September 2, 2010

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች በአደጋ ውስጥ ናቸው ተባለ

(ለደጀ ሰላም መጦመሪያ፤ ታምሩ ገዳ ከለንደን):- ኢትዮጵያን በለም  በታሪክ እና በቅርስ ባለቤትነት ተጠቃሽ ከሆኑት ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን ያደረጓት ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶቿ እጅግ አስጊ በሆነ የመጥፋት አዝማሚያ ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ። “የኢትዮጵያ ገዳማት ፣ አድባራት እና የአብነት ት/ቤቶች (የቆሎ ት/ቤቶች) ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ” በሚል ርዕስ ዙሪያ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ በማድረግ ለግንዛቤ ያህል ለንደን ውስጥ ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  አማኞች እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ባለፈው ሣምንት ገለጻ ያደረጉት
እዚሁ እንግሊዝ አገር ውስጥ በተለዋጭ የተፈጥሮ ሀብት ዙሪያ ከፍተኛ ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙት አቶ በላቸው ጨከነ በአሁኑ ወቅት በርካታ ዓመታት ያስቆጠሩት ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት በእድሳት እጦት ምክንያት በውስጣቸው የሚገኙት ውድ እና ብርቅዬ ቅርሶች መበላሸት፣ ዘራፊዎች እነዚህ ብርቅዬ እና ውድ የሆኑ ንዋየ ቅድሳት ለመስረቅ ማተኮራቸው፣ በተለያዩ ጊዜያት በገዳማት እና በዙሪያቸው በሚገኙ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ መድረስ እንዲሁም የቆሎ ተማሪዎች እና መምህራኖቻቸው በምግብ እጦት እና በእርዛት ምክንያት ቀያቸውን እየለቀቁ ወደ ከተሞች መሠደድ በታሪካዊ የኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ካነጣጠሩት ዋነኛ ችግሮች የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

አቶ በላቸው ከዚህ ጸሐፊ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እነዚህ ታሪካዊ እና ብሔራዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ኃላፊነት እንዳልሆነ ይልቁንም አገራችንን ፣ ባህላችን ፣ ቅርሳችንን እንወዳለን የሚሉ ወገኖች በሙሉ በግል ፣ በቤተሰብ እና በቡድን በመሆን በቅርሶች ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች ሊታደጉ ይገባቸዋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንን የማሰባሰብ ዘመቻን በተመለከተ በአሜሪካ የሚገኙ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እያደረጉት ያለውን ጥረት አቶ በላቸው ሳያመሰግኑ አላለፉም። በተለያዩ ወቅቶች ከኢትዮጵያ በድብቅ መጥተው በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በቫቲካን (ኢጣሊያ) . . . ወዘተ በመሳሰሉት አገሮች ከሦስት ሺህ በላይ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ንዋየ ቅድሳት እና የብራና መጻሕፍት ለባዕዳኑ ሙዚየሞች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ማስገኛ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ ሲሉ አቶ በላቸው በቁጭት ተናግረዋል። በየዓመቱ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ወደ ሀገር ቤት ጎራ ከሚሉት ጎብኚዎች መካከል ከ85% በላይ የሚገመቱት አመጣጣቸው እነዚህኑ በመጥፋት ላይ የሚገኙትን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ የኢትዮጵያ አሻራዎች የሆኑትን ቅርሶች ለመመልከት እንደሆነ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ አካትተዋል። አቶ በላቸው በቅርቡ ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ጀርመንኛ የተተረጎመ ዘመናዊ የሕፃናት መማሪያ ዲቪዲ በማዘጋጀት የዜግነት ድርሻቸውን መወጣታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)