መታወቂያ ይሰጠን መባሉን ሲነቅፉ፣ ‹‹መታወቂያ ምን ይሠራልናል? የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆንነው እና ያልሆንነው ባልተለየንበት ሰዓት መታወቂያውን ሌላ ሥራ ልንሠራበት ነው ወይ?› በማለት ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል፡፡

መምህር ዘመድኩን በቀለ፦ ማኅበሩ መሰብሰብ ከጀመረ ጥቂት ጊዜው እንደሆነ ያወሱት መምህር ዘመድኩን ከ‹‹የአገልጋዮች ማኅበር›› የማኅበሩ አባላት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለእያንዳንዳቸው ከ50‚000 - 60‚000 ብር አውጥታ የምታስተምራቸው ደቀ መዛሙርት ሆነው ሳለ የዕውቅናው ጉዳይ እስከ አሁን ስለምን ሳይገኝ እንደቆየ ጠይቀዋል፡፡ በምትኩ በማፊያው ቡድን የሚመራውን እና ራሱን ‹‹የቅድስት ማርያም የስብከተ ወንጌል ማኅበር›› እያለ የሚጠራው አካል ከስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዕውቅና አግኝቷል በመባሉ የተገረሙት አስተያየት ሰጪው ‹‹ዕውቅና ለማግኘት ብዙ ብር ያስፈልጋል›› በማለት በተሣልቆ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹ላለመሞት የሚንፈራገጠው ይህን ስብስብ አደንቀዋለሁ›› ካሉ በኋላ ወደ ቤቱ መለስ ብለው ‹‹እኔን የበለጠ የሚያስጨነቀኝ ዕውቅና የማግኘት ጉዳይ ሳይሆን የውስጥ አንድነታችን ሁኔታ ነው፤ ለመሆኑ እኛ ራሳችን አንድ ነን ወይ? “የደቡብ ልጆች”፣ የእገሌ ልጆች እየተባባልን አልተለያየንም ወይ? ለሴሚናር እና ለስብሰባ ሲሆን ምስኪኑ አገልጋይ ይጠራል፤ ዱባይ እና ደቡብ አፍሪካ ሲሆን ግን ታዋቂዎቹ እና ሀብታሞቹ ይሄዳሉ. . . ›› በማለት ንግግራቸውን ሳይጨርሱ መነጋገርያውን መልሰው ተቀምጠዋል፡፡


ባሕታዊ ሶፎንያስ ‹‹በውስጣችን ብዙ ነገር አለ፤ እንዳንናገር ግን ፍርሃት አለብን›› በማለት በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በኩል ብልሹ ምግባርን እና አሠራርን ከማጋለጥ አኳያ በአገልጋዩ ላይ የሚታየውን ስጋት ገልጸዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዝሙር የሆነችው ዘማሪት መሠረት ማሞ በበኩሏ ‹‹ከዚህ ስብስብ በኋላ የተነሡ ማኅበራት ዕውቅና ሲያገኙ ይህ ማኅበር እንዴት ዕውቅና አላገኘም?›› በማለት ጥያቄ አቅርባለች፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም፣ በቦታው ላይ ከተመደቡ አንድ ዓመት እንዳልሞላቸው ገልጸው፣ ‹‹ይሁንና እኔ እስከማውቀው በእኛ መምሪያ እውቅና የተሰጠው ማኅበር የለም›› በማለት ለአንድ ቡድን ተሰጥቷል ተብሎ የተወራውን ዕውቅና አስተባብለዋል፡፡ ስብሰባው በቀጣይ በሚተላለፈው ጥሪ መሠረት ለመገናኘት ቀነ ቀጠሮ በመስጠት ያለውጤት ተጠናቅቋል፡፡

6 comments:

Unknown said...

Melkam hibret new beteley Likemezemiran Kinetibeb yanesut hasab libin yemineka ena weqitawi bemehonu Endih aynet abatochin endi tebikilin huletunim mahiberat bebetu endiakoylin yemebetachin amalajinet ayleyen.please keep sending such an important points as imidiat as possible/as what u are doing/

Anonymous said...

እንደው በኼድንበት በተሰበሰብንበት ሁሉ ይኼ የመለያየት ጭቅጭቅ አያጣንም ማለት ነው፡፡

ይህ ማኅበርም ሆነ ሌሎቹ ማኅበራት ውጤታማ እንዲሆኑ ካስፈለገ መጀመሪያ በቤተክርስቲያኗ ከላይ እስከታች የሰፈነው በዘር፣ በጎጥ፣ በጥቅማጥቅም፣ ወዘተ. ላይ የተመሠረተ መለያየት ሊወገድ ይገባል፡፡

ለዚህም ማዶ ለማዶ ሆነው የሚወጋገዙት አባቶች መጀመሪያ አርአያውን ማሳየት አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ልፋታችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የሚሆንብን ይመስለኛል፡፡ "አጥፍተኃል ይቅርታ ጠይቅ!" ሳይሆን "አጥፍቻለሁ ማረኝ!" ብሎ እግር ላይ መውደቅን ያሳዩንና እስኪ ከልባችን ሆነን "በእንተ ብጹዕ" ለማለት ያብቁን፡፡

ኦ አባ ቅዱስ ዕቀቦሙ በስምከ ወበኃይልከ ዕቀቦሙ
ከመ ይኩኑ አሐደ ብነ ከማነ

ዲያቆን መሐሪ ገብረማርቆስ

DEREJE THE AWASSA said...

dear dejeselams
God bless you
i hope this is the beginning. our church needs their integrity and unity.please let be what God likes. my comment is if they are united and work for our church we can contribute something, even money for their idea to strength the college. thus please Dejeselames let us know how to get their address and let us know what they need from the people to contribute.
Long live tewahido

Anonymous said...

this is good news for our church. we need unity we have to be united. I believe that unity is the only way to protect our church. May God Bless our church and our country.

Anonymous said...

እግዚአብሔር መልካሙን ሁሉ እንዲያደርግ ጸሎት ያስፈልጋል ጸልዩ!!!!

Anonymous said...

እግዚአብሄር አምላክ ዘመኑን ይባርክልን አምላካችን የሰላምን ዜና አብሳሪ ያድርጋችሁ ያልታወቀ ያልተጣራ ወሬ ፖስት ከማድረግ እርሱ ይጠብቃቹ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)