August 30, 2010

ፍርድ ቤቱ በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› ደራሲ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ


(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 29/2001፤ ነሐሴ 23/2002 ዓ.ም):- በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ ምክንያት በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና በጋሻው ደሳለኝ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ በቀረበበት ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ ላይ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሳቢያ ጉዳዩ ለነሐሴ 25 ቀን 2002 ዓ.ም ተቀጠረ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት እጁ ታስሮበት ከነበረው ካቴና ተፈትቶ የቀረበው ዘሪሁን ሙላቱ በበኩሉ፣ ‹‹ስለ መጽሐፉ አንዳችም የማውቀው ነገር የለም፤ ከቤተሰቦቼም ይሁን ከሌሎች ጓደኞቼ ጋራ እንዳልገናኝ ተከልክያለሁ፤ በአ.አ.ዩ የፒ.ኤች.ዲ ተማሪ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ረዳት የሌላት ታማሚ እናት አለችኝ፤›› በማለት የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ያቀረበው ጥያቄ ዳኛው ፖሊስ ምርመራውን በሚገባ አጣርቶ እንዲቀርብ አንድ ተጨማሪ ቀጠሮ ልስጥ በማለታቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡


በችሎቱ መጀመርያ ላይ ዳኛው ምርመራው ከምን እንደ ደረሰ ሲጠይቁ የምርመራ መዝገቡን የያዙት ፖሊስ ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍን እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንደ ተጻፈ የሚያሳይ እና የከሳሾችን ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ ለዳኛው አቅርበዋል፤ ዳኛውም በቅድሚያ ቆጣ ብለው ጊዜ ቀጠሮ የሰጡት የተጠርጣሪው መታሰር ለምርመራ ይጠቅማል ብለው በማሰብ መሆኑን አስገንዝበው ፖሊስ ስለምን እንዲህ ያሉ ደብዳቤዎችን በዚህ መልኩ እንደሚያቀርብ ጠይቀዋል፤ ፖሊስም ደብዳቤው በከሳሽ ወገኖች(እነወ/ሮ እጅጋየሁ) የቀረበ እና ከጉዳዩ ጋራ በተያያዘ አንድ ተጨማሪ ሰው በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደሚፈልግ፣ ተጠርጣሪው የዋስ መብቱ ተከብሮለት ቢወጣ ወይም አሁን ባለበት ሁኔታ ከሰው ጋራ እንዲገናኝ ቢፈቀድለት ምርመራው ስለሚደናቀፍ እስከ ቀጣዩ ቀጠሮ ድረስ ሲጠበቅበት በነበረው አኳኋን በማረፊያ ቤት ለብቻው ተገልሎ እንዲቆይለት ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡

ዳኛው በፖሊስ የቀረበላቸውን ‹መጽሐፍ› ይዘው፣ ‹‹ይህ መጽሐፍ ከአንተ እጅ ነው የተያዘው?›› በማለት ተጠርጣሪውን ጠይቀዋል፤ ዘሪሁንም ‹‹አይደለም›› በማለት በአጭሩ መለሰ፡፡ ፖሊስም መጽሐፉ በግል ተበዳዩዋ ወ/ሮ እጅጋየሁ ከመንገድ እንደተገዛ፣ ‹መጽሐፉ› ከመውጣቱ በፊት ተጠርጣሪው ረቂቁን ለግል ተበዳዩዋ ልኮላቸው እንደ ነበር አስረድቷል፡፡ ዳኛውም ዘሪሁንን፣ ‹‹አንተ ስለዚህ መጽሐፍ የምታውቀው አለ?›› በማለት ሲጠይቁት፣ ‹‹አንዳችም የማውቀው ነገር የለም፤›› በማለት ይመልሳል፡፡ ዳኛውም እንደገና፣ ‹‹ታዲያ ፖሊስ ዝም ብሎ ይይዝሃል እንዴ?›› በማለት ‹‹ፖሊስ ጉዳዩን በሚገባ እንዲያጣራ አንድ ተጨማሪ ቀጠሮ እሰጣለሁ›› በማለት ይናገራሉ፡፡ ዘሪሁንም ቤቱ አላግባብ እንደተሠበረ እና ንብረቱ እንደ ተዘረፈ፣ ከቤተሰቦቹ እንዳይገናኝ መታገዱን፣ በአ.አ.ዩ የድኅረ ምረቃ ትምህርቱን በመከታተል ላይ መሆኑን፣ ቋሚ አድራሻ እና ሥራ እንዳለው፣ እርሱ ብቻ የሚረዳቸው ታማሚ እናት ያሉት መሆኑን በመዘርዘር የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ጠይቋል፡፡ አያይዞም በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ አንድ ግለሰብ በሽጉጥ ያስፈራራው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ ዳኛውም፣ ‹‹በሕግ ጥላ ሥር ሆነህ ስለ ፒ.ኤች.ዲ ማሰብ አዳጋች ነው፤ ክሱ ዋስትና ባያስከለክልህም ‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች› ብለህ የሰዎችን ምስል በጨዋታ ካርታ ውስጥ አድርገህ ማውጣት ወንጀል ነው፡፡ ከሃይማኖት ጉዳይ ጋራ የተያያዘ ነገር ሲሆን ደግሞ አደገኛ ይሆናል፡፡ ይህ ድርጊት ትክክለኛ ነው ብለህ ታምናለህ?›› ሲሉ ዘሪሁን፣ ‹‹ጸሐፊው ስለ ጻፈው ነገር መረጃ ካለው እና በስሙ ካወጣ ይችላል›› ብሎ ይመልሳል፡፡ ‹‹መረጃው ትክክል ካልሆነስ?›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ጸሐፊው ይጠየቅበታል፤ እኔ ግን አልመረመርም አላልኩም፤ ጉዳዩ ከእኔ ጋራ ተያያዥነት ስለሌለው የዋስትና መብት ይፈቀድልኝ ነው ጥያቄዬ›› ብሎ ይመልሳል፡፡

ዳኛውም ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደ ሆነ፣ የቀረበውም ክስ የተጠርጣሪውን የዋስትና መብት የማያስከለክል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ተጠርጣሪው በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ‹‹በሽጉጥ አስፈራራኝ›› ያለውን ሰው መክሰስ እንደሚችል፣ ይሁንና ፖሊስ ተከሳሹ የምርመራ ሂደቱን የሚያበላሽ መረጃ ያወጣል ብሎ ካመነ ተጠርጣሪውን በማረፊያ ቤት ለብቻ ማቆየቱ በሕግ የተፈቀደ እንደ ሆነ፣ ስሙ ለችሎቱ በቀረበው ደብዳቤ የተጠቀሰው ሌላው ተፈላጊም በቁጥጥር ሥር እስከሚውል ድረስ ዳኛው እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2002 ዓ.ም ያለውን ተጨማሪ ጊዜ ፈቅደው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ እንዲቀርብ በማሳሰብ የዕለቱን ውሎ አጠናቀዋል፡፡

1 comment:

Anonymous said...

መቼም ይህች በአባ ጳውሎስና በአቶ መለስ ዘረኛ ድጋፍ የምትመራው ቤተክርስቲያናችን ጣጣ ፈንጣጣዋ ከበዛ እነሆ 19 ዓመት ሞላት። አባ መርቆሬዎስን የደርግ ደጋፊ ሲል የነበረው መለስ /ወያኔ እርሱ በከፋ መልኩ በማፍያ አመራሩ ጳጳሳትን ከማስደብደብ ጀምሮ በዚሁ ጠንቅ እስከሞት ማድረሱ ይታወቃል። መለስ እንደደርግ አዋጅ አያስነግር እንጂ ሃይማኖት የለሽ ለመሆኑ ማረጋገጫው ቤተክርስቲያናችንን የሚያምሳት የአባ ጳውሎስን የነገር እሳት ዝም ብሎ መመልከቱ ከበቂ በላይ ማረጋገጫ ነው። የሚከፋው ደግሞ አሥር አግብታ አሥር ፈት የሆነችው መበለት የቤተክርስቲያናችንን ጓዳ ጎድጓዳውን እንድታዝበት ፈቃድ የተሰጣት በአባ ጳውሎስ መሆኑ እየታወቀ ብንጮህ፤ ብንጮህ ሰሚ አላገኘንም። ይሄ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበ የተባለው ሰውዬ በአባ ሳሙኤል ላይ ለጻፈው ስም አጥፊ ጽሁፍ አባ ጳውሎስ፤ መበለት እጅጋየሁና፤ መለስ(በደህንነቶቹ)በኩል የጋራ ስምምነት አድርገው ያለማንም ከልካይ እንዳሻው በነጻነት እንዲኖር መፍቀዳቸውን አይተን ፍርዱን ለእግዚአብሄር ሰጥተን ነበር። የሚገርመው ግን ንጹህ ሰው ነው የተባለለት ሰውዬ በነሱ ላይ መጻፍ ሲጀምር ጨርቃቸውን ጥለው አገር ይያዝ፤ መንደር ይቃጠል ማለታችው ነው። በዚህ ሀገር ላይ ህግ የሚኖረው ወያኔ እስከደገፈህ ድረስ ብቻ ነው። ያለበለዚያ እንደ አባ ሳሙኤል ኤሎሄ ኤሎሄ ከማለት በስተቀር ዋጋ የለህም። ስለሆነም ዛሬ በአቶ ዘሪሁን ላይ የቀረበው ክስ ከሳሾችን ለማስደሰት ካልሆነ በስተቀር እንደፍትህ በተገቢው ጊዜ የተደረገ ባለመሆኑ ትክክል አይደለም። ፍትህ ማለት ቤተክርስቲያናችንን ራሳችን እንድንመራ ወያኔ እጁን መሰብሰብ ሲችል ብቻ ነው። በወያኔ ዘመን ምንም ማድረግ ባንችል ለትውልድ የሚቆይ ወያኔ ይህችን ቤተክርስቲያን በታሪኳ አይታ የማታውቀን ግፍ እንደፈጸመባት በጽሁፍ ማስፈርፈር አይሳነንም። ትንሳዔ ለቤተክርስቲያናችን ውድቀት ለጠላቶቿ። ገሞራው ነኝ ከአዲስ አበባ

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)