August 5, 2010

እርቅ በማያውቁ አባቶች እና በ“ሰላም ድርድራቸው” ዙሪያ መታወቅ ያለባቸው ነጥቦች

(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 4/2010):- ሰላምን ልትሰብክ በተመሠረተች፣ ስትሰብክም በምትኖር ቤተ ክርስቲያን ላይ በተሾሙ አባቶች መካከል ሰላም ከራቀ፤ ከደካማ ሥጋችን በእውነት የተዋሐደውን አምላክ እየሰበከች «ተዋሕዶ» የምትባልን ቤተ ክርስቲያን እንዲመሩ በተሾሙ አባቶች መካከል  በእውነት መዋሐድ ከጠፋ ይኸውና አንድ ሕጻን ተወልዶ ለዐቅመ አዳም ደረሰ፡፡ በእነሱ ሳይኾን በፈጠሩት ችግር ዕድሜ መጠን ሲያስቡ ቆይተው ይመስላል፤ ይኸውና ችግሩ 19 ዓመት ሞልቶት ለአካለ መጠን ሲደርስ ሰላምን በመካከላቸው ለማውረድ ለውይይት መቀመጣቸውን ሰምተን፣ በዚህም በእጅጉ ደስ ብሎን ነበር። ምክንያቱም በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ይጠብቁ፣ መንጋውንም ይሰበስቡ ዘንድ የተቀመጡትን አባቶች መለያየት እያየን፤ ያንንም ተገን አድርጎ በየደረጃው ባለው የቤተ ክርስቲያን ምልአት የሚፈጠሩ የጥፋት ሆያ ሆዬዎችን እያየን ስናዝን ኖረናልና፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል ተከስቶ የአንድ ወጣት ዕድሜ ያስቆጠረው ችግር መፈታት ማለት ብዙ ነገር ነው፡፡ ከሁሉም በፊት እንኳን ችግሩን እኛው ፈጥረነለት፣ ችግር ሳንፈጥርም መለያየት ይፈጠር ዘንድ “የማይበረብረው ዝናር፣ የማይወረውረው ጦር” የሌለው ዲያብሎስ በዚህ ውይይት ያፍር ነበር፡፡ በእኛ ፈንታ እሱ ይሳቀቃል፡፡ እሱ ሲሳቀቅና ሲያፍር ደግሞ በቅተው በመገኘታቸው እግዚአብሔር መርጦ ለሹመት ያበቃቸው አባቶች ወደ ልቡናቸው ይመለሱና የሕጻን ጨዋታቸውን ያቆማሉ፡፡ ለመረጣቸው አምላክ ያድራሉ፡፡ ከማስበርገግና ከማሳፈር ይልቅ በፍቅራቸውና በመዐዛ ቅዳሴ ወትምህርታቸው በጎቹን ይሰበስባሉ፡፡ አጅሬ ሲያፍርና ሲሳቀቅ በእሱ አነቃቂነት ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ለ18 ዓመታት የበቀሉት ልዩ ልዩ አረሞች ተነቅለው ይጣላሉ፡፡ ምናልባት ለወዲያው መነቀል ባይችሉ በየበቀሉበት እየደረቁ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የአንድነት ዝማሬና አገልግሎት እየተረጋገጡ ትቢያ ይኾናሉ፡፡

ዛሬ አካለ መጠን ደረሰ ያልነው ችግር በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ከተጣበቀበት ጊዜ ጀምሮ በዲያብሎስ ተብታቢነት ቤተ ክርስቲያናችን በብዙ ችግሮች ተወጥራ ቆይታለች፡፡ አሁንም እንደተወጠረች ትገኛለች፡፡ በመመረጣቸው የተቀዳጁትን አክሊል /አስኬማ/ ከልለው ስለእውነት እውነትን የሚያገለግሉ፤ አርአያ የሚኾኑን አበው ቁጥር ቀንሶብናል፡፡ በእርባና ቢስነቱ ዓለም ገሸሽ ያደረገው ጎጣዊ አስተሳሰብ በቤታችን ሙቀት ልምላሜ እየተሰማው አለ፡፡ ፍቅረ ንዋይ ካለ ቤቱ ገብቶ ይሽሞነሞናል፡፡ በዚህም በዚያም በሚያስገርም ሁኔታ ለአስተዳደር ያልተጠሩ፣ ለማስተባበር ያልተመረጡ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኗ ማዕከላዊ ጉዳይ ዋና ተዋንያን ወተዋንያት ኾነው ይታያሉ፡፡ በዚህም «በእኔ የሕይወት ዘመን ባልኾነ» የምንላቸው አሰቃቂ ተግባራት በተቀደሰው ስፍራ ሲፈጸሙ ዐይተናል፡፡ የአባቶችን ልዩነት በማባባስ ቤተ ክርስቲያኗን ለማፍረስ የኑፋቄ ፈንጃቸውን ታጥቀው በግራም በቀኝም የተሰገሰጉ መናፍቃንና ሙዋርተኞች በዝተዋል፡፡ ከንቱ ግለሰቦች የተቀደሰችውን ቤተ ክርስቲያን ለግል ዓላማቸው /ፖለቲካ፣ ገንዘብና የግል ዝና/ ማስፈጸሚያ አውለዋል፡፡. በዚህ የችግር ባሕር ያሉ፣ የአክሊላቸውን ትርጉም የተረዱ እውነተኛ አበው ዐቅም አንሷቸው በኃዘን ተውጠው ይኖራሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ችግር በእውነት የተረዱና መፍትሔንም ሊያመጡ የሚችሉ ኃይሎች ቢኖሩም የችግሩ ውል የለሽ ትብትብ የፈለጉትን ደገኛ ተግባር እንዳይፈጽሙ ሸብቦ ይዟቸው ጥርሳቸውን እያፋጩ ብቻ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል፡፡  
በእውነት ይህ ሁሉ ውትብትብ በመካከላቸው ተገድግዶ እናትና ልጅ እየተነፋፈቁ እንዲኖሩ ተገደዋል፡፡ እናት /ቤተ ክርስቲያን/ ድምጿ ለልጆቿ /ምእመናን/ እንዳይደርስ የልጆቿን እንባም እናት እንዳታይ ኾኗል፡፡ ልጆች የእናታቸውን ሙቀት አጥተዋል፡፡ እናትም የልጆቿ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የየዋሕነት ሞገስ ናፍቋታል፡፡
ይኸንን ሁሉ ችግር እያሰብን፤ የቻለ «ምነው ተውካት? ምነውስ ተውከን?» እያለ ከአምላክ ጋር በሚሞግትበት፤ ያንን ማድረግ
ያልቻለው ደግሞ ዝም ብሎ አንገቱን ደፍቶ በሚያለቅስበት፤ ያልጸናው ደግሞ ጥሎ ሊሮጥ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት በሚቆጥርበት፤ ቀድሞ የተሸነፈው ላለመመለስ ርቆ በነጎደበት በዚህ ወቅት የተተበተበውን ለማፍታታትና ውሉን ለመያዝ አባቶች ዋሺንግቶን ዲሲ ላይ በአንድ አዳራሽ ጣራ ስር ተቀመጡ የሚለውን ዜና ስንሰማ በእጅጉ ደስ ብሎን ነበር፡፡   
በችግሩ የጨቅላነት ዘመን አንዱ ሌላውን ያሸነፈ ወይም ያበሳጨ እየመሰለው በግራም በቀኝም ብዙ የጨቅላ ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ በሁለቱም በኩል በአደባባይ ሲፈጸሙ የቆዩ በመኾናቸው እዚህ አምጥቶ መዘርዘሩ  ለቀባሪ ማርዳት ይኾናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በታች ለምናቀርበው አጭር ሐተታ ራስ የኾነውንና ለሰላም ውይይቱ ቀላል የማይባል እሰጣገባ ውስጥ ይከታቸዋል ተብሎ ተጠበቆ የነበረውን አንድ ነጥብ ብቻ እናቅርብ፡፡ ይኸውም እሰጣገባውና መሳሳቡ በሁለቱም ክህነትና በሾሟቸው ላይ የፈጠረው ችግር ነው፡፡

በመጀመሪያ በዚህ ጽሑፍ፤ የውስጡን /በሀገር ቤት ያለውን/ ከውጪ ለመለየት ሲባል እንደምንሰማው የኢትዮጵያው ሲኖዶስ - የስደቱ ሲኖዶስ ወይም ሐሰተኛው /የወያኔው/  ሲኖዶስ - እውነተኛው /ሕጋዊው/ ሲኖዶስ ማለት አልተፈለገም፡፡ በመንደርተኛነት ጣዖት ተተብትቦ ለሚናውዝ አንዱንና ዓለም ዐቀፋዊውን ሲኖዶስ «የኢትዮጵያ» እና «የውጭ» ብሎ ቢል፤ ሕገ እግዚአብሔርን በደሙ ሙቀትና እንደፍላጎቱ መጠን ለሚተረጉም ሌላውን «ሐሰተኛ» ብሎ የራሴ የሚለውን «ሕጋዊ» ቢል ከንቱነቱንና አላዋቂነቱን ከማስመስከሩ ያለፈ ምንም አልፈየደም፡፡ ሐሰተኛም ኾነ ሕጋዊ የሚሉት ቃላት ለሲኖዶስ የሚቀጸሉ አይደሉምና፡፡ ሲኖዶስ በሚመራውና በሚያነቃቃው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት በቦታ የማይወሰን ቅዱስ ጉባኤ ነውና፡፡ የኢትዮጵያ፣ የአርመን፣ የግብጽ ወዘተ ቢባል ሲኖዶስ ሠራተኞቹንና የተሾሙበትን አገር ለመግለጽ እንጂ ሲኖዶስ በአበው ሐዋርያት አንድ ጊዜ የተመሠረተ ዓለም ዐቀፋዊ ቅዱስ ተቋም ነው፡፡ በመኾኑም በዚህ ጽሑፍ በሁለቱም በኩል ያሉትን አባቶች ለያይቶ ለመጥራት ሲባል «በሀገር ቤት ያሉት አባቶች» ፣ «በዝርወት ያሉት አባቶች» ማለት ተመርጧል፡፡

በተባለውም ይሁን ባልተባለው ምክንያት በዝርወት ያሉት አባቶች አገር ጥለው በመውጣት «ሲኖዶሱ ተሰዷል» ማለት ሲጀማምሩ፤ በሀገር ቤት ያሉት አባቶች ያጠቃን መስሏቸው /ወይም ነገሩን ከስሩ ነቅለው የጣሉ መስሏቸውም ሊኾን ይችላል/ የጥፋት ምርጊታቸውን መወርወር ጀመሩ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ሸክም እያበዛ ከሄደው ምርጊት አንዱ በዝርወት ያሉትን አባቶች በማውገዝ /የአራተኛውን ፓትርያርክ የአቡነ መርቆርዮስን ሲቀር/ ስመ ጵጵስና እያነሱ /ካልጠፋ የቅዱስ ስም/ ለአዳዲስ ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት መስጠት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ባለ ሁለት አቡነ መልከ ጸዴቅ፣ ሁለት አቡነ ኤልያስ፣ ሁለት አቡነ ዜና ማርቆስ፣ሁለት  አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ሁለት አቡነ ይስሐቅ ኾነች፡፡ ይኽ ተግባር በወቅቱ ምናልባት በዝርወት ያሉትንና ስማቸውን «የተነጠቁትን» አባቶች ማበሳጨቱ የቀረ አይመስልም፡፡ ሁሉንም ከራስ ክብርና አልደፈርም ባይነት አንጻር ለሚያይ ሰው እውነት ነው ያበሳጫል፤ ያሳምማልም፡፡ ከግል ክብርና አስተሳሰብ ርቆ ልብ ብሎ ላስተዋለው ግን፤ ነገሩ ከማበሳጨት ይልቅ የሚያሳፍር ነው፡፡ በመኾኑም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች አፈርን፡፡ አንገታችንን ደፋን፡፡

ለዚህ የመልስ ምት ይመስላል፤ በዝርወት ያሉት አባቶች ፈራ ተባ እያሉ የጀመሩትን የ«ሲኖዶሱ ተሰዷል» ጅራፍ አጠናክረው ማስጮኽ ጀመሩ፡፡ የበለጠ ኃይል ያገኙ እየመሰላቸውም ቤተ መንግሥቱን ከሚቃወሙ ኃይሎች ጋር አብረው አደባባይ መቆም፣ አብረውም «ይውደም» ማለት ጀመሩ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ዲያብሎስ ቤተ ክርስቲያኗን ለመጉዳት የዘረኝነት ሠይፍ፣ የፍቅረ ንዋይ ጦር፣ የኑፋቄ ሻምላ አስይዞ በቤተ ክርስተያኗ ውስጥ ባሰማራቸው ጆቢራዎች ገፋፊነት፤ ሁለቱም ከያቅጣጫው ድንጋያቸውን ሲወራወሩ ቆዩ፡፡ ሀገር ቤት ያሉት በዝርወት ካሉት መራርጠው አውግዘናል አሉ፡፡ በውጭ ያሉትም በብስጭት ነጥብ ያስመዘግብልናል ያሉትን ሲያደርጉ ቆዩ፡፡ ይኸ መወራወር ቆየ ቆየና የባሰ ጉድ አመጣ፡፡ በዝርወት ያሉቱ አባቶች «እስቲ ምን ታደርጊ ሸንካሊት» የሚል በሚመስል አካሄድ ሰብሰብ አሉና አስራ ሦስቱን ሾሟቸው፡፡ የእነሱ እንደተወሰደባቸው እነሱም /አሁንም ካልጠፋ ስም/ ኢትዮጵያ ካሉቱ እየመነተፉ ወስደው አቡነ ሚካኤል፣ አቡነ ያዕቆብ፣ ---አቡነ ዲሜጥሮስ ወዘተ. እያሉ ሾሙ፡፡ ይኸ ሲኾን ዕብደቱ ጫፍ ደረሰ፡፡ ሀገር ቤት ያሉቱ ፈጥነው ተሰበሰቡና እገሌ ወእገሌ ሳይሉ /አራተኛውን ፓትርያርክም ጭምር/ በዝርወት ያሉትን በመላ አውግዘው «አባ እከሌ» እያሉ ጠሯቸው፡፡ ያንንም ለእሱ ብቻ በተከፈተ በሚመስለው የቤተ ክህነቱ ድረ ገጽ http://www.eotc-patriarch.org በእንግሊዝኛም ጭምር ተርጉመው ለጠፉት፡፡ ይኸው ዜና የደረሳቸው በዝርወት ያሉት አባቶችም ቀድመው ተዘጋጅተው ይጠብቁ በሚመስል አኳኋን ፈጥነው ተነሱና በሀገር ቤት ያሉትን አውግዘው «አባ እከሌ» እያሉ ጠሯቸው፡፡ እኛ ግራ የተጋባኖች የባሰ ስንደናበር ቆየን፡፡
በእውነቱ በጨዋ አመለካከት ላየው፣ እንደ ሁለቱም አካላት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ከኾነ፣ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ አባት አልባ ናት፡፡ ወይም በውጉዛን የምትመራ ናት፡፡ ይህ የሁለቱም አሳዛኝ ጨዋታ የፈጠረብን ዐቢይ ድንጋፄ ከኅሊናችን ሳይጠፋ፣ ተጫዋቾችም ለቀጣዩ ጨዋታ እየተዘጋጁ በሚመስሉበት ሁኔታ፤ በውጭ ካሉቱ አባቶች አንዱ /ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ/ በሞተ ሥጋ ተጠሩ፡፡ ይኸንን የሰሙት በሀገር ቤት ያሉት አባቶች ሰብሰብ አሉና «ለምዉቱ ውግዘቱን አንስተናል፣ አስከሬናቸው ወዲህ ይምጣና ይቀበር» አሉና ዐወጁ፡፡ በጦር ሜዳ ሲፋለም ከጎኑ የወደቀን የጦር ወንድም አስከሬን ጠላት እንዳይወስደው የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ወታደር፤ በውጭ ያሉቱ የወንድማችንን አስከሬን አንሰጥም ብለው እንቢኝ አሉ፡፡ እንዳሉትም ለአንድ ብፁዕ አባት አይደለም ለማንኛውም በአርአያ ሥላሴ ለተፈጠረ ሰው በማይደረግ አኳኋን አስከሬናቸውን በሳጥን አድርገው አስቀመጡት፡፡ አምላካቸው «እስመ መሬት አንተ ወውስተ መሬት ትገብእ» /ዘፍ. 4-19/ ያላቸውን ትእዛዝ ወደ መጡባት አፈር ተመልሰው አፈርን በመቅመስ እንዳይፈጽሙ ከለከሏቸው፡፡ ከንቱነት፡፡
የብፁዕነታቸው ማለፍና በዚህ ዓለም የቀረ በድናቸው ያለበት ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያን ልጆች እንቅልፍ የነሣ፤ እንዲያውም የሚያቃዠን ነገር ቢኾንም፤ አባቶች ዛሬ ዋሺንግቶን ዲሲ ላይ እንዲገናኙ መንገድ የከፈተው የእሳቸው ዕረፍት በሁለቱም ወገን የፈጠረው ድንጋጤና ልባቸውን የደቃው  የ«ለካ እንሞታለን» ጥያቄ እንደኾነ ብዙ አስተዋዮች ይስማሙበታል፡፡ ሞት ያስደነገጣቸው «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ» /መዝ.102-14/ እያሉ ዘወትር ዳዊታቸውን ይደግማሉ ተብሎ የሚታመንባቸው አባቶች መኾኑ ግን ድንጋጤያቸው ግራ የሚያጋባና የበለጠ ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው፡፡
እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ ከላይ በሁለቱም ወገን ባሉ አባቶች የተፈጸሙትን ተግባራትና በሁለቱ ክህነት ላይ የፈጠረውን ገጽታ ስንመለከት፤ ይኸው ሁለቱንም ሲያቆስል የቆየ የመወጋገዝና የውግዘቱ አነሳስ ሁኔታ ትልቁ የመወያያ ነጥብ ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ እውነት ነው ሊወያዩበትም ይገባ ነበር፡፡ መፍትሔው ግን አይርቃቸው ነበር፡፡ ለዚህም ርቀው መሔድ አያስፈልጋቸውም፡፡ ገና 60 ዓመት ብቻ ያስቆጠረው ግን ብዙ ፈተናን ያስተናገደውን የቤተ ክርስቲያኗን የጵጵስና የታሪክ መዝገብ ማገላበጥ ብቻ ይበቃል፡፡ ለነገሩ ሁሉም የሚያውቁት በመኾኑ መዝገብ ወደማገላበጥም ላይወስዳቸው ይችላል፡፡ በእውነት ቅንነቱ ካለ፡፡
እንደሰሚታወቀው በፍትሐ ነገሥት (አንቀጽ 4 ቁጥር 50) በሥርዋጽ ገብቶ የሚገኘውና «ወሰብአ ኢትዮጵያ ኢይሢሙ ላዕሌሆሙ ሊቀ ጳጳሳት እማእምራኒሆሙ ወበኢሥምረተ ርእሶሙ ... የኢትዮጵያ ሰዎች ከዐዋቂዎቻቸው ወገን በራሳቸውም ፈቃድ ሊቀ ጳጳሳትን ለራሳቸው አይሹሙ» የሚለው የግብጽ ወንድሞቻችን አሳሪ ሕግ ከ1600 ዓመታት በኋላ ተሽሮ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን አበው በራሳቸው ሕዝብ ላይ የተሾሙት በ1921ና በ1922 ዓ.ም ነበር፡፡ እነዚህ አበው ሀገረ ስብከት ተደልድሎላቸው የተሾሙበትን ሕዝብ በማገልገል ላይ ሳሉ ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ ቀደም ብለው ካረፉት አቡነ ሳዊሮስ /1868 - 1925 ዓ.ም/ በስተቀር እነዚህ ጳጳሳት ከሕዝባቸው ጋር መከራን መቀበል ጀመሩ፡፡ በመከራው ብዛትም ሁለቱ ማለት አቡነ ጴጥሮስ /1861 - 1931 ዓ.ም/ እና አቡነ ሚካኤል /1870 - 1929 ዓ.ም/ ልጆቻቸውን እያጽናኑ ባሉበት በሰማእትነት አለፉ፡፡ አቡነ ይስሐቅ /1871 - 1947 ዓ.ም/ ተጋዙ፡፡ ድካም ተጫጭኗቸው አዲስ አበባ ላይ የቆዩት አቡነ አብርሃም /1861 - 1931 ዓ.ም/ ብቻ ነበሩ፡፡ እኒህ አረጋዊ አባትም አገሩን ትተው የሔዱትን የግብጻዊ ሊቀ ጳጳስ የአቡነ ቄርሎስ መንበር ጠባቂነት አደራ ይዘው ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያውያንን የቆየ ፍላጎት ያጠናውና ያንን ፈቀድኩ በማለት የኢትዮጵያውያንን ይሁንታ ሊያገኝ የፈለገው ፋሺስት ጣሊያን አረጋዊውን አባት «ኢትዮጵያውያንን ይሹሙ» በማለት ግዳጅ በጎሰመው ሁኔታ ያግባባቸው ገባ፡፡
በፋሺስቱ ጉትጎታ ላይ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምክርና ግፊት ታክሎበት አቡነ አብርሃም (1861 - 1931 ዓ.ም) በዕውቀትም በቅድስናም ከተመሰከረላቸው ሊቃውንት መርጠው አምስት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ፡፡ እሳቸው ሲያልፉም በእሳቸው አንብሮተ ዕድ ከተሾሙት አንዱ የኾኑት አቡነ ዮሐንስ (1875 - 1948 ዓ.ም) መንበረ ሊቀ ጵጵስናውን በመያዝ ስድስት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾሙ፡፡ በዚህ ዓይነት በአምስቱ ዓመታት ወረራ ወቅት ሁለት ጳጳሳት በሰማእትነት አልፈው አስራ አንድ አዳዲስ ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት በኢትዮጵያውያን አበው ተሹመው ሀገሪቱ ከወራሪው ኃይል ነጻ ወጣች፡፡ ሰላም ተመለሰ፡፡ 
ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ መንበረ መንግሥታቸው ተመለሱ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርም ለወዲያው በእጨጌው አማካይነት ሥራውን ጀመረ፡፡ በዘመነ ችግር ቤተ ክርስቲያኗንና ሕዝቡን ትታ የሔደች የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በወረራ ወቅት የተሾሙትን አባቶች አውግዛ ነበር፡፡ ያው ግፊቷ ሰላም ሲመለስም ተጠናክሮ በመቀጠሉ ቤተ ክርስቲያኗ ቆይቶ ልታገኝ የሚገባትን ድል /ፕትርክናን/ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በወረራው ጊዜ የተሾሙት አባቶች ለጊዜው ካለ ሥራ በየሀገረ ስብከታቸው እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡ ያ ሲደረግም በኦፊሴል የተነገረው «ሥልጣናቸው ተይዟል» የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ከተሰጡት ሐሳቦች ዛሬም ድረስ አመዝኖ የሚገኘው «ሹመቱ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ ነበር» የሚል ነው፡፡ ለዚህም ከሚሰጡት ምክንያቶች ውስጥ ዋናው በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተመርጠው በሊቀ ጵጵስናው መንበር ተቀምጠው የነበሩት አበው ጳጳሳት የመሾም ሥልጣን አላቸው የሚል ነው፡፡ ይኸም በወቅቱ ተሹመው የነበሩት አበው ከጊዜያዊ እግድ በኋላ ወደ ሙሉ የጵጵስና አገልግሎት በመመለሳቸው ተረጋግጧል፡፡
ዛሬም በእኛ ዘመን መልኩን ቀይሮ የተከሰተው ችግር ከዚያ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ምናልባት በሁለቱም ወገን የተላለፈውና አስተዋይነት የጎደለው መወጋገዝ ነገሩን አክብደን እንድናየው ካላደረገን በስተቀር፡፡ ውግዘቱም የሚነሳበትና የተሾሙትም አባቶች ሁኔታ በሁለቱም ስምምነት መፍትሔ ያገኝ ዘንድ የሚከብዳቸው አይኾንም፡፡ ሁሉም በክህነታቸው ሥር ነውና፡፡
የእነሱ የ18 ዓመት እሰጥ አገባ በደሙ የመሠረታትን መድኃኔ ዓለምን አሳዝኗል፤ በዚያም የተነሣ ልጆቿ ግራ እንዲጋቡና እንዲበተኑ አድርጓል፡፡ አንዱ ችግር ሌላውን እየወለደም (በሰው ሰውኛው) ቤተ ክርስቲያናችን ከባድ የችግር ማጥ ውስጥ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ በመኾኑም አባቶቻችን ወደ ልቡናቸው ይመለሱ፡፡ ለመዘነው በእጅጉ ቀላል የኾነውን ችግራቸውን ይፍቱ፡፡ ላልተቀበሉት ምድራዊ ኃላፊነት ሳይኾን ለተጠሩበት ለሰማያዊ ኃላፊነታቸው ይጨነቁና እሱን በአግባቡ ለመወጣት ይትጉ፡፡ ይቅር ይባባሉ፡፡ መካሪ ሊኾኑ ተመርጠው ሳለ ምንም እንደማያውቅ ሕጻን መካሪ ፈላጊ ኾነው አይታዩ፡፡ እስከ አሁን ኾነው ቆይተዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ይብቃ፡፡ እግር እስኪላጥ ቢሔዱ በእናት ቤት እንደማረፍ ያለ እውነተኛ ዕረፍት የለምና በእናት ቤተ ክርስቲያናችን ጉያ ውስጥ ሰላም አግኝተን እንኖር ዘንድ ይተባበሩን፡፡ አያስጨንቁንም፡፡ ያንን ያላደረጉ እንደኾነ ለ18 ዓመታት እንደቀለሉብን ወደፊትም እንደቀለሉ ይሸኛሉ፡፡ ልቡና ይስጥልን፡፡ አሜን፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)