August 20, 2010

እጅጋየሁ እና ፋንታሁን ከፓትርያርኩ ጋራ መከሩ

  • ታግዶ የቆየውን የእነ በጋሻው የአሰበ ተፈሪ ጉባኤ አስፈቀዱ
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 20/2010፤ ነሐሴ 14/2002 ዓ.ም):- ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› በሚለው ‹መጽሐፍ› ‹‹ቅዱስ ፓትርያሪኩን ማስፈራሪያ እና የንግድ ምልክት ያደረጉ የዘመናችን አፍኒን እና ፊንሐስ›› የተባሉት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና ወይዘሮ እጅጋየሁ በየነ በሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ጉዳይ ላይ የሱባኤውን መጠናቀቅ ሳይታገሡ ፓትርያሪኩ ወደሚገኙበት ድሬዳዋ በርረው መክረው መመለሳቸው ተሰማ፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነሐሴ ስምንት ቀን 2002 ዓ.ም ምሽት ፓትርያሪኩ ለሱባኤው ሄደው ባረፉበት በድሬዳዋ መካነ ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ ወአርሴማ ገዳም የደረሱት ወ/ሮ እጅጋየሁ እና ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን መጽሐፉን ስላዘጋጀው ‹‹ስውሩ ጸሐፊ››፣ በመጽሐፉ ይዘት እና መጽሐፉን በማሳተም ረድተዋል ብለው በሚጠረጥሯቸው አካላት ማንነት ዙሪያ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ሲመክሩ አምሽተው (8pm - 4:30AM) እሑድ ዕለት ጎሕ ሳይቀድ (ምሽት 02፡30 ገብተው ሌሊት 10፡30) ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን የድሬዳዋ ምንጮች ለደጀ ሰላም አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ወ/ሮ እጅጋየሁ ‹መጽሐፉ› በቀድሞ ወዳጃቸው ባሁኑ ባላንጣቸው ‹ሊቀ ትጉሃን› ዘሪሁን ሙላቱ መጻፉን፣ በዚህም ዙሪያ በደጀ ሰላም ላይ ብዙ እየተባለ መሆኑን አመልክተው፣ መጽሐፉ እንዲጻፍ በመደገፍ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ፣ በማሳተሙ ረገድ ደግሞ የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል እጅ ያለበት መሆኑን እንደሚያምኑ ለአቡነ ጳውሎስ መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡ ‹መጽሐፉ› መታተሙን እንደ ሰሙ ወደ ሕዝብ ደኅንነት ጽ/ቤት አቤት ማለታቸውን ያልሸሸጉት ወ/ሮ እጅጋየሁ ይሁንና ‹‹ዘወር በይ ብለው አስወጡኝ›› በማለት ያለአንዳች ውጤት መመለሳቸውን ለፓትርያሪኩ በመማረር ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአሰበ ተፈሪ ደብረ ሰላም ልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዳይካሄድ በምዕራብ ሐረርጌ እና ኦጋዴን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሐላፊ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እንዲሁም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ትእዛዝ ታግዶ የነበረው የእነ በጋሻው ደሳለኝ ጉባኤ በመጪው ዓመት፣ ከጥቅምት 26 - 27 ቀን 2003 ዓ.ም እንዲካሄድ መፈቀዱ ተሰማ፡፡  የታገደው ጉባኤ እንዲካሄድ ለፓትርያርኩ ጥያቄውን ያቀረቡት ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ድሬዳዋ የነበሩት ወ/ሮ እጅጋየሁ ናቸው፡፡ ፓትርያሪኩም የወይዘሮዋን ጥያቄ ተቀብለው ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ስልክ በመደወል በሰጡት የቃል ማሳሰቢያ መሠረት ጉባኤው እንዲካሄድ የተፈቀደ መሆኑን የሚያመለክት ደብዳቤ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ፊርማ ለደብሩ አስተዳደር የተጻፈ ሲሆን የደብሩ አስተዳደር በበኩሉ ለአጥቢያው የስብከተ ወንጌል ኮሚቴ ይህንኑ ውሳኔ በዛሬው ዕለት ደብዳቤውን በመምራት ማሳወቁን ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች፣ ቀድሞ ነገር ጉባኤው የታገደበት ምክንያት በሚገባ ሳይጤን አሁን በወ/ሮ እጅጋየሁ አስታዋሽነት (ጫና) ብቻ እንዲካሄድ መፈቀዱ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ውሳኔ ሰጪ አካላት ፋይዳ እና ክብር አጠያያቂ እንደሚያደርገው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይኸው ጉባኤ እነ በጋሻው ደሳለኝ በአካባቢው ባቋቋሙት እና ‹‹ማኅበረ ጽዮን›› እየተባለ በሚታወቀው አካል የተዘጋጀ ነው፡፡

Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)