September 29, 2010

የመስቀል ደመራ በዓል መርሐ ግብር ሪፖርታዥ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 28/2010፤ መስከረም 18/2003 ዓ.ም):-  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሥጋውን የቆረሰበት፣ ደሙን ያፈሰሰበት እና ነፍሱን የካሰበት ቅዱስ መስቀል የፍቅር ፍጻሜ፣ የሰላም ማረጋገጫ እና የአንድነት ዙፋን ነው፡፡ ክርስቶስ በደሙ ለዋጀው ሕዝብ ቀዋሚ ዓርማ በሆነው ቅዱስ መስቀል ሰማያውያን እና ምድራውያን ታርቀዋል፡፡ መስቀል ለመላእክት እና ለሐዋርያት የስብከታቸው ማእከል፣ ለእኛ ለምናምንበትም ኀይል እና ጽንዕ ነው፡፡ ከአበው እንደ ወረስነው መስቀል በደረታችን ላይ፣ መስቀል በጣታችን ላይ፣ መስቀል በየልብሳችን ላይ፣ መስቀል በአብያተ ክርስቲያን ጉልላት፣ በር እና መስኮት ላይ፤ መስቀል በንዋያተ ቅድሳት ላይ፣ መስቀል በካህናት እጅ ላይ፣ የመስቀሉ ባለቤት እግዚኣ ሕያዋን ወሙታን ነውና መስቀል በሙታን መቃብር ላይ ሳይቀር ይገኛል - በዚህም ዘወትር እንሳለመዋለን፤ እንባረክበታለን፤ በረከት እና ረድኤትም እናገኝበታለን (ማቴ.10÷38)፡፡

September 27, 2010

ማስታወቂያ፦ ደጀ ሰላምን በኢሜይል

በዚህች የጡመራ መድረካችን የምናቀርባቸው ዜናዎች፣ ሐተታዎችም ሆኑ ሪፖርታዦች ከአንባብያኑ ከእናንተ ከደጀ ሰላማውያን መድረሳቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። ሰው መቸም “ያዘጋጀውን ሲበሉለት፣ የወለደውን ሲስሙለት” ነውና ደስታው ይህንን ለማድረግ ዘወትርም እንሞክራለን። እነሆ አሁንም የደጀ ሰላም ዝግጅቶች በወጡ ቁጥር ያለምንም ችግር እንዲደርሷችሁ እና ለወደፊቱም ለማስቀመጥ ብትፈልጉት ቀላል ይሆንላችሁ ዘንድ አዲስ የኢ-ሜይል አቅርቦት ጀምረናል። ቀላል እና ሦስት ደረጃ ያለው ነው።

የኢሉ-አባ-ቦራው የአክራሪዎች ችግር እና ሃይማኖታዊ ምልከታዎቹ

(ደጀ ሰላማዊው)
በኢሉ-አባ-ቦራ (ገቺ) አካባቢ የቀረበው ዘገባ ብዙ ነገሮች ከውስጣችን እንዲያቃጭሉብን ከማድረጉም በላይ ብዙ ነገሮችን ዞር ብለን እንዳስታውስ አስገድዶናል :: የሆነው ሆኖ ግን ችግሩን ከውስጥም ብንመለከተው መልካም እይታ ስለመሰለን የራሳችንን እይታ እንደሚከተለው አናቅርባለን፡፡ ጣታችንን ወደ ጠላታችን ስንጠቁም ሦስቱ ወደኛ ስለሚያመለክት ከራሳችን እንጀምርና የመፍትሔውን ሐሳብ አብረን እናክልበታለን፡፡

September 26, 2010

ራሳቸው ሳይታመኑ ስለመታመን ለሚያስተምሩ በሙሉ!!

 • ከምእመናን ተሰብስቦ ለባለቤቱ ሳይደርስ የቀረ የዘማሪ ልዑል ሰገድ ዐሥር ሺሕ ብር ተመለሰ
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 26/2010፤ መስከረም 16/2003 ዓ.ም):- በአገልግሎት ላለ ለማንኛውም ሰው በቀዳሚነት የሚነገር መጽሐፋዊ ቃል “በጥቂቱ መታመን እና በብዙው መሾም” ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዘመናችን እንደአሸን ከፈሉት ሰባኪዎቻችን አካባቢ ያጣነው ደግሞ ይኼው ነው።  ለዚህ ማሳይ አንድ ታሪክ እናንሣ። መስከረም አራት ቀን፣ 2003 ዓ.ም ዘማሪ ልዑል ሰገድ ጌታቸው ለቅርብ ባልንጀራው መምህር ዘመድኩን በቀለ በስልክ ደውሎ ያሰማው የምሥራች ‹‹እልል በል! ብሬ ተመለሰ፡፡›› የሚል ቃል ነበር፡፡ በዚህ ቀን ዘማሪው ከአምስት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ታሞ በአልጋ ላይ በዋለበት ወቅት ወደ ባንኮክ ሄዶ ለመታከም እንዲችል ከምእመናን ተለግሶት ነገር ግን በእጁ ሳይደርሰው ከመንገድ ተጠልፎ የቀረበትን አሥር ሺሕ ብር አርማጌዶን ቪሲዲ ላይ “ስሙ ለሰማይ ለምድር የከበደ ሰባኪ” ተብሎ ከተጠቀሰው እና "የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች" ተብለው ከሚጠቀሱት ከነ በጋሻው ደሳለኝና ከያሬድ አደመ የጥብቅ ወዳጅ ከሆነ አንድ ቀሲስ በቼክ ተቀብሏል፡፡ (ዋናው የሰውየው ስም ሳይሆን ታሪኩ በመሆኑ ለጊዜው ስሙን ዘለነዋል)

ስለ ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን የወጣው መመሪያ ግልጽነት እንደሚጎድለው እና በእኩልነት እንደማይተገበር ተመለከተ

 •  የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የሰባክያንን እና ዘማርያንን ስምሪ ለመቆጣጠር ተስኖታል
 •  የሰባክያን ድልድል፣ የደመወዛቸው አለመሻሻል እና ስብከተ ወንጌልን እንደ ዋነኛ አገልግሎት አለመቁጠር ጉልሕ ችግሮች ሆነዋል
 • ‹‹ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት ታዋቂ ሳይሆን ዐዋቂ ሰባኪ ነው፤ በታዋቂ ሰባክያን ምእመኑ አድናቂ እንጂ ተነሳሒ አልሆነም››  (የሰሜን ወሎ ተወካይ)
 • ‹‹በዚህ ዘመን ወንጌል የእንጀራ ልጅ ሆኗል፤ ሰባኪው ከፍቅረ ንዋይ ጋራ ከተቆራኘ መጻጉዕ ይሆናል፤ ሰባኪው እና እግዚአብሔር ሳይገናኙ እሰብካለሁ ማለት መንጋውን  ማደናበር ራስንም ግራ ማጋባት ነው፤ ሰባኪው እና እግዚአብሔር ከተገናኙ ግን ባሕሩም መረቡም ዓሣውን ይሰጣሉ፤ የዓሣውም ብዛት መረቡን አይቀደውም›› (ብፁዕ አቡነ ማርቆስ)
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 25/2010፤ መስከረም 15/2003 ዓ.ም):-  ሕጋውያን ያልሆኑ ሰባክያንን እና ዘማርያንን ስለመቆጣጠር በቅዱስ ሲኖዶስ ተደንግጎ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ለመላው አህጉረ ስብከት የተላለው መመሪያ ሕጋዊ እና ሕገ ወጥ የሆኑ ሰባክያንን እና ዘማርያንን ከመለየት አኳያ ግልጽነት የሚጎድለው፣ በሁሉም አህጉረ ስብከት በተመሳሳይ መልኩ ሊተገበር ያልቻለ፣ በምትኩ ቲፎዞ እና ተቀናቃኝ የሚለይበት እንዲያውም መመሪያውን የሚያስፈጽሙ አካላትን ከሕዝቡ ጋራ በማጋጨት የልዩነት መንሥኤ እንደ ሆነ Yአህጉረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ተጠሪዎች አመለከቱ፡፡

September 23, 2010

በገቺው የአክራሪ ሙስሊሞች ሁከት 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

 •  ሁከቱ ክርስቲያኖችን በኢኮኖሚ ለማዳከም እና ለማሸማቀቅ ያለመ ነው
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 23/2010፤ መስከረም 13/2003 ዓ.ም):-  በኢሉአባቦራ ሀገረ ስብከት በገቺ ወረዳ አራት ቀበሌዎች እና ዘጠኝ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከአንድ ወር በላይ በአክራሪ ሙስሊሞች ሲፈጸም የቆየው ክርስቲያኖችን አግቶ የመውሰድ፣ መኖሪያቸውን ከብቦ የማስጨነቅ እና በሽመል የመደብደብ፣ የቡና እና ሌሎች ቋሚ ተክሎቻቸውን በሌሊት የመመንጠር፣ ሰብሎቻቸውን የማጥፋት፣ ከብቶቻቸውን ነድቶ የመውሰድ፣ አርዶ እና ተቃርጦ የመብላት የጥፋት ተግባራት መገታታቸውን እና የድርጊቱ ፈጻሚዎች የሆኑ 13 ግለሰቦች ካጠፏቸው ንብረቶች ጋራ በቁጥጥር ሥር ውለው በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የአካባቢው ደጀ ሰላማውያውን አመለከቱ፡፡

September 22, 2010

የኢሉአባቦራው የአክራሪዎች ችግር ከአንድ ቀበሌ በላይ የተዛመተ ችግር ነው

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 22/2010፤ መስከረም 12/2003 ዓ.ም):-  በኢሉ አባቦራ ሀገረ ስብከት የገቺ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከጳጉሜ አምስት ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በሚገኙ አክራሪ ሙስሊሞች ተከበው ለጥቃት ተጋልጠው እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል። ነገር ግን እማኞች እንደሚናገሩት ከሆነ የኢሉአባቦራው የአክራሪዎች ችግር ከአንድ ቀበሌ በላይ ባሉ አካባቢዎች የተዛመተ ችግር መሆኑ ታውቋል።

September 21, 2010

በስብከተ ወንጌል መስፋፋት እና መጠናከር ላይ ያተኮረ ዐውደ ትምህርት ተጀመረ

 • ዐውደ ምሕረቱ በቡድንተኛ፣ ጥቅመኛ እና ፌዘኛ ሰባክያን ተሞልቷል
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 21/2010፤ መስከረም 11/2003 ዓ.ም):-  በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚደረገው ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋት እና የማጠናከር ጥረት ዐውደ ምሕረቱ ቀላል ግምት በማይሰጣቸው ቡድንተኛ፣ ለቁሳቁስ እና ለገንዘብ ፍቅር ተላልፈው በተሰጡ እና ለምእመናኑ ዋዛ ፈዛዛ እየተናገሩ ካላሣሣቁ ያስተማሩ በማይመስላቸው ሰባክያን እየተሞላ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

የገቺ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአክራሪ ሙስሊሞች ተከበዋል


(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 21/2010፤ መስከረም 11/2003 ዓ.ም):-  በኢሉ አባቦራ ሀገረ ስብከት የገቺ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከጳጉሜ አምስት ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በሚገኙ አክራሪ ሙስሊሞች ተከበው ለጥቃት ተጋልጠው እንደሚገኙ በስፍራው የሚገኙ የዐይን ምስክሮች ለደጀ ሰላም ገለጹ፡፡

September 20, 2010

ቤተ ክህነቱ ያጣው የቤተ ክህነቱ ሰው

(ባሮክ ዘሣልሳይ ሺሕ)
1. መግቢያ
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ከጳጳሳቱ ሰብእና አንጻር ቤተክህነቱ ያለበትን ሁኔታ ማሳየት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ምእመኑ የቤተክርስቲያኗን ሐዋርያዊነት እና ርእቱነት ከጳጳሳቱ ተክለ ሰብእና አኳያ እንዳይመዝን በሒደት ማመልከትና ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይገባ መርዳት ነው፡፡ በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ በአባቶቹ ላይ ከሚታዩ ጉድለቶች በመነሣት በእምነቷ፣ በትውፊቷ፣ በቀኖናዋና በታሪኳ ርቱእነት እና ሐዋርያነት ላይ ምንም ዓይነት ብዥታ እንዳይፈጠርበት በቅድሚያ አሳስባለሁ፡፡ የቤተክርስቲያኗ ርቱእነት እና ሐዋርያነት የሚለካው በሰዎች ሰብአዊ ጉድለትና ድቀት ሳይሆን ወልድ ዋሕድ በሚለው መሠረተ እምነቷ እና ይኽን መሠረተ እምነት ነቢያት፣ ሐዋርያት ከአስተማሩበት ሥርዓተ ትምህርት አኳያ በመሆኑ ነውና፡፡

አቡነ ፋኑኤል ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ ተጠየቀ

 • የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤን በሕገ ወጥ መንገድ ለማስመረጥ የተደረገው ሙከራ በምእመናን ተቃውሞ ከሸፈ
 • ሊቀ ጳጳሱ የአጣሪ ኮሚቴውን ተግባር ለማሰናከል እየጣሩ ነው
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 20/2010፤ መስከረም 10/2003 ዓ.ም):-  ለካህናት እና ምእመናን ያላቸውን ንቀት እና አነስተኛ አባታዊ ክብር በተደጋጋሚ በማሳየት የሚታወቁት የሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል ሀገረ ስብከቱን ለመምራት ባለባቸው ከፍተኛ የብቃት ማነስ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገረ ስብከቱ እየተባባሱ ለመጡት ውዝግቦች መንሥኤ በመሆናቸው ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ የሐዋሳ ከተማ ምእመናን ጠየቁ፡፡ ምእመናኑ ከሊቀ ጳጳሱ በተጨማሪ በእርሳቸው አቅራቢነት ከፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ በሕገ ወጥ መንገድ የተሾሙት መልአከ ኀይል አባ ገብረ ጊዮርጊስ አብርሃም ከደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪነት ሐላፊነታቸው እንዲወገዱ ጠይቀዋል፤ ይህንኑ ጥያቄ ለሚመለከታቸው የመንግሥት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካላት አቅርበው እና ተከታትለው የሚያስፈጽሙ የምእመናን ተወካዮችንም መርጠዋል፡፡

September 19, 2010

በሐዋሳ ገብርኤል ሊካሄድ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ምርጫ በሕዝበ ክርስቲያኑ ተቃውሞ ተሰናከለ፤

  . የገዳሙ አጥቢያ ምእመናን ሕገ ወጡን ምርጫ ተቃውመዋል፣ 
  . ሊቀ ጳጳሱ የአጣሪ ኮሚቴውን ተግባር ለማሰናከል እየጣሩ ነው፣

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 19/2010፤ መስከረም 9/2003 ዓ.ም):-  በአገልግሎት ላይ ያለውን የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደንብ(ቃለ ዓዋዲ) እና በገዳሙ የውስጥ አስተዳደር ከተደነገገው ውጭ ከሀገረ ስብከቱ በተላከ ግለሰብ በተጠቆሙ አስመራጮች ዛሬ እሑድ ለማካሄድ ታቀዶ የነበረው ምርጫ በጽኑ ተቃውሞ ገጥሞት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ዝርዝሩን እንዳጠናቀቅን የምናቀርብ ሆኖ ለዚህ ተቃውሞ መንደርደሪያ የነበረውን ጉዳይ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

September 18, 2010

መንግሥት ከጳጳሳቱ ጋራ የሚያደርገው ውይይት እንደቀጠለ ነው

 • የጥቅምቱ ሲኖዶስ የመንግሥት እና ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ግንኙነ ከመወሰን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ከመፍታት አኳያ ወሳኝ ጉባኤ መሆን እንደሚገባው ተገለጸ
 • ‹‹እኛ ይህን መንበር ከያዝን በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላም አጣች፤ ተደፈረች›› (ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ)
 •  ‹‹የብፁዓን አባቶችን መኖሪያ ቤት የሰበሩ እና ብፁዓን አባቶችን የደበደቡ ለምን ለፍርድ አልቀረቡም?›› (ብፁዕ አቡነ ሚካኤል)
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 18/2010፤ መስከረም 8/2003 ዓ.ም):-:- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፕትርክና ራሷን ከቻለችበት ጊዜ አንሥቶ ያሉት ኀምሳ ዓመታት ሰላሟን ያጣችበት እንደ ሆነ፣ በተለይም አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሥልጣን የቆዩባቸው ያለፉት 18 ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቱ ክብሯ የተደፈረበት እና በእጅጉ የተዋረደችበት ወቅት መሆኑን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ተወካይ ጋራ ውይይት የተቀመጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተናገሩ፡፡ ጳጉሜን አራት ቀን 2002 ዓ.ም ተጀምሮ መስከረም ስድስት ቀን 2003 ዓ.ም ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ቀጥሎ በዋለው አራተኛ ዙር ስብሰባ ቀደም ሲል በነበሩት ውይይቶች ያልተገኙ፣ በአመዛኙ የተቃውሞ አቋም እንዳላቸው የሚታመኑ እና ለጊዜው በአዲስ አበባ የቆዩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ መረሳ ረዳ ጋራ ኀይለ ቃል እና ተግሣጽ የበዛባቸው የሐሳብ ልውውጦችን አድርገዋል፡፡

September 15, 2010

የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ባለ ሥልጣን አቡነ ፋኑኤልን አስጠነቀቁ፤ ያሬድ አደመ ከማንኛውም የመድረክ አገልግሎት ታገደ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 15/2010፤ መስከረም 5/2003 ዓ.ም):- ነሐሴ 21 ቀን ማምሻውን በሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል፣ “ምእመናን ሁላችሁ በዚህ ጉባኤ ተሳተፉ፤ ባትሳተፉ. . . !” በሚል ማሳሰቢያ ተጀምሮ ከነሐሴ 22 - 23 ቀን 2002 ዓ.ም በሐዋሳ መስቀል አደባባይ ከተካሄደው የእነ በጋሻው ደሳለኝ ስብሰባ በኋላ ያሉት የሳምንቱ ዕለታት ለቡድኑ የተመቹ አይመስሉም፤ እንዲያውም “እኛ የፈቀድነው ካልሆነ በቀር የደቡብን ምድር የሚረግጣት ሰባኪ እና ዘማሪ አይኖርም” በሚል የነዟት ውርድ ወደ ራሳቸው መልሳ ያስተጋባችበት እና ክፉኛ የተቀለበሰችበት አሳፋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል። በአቡነ ፋኑኤል አገላለጽ “ጥንቃቄ የጎደለው” የቡድኑ ቀንደኛ መሪዎች ጠባይዕ በቀቢጸ ተስፋ ፈጦ እና ገጦ እየወጣ መመለሻ ወደሌለው አዘቅት ይዟቸው እየነጎደ ይመስላል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

መንግሥት ከፓትርያርኩ እና ከጳጳሳቱ ጋር ምሥጢራዊ ስብሰባ አካሄደ፣ ማሳሰቢያም ሰጠ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 15/2010፤ መስከረም 5/2003 ዓ.ም):-  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር እና በየደረጃው በሚገኙ አካላት በየጊዜው የሚፈጸሙ በደሎች እየተባባሱ ሕዝቡን በሚያስቆጡበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውንና ሕዝባዊ ቁጣው እየከፋ ሄዶ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ዕንቅፋት ከመሆኑ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በራሱ ውስጣዊ ተቋማዊ አሠራር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሻ፣ “መንግሥት በቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት  የሚገደደው ሲኖዶሱ በሙሉ ሥልጣኑ እና ኀይሉ    እየወሰነ ስለማይሠራ መሆኑን፤ አባቶች በተለይም ፓትርያርኩ የሚፈጽሟቸው ምእመኑን የሚያስቆጡ ተግባራት ውለው አድረው ለአገሪቱ ሰላም እና ልማት ዕንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ በአስቸኳይ ይቋጭ” ሲል መንግሥት ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡

September 14, 2010

መንግሥት “በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም” ተባለ እንጂ ሃይማኖት ላይ ወንጀል ሲፈጸም ዝም ይላል ተባለ እንዴ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 14/2010፤ መስከረም 4/2003 ዓ.ም):- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን “ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነጻ ወጣች” ከተባለ አሥርት ዓመታት እየተቆጠረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ የመንግሥትን ሕጋዊ ከለላ ያጣች ከመሰለችበት ደረጃ ደርሳለች። በዚህች መጦመሪያ መድረካችን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ዓይን ያወጡ ወንጀሎችን ብናትትም፣ ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች የእኛን ጩኸት እየጮኹ ቢገኙም፣ ምእመናንንም አቤቱታተቸውን ቢያሰሙም መንግሥት እና የዜጎች መብት ማስከበሪያ ማሽኑ ሊሰማ አልቻለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ የቤተ ክርስቲያን ባልሆኑ ሰዎች ስትመዘበር እና ስትበረበር፣ ሕግ ሲፈርስ እና አገራዊ ሞራልና ስብዕና ሲናድ መንግሥት ዳር ቆሞ እየተመለከተ ነው ወይም “አበጃችሁ” ባይ ሆኗል።

September 11, 2010

“አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ለእናንተ አድርጉ” /ሕዝ 18፥31/

(በማሞ አየነው፤ ከማ/ቅዱሳን ድረ ገጽ የተወሰደ)፦ የሰው ልጅ ለሥጋዊና መንፈሳዊ እንቅስቃሴው አመች በሆነ መልኩ እግዚአብሔር ለሚያፈራርቃቸው ዘመናት ቀመር ሲያወጣ ኖሯል፡፡ ጊዜያትንም ከደቂቃ ሽራፊ እስከ ሺህ ዘመናት ድረስ ከፋፍሎ ይጠቀማል፡፡ በዚህ የጊዜ ቀመርም ትናንትን ያስረጃል፤ ዛሬን ደግሞ አዲስ ያደርጋል፡፡ በጊዜ ዑደትም ብዙ ሺህ አዲስ ዓመታት አልፈው ብዙ ሺህ አዲስ ዓመታት መጥተዋል፡፡ የዘመናት መፈራረቅ ሰው የእግዚአብሔርን ሥራ እንዲያደንቅ፣ መግቦቱንም እንዳይረሳ ያደርጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ቃል ኪዳኑን እንዳልረሳ፣ ፍጥረቱን እንዳልዘነጋ ያመለክታል፡፡

September 10, 2010

ዘሪሁን ሙላቱ ወደ ቃሊቲ ወኅኒ ቤት ወረደ

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 10/2010፤ ጳጉሜን 5/2002 ዓ.ም):- የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘሪሁን ሙላቱ የግል ተበዳዮች ነን ባሉት በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የቀረቡበትን የሰው ምስክሮች እንዲከላከል በመወሰን ጉዳዩን ለመመልከት ለመስከረም 14 ቀን 2003 ዓ.ም ቀጠረ፡፡ እስከዚያው ድረስ ተጠርጣሪው ማረፊያ እና ምግብ ወደሚያገኝበት ወደ ቃሊቲ ወኅኒ ቤት ተዛውሮ እንዲቆይ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

September 9, 2010

ሁለቱ ማኅበራት:- "የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር" እና "የአገልጋዮች ኅብረት"

(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 9/2010፤ ጳጉሜን 4/2002 ዓ.ም):- ነሐሴ 23 ቀን 2002 ዓ.ም ‹‹የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን ማኅበር›› ከኮሌጁ ደቀ መዛሙርት እና ከኮሌጁ አስተዳደር ጋራ በመተባበር ሲደክሙበት የቆዩትን የስብከተ ወንጌል ጉባኤ እንዲሁም በጥሬው እና በቃል ኪዳን ከመቶ ሺሕ ብር በላይ የተገኘበት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በማካሄድ የተግባር አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ‹የአገልግሎት ስልት ለውጥ› እንደሚያስፈልገው አመለከተ

  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 8/2010፤ ጳጉሜን 3/2002 ዓ.ም):- ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ተዋቅሮ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በማበርከት ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ከነሐሴ 22 - 23 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ በ2000 ዓ.ም ያወጣውን የአራት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ሁለተኛ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል::

  September 8, 2010

  በዋስ እንዲለቀቅ የተወሰነለት ዘሪሁን ዳግመኛ ተይዞ ፍርድ ቤት ቀረበ

  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 8/2010፤ ጳጉሜን 3/2002 ዓ.ም):-  በእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና በጋሻው ደሳለኝ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት ዘሪሁን ሙላቱ በተከሰሰበት ጉዳይ በቂ ማስረጃ ያልቀረበበት በመሆኑ በትናንትናው ዕለት በ2500 ብር ዋስ እንዲለቀቅ በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍረድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የተወሰነለት ቢሆንም “የግል ተበዳይ ነን” ያሉት እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ‹‹ፖሊስ አላግባብ ለቆብናል›› በሚል በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ይግባኝ በመጠየቅ ባመለከቱት መሠረት ተጠርጣሪው ከመንገድ ተይዞ በማረፊያ ቤት ካደረ በኋላ ዛሬ ጠዋት በችሎቱ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

  የሐምቡርግ ኪዳነ ምሕረት ቅዳሴ ቤት ተከበረ  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 8/2010፤ ጳጉሜን 3/2002 ዓ.ም):- በሀገረ ጀርመን የሐምቡርግ ኪዳነ ምሕረት ቅዳሴ ቤት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ በመሩት ደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ተከበረ፡፡

  ዘሪሁን ሙላቱ በ2500 ብር ዋስ ተለቀቀ

  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 8/2010፤ ጳጉሜን 3/2002 ዓ.ም):- በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ለ2500 ብር የሚበቃ ዋስ ጠርቶ ወይም 2500 ብር አስይዞ በዋስ እንዲፈታ የአዲስ አበባ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ውሳኔ ሰጠ፡፡ በተለምዶ አፍንጮ በር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ በትናንት ዕለት ረፋድ ላይ በሰጠው በዚሁ ውሳኔ በ‹መጽሐፉ› የግል ተበዳይ ነን ያሉት እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ክስ ባቀረቡበት ጉዳይ በተጠርጣሪው ላይ በቂ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻላቸውን በመጥቀስ ተችቷል፡፡ የአንድን ግለሰብ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት ከዚህ በላይ አግዶ መቆየት ተገቢ ባለመሆኑ ተጠርጣሪው ለ2500 ብር የሚበቃ ዋስትና አቅርቦ እንዲለቀቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

  September 7, 2010

  በለንደን በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ቀልብን የሳበው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ

  (ነጻ አስተያየት ከለንደን - ታምሩ ገዳ):-የለንደን ከተማ ላለፉት ስድስት ሣምንታት በይዘቱ እና በዓይነቱ ታላቅ ትኩረት የሳበ መንፈሳዊ አገልግሎትን በማስተናገድ ተጠምዳ ሰንብታለች። ይህ ማዕከሉን በለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በማድረግ በለንደን ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ በአውሮፓ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ የተካሄደው የመላው አውሮፓ ዓመታዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ  ሐምሌ 9 – 11 2002 ዓ.ም  (ጁላይ 16 – 18 2010 ) እንዲሁም 3ኛው የደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ መንፈሳዊ ጉባኤዎች ጥምረት የአብዛኛው የለንደን ምዕመናን ስሜት የገዛ ነበር።

  September 2, 2010

  የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች በአደጋ ውስጥ ናቸው ተባለ

  (ለደጀ ሰላም መጦመሪያ፤ ታምሩ ገዳ ከለንደን):- ኢትዮጵያን በለም  በታሪክ እና በቅርስ ባለቤትነት ተጠቃሽ ከሆኑት ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን ያደረጓት ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶቿ እጅግ አስጊ በሆነ የመጥፋት አዝማሚያ ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ። “የኢትዮጵያ ገዳማት ፣ አድባራት እና የአብነት ት/ቤቶች (የቆሎ ት/ቤቶች) ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ” በሚል ርዕስ ዙሪያ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ በማድረግ ለግንዛቤ ያህል ለንደን ውስጥ ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  አማኞች እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ባለፈው ሣምንት ገለጻ ያደረጉት

  September 1, 2010

  ያሬድ አደመ በኮፒ ራይት ጥሰት ሊከሰስ ነው

  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 1/2001፤ ነሐሴ 26/2002 ዓ.ም):- የሐውልቱ ቡድን አባል የሆነው እና በቅርቡ በሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤት ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ ሆኖ በአቡነ ፋኑኤል የተሾመው ላእከ ወንጌል ያሬድ አደመ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 496/10 ስለ አእምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ የተደነገገውን በመተላለፍ ያለባለቤቶቹ ፈቃድ ባሳተማቸው አራት የመዝሙር መጻሕፍት፣ “ያልተገባ ጥቅም አግኝቷል፤ በአሳታሚዎቹ ላይ ከሃያ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ኪሳራ አድርሷል” በሚል በኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ክስ ሊመሠረትበት ነው፡፡

  ሐውልቱን በመቃወም የተጠረጠሩት የቦሌ መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ጸሐፊ ከቦታቸው ተነሡ

  • አ.አ የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊዎች ዝውውር ተበራክቷል
  • ጸሐፊዎች በመቶ የአንድ ሺሕ ብር ጉቦ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ
  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 1/2001፤ ነሐሴ 26/2002 ዓ.ም):- የቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ጸሐፊ ሆነው ሲሠሩ የቆዩት መምህር የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ወደ ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተዘዋወሩ - የዝውውሩ መንሥኤ በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ ሳቢያ በስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት እና በካቴድራሉ የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ የሆነው ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ፣ ‹‹ለረጅም ጊዜ በሥራው ላይ እንደማይገኝ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሪፖርት አላቀረብኽም›› በሚል እንደ ሆነ ተመልክቷል፡፡ ይኹንና አንዳንድ የዜናው ምንጮች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በጸሐፊነት ደርበው የሚሠሩት መምህር የማነ ከካቴድራሉ ጸሐፊነታቸው የተነሡበት ዐቢይ ምክንያት በካቴድራሉ ደጃፍ የቆመው የአቡነ ጳውሎስ ‹‹ሐውልተ - ስም›› ተቃዋሚ በመሆናቸውም ጭምር ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

  “የትኛው ሰባኪ፣ የትኛው ዘማሪ እዚህ አደባባይ መቆም እንዳለበት ወስነን እስክንነግራችሁ ድረስ በያላችሁበት ቁሙ!!” (በጋሻው ደሳለኝ)


  (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 1/2001፤ ነሐሴ 26/2002 ዓ.ም):- ከነሐሴ 22 – 23 ቀን 2002 ዓ.ም በሐዋሳ መስቀል አደባባይ በተጠራው እና በበርካታ የፕሮቴስታንት አብያተ እምነት ተከታዮች ተሞልቶ በነበረው እንግልጋ (ስብስብ) “የቅድስት ማርያም ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ማኅበር›” እየተባለ የሚጠራ ቡድን ቃል አቀባይ የሆነው በጋሻው ደሳለኝ “‹…ክልሉ የኛ ነው፤ ከዚህ በኋላ የትኛው ሰባኪ፣ የትኛው ዘማሪ እዚህ አደባባይ ላይ መቆም፣ ይህችን ምድር መርገጥ እንዳለበት ወስነን በቅርብ ቀን እንገልጽላችኋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ በያላችሁበት ቁሙ!›› ማቱን በሐዋሳ የደጀ ሰላም ምንጮች አመለከቱ፡፡

  ፍርድ ቤቱ በዘሪሁን ሙላቱ ላይ ሦስተኛ ቀጠሮ ሰጠ


   (ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 1/2001፤ ነሐሴ 26/2002 ዓ.ም):- የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞችበሚለው መጽሐፍሳቢያ የስም ማጥፋት ክስ የቀረበበትን የሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱን ጉዳይ የሚመለከተው በአዲስ አበባ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በተጠርጣሪው ላይ የሚሰበሰቡት መረጃዎች እንዲጠናቀቁ በማሳሰብ ለጳጉሜን ሁለት ቀን 2002 .ም ጠዋት ሦስተኛ ቀጠሮ ሰጠ፡፡

  ማስታወቂያ፦ የድረ ገጽ አድራሻ ለውጥ

  የሎስ አንጀለስ ቅድስት ሥላሴ ወገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን  ሰበካ ጉባኤ ይህንን ዌብሳይት (http://www.kidistselassie.org) የዕለት ከዕለት የሰበካ ጉባኤ እንቅቃሴ እንድንዘግብበት ጥያቄ ሰላቀረበልን  ከዛሬ ጀምሮ አብነት ትምህርት ቤታችንን  “ደበሎ”  በሚል ስያሜ፤ http://debelo.org በማለት የቀየርነው መሆኑን ተጠቃሚዎቻችን እንዲያውቁት ስንገልጽ ይህ አጋጣሚ ግን የአብነት ትምህርት ቤታችንንም በተደራጀና ስፋት ባለው ሁኔታ ለማቅርብ እንደሚመች በአክብሮት እናሳስባለን።

  Blog Archive

  የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

  ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)