August 15, 2010

እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ የ “ሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች ”መጽሐፍ ደራሲን ለመክሰስ በዝግጅት ላይ ናቸው

  • ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ቀርበው ሪፖርት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ወጣባቸው፤  
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 15/2010፤ ነሐሴ 8/2002 ዓ.ም):- በቅርቡ ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› በሚል ርእስ፣ ፈታሔ በጽድቅ በሚል የፈጠራ ስም የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬን፣ የወ/ሮ እጅጋየሁ በየነን፣ የበጋሻው ደሳለኝን እና የያሬድ አደመን “ገመና፣ ኀጢአት እና የሙስና ድርጊቶች” በማጋለጥ ባለ ኀምሳ ገጽ ጽሑፍ ያወጣው ስውሩ ጸሐፊ ዘሪሁን ሙላቱ ከዓርብ ነሐሴ ሰባት ቀን 2002 ዓ.ም (ኦገስት 13/2010) ጀምሮ በሚታሰቡ አምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ቀርቦ ሪፖርት እንዲያደርግ የሚያዝዝ ማሳሰቢያ ወጣበት፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በሆኑት አወዛጋቢው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ትእዛዝ በቁጥር 8785/2467/02 በቀን 7/12/02 መውጣቱ የተገለጸው ይኸው ማሳሰቢያ “ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ ኾነው እንዲሠሩ በተመደቡበት የቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ለረጅም ጊዜ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ” በመግለጽ አገልግሎቱን ሲበድሉ መቆየታቸውን ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ከዓርብ ነሐሴ ሰባት ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰቡ አምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ቀርበው ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ሪፖርት ካላደረጉ ግን ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደ ለቀቁ ተቆጥሮ በቦታው ላይ ሌላ ሰው የሚሾም መኾኑ ተገልጧል፡፡ በአድራሻ ለሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ፣ በግልባጭ ለሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር መምሪያ እና ለቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ግልባጭ የተደረገው ይኸው ማሳሰቢያ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት መግቢያ እና በካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በትላትናው ዕለት እንዲለጠፍ ተደርጓል፡፡
በሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ላይ ከተመደበበት ካቴድራል ለሀገረ ስብከቱ ርምጃ መነሻ የሚሆን ውሳኔ ባልተላለፈበት ሁኔታ ይህ ዓይነቱ ማሳሰቢያ መውጣቱ፣ “ተገቢ አካሄዱን ያልጠበቀ እና ለግለሰቦች ቂም በቀል ለማመቻቸት ታስቦ ነው” ሲሉ  ሂደቱን በቅርበት የሚከታተሉ የካቴድራሉ አገልጋዮች ተችተዋል፡፡
በአንጻሩ ‹ስውሩ› ጸሐፊ ዘሪሁን ሙላቱ ጽሑፉን አሳትሞ ካወጣበት ዕለት ጀምሮ የወትሮ መኖርያውን በመቀያየር እና ዳናውን በማጥፋት የ‹መጽሐፉ›ን ሥርጭት በማጧጧፍ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ‹መጽሐፉ› እስከ አሁን ድረስ በ10‚000 ኮፒ እንደ ታተመ የተነገረ ሲሆን በተለይም በሐዋሳ እና በአዲስ አበባ ምእመናን ለሱባኤው በከፍተኛ ቁጥር በተሰባሰቡባቸው እንደ እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ባሉ አብያተ ክርስቲያን እንዲሁም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በከፍተኛ ቁጥር በመሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡ በአንዳንድ ሥፍራዎች ሥርጭቱ በባለሀብቶች የታገዘ ሲኾን 15.00 ብር የኾነውን የሽፋን ዋጋ ከኻያ እስከ ኀምሳ ብር በኾነ ዋጋ የሚሸጡ ነጋዴዎች እና ግለሰቦችም አጋጥመዋል፡፡
መጽሐፉ በአጭር ጊዜ ባገኘው ከፍተኛ ሥርጭት እና ተነባቢነት በእጅጉ የተደናገጡት እነ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ እና ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጽሑፉ በይፋ ታትሞ መውጣቱን ከሰሙበት ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ የ‹ስውሩን› ጸሐፊ መግቢያ እና መውጫ በማጥናት እና በማስፈለግ ሲባዝኑ፣ የሚያሳርፉበትን የበቀል ብትር በተመለከተ ሲመክሩ ሰንብተዋል፡፡ እነ በጋሻው ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ‹‹እኛ የጌታ ነን፤ ከጌታ ጋራ የሆነ እንኳን ኀምሳ ገጽ አመስት መቶ ገጽ ቢጻፍበትም አይፈራም፤›› በማለት ካፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት ምላሽ በመስጠት ክሳደ-ልቡናቸውን ማደንደናቸው ተሰምቷል፡፡
ቀደም ሲል ወይዘሮ እጅጋየሁ እርሳቸውን የሚመለከተው የጽሑፉ ረቂቅ እንዲደርሳቸውና ጽሑፉ እንዳይታተም ከ150‚000 - 200‚000 ብር ጉቦ እንዲሰጡ በጸሐፊው መጠየቃቸው የተነገረ ቢሆንም ጸሐፊውን በማስፈራራት እና “ደፍሮ አያሳትመውም” በሚል ተዘናግተው እንደ ቆዩ ተነግሯል፡፡ ከስድስት ወራት በፊት ስውሩ ጸሐፊ አገር ለቅቆ መሄድ እንደሚፈልግና ይህን የውጭ ጉዞውን ከፓትርያርኩ ጋራ ተነጋግረው እንዲያመቻቹለት ያቀረበላቸውን ተማፅኖ ባለመፈጸም ቂም ያተረፉት ወ/ሮ እጅጋየሁ፣ የአዲሱ ‹መጽሐፍ› ኮፒ ማክሰኞ ዕለት ሲደርሳቸው የጸሐፊውን ‹‹አከርካሪ እንደሚሠብሩ›› አልያም ‹‹ራሳቸውን እንደሚያጠፉ›› በመዛት ጸሐፊውን አድኖ ለመያዝ ወደ ሕዝብ ደኅንነት እና ጸጥታ ቢሮ ያመለክታሉ፡፡ ከቢሮው የተሰጣቸው ምላሽ ግን አፋቸውን የሚያሲዝ፣ ጆሯቸውን ጭው የሚያደርግ ነበር፡፡
ቢሮው ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ዘሪሁን ሙላቱ “ተከሥተ ዘሪሁን” በሚል የፈጠራ ስም፣ ‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› በሚል ርእስ በወቅቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት እና የአቡነ ጳውሎስን ቅጥ ያጣ ቤተ ዘመዳዊ አስተዳደር ለማረም ሌሎች ብፁዓን አባቶችን በማስተባበር በተጋደሉት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ላይ አባቶችን የሚያዋርድ ስም አጥፊ ጽሑፍ ባወጣበት ወቅት ወይዘሮዋ በጸሐፊው ላይ የነበራቸውን አቋም አስታውሷቸዋል፡፡
በወቅቱ ለቤተ ክርስቲያን ሥር የሰደደ አስተዳደራዊ ችግር የሠለጠነ መፍትሔ ለመሻት እና የፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን ዓምባገነናዊነት ለመግራት የተባበረ አቋም የነበራቸውን ብፁዓን አባቶች የማስደብደብ ሙከራ ያደረጉት ወይዘሮ እጅጋየሁ፣ ስም አጥፊው ጸሐፊ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ በሕግ እንዲጠየቅ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ፊርማ በወጣ ደብዳቤ በተጠየቀበት ወቅት ‹‹የቤተ ክርስቲያን ልጅ ነው፤ እኔ ዐውቀዋለኹ፤ ለፈጸመው ተግባር ሐላፊነቱን እወስዳለኹ፤›› በማለት ተከላክለውለት(ታድገውት) ነበር፡፡ ‹‹በሰፈሩት ቁና...›› እንዲሉ ‹‹ያ ምስክርነትዎ የት ደረሰ?›› የተባሉት ወይዘሮዋ በብስጭት ለሌላ የበቀል ሙከራ በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን በቦሌ ደብረ ሳሌም መጥምቁ ዮሐንስ እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ካቴድራል የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ ሆኖ ያለ አንዳች ሥራ በየወሩ የሚያገኘውን 1600.00 ብር በስልክ በሰጡት ትእዛዝ ለማሳገድ ሞክረው በካቴድራሉ አስተዳደር ተቃውሞ ካልተሳካላቸው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ጋራ ዐርብ ዕለት መምከራቸው የተዘገበው ወይዘሮ እጅጋየሁ በስውሩ ጸሐፊ እና ‹‹ግብረ አበሮቹ ናቸው›› ባሏቸው ሌሎች ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመሥረት መወሰናቸው ታውቋል፡፡ በክሱ የማይካተቱትን እና የ‹መጽሐፉ›ን ዝግጅት፣ ኅትመት እና ሥርጭት ረድተዋል በሚል የተጠረጠሩ ሌሎች ሠራተኞችም ከደረጃቸው ዝቅ የማድረግ ወይም ወደማይፈልጉት ቦታ የማዘዋወር ዕጣ ፈንታ እንደሚጠብቃቸው ተሰምቷል፡፡
የክስ ዶሴ እየተሰናዳባቸው ከሚገኙት ግለሰቦች መካከል ለጸሐፊው ዳጎስ ያለ ገንዘብ አስቀድመው በመስጠታቸው እንደ እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ እና በጋሻው ከመጋለጥ ለጊዜው ያመለጡት እና ‹‹መጽሐፉን በማዘጋጀት እና በማሳተም ሂደት መርዳታቸው በእነ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ተደርሶባቸዋል፤›› የተባሉት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ይገኙበታል፡፡ ቀደም ሲል ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ከሚፈለጉባቸው በርካታ የወንጀል ተግባራት መካከል በአስተዳዳሪነት በሚሠሩባት የሰፋሪ ገነት አቃቂ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለጠበል ቤት ማሠርያ ተብሎ በምእመናን ገንዘብ የተገዙትን የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች መዝረፋቸው እየታወቀ በዝምታ ታልፈው ነበር፡፡ ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ በብላሽ ሲበላው የቆየው የካቴድራሉ ደሞዝ አሁን እነርሱ ሲነኩ ትዝ ያላቸው ግለሰቦች፣ የቁስቋም ምእመናን በሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ላይ ከዘመን በፊት ያቀረቡት የክስ አቤቱታም የታወሳቸው አሁን ከጀርባ እንደ ተወጉ ሲሰማቸው ነው፡፡ በመሆኑም አቤቱታውን የሚያጣራ ልዑክ ወደ ሥፍራው በመላክ ክሳቸውን ለማጠናቀር ተስማምተዋል፡፡
እነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በጸሐፊው እና ተባባሪዎቹ ናቸው በሚሏቸው ላይ ለመመሥረት ለሚያስቡት ጠቅላላ የክስ ሂደት የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ፣ የፈረንሳይ ደብረ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ በቀለ እና የደብረ ነጓድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ጸሐፊ መምህር ሰሎሞን በቀለ በእማኝነት መዘጋጀታቸውን እና በምክር በኩል እየረዱ መሆኑ ታውቋል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)