September 23, 2010

በገቺው የአክራሪ ሙስሊሞች ሁከት 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

  •  ሁከቱ ክርስቲያኖችን በኢኮኖሚ ለማዳከም እና ለማሸማቀቅ ያለመ ነው
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 23/2010፤ መስከረም 13/2003 ዓ.ም):-  በኢሉአባቦራ ሀገረ ስብከት በገቺ ወረዳ አራት ቀበሌዎች እና ዘጠኝ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከአንድ ወር በላይ በአክራሪ ሙስሊሞች ሲፈጸም የቆየው ክርስቲያኖችን አግቶ የመውሰድ፣ መኖሪያቸውን ከብቦ የማስጨነቅ እና በሽመል የመደብደብ፣ የቡና እና ሌሎች ቋሚ ተክሎቻቸውን በሌሊት የመመንጠር፣ ሰብሎቻቸውን የማጥፋት፣ ከብቶቻቸውን ነድቶ የመውሰድ፣ አርዶ እና ተቃርጦ የመብላት የጥፋት ተግባራት መገታታቸውን እና የድርጊቱ ፈጻሚዎች የሆኑ 13 ግለሰቦች ካጠፏቸው ንብረቶች ጋራ በቁጥጥር ሥር ውለው በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የአካባቢው ደጀ ሰላማውያውን አመለከቱ፡፡
እንደ ደጀ ሰላማውያኑ ገለጻ ከሆነ ወረዳው በጠንካራ የፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎች ስምሪት ውስጥ ይገኛል፤ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትንም በቀጣይ አድኖ ለፍርድ የማቅረቡ ዘመቻ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከሀገረ ስብከቱ እና ከገቺ ወረዳ ቤተ ክህነት ሐላፊዎች፣ ከወረዳ ምክር ቤቱ የካቢኔ አባላት እና የፖሊስ ኀይል ጋራ በተደረገ ስብሰባ ከሁለቱም ወገኖች ተውጣጥተው ለችግሩ ዘላቂ እልባት የሚሰጡ የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠዋል፡፡ ይሁንና ከዚህ ቀደም በአካባቢው በደረሰው ጭፍጨፋ እና ከዚያም በኋላ በተለያየ መንገድ ከጅማ እስከ መቱ ድረስ በተዘረጋው እና ተባብሶ ከቀጠለው የአክራሪዎቹ ሰንሰለታማ ተጽዕኖ አኳያ ሁኔታው ሀገረ ስብከቱን ባካተተ መልኩ በሌላ ገለልተኛ አካል ቢታይ የተሻለ ዋስትና እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡


ለችግሩ የቅርብ ጊዜ መንሥኤ እንደ ሆነ የተገለጸው በገቺ ወረዳ ጂሳ እና ቦረታ በተባሉ ኩታ ገጠም ቀበሌዎች መዋሰኛ ላይ ከሁለት ዓመት የይዞታ ክርክር በኋላ ባለፈው ዓመት ግንባታው ተጀምሮ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የመድኃኔዓለም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መሠራት ሳቢያ በአክራሪዎች ላይ ያደረው ክፉ የቅንዓት መንፈስ እንደ ሆነ ተገልጧል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራው ቦታውን በበጎ ፈቃዱ ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ማሠሪያ በማመልከቻ ጽፎ ባበረከተ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን ቦታ ላይ ቢሆንም አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሙስሊሞቹ በሰጧቸው አጓጉል ተስፋ ሳቢያ አክራሪዎቹ ምእመናንን በማሸማቀቅ የሕንጻ ሥራውን የሚያሰናክሉ ድርጊቶችን ለመፈጸም እንደተነሣሱ ተመልክቷል፡፡ በዚህ የተነሣ በጎሌ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የልማት ጣቢያ ሠራተኞች እና በትምህርት ቤቶች ክርስቲያን መምህራን አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ግፊት ሲደረግባቸው ቆይቷል፡፡

ሐምሌ 21 ቀን 2002 ዓ.ም በገበር ቀበሌ አንዳንድ አሰጋጆች ቅሰቀሳ የተነሣሱ ሙስሊሞች ‹‹ክርስቲያኖች ደብድበውብን ነው›› በሚል በሐሰት አንድ ሙስሊምን በቃሬዛ ተሸክመው ወደ ሕክምና ቦታ ይሄዳሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የክርስቲያኖቹን መኖሪያ በመክበብ ምእመናኑን በሽመል የመቱ ሲሆን የቀበሌው አስተዳደር ዘግይቶ ጣልቃ በመግባት ደብዳቢዎቹ ይቅርታ እንዲደረግላቸው እና ዕርቅ እንዲፈጠር ማድረጉ ተዘግቧል፡፡ 


ይሁንና ከነሐሴ 10 ቀን ጀምሮ በጂሳ ቀበሌ የክርስቲያኖችን የቡና ተክሎች የመቁረጥ፣ ሌሎችም ደራሽ ሰብሎቻቸውን የማጥፋት፣ ከብቶቻቸውን፣ በጎቻቸውን እና ፍየሎቻቸውን የመዝረፍ እና አርዶ የመብላት ተግባር በተመረጡ ምእመናን ላይ ሲፈጽሙ መቆየታቸው ተመልክቷል፡፡ መስከረም ስምንት ቀን ለዘጠኝ አጥቢያ ድርጊቱን ለመከላከል በሞከረ አንድ ክርስቲያን ላይም በፈጸሙት ድብደባ አቁስለውታል፤ ምእመኑ በአቅራቢያው ጤና ጣቢያ ሕክምና አግኝቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡

ዛሬ በገቺ ወረዳ ላይ በተደረገው የጋራ ውይይት የወረዳው ባለሥልጣናት ድርጊቱን ከዘራፊዎች ስርቆት ጋራ በማያያዝ የድርጊቱን ፈጻሚዎች በአስቸኳይ ለፍርድ እንደሚያቀርቡ ቢናገሩም አንዳንድ የጉዳዩ ተከታታዮች ግን ችግሩ በተጠቀሱት ቀበሌዎች የጠንካራ ክርስቲያኖች የኑሮ መሠረት የሆኑትን የግብርና ሀብቶቻቸውን በማጥፋት በኢኮኖሚ ለማዳከም፣ በእምነታቸው ጠንክረው የሰበካቸውን የልማት እንቅስቃሴ ከመደገፍ እንዲታቀቡ ለማድረግ፣ ወትሮም በሀገረ ስብከቱ ሣስቶ በሚገኘው የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ግንዛቤ የሌላቸው ምእመናን ግራ እንዲጋቡ እና ተስፋ እንዲቆርጡ በማድረግ አካባቢውን ለቀው እንዲሰደዱ አልያም ችግሩን መቋቋም ተስኗቸው እምነታቸውን እንዲቀይሩ ለማስገደድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኑሮ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ምእመናንን በጋብቻ ይዞ፣ በመውጫቸው እና በመግቢያቸው ማጨናነቅ እንዲሁም ንብረቶቻቸውን በመዝረፍ እምነታቸውን ማስቀየር እየጎሉ የመጡ የኢጥሙቃኑ ጫና መፍጠሪያ ስልቶች ናቸው፡፡  

በመሆኑም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ መንፈሳውያን ማኅበራት እና ገባሬ ሠናይ ምእመናን አቅማቸውን በማቀናጀት በአካባቢው ቋሚ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም በቋንቋው የሚናገሩ፣ ባህሉን የሚያውቁ ነዋሪ ካህናትን በማፍራት፣ ችግር ፈቺ የአንድነት ጉባኤያትን በማዘጋጀት፣ ለሰባክያን መንቀሳቀሻ በጀት የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት እንዲራዱ ጥሪ ተላልፏል፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)