September 7, 2010

በለንደን በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ቀልብን የሳበው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ

(ነጻ አስተያየት ከለንደን - ታምሩ ገዳ):-የለንደን ከተማ ላለፉት ስድስት ሣምንታት በይዘቱ እና በዓይነቱ ታላቅ ትኩረት የሳበ መንፈሳዊ አገልግሎትን በማስተናገድ ተጠምዳ ሰንብታለች። ይህ ማዕከሉን በለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በማድረግ በለንደን ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ በአውሮፓ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ የተካሄደው የመላው አውሮፓ ዓመታዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ  ሐምሌ 9 – 11 2002 ዓ.ም  (ጁላይ 16 – 18 2010 ) እንዲሁም 3ኛው የደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ መንፈሳዊ ጉባኤዎች ጥምረት የአብዛኛው የለንደን ምዕመናን ስሜት የገዛ ነበር።
ቁጥራቸው ከ300 በላይ የሚገመቱ ከመላው አውሮፓ የተውጣጡ የተዋሕዶ ልጆችን በጉባኤው ላይ ለመቀበል የቤተ ክርስቲያኒቱ  ሰበካ ጉባኤ ያዋቀረው የዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ ከምዕመናኑ ጋር በመቀራረብ እንግዶቹን ለመቀበል ወራት የፈጀ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን በፕሮግራሙ ላይ የነበሩት እንቅስቃሴዎች ያስረዳሉ።
በዚህ የስብከት ወንጌል ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የአለም ማዕዘናት በመምጣት የወንጌል ትምህርት የሰጡ አባቶች መካከል መልአከ ሳሌም አባ ገብረ ኪዳን እጅጉ (ከአሜሪካ ) ፣ አባ ወልደ ትንሣኤ ጫኔ (ከፈረንሣይ ) ፣ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ጌጡ የኋላሸት (ከስዊድን) ፣ ሊቀ ጉባኤ ጥበበ ሥላሴ  አሰፋ ፣ መልአከ ሰላም ቀሲስ አዲስ አበበ እና መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለው አስቻለው ( ከለንደን ) ፣ ዲ/ን ብርሃኑ አድማሴ (ከኢትዮጵያ) ፣ መምህር አምሳሉ ተፈራ (ከጣሊያን) ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህ ጉባኤ ላይ ምዕመናኑ የዘር ፣ የቀለም ፣ የብሔር ፣ የዕድሜ እና የጾታ ልዩነት ሳይገድባቸው ሁሉም በጋራ ከቅዳሴ አንስቶ የስብከተ ወንጌሉ ፕሮግራም እስከሚጠናቀቅበት ምሽት ድረስ የሚዘልቀውን ፕሮግራም ያለ ድካም እና መሰልቸት ሲከታተሉ ለተመለከተ እግዚአብሔር በስደት ላይ ተበታትኖ የሚኖር ሕዝቡን ሊያስተምረው ምን ያህል እንደወደደ መገመት አይከብድም።
የወንጌል መምህራኑ በበኩላቸው በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ፣ ከነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም የራሳቸውን ተሞክሮ እያጣቀሱ በምዕመናኑ ልብ እና  አዕምሮ ውስጥ የወንጌል ዘርን ሲዘሩ ሠንብተዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለ ሕዝበ ክርስቲያን ወይም ሕዝበ ክርስቲያኑ ያለ ቤተ ክርስቲያን መኖር አይችሉም ያሉት አቡነ እንጦንስ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጉባኤው እንዲሳካ ላደረጉ ወገኖች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለሐዋሪያዊ ተልዕኮ ከምድረ አሜሪካ የመጡት መልአከ ሳሌም አባ ገብረ ኪዳንም በበኩላቸው በለንደኑ ጉባኤ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ብዙ ትምህርት መቅሰማቸውን ጭምር ተናግረዋል። በጉባኤው መሣካት መንፈሳዊ ቅናት ያደረባቸው አባ ገብረ ኪዳን አሜሪካ ውስጥ ተመሣሣይ ጉባኤዎች እንዲደረጉ ከወገኖቻቸው ጋር እንደሚመክሩ ተናግረዋል።
ይህን በመላው አውሮፓ የሚገኙ የተዋሕዶ ልጆችን ለ13ኛ ጊዜ ለማሰባሰብ ያስቻለውን ጉባኤ በጽንሠ ሃሳብ ደረጃ ከፈለቁት መካከል በስዊድን የመድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉት ሊቀ ትጉሃን ጌጡ ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። እግዚአብሔርን እና ወላዲተ አምላክን በመተማመን ያለ አንዳች የወረቀት ሠነድ እና ፊርማ ከሌሎች የሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ስዊድን ውስጥ የጠነሰሱት ሃሳብ ዛሬ ከ3000 በላይ ምዕመናንን ለንደን ውስጥ ተሰባስበው በዓይናቸው ለማየት በመብቃታቸው ፈጣሪን በማመስገን ደስታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በለንደን ቆይታቸው ወቅት ወደ አንዳንድ የለንደን ቤተ ክርስቲያናት ጎራ በማለት ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሰጡት ስብከተ ወንጌል ‘’ የካህን እና የሴት እንግዳ የለውም ‘’ የሚለውን አባባል በተግባር ያስመሰከሩ ሲሆን በክርስቲያኖች ዘንድ ፍቅር ፣ ህብረት ፣ ሰላም ፣ መቻቻል . . . ወዘተ መሠረታዊ ነገሮች ለመሆናቸው ምሳሌ ሆነዋል ሲሉ በወቅቱ በርካታ ምዕመናን ለዚህ ጸሐፊ ነጻ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ሊቀ ትጉሃን ጌጡ ከዚህ ጸሐፊ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር። ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በ አሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ለምን ልዩነት ተፈጠረ? መፍትሔውስ ምንድን ነው ይላሉ? . . . ወዘተ ይገኙበታል። እንደ እርሳቸው እምነት ምዕመናኑ ዘወትር ጥሩ ካህናትን ማየት ይሻል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተፈጠሩት አንዳንድ ያለመግባባቶች ተቀርፈው በምትኩ መቻቻል ፣ አንድነት እና ፍቅር እንዲሠፍን የሁሉም ምዕመናን ፅኑ ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል። ‘’ . . . አንዳንድ በፖለቲካ ይሁን በዘረኝነት ወይም በግል ወዳጅነት ወደ ባለሥልጣናቱ ጠጋ ጠጋ ያሉ ወገኖች የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት አይፈልጉም። ከእኛ ይልቅ እነርሱ ይሰማሉ ፤ እኛ አቅም አጠረን ፤ አልታመንንም። ይህንን በደንብ እናውቃለን። ችግሩ እዚህ ላይ ነው። ከዚያ ውጪ ምን ይሻላል? ብለን ከማሰብ ከማልቀስ አልቦዘንም። ‘’  ያሉት ሊቀ ትጉሃን ጌጡ ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መፍትሔው አዘውትሮ እንደሆነ አስምረውበታል። ‘’ የቃላት ጦርነት ፣ የወረቀት ጋጋታ ፣ የትችት ብዛት ዋጋ የለውም ፤ ይልቁንም የርህራዔ ጸሎት ፣ የአርቆ ማሰብ ጸሎትን እየጸለይን ይህ በኃጢአታችን ያበላሸነውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ( አካላችንን ) እግዚአብሔርን በንስሐ ገብተን ብንለምነው እርሱ ችግሩን ይፈታዋል (ሉቃ  21 )።
ይህንን ችግር እና መፍትሔውን በእስራኤል ታሪክ የምናውቀው ነው። እስራኤል እግዚአብሔርን ክደው ጣዖት ሲያመልኩ የመጣባቸውን መከራ የሚቋቋሙት በንስሐ እንጂ በትግል በኃይል አልነበረም። ‘’ እግዚአብሔር የምህረት አምላክ መሆኑን ካህን በመሆኔ ብቻ ሳይሆን በግል ሕይወቴም አይቼዋለሁ። እስቲ ሁላችንም ከራሳችን እንነሳ እና መጀመሪያ እራሳችንን (ሕየወታችንን ) ንጹህ ፣ ቅዱስ ፣ የዋሆች ፣ ትጉህ ፣ ተገዢ . . . ወዘተ እናድርገው በጎደለው እግዚአብሔር ይሞላዋል’’  በማለት ኀዘን እና ቁጭት በተሞላበት መልኩ አስተያየታቸውን ሠጥተዋል። ለተከታታይ ሦስት ቀናት የተካሄደው 13ኛው የመላው አውሮፓ አመታዊ  የስብከተ ወንጌል ጉባኤ የመጠናቀቂያ ዕለት ከአመታዊው የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል ( አብርሃም ሥላሴዎችን በሰው አምሳል ከድንኳኑ ተቀብሎ ያስተናገደበት ወቅት ዘፍ 18 ፡ 1 – 33 )  መገጣጠሙ ጉባኤውን የተለየ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህ ክብረ በዓል ላይ ታቦት በመውጣቱ በኢትዮጵያ የሀገር ባህል ልብስ (ነጠላ ፣ ቀሚስ ፣ሱሪ ) የተዋቡት ሕዝበ ክርስቲያን ከወቅቱ የለንደን የበጋ ጸሐይ ጋር በመደመር በ አካባቢው ለሰዓታት የቆየ ደማቅ ብርሃን እንዲያበራ አድርገውታል። የሰንበት ት/ቤቱ መዘምራን ከሌላ ስፍራ ከመጡ መዘምራን ጋር በመሆን ምዕመናኑን እየመሩ ያሰሙት የነበረው ያሬዳዊ ዜማዎች የመሰጧቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና ቱሪስቶች ይህ በገንዘብ እና በጥበብ የማይገኝ ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቸኛ መንፈሳዊ ቅርስ የሆነውን ሥርዓተ ቤተ ከርስቲያን በማስታወሻነት ለመያዝ በምስል መቅረጫዎቻቸው ለማስቀረት ተሯሩጠዋል። አንዳንዶቹም የበዓሉን ምንነት ለማወቅ ሲጠይቁ ተስተውለዋል። በዚህ ክብረ በዓል ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢዝልንግተን አካባቢ (ሰሜናዊ ለንደን) ከንቲባ ሚስስ ሙና ስለ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያን አምልኮተ እግዚአብሔር ያላቸውን እውቀት ፣ ፍቅር እና አክብሮት ለምዕመናኑ ገልጸዋል። ምዕመናኑም በጸሎታቸው እንዲያስቧቸው ተማጽነዋል።
ይህ ‘’ የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል ‘’ ሚክ 6፡9
በሚል ነቢያዊ ጥቅስ የተከፈተው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ሲጠናቀቅ ለመጪው ዓመት በስዊድን ሀገር ለመገናኘት ቀጠሮ በመያዝ ከእንግሊዝ ውጪ የመጡ ምዕመናን በለንደን ከሚኖሩ ወገኖቻቸው ጋር ተመራርቀው ተሸኛኝተዋል። ከዚያ በመቀጠል በለንደን ፣ በማነችስተር ፣ በበርሚንግሃም ፣ በኒውካስል እና ስቶክ ኦን ትሬንት ከተሞች ለሳምንታት የተሰበከው የ3ኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ አመታዊ መንፈሳዊ ጉባኤ በመንፈሳዊ አስተማሪነቱ ከብዙዎች ምዕመናን  አእምሮ የማይጠፋ ትዝታን ጥሏል ተብሎ ይገመታል። ዲ/ን ብርሃኑ አድማሴ በዚህ ጉባኤ ላይ መድረኩን በአመዛኙ ከታላላቅ መምህራን የተረከበበት አጋጣሚ ነበር። ዲ/ን ብርሃኑ አድማሴ አስኳል እውቀቱን ከመንፈሳዊ ተሰጥዖው ጋር እያዋዛ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሚገባው ቋንቋ እና አቀራረብ ስለ ‘’ ሰጥቶ መቀበል ፣ አፅዋመ ቤተ ክርስቲያን ፣ ደብረ ታቦር ፣ እና ቅዱስ ጋብቻ ‘’ አስተምሯል። ስለ ቅዱስ ጋብቻ የሰጠው ትምህርት እና ምክር የአብዛኛውን የማህበረሰባችንን መሠረታዊ ችግሮችን የዳሰሰ ነበር። ይህ ትምህርት ለተከታታይ ቀናት በተሰጠበት ወቅት ምዕመናኑ ትምህርቱን ለራሳቸው ለማስቀረት ወይም ለወዳጆቻቸው ለማዳረስ በተለያዩ የድምጽ መቅረጫዎች ለመቅረጽ ሲረባረቡ ተስተውለዋል። በስተኋላ ግን የጉባኤው አስተባባሪዎች ሁሉንም ስብከተ ወንጌል ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ቀርጸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለምዕመናኑ እንዲዳደረስ እንደሚያደርጉ በድጋሚ ቃል በመግባታቸው ምዕመናኑ ትዕዛዙን በይሁንታ ተቀብሎታል።
ይህ የቅዱስ ጋብቻ ስብከት ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በገሃዱ አለም የሚታዩ የማህበረሰባችን ውጣ ውረዶች ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ አቅራቢን ጨምሮ በርካታ ምዕመናንን በታዋቂው ኢትዮጵያዊ የስነ ጽሑፍ ሰው ዶ/ር ሃዲስ አለማየሁ ተደርሶ በተራኪው ፍቃዱ ተክለ ማርያም አማካኝነት በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከመፃሕፍት አለም የትረካ ፕሮግራም ከአንድ አመት በላይ አጓጊ በመሆን የተተረከው ‘’ ፍቅር እስከ መቃብርን ‘’ መጽሐፍ አስታውሷል። መጽሐፉ በውስጡ የያዛቸው ገጸ ባሕርያት እና መቸቶች በወቅቱ ሬዲዮኑን በድንገት የከፈተ ማንኛውም የአማርኛ ቋንቋ ሰሚ ቀልብ እና ጆሮዎች ለአፍታም ቢሆን መሳቡ አይካድም።
http://gallery1.debre-genet-ks.org/#5
የብዙዎቹን ምዕመናን ቀልብ በመሳብ ልባቸውን ጭምር ያንኳኳው የዲ/ን ብርሃኑ ስብከትም ቢሆን የደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በኪራይ የምትጠቀምበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መያዝ ከነበረበት 500 – 600 መቀመጫዎች ተጠብበው ሁሉም ሕዝበ ክርሰቲያን ፕሮግራሙን በተመስጦ እንዲከታተል አድርጎታል። ስብከተ ወንጌሉን ተከትሎ ምዕመናኑ እንዲብራሩላቸው የሚፈልጉት ጥያቄዎችን በጽሑፍ እና በግንባር እንዲያቀርቡ የተደረገው ፕሮግራም የጉባኤው ሌላኛው ጠንካራ ጎን ነበር። በርካታ ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ የሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝታዋል። ከአንዲት ምዕመን ቀረበ የተባለው ‘’ እጮኛዬን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዤው ብመጣ ችግር አለው . . . ወዘተ ? ‘’ ለሚለው ጥያቄ ‘’ እርሱ ይምጣ እንጂ ችግር የለውም ‘’ የሚለው አጭር ምላሽ ብዙዎቹን በጊዜው ፈገግ ያደረገ ቢሆንም መልዕክቱ ቤተ ክርስቲያን የጠፉ ልጆቿ ሲመለሱ ዘወትር ደስ ይላታል ከሚለው አምላካዊ ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው። በሃይማኖት የማይገናኙ ጥንዶች እንኳን ወንዱ በሴቷ ወይም ሴቷ በወንዱ እንዴት እንደሚቀደሱ መለያየት እንደሌለባቸው ( 1ቆሮ 7 ፡ 10 – 12 ) የተሰጠው ትምህርት ቀደም ሲል በዚህ መልኩ ወደ ትዳር የገቡ ወገኖች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያመላከተ ትምህርት ነበር። በስተመጨረሻ ‘’ ነጠላ ዜማዬ ነች . . . ‘’ በማለት ስለ ኢትዮጵያ ፣ ስለ ሕዝቧ አንድነት እንዲሁም ስለ ጎረቤቶቿ ሰላም እና ፍቅር ያዜመው ዲ/ን ብርሃኑ ከምዕመናኑ ሞቅ ያለ የሞራል ድጋፍ እና መንፈሳዊ ምርቃት ተችሮታል።
የስብከተ ወንጌል ጉባኤው ያማረ እና የተዋጣለት እንዲሆን በመቶ የሚቆጠሩ የለንደን ነዋሪዎች ቤታቸውን ለእንግዶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመልቀቅ ክርስቲያናዊ ተግባር የፈጸሙ ሲሆን በግል ደረጃ አቶ ኃይሌ (በግጥም እና ምስጋና ፣ ዘማሪት ሀረገ ወይን ፣ አቶ ወንደሠን (በመንፋሳዊ ድራማ እና ዝግጅቱን በድምፅ በመቅረጽ ) በኩል ስማቸው ለአብነት ያህል ተጠርተዋል።
ከሁሉም በላይ ስሙ ጎላ ብሎ ሊጠራ የሚገባው ወንድም መዘምር ዲ/ን ምንዳዬ ብርሃኑ ከመንፈሳዊ ወንድሙ ዲ/ን ብርሃኑ ጋር በመሆን በፕሮግራሞቹ ጣልቃ በመግባት ምዕመናኑን በመንፈሳዊ መዝሙሮቹ አስተምሯል፤ ፈጣሪውን በጋራ አመስግኗል። ‘’ ብዙ እንድንዘምር ፣ ፈጣሪን እንድናመሰግን ቦታ እና ጊዜ አገደን . . . ወዘተ ‘’ የሚለው ዲ/ን ምንዳዬ የተዋጣለት እና መለኮታዊ የሆነውን ጣዕመ ዝማሬውን በተሣካ ሁኔታ እንዲያቀርብ አርቲስት ተመስገን የተባሉ የባህላዊ እና ዘመናዊ ሙዚቃ ተጫዋች ከዲ/ን ምንዳዬ እያንዳንዱ ዜማ ጋር የሚሄድ የክራር ቅኝታቸውን በማሰተካከል ያደረጉት ጥረት ምዕመናኑ መዝሙሮቹን በሃይማኖታዊ የምስጋና መሣሪያዎች ( ክራር ፣ በገና ፣ ከበሮ . . . ወዘተ ) አማካኝነት ፈጣሪውን እንዲያመሰግን አድርገዋል። በዲ/ን ምንዳዬ እና አርቲስት ተመስገን መካከል የነበረው ሙያዊ ጥምረት ሁለቱ ወንድሞች ቀደም ሲል አገር ቤት አብረው ያገለገሉ አስመስሏል። ዲ/ን ምንዳዬ በቪሲዲ መልክ ያስቀረጸው ‘’ ደጅሽ ላይ ቆሜ ስለምንሽ ‘’ የሚለው ቁጥር 6 አዲስ መንፈሳዊ አልበሙ ለንደን ላይ እንዲመረቅ አጋጣሚው መፍቀዱ ለንደኖች እድለኞች እና የበረከቱ ተካፋዮች አድርጓቸዋል።  
ጉባኤው ባማረ እና በደመቀ ሁኔታ እንዲከናወን ስፖንሰር የሆኑት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ( አንድ ከለንደን አዲስ አበባ ደርሶ መልስ የአየር ቲኬት ) ፣ ስንቄ እና ኮከብ የተባሉ ሁለት ታዋቂ የለንደን ሬስቶራንቶች (ምዕመናኑ ምግብ እንዲቋደሱ በማድረግ ) ፣ አንድ ምዕመን ለሠንበት ት/ቤቱ ተማሪዎች ሙሉ ልብስ በማሰፋት ሌሎችም ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ወገኖች ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዝግጅቱ አጠቃላይ ወጪነት የያዘችውን 14 ሺህ ፓውንድ ( ወደ 280 ሺህ ብር ) ከሞላ ጎደል እንዲሸፈን ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸው የምዕመናኑ እና የቤተ ክርስቲያኑ ጥምረትን ያመለክታል። ወደፊትም በሁሉም ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ሊተገበር የሚገባ ተግባር ነው። የዝግጅት ኮሚቴውም አጠቃላይ ወጪ እና ገቢውን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በበዓሉ ማጠናቀቂያ ዕለት እድሜያቸው በግምት ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ሕፃናት ለወላጆቻቸው እና ለወገኖቻቸው ያሰሙት የግዕዝ እና የአማርኛ መዝሙራት እንሰሳ እንኳን አፍ አውጥታ እንድትናገር ያስቻለ ፈጣሪ በአምሳሉ የተፈጠሩትን የሕፃናት የምስጋና አፍ ለመስማት ምን ያህል እንደሚሻ በገሃድ የታየበት መድረክ ነበር። ሕፃናቱ ላሳዩት ክርስቲያናዊ ጨዋነት እና ዝማሬ ከታዳሚዎቹ በሙሉ ሞቅ ያለ ጭብጨባ እና የእልልታ ምስጋና አግኝተዋል። የፕሮግራሙ ማሣረጊያ የሆነው ‘’ የጥብርያዶስ አሣዎች ‘’ በሚል ርዕስ በሠንበት ት/ቤቱ የተዘጋጀው መንፈሳዊ ድራማ የሁሉንም ቀልብ የሳበ ነበር። ድራማው በተለይ በፈረንጆች የአሻንጉሊት ፊልሞች አእምሯቸው የጦዘውን ታዳጊ ሕፃናትን ሣይቀሩ የተዋኒያኑን ድምፅ እና እንቅስቃሴ በቅርቡ ለመከታተል ያስችላቸው ዘንድ የተዘጋጁላቸውን ወንበሮች ወደ ጎን በመተው ከመድረኩ ፊት ከወለል ላይ ተኰልኩለው በተመስጦ እንዲከታተሉ አድርጓቸዋል። ተውኔቱን በቪዲዮ ካሜራቸው የቀረጹት አያሌ ናቸው።
በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር የቅርብ እገዛ እና ክትትል እየተደረገለት በሰባት የዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት አማካኝነት ሕዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ ልቡ ዝግጅቱ የራሱ እንዲሆን አድርጎ ተሣታፊ ያደረገው የስብከት ወንጌል ጉባኤ ሙሉ በሙሉ አልጋ በአልጋ የተጓዘ ነው ማለት አይቻልም። አሣዛኝ ገጠመኞችም አልታጡበትም። ለምሳሌ ያህል ዘማሪያኑ እና ምዕመናኑ ፈጣሪን ለማመስገን ድምፃቸው ከፍ አድርገው ሣለ ‘’ . . . የአካባቢው ነዋሪዎች ለካውንስሉ (መስተዳድሩ) አቤቱታ በማቅረባቸው ድምፃችሁን ቀንሱ ፣ በሮች እና መስኮቶች ይዘጉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለቤቶች ( ነጮቹ ) ቦታውን ለሌላ አገልግሎት ስለሚፈልጉት ፈጥናችሁ ውጡ ወይም የፕሮግራም መጋጨት ስለተፈጠረ በሚቀጥለው ቀን ስብከተ ወንጌል አይኖርም . . . ወዘተ ‘’ የሚሉት ማስታወቂያዎች እና ምክሮች በርካታ ምዕመናን ስታቸውን ነክቷል። ሁኔታውም ‘’ የሰው ወርቅ አያደምቅ ‘’ መባሉ እውነትነት እንዳለው በተግባር ተስተውሎበታል።
ይህ ጊዜ የማይሰጠው የሕዝበ ክርሰቲያኑ የወንጌል ርሃብ ጥያቄ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደርም ችግር መሆኑ ባይካድም ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው ወገኖች በአዲሱ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ ( አዲስ አመት ) አንድ አዲስ የሆነ መንፈስን የሚያረጋጋ ሃሣብ ይዘው እንዲመጡ የብዙ ምዕመናን ተስፋ ነው። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለሰላሳ አመታት የራሷ የሆነ ቋሚ ስፍራ ሣይኖራት ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው ስፍራ ስትንከራተት የቆየቸው የለንደን ርዕሰ አድባራት ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም  ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግዢን ለማጠናቀቅ በለንደን የሚኖሩ ከሰላሳ በላይ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ከሚመለከታቸው  የቤተ ክርስቲያኒቱ ኃላፊዎች እና ምዕመናን ጋር በመሆን  አላማቸውን ግቡን እንዲመታ ማድረጋቸው እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በስተመጨረሻ የራሷ የሆነ ቋሚ ሥፍራ ማግኘቷ በመንፈሳዊ አርአያነቱ ሊጠቀስ ይገባል። በጊዜው የነበረውን ሁኔታም ይህ ጸሐፊ በታዋቂው ‘’ የድሬ ቲዩብ ‘’ ድህረ ገጽ አማካኝነት በምስል የተደገፈ ዘገባ አቅርቧል።
                                                                         እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ
                                                                                          አሜን
                                                                             

11 comments:

Anonymous said...

እባካችሁ መስማት ለሚፈልጉ ሰዎች (እኔንም ጨምሮ) ሊንክ ካለ ፖስት ብታደርጉልን፡፡ እስካሁን ሰዎችን ጠይቄ ነበር አላገኘሁም፡፡

Anonymous said...

እባካችሁ መስማት ለሚፈልጉ ሰዎች (እኔንም ጨምሮ) ሊንክ ካለ ፖስት ብታደርጉልን፡፡ እስካሁን ሰዎችን ጠይቄ ነበር አላገኘሁም፡፡

Anonymous said...

please the photos of the london gubae from their site. and they promised us that all the preachings will be lonched on their site after they cell it first. here is their website. by they it is alredy one of Dejeselam links. http://www.debre-genet-ks.org/index.html

Anonymous said...

please the photos of the london gubae from their site. and they promised us that all the preachings will be lonched on their site after they cell it first. here is their website. by they it is alredy one of Dejeselam links. http://www.debre-genet-ks.org/index.html

Anonymous said...

ለተጨማሪ ስዕላዊ መግለጫ ይህን ይጫኑ

http://gallery1.debre-genet-ks.org/#home

Anonymous said...

Good to read these kinds of success stories from this blog.
KHY

Ehete micheal said...

Egizabher yemsgen endhi aynet zena mesmate..eleleleleleelelele Ahunem Egizabher endhi yalewm melkam zena yeseman.
Ehete micheal

Anonymous said...

Egziabher ystlin, abatochin ina memhranin Egziabher ytebikiln, ketechale gn yesbketu (yetmhrtu) dmts binor ina binsemaw melkam neber.

Anonymous said...

Egziabher ystlin, abatochin ina memhranin Egziabher ytebikiln, ketechale gn yesbketu (yetmhrtu) dmts binor ina binsemaw melkam neber.

Anonymous said...

Egziabher ystlin, abatochin ina memhranin Egziabher ytebikiln, ketechale gn yesbketu (yetmhrtu) dmts binor ina binsemaw melkam neber.

Anonymous said...

very sensational and detailed way of presentation,would even more appreciable if followed by video clips.God bless your career.

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)