August 2, 2010

በሐዋሳ የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት እና የሀገረ ስብከቱ ‹ልኡካን› ውዝግብ

  • ‹‹ከእኛ ወገን አልያም ከዐመፀኛ ኀይሎች ጋራ ለመኾናችሁ ሚናችኹን ለዩ! በእንጀራችኹ ፍረዱ!! ፓትርያሪኩም ቢኾኑ አያድኗችኹም!!›› (አቡነ ፋኑኤል)
  • ‹‹በእንጀራችሁ ፍረዱ!›› (ሥራ አስኪያጁ)
(ደጀ ሰላም፣ ኦገስት 2/2010)፦ በሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት በሐዋሳ ከተማ በሚገኙ ሦስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከቃለ ዐዋዲው ውጭ የሰበካ ጉባኤ አባላትን እንዲያስመርጡ ከሀገረ ስብከቱ በተላኩ ግለሰቦች ሳቢያ ውዝግብ ተቀሰቀሰ፤ በውዝግቡ የተልእኮው አስፈጻሚ እና ተባባሪ ኾነው የመጡ ራሱን ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ፀረ - ኤድስ ማኅበር›› እያለ የሚጠራው ቡድን አባላት በተቃወሟቸው የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ላይ አካላዊ ጥቃት አድርሰዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በመንበረ ጵጵስናው ትእዛዝ እና ራሳቸው በማስፈራራት የሰበሰቧቸውን ካህናት በሁለት መኪና ጭነው ወደ ፓትርያሪኩ ለመግባት እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ድርጊቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሐምሌ 12 ቀን 2002 ዓ.ም የሀገረ ስብከቱን አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አለቆች እና ካህናትን በመንበረ ጵጵስናው ሰብስበው፣ ‹‹በሀገረ ስብከቱ ወሳኙ እኔ ነኝ፤ አላያችኹም እንዴ አለቃውን [አባ ገብረ ዋሕድን] መንቅሬ እንዳስወጣኹት፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ቢኾን በሲኖዶሱ ያለኹት እኔው ነኝ፤... ከእኛ ወገን ናችሁ ወይስ ከዐመፀኛ ኀይሎች ጋራ? አቋማችኹን ለዩ! ፓትርያሪኩም ቢኾኑ አያድኗችኹም!!›› ማለታቸውን ተከትሎ የተፈጸመ መኾኑን የደጀ ሰላም ምንጮች ተናግረዋል፡፡
- - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - - -
ትላንት ሐምሌ 25 ቀን 2002 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ በሚገኙት የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ የኆኅተ ሰማይ በዓለ ወልድ እና የዳቶ ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያን፣ ‹‹የቀድሞውን የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር በመለወጥ አዲስ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ እናካሂዳለን፤›› በሚሉ ከሀገረ ስብከት በመጡ ልኡካን እና ድርጊቱ የሰበካ ጉባኤውን ቃለ ዐዋዲ አንቀጽ ስምንት እና ዘጠኝ እንደሚጥስ በተቃወሙ የየአጥቢያዎቹ ምእመናን መካከል ውዝግብ ተቀስቅሶ እንደ ነበር የደጀ ሰላም ምንጮች ገለጹ፡፡ መልእክተኞቹ ለሕገ ወጥ ተልእኳቸው መሠረት ያደረጉት በተለይም ለሀገረ ስብከቱ ብልሹ አሠራር አልመች ባሉት ሦስቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሐምሌ 12 ቀን 2002 ዓ.ም አዲስ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ እንዲካሄድ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ፊርማ የታዘዘበትን ደብዳቤ በመያዝ ነው፡፡ ድርጊቱ ሐምሌ 22 ቀን 2002 ዓ.ም የሐዋሳ ምእመናን ተወካዮች ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ ባደረጉት ውይይት የአጣሪ ኮሚቴው ተግባር እስኪጠናቀቅ ድረስ የሰበካ ጉባኤ አባላት ምርጫ እንዳይካሄድ የተደረሰውን ስምምነት የሚፃረር እንደ ኾነ አስተያየታቸውን ለደጀ ሰላም የሰጡ ምእመናን ተናግረዋል፡፡

የሕገ ወጡ ምርጫ አስፈጻሚ ኾነው የተላኩት ግለሰቦች፣ በኆኅተ ሰማይ በዓለ ወልድ - በኩረ ትጉሃን አማረ ግርማ እና መጋቤ ልኡካን አንዳርጋቸው፣ በዳቶ ኪዳነ ምሕረት ቀሲስ አስረስ እና መጋቤ አእላፍ ኀይለ ጽዮን፣ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ በአቡነ ፋኑኤል ‹መጋቤ ልኡካን› የተባለው ያሬድ አደመ፣ ጌራ ወርቅ እና መጋቤ ሐዲስ ፍሥሐ ለማ የሚባሉ ናቸው፡፡ አሁን በሐላፊነት የሚገኙ የየአጥቢያው ሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት ዕድል አግኝተው አንዳችም ሐሳብ እንዳይሰጡ መድረክ እንዲነፈጉ፣ የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች እና አገልጋይ ካህናት፣ ‹‹ከእኛ ወገን ናችሁ ወይስ ከሌላ - አቋማችኹን ለዩ!›› እየተባለ ከሊቀ ጳጳሱ የተሰጠው ትእዛዝ ግልጽ ወጥቶ በልኡካኑ ይነገርበት የነበረው ይኸው ተልእኮ ከምእመናን ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ በተለይም በኆኅተ ሰማይ በዓለ ወልድ ምእመናኑ የሰበካ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲ አንቀጽ ስምንት እና ዘጠኝ ወጥቶ እንዲነበብ በማድረግ ልኡካኑን ፊት ለፊት ‹‹አንቀበላችኹም!›› ብለዋቸዋል፡፡ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ደግሞ የሕገ ወጡ ተልእኮ አስፈጻሚ ቡድን መሪ ኾኖ የመጣው ያሬድ አደመ፣ ‹‹አንተ ከዚህ በፊት የፈጸምኸው የሙስና ተግባር ሳያንስህ አሁን ዳግመኛ ተመልሰኽ ለምን ትበጠብጠናለኽ?›› የሚል ጠንካራ ተቃውሞ ከምእመናኑ ሲገጥመው እርሱን ተከትለው የመጡ የ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ፀረ-ኤድስ ማኅበር›› አባላት ውዝግቡን በማባባስ የተቃወሟቸውን እስከ መደብደብ መድረሳቸውን ትዕይንቱን በምስል ወድምፅ ያስቀሩ የደጀ ሰላም ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ እነዚሁ የማፊያ ቡድን አባላት ከቀትር በኋላ በመደበኛው የገዳሙ ሰንበት ት/ቤት መርሐ ግብር ሰዓት በስፍራው በመገኘት ‹‹አዲስ የሰንበት ት/ቤት አመራር እናስመርጣለን፤›› በሚል ተጨማሪ ሁከት መቀስቀሳቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚሁ ሁከት በያሬድ አደመ የተደራጁ የ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ፀረ-ኤድስ ማኅበር›› ወጣቶች የሰንበት ት/ቤቱን አባላት ደብደበዋል፤ በድብደባው መኳንንት አየለ የተባለ የሰንበት ት/ቤቱ አባል ጥርስ መጎዳቱን ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ እነ ያሬድ አደመ ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ደብዳቤ እና በሕገ ወጥ መንገድ በተሾሙት የደብሩ አስተዳዳሪ አባ ኀይለ ጊዮርጊስ አብርሃም አይዞህ ባይነት የሰንበት ት/ቤቱን ቁልፍ ሠብረው በሌላ ቁልፍ በመለወጥ ከቃለ ዐዋዲው እና ከጠቅላላ ጉባኤው ዕውቅና ውጭ አዲስ አመራር በመተካታቸው በሕጋዊው የሰንበት ት/ቤቱ አመራር መከሰሳቸውን መግለጻችን ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ለዓመታት ባደረሱት አስተዳደራዊ በደል እና ዐይን ባወጣ ሙሰኛነታቸው ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ የምእመናን አቤቱታ የቀረበባቸው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ፀሐይ መልአኩ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን አድባራት አለቆች እና የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊዎች በማስፈራራት የሀገረ ስብከቱን ችግር በሚያጣራው ኮሚቴ ላይ ከወዲሁ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መኾኑን ውስጥ ዐዋቂ ደጀ ሰላማውያን ገለጹ፡፡

ምንጮች ለደጀ ሰላም እንዳደረሱት ነገሩ ባጭሩ እንዲህ ነው፤ ሐምሌ 23 ቀን 2002 ዓ.ም ሥራ አስኪያጁ የደብር አለቆች እና ጸሐፊዎች የየሰበካ ጉባኤያቸውን ማኅተም በመያዝ እንዲመጡ ያዝዛሉ፡፡ የታዘዙትን ከማድረግ በቀር ምርጫ የሌላቸው አስተዳዳሪዎች እና ጸሐፊዎችም፣ ‹‹ሥራ አስኪያጁ ትጉህ አገልጋይ ናቸው፤ ለአጭር ጊዜ የታሰሩት በፀረ ሰላም እና አሸባሪ ኀይሎች ተንኮል ነው፤ ይኹንና በቅዱስ ፓትርያሪኩ ጥረት ሊፈቱ ችለዋል፤...›› የመሳሰለው ይዘት ባዘለው እና ራሳቸው ሥራ አስኪያጁ ባዘጋጁት ደብዳቤ ላይ እንዲፈርሙ ያስገድዷቸዋል፡፡ እነርሱ ይህን ሲቃወሙ አጅሬ ወዲያው የእያንዳንዳቸውን ማኅተም እየተቀበሉ ባዘጋጁት ጽሑፍ ላይ ያትሙበታል፡፡

በዚህ አሳፋሪ አካሄድ ያልተገቱት ሥራ አስኪያጅ ወደ ሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ተመልሰው እንደለመዱት እነርሱንም ፈርሙ ይሏቸዋል፤ ካህናት አባቶች ጭምር የሚገኙባቸው የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም፣ ‹‹እንዴት ተደርጎ! ፀረ ሰላም የምንላቸውኮ የንስሐ ልጆቻችን የኾኑ ምእመናን ናቸው፤ እናውቃቸዋለን፤ እንደምን በእነርሱ ላይ እንፈርማለን? ስለ እርስዎ በጎነት መፈረም እንችላለን፤›› ይሏቸዋል፡፡ በዚህ የተበሳጩት ሥራ አስኪያጅም ‹‹በእንጀራችኹ ፍረዱ!!›› እንዳሏቸው እነዚሁ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ጫና ዓላማ ካህናቱን አስፈራርተው እና ይዘው ሄደው ወደ ፓትርያሪኩ በመግባት ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ፣ በአጣሪ ኮሚቴው ምርመራ ሂደት እና ውጤት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር በማሰብ እንደ ኾነ ኹኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ ምእመናን ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በአድባራት አለቆች እና አገልጋይ ካህናት እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች መካከል ከፍተኛ ግራ መጋባትን የፈጠረ መኾኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

4 comments:

Anonymous said...

እግዚኦ አቤቱ ይቅር በለን::

Anonymous said...

Thank you DS

zekere said...

egziabher yebarkachhu ds

Unknown said...

እግዚአብሄር ልብ ይሰጥልን!

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)