August 7, 2010

ሰበር ዜና፦ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ አረፉ

(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 7/2010)፦ ሰሞኑን ለአባቶች ድርድር አሜሪካ የሰነበቱትና አርብ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ተነሥተው ቅዳሜ ጠዋት አዲስ አበባ የደረሱት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ፣ ቤታቸው እንኳን ሳይደርሱ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ በዚህ ጊዜ አሉ ከሚባሉት ሊቃውንት መካከል ተጠቃሽ ሲሆኑ በአንደበት ርቱዕነታቸው፣ በቅኔ አዋቂነታቸው፣ በሰባኪነታቸው የተመሰገኑና የተከበሩ ነበሩ።

መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ሰሞኑን በተካሄደው የአባቶች የሰላምና የእርቅ ድርድር በተለይም ከአሜሪካኖቹ አበው ወገን “ይቅርታ ካልጠየቁን” በሚል ስሞታ ሲቀርብባቸው እንደነበር እና በዚህም ምክንያት ጉባዔው ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል።

ካልተሳካው የእርቅ ውይይት በኋላ የልኡካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ዛሬ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደ ደረሰ ልባቸውን የመውጋት እና ብርድ ብርድ የማለት ስሜት እንደሚሰማቸው አብረዋቸው ለነበሩት አባቶች የተናገሩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ የሐኪም ርዳታ እንዲያገኙ ወደ አንድ ክሊኒክ ከደረሱ በኋላ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ በቀድሞው ሥርዐተ መንግሥት በአንድ ወቅት ክፉኛ ይሠቃዩበት ከነበረው የሳምባ ሕመም ወደ ኢየሩሳሌም ተልከው ባገኙት ከፍተኛ ሕክምና ሙሉ በሙሉ የዳኑት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት በብሉይ ኪዳን መምህርነታቸው፣ ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ በኅትመት ላይ በነበረው ‹‹ትንሣኤ›› መጽሔት በአዘጋጅነት በሌሎቹም የቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙኀን መገናኛዎች በጽሑፋቸው እና በሚያበረክቷቸው ደገኛ ቅኔዎች ይታወቃሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት አስከሬናቸው በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ገብቶ ምርመራ የተደረገለት ሲኾን ጸሎተ ፍትሐቱ እና የቀብር ሥነ ሥርዐቱ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወይም መጋቤ ብሉይ ሰይፈ በኑሮ እና በአገልግሎት ብዙ እንደ ደከሙበት በሚታወቀው በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡ ለቀብር ሥነ ሥርዐቱ በውጭ የሚገኙት የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሁለት ልጆች እስከሚደርሱ ሊጠበቅ እንደሚችል የተነገረ ሲኾን በመንበረ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት ምንጮች ግን ቀብሩ በነገው ዕለት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲከናወን የታሰበ መኾኑ ተገልጧል፡፡

የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ ሐላፊ የነበሩት የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ድንገተኛ ሞት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች በተለይም በሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ኀዘን እንደ ፈጠረ ተዘግቧል፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ፍልሰት እና ዕርገት በማሰብ በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ እስከ ዐሥራ አምስት ቀን የሚጾመውን ጾም(ጾመ ማርያም፣ ጾመ ፍልሰታ) ምክንያት በማድረግ በድሬዳዋ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በቀብር ሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመገኘት ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ እንደ ኾኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡


ዝርዝር ታሪካቸውንና ተያያዥ ጉዳዮች እንደደረሰን እናቀርባለን።
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)