August 24, 2010

ዘሪሁን ሙላቱ እና በጋሻው ደሳለኝ እንዲወገዙ እና እንዲከሰሱ ሰባክያነ ወንጌል ጠየቁ

(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 24/2010፤ ነሐሴ 18/2002 ዓ.ም):- በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት አስቸኳይ ስብሰባ የተጠሩ በሀገረ ስብከቱ ገዳማት እና አድባራት ተመድበው የሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል፣ ‹‹ለወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ችግር እና ለአባቶች ክብር መደፈር መንሥኤ ነው›› ያሉት በጋሻው ደሳለኝ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት ጉባኤ እንዲወገዝ እና ክስ እንዲመሠረትበት፣ ‹ሊቀ ትጉሃን› ዘሪቱ ሙላቱ ደግሞ እንዲወገዝ ጥያቄ የሚያቀርብ የአቋም መገለጫ አወጡ፡፡ ስብሰባው ‹‹በሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ የተነሣ ክፉኛ ለተረበሹት ለሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ በመወገን፣ ሰባኪውን በፀረ ዘሪሁን አቋም ዙሪያ አስተባብሮ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲወገዝ ለመጠየቅ እና መጽሐፉን በማሰራጨት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል የተባሉትን ሰባክያነ ወንጌል ለማስጠንቀቅ ታስቦ የተጠራ ነበር፡፡

ይኹንና ሰባክያነ ወንጌሉ ‹‹ከሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች በፊት በወጡ የዘለፋ ጽሑፎች የሃይማኖት አባቶች ሲሰደቡ የት ነበራችሁ?›› በማለት ሰብሳቢዎቹን ሞግቷል፡፡ ሀገረ ስብከቱ በቀጣይ የገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎችን እና ጸሐፊዎችን ጠርቶ በተመሳሳይ አጀንዳ ለማወያየት ያቀደ ቢሆንም በትላንቱ ስብሰባ በታየው የሰባክያኑ ጥብዓት የተመላበት ጥያቄ እና አስተያየት እንዲሁም መጨረሻ ላይ በተያዘው የብዙኀኑ ተሰብሳቢ የተባበረ አቋም የተነሣ ከፍተኛ መደናገጥ እና ፍርሃት ውስጥ ገብቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በስልክ በተላለፈ አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ መሠረት ከትናንት ረፋድ ጀምሮ እስከ ቀትር የዘለቀው ይኸው ስብሰባ የተካሄደው በሀገረ ስብከቱ የጉባኤ አዳራሽ ሲሆን የተመራው ደግሞ በሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ገብረ መስቀል እና በስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊው ላእከ ወንጌል በዕደ ማርያም ይትባረክ ሰብሳቢነት ነበር፡፡ ጥሪ የተደረገው በቁጥር ከ150 በማያንሱ የሀገረ ስብከቱ ገዳማት እና አድባራት ተመድበው ለሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል ቢሆንም የተገኙት ግን የጠቅላላው አንድ ሦስተኛ ያህል ተሳታፊዎች ብቻ ነበሩ፡፡

ከመድረኩ እንደ ተገለጸው የስብሰባው ዓላማ በ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ ተንቀናል፣ ተደፍረናል በሚል ቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊውን እንዲያወግዘው ለማሳሰብ፣ ጽሑፉን በማሰራጨት ተባብረዋል ከተባሉት ሰባክያነ ወንጌል ጋራ ለመወቃቀስ ነበር፡፡ ለዚህም ሲባል ‹‹አይዟችሁ ተናገሩ፣ ይህን በተመለከተ ምንም ነገር አይኖርም፤ ከሥራ አትባረሩም›› የሚል ማበረታቻ ከሰብሳቢዎቹ ሲነገር እንደ ነበር ተሳታፊዎቹ ይገልጻሉ፡፡

ይኹንና ብዙም ሳይቆይ ስብሰባው በተቃራኒ አካሄዶች ተቀየረ፡፡ ከብዙ በጥቂቱ የቀረቡት ልዩ ልዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የሚከተለውን ይመስላሉ፤

  • የተባለውን አቋም ከመያዛችን በፊት በመጽሐፉ ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱት ሰዎች የታሙበትን ነገር ላለማድረጋቸው እንደምን ርግጠኛ መሆን እንችላለን?
  • ትናንት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ላይ ‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› በሚል ርእስ ሲጻፍባቸው በመቃወማችን ማስፈራሪያ እየደረሰብን ጨለማ ውስጥ ተጥለን ነበር፡፡ አሁን ግን በአደባባይ መናገር በመቻላችን ተመስገን እንለዋለን፡፡
  ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› ከእርሱ በፊት የወጣውን ‹‹የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች››ን እያመሳከረ ጽፏል፡፡ ከዚህም ቀደም ብሎ የ‹‹ስድብ አፍ›› ተጽፏል፡፡ በመሆኑም ይህ ስብሰባ ችግሩን ከምንጩ የማድረቅ ዓላማ ካለው
  መወገዝም ሆነ መከሰስ ያለበት ጀማሪው ነው እንጂ ተከታዩ አይደለም፡፡
  • ‹‹የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች›› መጽሐፍ ሲጻፍ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስፖንሰር አድራጊነት ‹‹የስድብ አፍ›› የሚል ምላሽ እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡ ታዲያ ዛሬ በዚህ ስብሰባ ያን ምላሽ ያዘጋጀው ጸሐፊ እንዲወገዝ የሚያደርገው ችግር ምንድን ነው?
  • መጽሐፉ በዋናነት አተኩሮ የተጻፈው በግለሰቦች ላይ ነው፡፡ ቀደም ብሎ በተጻፈው ጽሑፍ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሲሰደቡ ሀገረ ስብከቱ ስለምን እንዲህ   ዐይነት የስብሰባ ጥሪ አላደረገም?
  • እኛ የበታች ሠራተኞች ነን፤ ነገሩን ካመናችሁበት ስለምን ራሳችሁ(ሀገረ ስብከቱ) በደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄውን አታቀርቡም?
  • በ‹‹ዳ ቬንቺ ኮድ›› ክርስቶስ ሲሰደብ ይህን የመሰለ የመምህራ ጉባኤ ያልጠራች ቤተ ክርስቲያን ግለሰቦች ተሰደቡ ብላ መሰብሰቧ የሚያሳፍር ነው፡፡
  • ‹‹የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች›› ጸሐፊን ዲያቆን በጋሻው ደሳለኝን ቤተ ክርስቲያን አውግዛ ካልለየች ሌሎችም የኀጢአት እና የክፋት ምንጮች መፈጠራቸው አይቀርም!!
  • ይህ ስብሰባ የተጠራው ፋንታሁን ስለ ተሰደበ ነው፤ እስከ አሁን የሃይማኖት አባቶች ሲሰደቡ ግን ምንም አልተባለም፡፡.....አሁንም ‹‹ኢየሱስ ማን ነው?›› እያሉ ኑፋቄ የሚጽፉቱም ይመርመሩ፤ ‹‹የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች››፣ ‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› እና ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› የጻፉት ደግሞ ይወገዙ!!

ያለመግባባት ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረው ይኸው ስብሰባ በመጨረሻ፣ ‹‹ለብዙዎቹ የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ተጠያቂ እና ለቤተ ክርስቲያን አባቶች መደፈር መንሥኤ ሆኗል›› ያለውን በጋሻው ደሳለኝን ፓትርያርኩ በተገኙበት ጉባኤ እንዲወገዝ፣ በቁጥጥር ሥር ውሎ በማረፊያ ቤት የሚገኘው ስውሩ ጸሐፊ ዘሪሁን ሙላቱ ደግሞ እንዲወገዝ በመስማማት ተጠናቅቋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንሁን ሙጬ በዚህ ስብሰባ ላይ ባይገኙም በተመሳሳይ ሰዓት ብዙም በማይርቀው መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የሱባኤውን ወቅት በድሬዳዋ አሳልፈው ትላንት ቀትር ላይ ወደ አዲስ አበባ ለተመለሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከገዳማት እና አድባራት ተውጣጥተው፣ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ከተሰለፉ ካህናት ጋራ አቀባበል በማድረግ ላይ ነበሩ፡፡ አቀባበሉን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለደጀ ሰላም የሰጡ አንዳንድ ካህናት ፓትርያርኩ ወጣ ብለው በተመለሱ ቁጥር እርሳቸውን በዚህ መልኩ መቀበሉ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየተቆጠረ መምጣቱን በመጥቀስ ተችተዋል፡፡ ጉዞ የሚያበዙት አቡነ ጳውሎስ ወጥተው በገቡ ቁጥር ካህናቱ ለአቀባበል ሲሰለፉ በሌላው አገልግሎት ላይ መስተጓጎል ይፈጥራል፤ አቀባበሉን ብዙ ጊዜ የሚያዘጋጁት እነ መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም እና ሀገረ ስብከቱ ለተሰለፉት ካህናት አጥቢያዎቹ ውሎ አበል እንዲከፍሉ ስለሚያዝዙ በዚህም በኩል የወጪ ጫና እየፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ አማርረዋል፡፡ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን የዘንድሮውን የፍልሰታ በዓል ያከበሩት ፓትርያርኩ ለሱባኤው በሰነበቱበት ድሬዳዋ ነበር፡፡ ይህ የድሬዳዋ ጉዟቸው በሱባኤው ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የመጀመሪያው ከወ/ሮ እጅጋየሁ ጋራ ለአቤቱታ የተጓዙበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)