September 8, 2010

ዘሪሁን ሙላቱ በ2500 ብር ዋስ ተለቀቀ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 8/2010፤ ጳጉሜን 3/2002 ዓ.ም):- በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ለ2500 ብር የሚበቃ ዋስ ጠርቶ ወይም 2500 ብር አስይዞ በዋስ እንዲፈታ የአዲስ አበባ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ውሳኔ ሰጠ፡፡ በተለምዶ አፍንጮ በር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ በትናንት ዕለት ረፋድ ላይ በሰጠው በዚሁ ውሳኔ በ‹መጽሐፉ› የግል ተበዳይ ነን ያሉት እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ክስ ባቀረቡበት ጉዳይ በተጠርጣሪው ላይ በቂ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻላቸውን በመጥቀስ ተችቷል፡፡ የአንድን ግለሰብ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት ከዚህ በላይ አግዶ መቆየት ተገቢ ባለመሆኑ ተጠርጣሪው ለ2500 ብር የሚበቃ ዋስትና አቅርቦ እንዲለቀቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ጉዳዩን የሚከታተሉት መርማሪ ፖሊስ የግል ተበዳዮቹ በተጠርጣሪው ላይ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሌላ ክስ መመሥረታቸውን እና ጉዳዩ በዚያው መደበኛ ችሎት እንዲታይ እንደሚፈልጉ ቢያስረዱም ዳኛው፣ ይህ ከሆነ ቀድሞም ጉዳዩን ለዚህ ችሎት ማቅረብ እና በዚህም ሳቢያ የተጠርጣሪውን የዋስትና መብት ነፍጎ ማቆየት አስፈላጊ እንዳልነበር በመግለጽ ተችቷል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቅጽር ግቢ ለምስክርነት ካዘጋጇቸው ጋራ እንደ ነበሩ ተዘግቧል፡፡ ወይዘሮዋ ተጠርጣሪውን ስውር ጸሐፊ ከሶ ለማስቀጣት - አንዳንድ የሕግ አስከባሪ እና የፍትሕ አካላት በገንዘብ ለመደለል እስከ መሞከር፣ ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም በተለያየ ምክንያት የበደላቸውን አካላት እና ግለሰቦች (ለብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እስከ ማስደወል ድረስ) በማግባባት ተደራራቢ ክስ እንዲመሠረትበት - ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበር የተነገረ ሲሆን ሙከራቸው ሁሉ እንዳልያዘላቸው ታውቋል፡፡

ወይዘሮዋ ሐምሌ 25 ቀን 2002 ዓ.ም የነበረውን የፍርድ ቤቱን ውሎ ለመከታተል በተገኙበት ወቅት ቀድሞ ከመኪናቸው ጋቢና የማይለዩት ወዳጃቸው ዘሪሁን ሙላቱ ከተቀመጠበት በመነሣት ‹‹ወ/ሮ እጅጋየሁ፣ መጽሐፍ እንደተጻፈብዎት ሰምቼ እኮ በጣም አዘንኹ፡፡ እነዚህ ክፉዎች!! ...›› በማለት አላግጦባቸዋል፡፡ ሴትዮዋ በአነጋገሩ ክፉኛ በመበሳጨት፣ ‹‹የዘራሁትን ነው ያጨድሁት›› በማለት ቁጭታቸውን መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ እንዲህ ያሉት ዘሪሁን ሙላቱን በተለይም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የኢትዮጵያ ዕሥራ ምእት በዓል አከባበር ኮሚቴ እንዲመጣ እና የጽ/ቤቱን ሥራ እንዲሠራ በማድረግ ወዲያውም ከእሳቸው ጋራ ያለው መቀራረብ ጎልብቶ በመጽሐፉ ይፋ ያደረገውን ገመናቸውን ለማወቅ ያስቻለው መሆኑን በንዴት በማስታወስ እንደ ሆነ የጉዳዩ ተከታታዮች ይገልጻሉ፡፡

ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ የዕሥራ ምእቱ በዓል አከባበር ኮሚቴ ጸሐፊ ከመሆኑ በፊት በቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ጠቅላላ አገልግሎት፣ ሰባኬ ወንጌል በኋላም የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊነት ተሰጥቶት ነበር፡፡ በ2000 ዓ.ም ለተቋቋመው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዕሥራ ምእት በዓል አከባበር ኮሚቴ ሥራ ሲባል በወይዘሮ እጅጋየሁ አቅራቢነት በፓትርያርኩ ትእዛዝ በቦሌ መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ከነበረው ተግባር ነጻ የተደረገ ቢሆንም የኮሚቴው ሥራ ሳይጠናቀቅ ከገንዘብ አጠቃቀም እና ንብረት አያያዝ ጋራ በተያያዘ በወቅቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ እንዲባረር ተደርጓል፡፡ ከዚያ በኋላ ቀድሞ በካቴድራሉ በተመደበበት የሥራ ገበታው ላይ አዘውትሮ ባይገኝም ወርኀዊ ደመወዙን ከመውሰድ ግን አልተከለከለም ነበር፡፡ ይህ ወቅት ስውሩ ጸሐፊ "ተከሥተ ዘሪሁን" በሚል የፈጠራ ስም ‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› የሚል ስም አጥፊ ጽሑፍ ለመጻፍ እና ለማሳተም አመቺ ጊዜ ያገኘበት ወቅት ነበር፡፡

ውሎ አድሮ ነገሩ ወደራሳቸው የተመለሰባቸው እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ እና የሀገረ ስብከቱ ሐላፊዎች፣ ‹‹ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ለረጅም ጊዜ በሥራ ገበታው ላይ እንዳልተገኘ እየታወቀ ከደመወዝ አለማገዳችሁ እና ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሪፖርት አለመቅረባችሁ ስሕተት ነው›› በሚል የካቴድራሉን ዋና ጸሐፊ መምህር የማነ ዘመንፈስ ቅዱስን ከሐላፊነት በማንሣት በለየለት መምህር ሰሎሞን በቀለን ተክተዋል፡፡ ውስጥ ዐዋቂዎች እንደሚናገሩት፣ መምህር የማነ ራሳቸው ወንድም እኅታቸውን በተለያዩ አድባራት ሰበካ ጉባኤያት አስተዳደር ውስጥ በተቆጣጣሪነት እና በጸሐፊነት በማስቀጠር፣ ለግላቸውም በተለያዩ ‹ኢንቨስትመንቶች› ላይ ለመሠማራት ያስቻላቸውን ሀብት አላግባብ ያካበቱ መሆናቸው ቢታወቅም በቅርቡ ከሐላፊነት የተነሡበት ምክንያት ግን የሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን በሥራ ገበታ አለመገኘት ሳይሆን የቆየ ጉዳይ መሆኑን በማውሳት የሀገረ ስብከቱን እግድ መቃወማቸው በአንድ በኩል፣ ለጊዜውም ቢሆን የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና ጸሐፊ እንደ መሆናቸው መጠን በሀገረ ስብከቱ ተባብሷል የሚሉትን ችግር በመዘርዘር ለፓትርያርኩ የጽሑፍ ሪፖርት ማቅረባቸው፣ በአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ - ስምዕ ተከላ ደስተኛ አለመሆናቸውን በተለያዩ መንገዶች በመግለጻቸው ሳቢያ እንደ ሆነ ተመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተለይም የንግድ ሕንፃዎች ኪራይ እና የአገልግሎት (ትምህርት ቤቶች እና የመቃብር ሐውልት ሥራዎች ተቋራጭነት ሳይቀር) ሥራዎች በሚከናወኑባቸው አድባራት እና ገዳማት በአስተዳዳሪነት ለመመደብ ከ30‚000 - 50‚000 ብር፣ በጸሐፊነት እና ሰባኬ ወንጌል ሆኖ ለመመደብ ከ10‚000 - 20‚000 ብር ጉቦ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሐላፊዎች እንደሚከፈል ብዙዎች በይፋ ይናገራሉ፡፡ ለምደባው ይህን ያህል ብር የሚከፍሉ አንዳንድ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች እና ሰባክያነ ወንጌል በእጅ መንሻ ያወጡትን ለመተካት የሚደራደሩት በሚመደቡበት አጥቢያ በምትኩ አላግባብ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም በማስላት እንደ ሆነ ውስጥ ዐዋቂዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ይህን "የቦታ ሽያጭ" በማቀላጠፍ እና የሚያስገኘውን ጥቅም በመጋራት የሚታወቁት ዋና ዋና ግለሰቦች ስም ዝርዝር ቢኖረንም ለጊዜው ግን ከማውጣት ተቆጥበናል። ይህ ድርጊት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ግን ማውጣታችን የማይቀር ነው።

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)