August 14, 2010

በርግጥ መጋቤ ብሉይ የተናገሩት የእርቁ እንቅፋት ሊሆን ይገባ ነበር?

(ገብር ሔር ዘመ/መንግሥት እንደጻፈው፤ ኦገስት 14/2010፤ ነሐሴ 8/2002 ዓ.ም)፦ በአንድ ወቅት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ በሰሜን አሜሪካ ለሚሰራጨው የሀገር ፍቅር ሬዲዮ የሰጡት መግለጫ ሰሜን አሜሪካንን ለአስራ ስምንት ዓመታት ላላነሰ ግዜ መኖሪያ ባደረጉት “ስደተኛ አባቶች” ዘንድ አቡዋራ ማስነሳቱን በተባራሪ ወሬ ሰምቼው ነበር። ሳይጀመር ለተጠናቀቀው የሰላምና ዕርቅ መሰናክል የሆነውም ይኸው መግለጫ እነደሆነ ይፋ ሲሆን ሊቁ የተናገሩትን ወይም የሰጡትን መግለጫ ለመስማት ልቡናዬ ተጋ። ግን ከየት አግኝቼ ማድመጥ እችላለሁ? እያልኩ ሳሰላስል የመረጃ ጎተራ የሆነችው ደጀ ሰላም በግራም በቀኝም፤ በድጋፍም በጥላቻም ለተሰለፈው ሁሉ ዕርቀ ሰላሙ ሳይጀመር እንዲያልቅ ምክንያት ሆነ የተባለውን የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴን ቃለ መጠይቅ እነሆ ብላ የመረጃ መረብ ሰሌዳዋ ላይ አወጣችውና የመረጃ ፍላጎት ጥማቴን አስታገሰችልኝ፡፡ በዚሁ እግረ መንገዴን ትጉሁን የደጀ ሰላም (የእርሱን አባባል ልጋራና) ጦማሪ (በልቶ ጠጥቶ ጠግቦ ረክቶ ሳያመሰግን ሹልክ ብሎ እንደሚሄድ ሰው እንዳይመስልብኝ) እግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛልህ እላለሁ፡፡
ወደ አስተያየቴ ስገባ፤ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ አንቱ የተባሉ ተጠያቂ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ እንደነበሩ እንኳን በኢትዮጵያ ባሉ አባቶች ዘንድ ሰሜን አሜሪካ በከተሙትም አባቶች ዘንድ ሳይቀር የሚታመን ነው፡፡ የሰጡት አስተያትም ሚዛን ደፍቶ በውጭ ባሉት አባቶች ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸውም ይኸው በእነርሱ ዙሪያ የተኮለኮሉት ሰባክያኑም፣ ቀዳስያኑም፣ ሁሉም “እንደርሱ ያለ ሊቅ ሰባኪና ቅኔ አዋቂ የለም፤ አልነበረምም፤ ለወደፊትም አይኖርምም” ማለት እስኪቀራቸው ድረስ የሚያሞካሿቸው ስለነበሩና፤ በአፍ በመጽሐፍ ያለውን እውነታ ከታሪክ ጋር አጣቅሰው፣ በውጭው ዓለም ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ሁሉ አቅፈን እንይዝበታለን ብለው በውጭ ያሉት ስደተኛ አባቶች የጣሉትን “በስደት ያለው ሕጋዊ ሲኖዶስ” የሚለውን ዳስ የቆመበት ምሰሶ መሠረት የሌለው፣ በስልጣን ጥማት፣ በወንዝ በጎጥ የተመሠረተ መሆኑን፣ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ በመሾም የቀኖና ጥሰት ተፈጸመ እየተባለ እንደ ሞኝ ለቅሶ ተመላልሶ የሚነገረውም ማደናገሪያ እንጂ እውነታው ምን እንደሆነ፤ ተዋናዮቹ ራሳቸው የተወኑትን ተውኔት ከመድረኩ ርቀው ሲሄዱ ትዕይንቱን ላላየው ሰው በተውኔቱ ውስጥ እንዳልነበሩ አድርገው ያቀረቡት አስቂኝ ድራማ እንደሆነ ፍንትው አድርገው በመግለጻቸው ይመስለኛል፡፡
“በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ ተሾመ” የሚለው የሰሜን አሜሪካዎቹ አባቶች ጩኸት ትክክለኛ እንዳልሆነ፣ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ቀኖና ጥሰው፣ መፈንቅለ ፓትርያርክ አድርገው በመንበሩ ላይ እንዳልተሰየሙ፣ ሲመታቸው (ሹመታቸው) በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የተፈጸመ፣ ከሲመቱ ማግስት ሀገር ጥለው በመውጣት “በአዲስ ስልት ድንገት ያጣነውን ስልጣን መልሰን በእጃችን ማስገባት አለብን” በማለት በሰሜን አሜሪካ የከተሙትን  ጨምሮ ሁሉም “ይደልዎ” (ይገባዋል) ብሎ የተቀበለው መሆኑን ብዙዎች የመሠከሩት ሆኖ ሳለ የመጋቤ ብሉይን ምሥክርነት እነዚህ ወገኖች ልዩና አዲስ ምስጢር ያወጣ ያክል አምርረው ሊይዙበት የቻሉበት ምክንያት ምንድር ነው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡
እንደኔ አመለካከት የመጋቤ ብሉይ መድፍ የጠላትን ወረዳ አሸብሮታል ባይ ነኝ፡፡ በዚያ ወገን ከተሰለፉት ብዙዎች  መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴን አርዓያ የደርጋሉ መባሉን ልብ በሉ፡፡ በአቡነ መልከ ጸዴቅ (አባ ሀብተ ማርያም) ዘንድ አሁን ያሉት የሲኖዶስ አባላት ሲናገሩ እንደተሰሙት “ሁሉ ደናቁርት ናቸው፣ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ግን ሊቅ” ናቸው፡፡ ስለዚህ ሊቅነታቸውን በተቀበሉትና በመሠከሩላቸው ሰው አንደበት “አቡሀ ለሀሰት” መሆናቸውና ዉጉዛን መባላቸውን ከመስማት የበለጠ ቅስም የሚሰብር፣ ተስፋ የሚያስቆርጥና የሚያንገበግብ ነገር ያለ ይመስላችሁዋል? እኔ አይመስለኝም፡፡
በእኔ ዕይታ በእርቁ ላይ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ እንዲገኙ የአሜሪካው ወገን ያልፈለገበት ምክንያት ይህ ጥላቻ ያመጣውና የፈጠረው ፍርሃትም ይመስላል። በውይይቱ ላይ የ“ቀኖና ተጣሰ” ጉዳይ የአሜሪካው ወገን መጫወቻ ካርታ ስለሆነ ይህን በዜሮ የሚያባዛና ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግን ሰው ማግለል ካልተቻለ ትርፉ ኪሳራ መሆኑን በአግባቡ የተረዱት ይመስላል። እንዲህ ካልሆነማ በየትኛው የድርድር መርሕና ደንብ ነው ተደራዳሪ ወገን የሚደራደረውን ወገን የሚመርጠው? ሁሉም በየፊናው ውጤት ያመጣልኛል፣ እውነታውን ያስረዳልኛል ብሎ የሚያምነውን በራሱ ይመድባል እንጂ “እገሌን ለድርድር እንዳትመድብ” እያለ በአንጻር ላለው ተደራዳሪ አስተያየት መስጠት አይችልም።
መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ከተደራዳሪነት እንዲወጡ/እንዲቀሩ የቀረበባቸው ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው። ቃለ ምልልሱን እንዳደመጥነው መጋቤ ብሉይ የሦስተኛውና የአራተኛው ፓትርያርኮች ፓትርያርክነት በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀባይነት የለውም የሚል ቃል አልሰነዘሩም። ዳሩ ግን  በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግን ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ይኼ ደግሞ በብዙዋቻችን ዘንድ የሚታወቅና የማይካድ ነው። የግብጽ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችንም ጠይቆ መረዳት፣ እርሳቸው እንደጠቀሱትም መዛግብትን ማገላበጥም ይቻላል፡፡ይህኮ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ዘንድ የሚታወቅ እውነታ ነው፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን  ተቀብላቸዋለች የሚሉ ከሆነ መከራከሪያቸውና ማስረጃቸውን ማቅረብ ነው። ከዚያ አልፎ ግን ቲፎዞን ለማሰባሰብ ታስቦና በሌላው ወገን ያለውንም ለመሳብና አጋር ለማድረግ ያልተባለን እንደተባለ አድርጎ የሦስተኛውንና የአራተኛውን ፓትርያርኮች ሕጋዊነት እንደሰረዘ አድርጎ ማቅረብ፤ በዚህ የተነሳም “የሁለት አሥርት ዓመታትን ታሪክ ሰርዟል፤ በእነዚህ ዓመታት የተደረጉ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ሁሉ እንዳልተፈጸሙ ተቆጥረዋል” ማለት ከሰማነው የመጋቤ ብሉይ ሠይፈ መግለጫ አንጻር ማሩን አምርሮ ወተቱን አጥቁሮ መናገር ነው፡፡
የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አልተቀበለችም ማለት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አልተቀበለችም ማለት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እስካልተደረሰ ድረስና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት እስከታመነ ድረስ የመጋቤ ብሉይ አስተያየት በእኔ በኩል የአምስተኛውን ፓትርያርክ ሕጋዊነት በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ቀኖናን ያልጣሰ መሆኑን ለማስጨበጥና ለማረጋገጥ የተናገሩት መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም የአሜሪካው ወገን ራሱ ለራሱ በሚመስለው መንገድ በተረጎመው ለሰላም ድርድሩ እንቅፋት ሆኗል ነው የምለው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የወከላቸው አራቱም የሰላም ልዑካን እዚህ ያሉትን ያወገዙ ወይም በውግዘቱ መሠረት ከእነርሱ ጋር ሕብረት የሌላቸው ናቸው፡፡ ሁሉም በቃልም ሆነ በተግባር የእነርሱን ሕገ ወጥነት በአንድም በሌላ ያንጸባረቀ ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከሁሉም ለይቶ አንዱን ጠላት አድርጎ መፈረጅና ከድርድር ውጭ እንዲሆን መጠየቅ ምክንያታዊ ነው ትላላችሁ? አይመስለኝም።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)