August 10, 2010

የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የቀብር ሥነ ሥርዐት ሪፖርታዥ

የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስን አጭር ታሪክ ለማንበብ (እዚህ PDF) ይጫኑ።
  • ‹‹ማወቅ ትርጉም ያገኘው በመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ነው፤ ከካባቸው በላይ ሊቅነታቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፤ ሊቅነት ብቻ ሳይኾን ይህ ጎደለህ የማይባል መልካም ጠባይዕ ነበራቸው፤ ለእርሳቸው እንዲህ ያለ አቋራጭ ጊዜ ይመጣል ብለን አልጠበቅንም፤ ሰላምን ለማምጣት በመፋጠን ላይ እንዳሉ ከረጅም መንገድ መጥተው ወደ ረጅም መንገድ ሄዱ - የሰላም መልእክተኛ ኾነው ሁሉንም በፍቅር እና በትዕግሥት እያዩ ነው የሄዱት፤ ይኼ ራሱ ትልቅ ምስክርነት ነው እኮ!!›› (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ)    
  • ‹‹በቅንነት እና በታማኝነት ያገለገሏት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፡፡›› (የኀዘን መግለጫው)
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 10/2010፤ ነሐሴ 4/2002 ዓ.ም) ነሐሴ አንድ ቀን 2002 ዓ.ም ጠዋት በድንገተኛ ሕመም በተወለዱ በስድሳ ሰባት ዓመታቸው ያረፉት እና በመ/ፓ/ጠቅ/ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ ሐላፊ የኾኑት የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የቀብር ሥነ ሥርዐት በትናንትናው ዕለት ከጠዋቱ 3፡00 - 9፡00 ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተካሄደ የጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዐት ተፈጸመ፡፡

ከዚህ ቀደም ብሎ አስከሬኑ ከነበረበት ሆስፒታል መኖርያቸው ወደ ኾነው እና ሲያገለግሉበት ወደ ነበረው የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት እና ሙሉ አደራረስ ሲደረግ አድሯል፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መመሪያ ሰጭነት በሌሎች የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራትም ጸሎተ ፍትሐት ተደርጓል፡፡

- ‹‹ጋሻ መመኪያዬ ሰይፈ ሆይ የእኔ አባት፣
ድንገተኛው ሞትህ ፈጀኝ እንደ እሳት፤
ላፍታ ተነሣና ምስጢሩን ተናገር፣
አይቃጠል ወገን አንጀቱም አይረር፤
.....
ድንቁርና ንገሥ ዛሬ ተሳካልህ፣
የዕውቀት ሁሉ ቁንጮ ሰይፈ ታሰረልህ፤››(ባለቅኔው)

-‹‹ለሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ
      እንተ ልማዱ ትሕትና
      ለቤተ ክህነት ዓይና፣
ለገብረ ሥላሴ ዐወቀ
      እንተ ንብረቱ ጽሙና
      ለባሕረ ምስጢር ወሰና፣
እስኪ ንገሪኝ እማማ
ትወልጅዋለሽ እንደገና
ያን የቅኔ ጎዳና
ያን የትርጓሜ ሳተና
ያነን የምስጢር ድንቅ ጀግና
ታገኝዋለሽ እንደገና?
እስኪ በይ ይኹና!!››(ባለቅኔው)

ሰኞ ነሐሴ ሦስት ቀን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የየመምሪያ ሐላፊዎች እና ሠራተኞች፣ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግ አርፍዷል፡፡ ከቀኑ አምስት ሰዓት በኋላ ባለቦታዎቹን የቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናት ጨምሮ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት በመጡ ሊቃውንት፡-      
‹‹በአምሳለ ወፍ ርግበ ጸዐዳ ትመስል
    ይእቲኬ ማርያም፣ ማርያም ይእቲ›› የሚለው የአርያም ድርሰት ተወርቧል፡፡ ወረቡ እንደ ተጠናቀቀ በመምህር ቀጸላ፣ በመምህር ዘአማን፣ በመምህር ዲበኵሉ፣ በሊቀ ኅሩያን በላይ መኰነን እና በመጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ የተዘጋጁ ሙሉ አርያም እና ሥላሴ ቅኔያት ቀርበዋል፡፡ ቅኔያቸውን ለማበርከት ጓጉተው በዙርያው ከነበሩት በርካታ ሊቃውንት መካከል በሰዓት መጣበብ ምክንያት ተመርጠው የተሰሙት የመምህራኑ ቅኔዎች ብዙዎቹ ለ75 ዓመታት አራቱን ጉባኤት እና ቅኔ ከነአገባቡ ሲያስተምሩ ኖረው ግንቦት 22 ቀን 2002 ዓ.ም በ102 ዓመታቸው ካረፉት መልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ ዐወቀ ጋራ የተሰናሰሉ እና የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴን የቅኔ፣ የትርጓሜ፣ የጽሕፈት እና የስብከት ዐዋቂነት፣ የሥራ ትጋት፣ ትሑት ሰብእና እና የመግባባት ችሎታ የሚመሰክሩ ናቸው፤ አንዳንዶቹም፣ የሞተ ዕረፍታቸው ድንገተኛነት ያጫረባቸውን ቁጭት እና ጥርጣሬ የሚገልጡ ነበሩ፡፡ በተለይም ለመጋቤ ብሉይ የረጅም ጊዜ የሥራ ባልደረባቸው የኾኑት የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ከቅኔያቸው በፊት እምባ ቀድሟቸው ‹‹እንግዲህ መስቀልን ማን ይጽፈዋል? ጥምቀትን ማን ይጽፈዋል?. . .›› በማለት መንሥኤው በውል ያልታወቀው የሊቁ በድንገት መለየት ያሳደረባቸውን ልባዊ ኀዘን በቅኔያቸው ገልጸዋል፡፡ በግእዝ እና አማርኛ የተነገሩትን ቅኔያት ምስጢር በመረዳት፣ ‹‹እውነት ነው!›› እያሉ ሳግ እየተናነቃቸው አሰምተው የሚያልቅሱ፣ እጃቸውን በቁጭት የሚጸፉ የሊቁ ወዳጆች በዐውደ ምሕረቱ ዙሪያ ተስተውለዋል፡፡

መጀመርያ ታመም ዘመድ ይጠይቅህ
ምንህን እንዳመምህ ይወቀው ወገንህ
በምን ተቀየምህን ምንስ አስቀየምንህ
ሹልክ ብለህ ወጥተህ ወገንህን ትተህ
ከቶ ላትመለስ በመቅረትህ ወሰንህ፤
ምንድነው ነገሩ እንዲህ ያስጨቀነህ
ምንድነው ምስጢሩ እንደዚህ ያስከፋህ
ሰይፈ ሆይ ተናገር ወገንህ ይካስህ
እንደወጣህ አትቅር ዐይን ዐይን ስናይህ፤
ድንቁርና ንገሥ ዛሬ ተሳካልህ፣
የዕውቀት ሁሉ ቁንጮ ሰይፈ ታሰረልህ፡፡

ከዚህ በመቀጠል የሊቁ ዜና ሕይወት እና ሥራዎች በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ አማኑኤል አማካይነት በንባብ ተሰምቷል፡፡ በሕይወት ታሪካቸው ሊቁ ከልደት እስከ ዕረፍት የነበራቸው የትምህርት አድማስ፣ የአገልግሎት ትጋት፣ የሥራ ፍሬ፣ ቤተሰባዊ ሕይወት እና መገለጫ ጠባዕያት በስፋት ተዘርዝረዋል፡፡ የድንገተኛ ዕረፍታቸው መንሥኤ ስለሆነው ሕመማቸው ምንም ያልተባለበት ይህው የሕይወት ታሪክ፣ ‹‹በክቡር መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ዕረፍት መሪር ኀዘን የደረሰባቸው ቤተ ሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ብቻ ሳይኾኑ በቅንነት እና በታማኝነት ያገለገሏት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፤›› ብሏል፡፡

ከጸሎተ ቅዳሴው በፊት የመጨረሻ መርሐ ግብር የነበረው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ቃለ ምዕዳን ነበር፡፡ ‹‹መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ሁሉንም በአክብሮት የሚቀበሉ፣ ይህ ቀረህ የማይባሉ መልካም ጠባይ የነበራቸው ሊቅ እና ወንድም ነበሩ፡፡ ብዙ ምሁራን እንዳሉ ይነገረናል፤ እናያለን፤ የእርሳቸው ግን የተለየ ነበር፤ በካባ እና ባማረ ልብስ የተደበቀ አልነበረም፤ ከካባቸው በላይ ሊቅነታቸው ጎልቶ ይታያል፤ ለሚጠየቁት ሁሉ ‹እሺ፣ ይኹን› ባይ ነበሩ፤ ፍጥነት፣ ጥራት እና ታማኝነት የሚያስፈልገው ተግባር ለመጋቤ ብሉይ ነበር የሚሰጠው፤›› ያሉት አቡነ ጳውሎስ የሊቁ መዋዕለ ዘመን እንዲህ ባጭሩ ይቋረጣል ብሎ የሚያስብ እንዳልነበር በመጥቀስ የመለየታቸውን አስደንጋጭነት አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹እንደ ባሕር ጥልቅነት ያለው መልካም ጠባይ ያላቸው እና ደከመኝ ማለትን የማያውቁ ነበሩ፤ ይህው አሁን እንኳ ሰላምን ለማምጣት በመፋጠን ላይ እንዳሉ ነው ከረጅም መንገድ መጥተው ወደ ረጅም መንገድ የሄዱት - የሰላም መልእክተኛ ኾነው፣ በአውሮፕላን ማረፊያ ጎንበስ ቀና ብለው አብረዋቸው የነበሩትን እየረዱ፣ ሁሉንም በፍቅር እና በትዕግሥት እያዩ ነው የሄዱት፤ ይኼ ራሱ ትልቅ ምስክርነት ነው እኮ!!›› በማለት አንክሯቸውን ገልጸዋል፡፡

በቃለ ምዕዳናቸው መጨረሻ፣ ‹‹ማወቅ ትርጉም ያገኘው በመጋቤ ብሉይ ነው፤ በሰው መተካት ለእግዚአብሔር ልማዱ ስለሆነ ለዚህ ጸሎት ያስፈልገናል፤ ከዚህ በቀር ወደኋላ መመለስ አንችልም፤ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከማኅበረ መላእክት፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ይጨምርልን፡፡›› በማለት ካሳረጉ በኋላ ሥርዐተ ቅዳሴውን መርተው ከድርገት በኋላ፣ ከሠርሆተ ሕዝብ በፊት አስከሬኑን በተዘጋጀለት መካን(ፉካ) በማሳረፍ የቀብር ሥነ ሥርዐቱ እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡ ሥርዐተ ቀብሩ በተጣደፈ አኳኋን እንደተፈጸመ የሚገልጹ የአንዳንድ የቤተሰብ አባላት እና ሌሎች ኀዘንተኞች ቅሬታ የተሰማ ሲኾን ከቅዳሴው በፊት የተከናወነው ሥነ ሥርዐት ከቅዳሴ በኋላ እንደሚኾን ጠብቀው ለመጡት ኀዘንተኞችም ኹኔታው ግርታን ፈጥሯል፡፡ ጥድፊያው ምናልባትም ፓትርያሪኩ  ለሱባኤው እና ለጤንነታቸው ወቅታዊ ተስማሚነት ወዳለው ወደ ድሬዳዋ ዕለቱኑ ያደርጉታል ተብሎ ከሚታሰበው የመልስ ጉዞ ጋራ ሳይያዝ እንደማይቀር አንዳንድ ተመልካቾች ግምት ወስደዋል፤ ሌሎችም ከቅዳሴው በፊት የተከናወነው መርሐ ግብር በቂ እንደ ኾነና ግብአተ መሬቱ ከድርገት በኋላ መፈጸሙ ሥርዐታዊ መኾኑን በአዎንታ በመጥቀስ ቅሬታውን ያጣጥሉታል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ለሊቁ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ዕረፍት ከተበረከቱ ቅኔዎች መካከል የቀረቡትን እና በአማርኛም በግእዝም ከተነገሩት አንዳንዶቹን ለዝክረ ነገር መርጠን አቅርበንላችኋል፡፡

ሀ) ‹‹ሕያው ልሳን›› የተባለው የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጅ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን ያቀረቡት፤
                  ጉባኤ ቃና     
፩.እፎኑመ ሞት ለሰይፈ ሥላሴ ዘፈርሆ
እስመ በፍኖት ተኃብዐ ከመ ይማኦ ጸኒሖ፡፡

፪.መኰንነ አቤል ቃየን ለሰይፈ ሥላሴ ተወክፎ
እምዕራፈ መቅሰፍት አየር ጽጌ ሞተ ግብት ሐቂፎ፡፡
                 
ሥላሴ ቅኔ
በገባዖን መቃብር
እመ ተዐየኑ ሠራዊት፣
ንግሥተ ሃይማኖት አዜብ
አሐቲ በዘታጸንዕ ሥርዐተ፣
ፈነወቶ ለገብረ ሥላሴ ዘሰይፈ ቀነተ፡፡

ወቤተ ትርጓሜ ተኀሥሥ እም ልባ
ዘይመርሐ ፍኖተ፤
እስመ ክልኤሙ አዕይንተ፣
ፍጡነ ኀጥአት አሐተ ዓመተ
ወትበኪ ኵለሄ ዕለተ፡፡

ኦ ሰይፈ ሥላሴ የቅኔው ገበሬ
የወልደ ማርቆስ የአክሊሉ ፍሬ
በቅድስት ሥላሴ መካነ ኁባሬ
መወድስ ሲዘርፉ ሊቃውንተ ኀሬ
ፍታሕ ሊተ አትልም ምኑ ነካህ ዛሬ፡፡

ወጋ ወጉ እንዳይቀር እያልን ዲማ ሞጣ
መወድስ ልንቀኝ ስንዘርፍ አገኝ አጣ
ቅኔ ብናበላሽ የምስጢሩን ጣጣ
አደራህ ሰይፍዬ በእኛ እንዳትቆጣ፡፡

ነገሩስ ሰይፍዬ!
ከወልደ ማርቆስ በመንፈስ ተወልደህ
የደንቢያው አክሊሉ ኮትኩቶ አሳድጎህ
ከገብረ ሥላሴ ከማዕዱ በልተህ
እኛም እናውቃለን
ትዕቢትና ቁጣ አይደለም ገንዘብህ፡፡

ኦ መጋቤ ብሉይ ዘልብከ ብሩህ
ወከመ ስምከ ልሳንከ በሊህ
በዚያ በጣፋጩ ለስላሳ አንደበትህ
በደስታው ባዘኑ
መወድስ ስትዘርፍ ቀስ ረጋ ብለህ
ታሪክ ስትነግረን በዘጋቢ ፊልምህ
ይበል! መልካም ብለን አጨበጨብንልህ
የዛሬ ሁለት ወር ይዘህ በትረ ሙሴ
ለመልአከ ገነት ለገብረ ሥላሴ
ተቀኝተህ ነበር መውድስ ሥላሴ፡፡
ዛሬ ድንገት ስትበር ልብህ ሀገር ናፍቆ
ነጣቂ ተኩላ ሞት መንገድ ላይ ሸምቆ
የምሥጢሩን ለዛ አንደበትህን አንቆ
ከመንጋው ለይቶ አልጋ ላይ ቢያውልህ
በመጽሐፈ ግንዘት ስንፈታህ ላንፈታህ
ቅኔ ምትዘርፍበት አንተ አንደበት ካጣህ
እባክህ ንገረን ምን እንቀኝልህ?

እየሰማሽ ነው እማማ!
ድንቅ ቅኔያቸው ሲፈታ
የዲማው ቅኔ ዘራፊ
        ሰይፈ ሥላሴ ቱማታ
መልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ
        የኒያ የሞጣው ዬኔታ
የቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጅ
        ሰዋስወ ብርሃን ማኅቶታ
የብሉይ ኪዳን ምሰሶ
        የሐዲስ ኪዳን ዋልታ
እስኪ ንገሪኝ አንድ አፍታ
ጎዳና ቅኔው ሲፈታ፡፡

ብሥራተ አብ ረድእ ትሩፍ
ብሎ ጀምሮ ሐዲስ ምዕራፍ
በእእምሮው ወንጌል ሲጽፍ
በትርጓሜው ሲረቅ ሲገዝፍ
በቅኔ ምሥጢር ሲፈላሰፍ
እንደ ስሙ ነበረ ሰይፍ፡፡

በቀዳሚ ገብረ ብሎ
ብሉያትን አደላድሎ
እምከርሰ እሙ አእሚሮ
እንዘ ይተግህ ለምህሮ
ቃል ሥጋ ኮነን ፈክሮ
በአንድምታ ተርትሮ
ሐዲሳትን አመሳክሮ
በራእየ ዮሐንስ ዘለቀ
ገብረ ሥላሴ ዐወቀ፡፡

ለሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ
እንተ ልማዱ ትሕትና
ለቤተ ክህነት ዓይና፣
ለገብረ ሥላሴ ዐወቀ
 እንተ ንብረቱ ጽሙና
 ለባሕረ ምስጢር ወሰና፣
እስኪ ንገሪኝ እማማ
ትወልጅዋለሽ እንደገና
ያን የቅኔ ጎዳና
ያን የትርጓሜ ሳተና
ያነን የምስጢር ድንቅ ጀግና
ታገኝዋለሽ እንደገና?
እስኪ በይ ይኹና!!


የመምህር ዲበኵሉ ግጥም እና ቅኔ
         
ምንድን ነው ነገሩ?
የተላኩበትን ወሬ ሳያበሥሩ
ሪፖርቱ ሳይቀርብ ዜና ሳያወሩ
እንደወጡ መቅረት ምንድን ነው ነገሩ፤

የተላኩበትን እግዚአብሔር ይርዳዎት
በሰላም ይምጡልን ብለን ሸኝተንዎት
ደኅና ኹኑ ብለው በመሰነባበት
ምንድን ነው ነገሩ እንደወጡ መቅረት፡፡

ጋሻ መመኪያዬ ሰይፈ ሆይ የእኔ አባት፣
ድንገተኛው ሞትህ ፈጀኝ እንደ እሳት፤
ላፍታ ተነሣና ምስጢሩን ተናገር፣
አይቃጠል ወገን አንጀቱም አይረር፤

አፈር አፈር ማለት የሰው ዐይን መጥላቱ
ታይቶበት አያውቅም ሰይፈ በሕይወቱ
ታዲያ ወገን መጥላት ከሩቅ መሰወሩ
ምንድነው ነገሩ፣ ምንድነው ምስጢሩ


መጀመርያ ታመም ዘመድ ይጠይቅህ
ምንህን እንዳመምህ ይወቀው ወገንህ
በምን ተቀየምህን ምንስ አስቀየምንህ
ሹልክ ብለህ ወጥተህ ወገንህን ትተህ
ከቶ ላትመለስ በመቅረትህ ወሰንህ፤
ምንድነው ነገሩ እንዲህ ያስጨቀነህ
ምንድነው ምስጢሩ እንደዚህ ያስከፋህ
ሰይፈ ሆይ ተናገር ወገንህ ይካስህ
እንደወጣህ አትቅር ዐይን ዐይን ስናይህ፤
ድንቁርና ንገሥ ዛሬ ተሳካልህ፣
የዕውቀት ሁሉ ቁንጮ ሰይፈ ታሰረልህ፡፡


ሞት የሚሉት ጠላት ይንሁሉ እያወቀ
በቅኔው ባለቤት በሰይፈ ላይ ሣቀ
በብሉያቱ ሊቅ በሰይፈ ላይ ሣቀ፡፡

ቅኔ ማን ይቀኝህ
መጽሐፍ ማን ይጻፍህ
ሰም እና ወርቅህን ማንስ ያራቅልህ
መጽሐፍ አንድምታን ማን ይተርጉምልህ
ታላቁ ዐይናማ ሊቅ ሰይፈ ተጋዘልህ፡፡

ወርቅ እና አልማዝ ዕንቈ ጽጌሬዳ
እንደ ቀላል ነገር ገባህ ከሞት ጓዳ፤
ያን ሁሉ ዕውቀትህን ለልጅ ላታወርሰው
ታላቁ ሊቅ ጀግና መድከምህ ለምነው?

ቅዱስ አባታችን እግዚአብሔር ያጽናዎት
ፈጣኑ ልጅዎን ሞት ወሰደብዎት
የሰይፈማ ነገር አከተመ በቃ
ሰው ይፈልጉልን ሰይፈን የሚተካ
ታላቋ እናትዎን ወራሪ እንዳይደፍራት
ቅዱስ አባታችን ሰው ይፈልጉላት፤
የዋህ እናትዎ ታሳዝነኛለች
ታላቁን ልጅ ቀብራ ትንሹን ደገመች፤
ታላቋ እናትዎን የልጆችን እናት
ሾተላይ ናት መሰል እስኪ ያስመርምሯት፤

የመጀመርያው ልጅ ወጣ ወጣ ሲባል
በአጭር ርቀት እንዲቆም ተገዷል
ለአካለ መጠን ሳይደርስላት ቀርቷል
በሞትም ማሰርያ ታስሮ ተለይቷል፤
ያ ታላቁ ልጇ በሞት ቢለያትም
በልጅ ልጅ ተክሳ ትኖር ነበር ጎጃም
በዚያ ሁሉ መከራ ከዐይኗ እምባ ሳይጠራ
የመጨረሻው ልጅ ሰይፈ ከዐይኗ ጠፋ፤

የሞት ቀስቶች ሁሉ በእሷ አነጣጠሩ
በደጋን መሎጊያው ሹሎች ተቀሰሩ፤
ምንድነው ነገሩ ምንድነው ምሥጢሩ
በአበባ እየታዩ መቅረት ሳያፈሩ፤

አለኝታችን ሰይፈ ተጠያቂው አባት
የትምህርት መሠረት የዕውቀት አብነት
እግዚአብሔር ነፍስህን በገነት ያኑራት፡፡

ጉባኤ ቃና
፩. ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ
   ሞተ ፍጡራን አእላፍ
   ኀበ ውስተ ቤቱ አብዖ
    ለበዓለ ቅኔከ ሰይፈ፡፡

፪. ጎጃም ተከዘት ዘኢተከዘት እምጥንታ
   አኮኑ ማሰና ክልኤቲ
   አንቅዕት ብርሃን አዕይንታ

፫. ጎጃም ወላድ ለቅኔያት
   ዉሉደ ሰይፈ ክብር ይባቤ
   እጓለማውታ ትኩኑ ኢያኀድገክሙ ትቤ፡፡

               ሥላሴ
ሰይፈ ኢትአንሥዑ ዕፄያተ አልዓዛር አልዓዛር
በከመ አንበብነ ቅድመ ዘሊቃውንተ መጽሐፈ
እስመ ሰይፍ እለያነሥኡ ይመውቱ ሰይፈ. . .

              መወድስ
ቤተ ክርስቲያን ወላድ ወላደ አእምሮ
ብካያ ትበኪ በለቢሰ ልብስ ጸልይ
በሞተ ፍጡራን ሞት ሠረገላ ዛቲ ዓለም፤
ቅኔያት ዉሉደ ሥጋሃ
እስመ አንቊ ዮም፤
ወለሞት ሠረገላ ዘያረውፆ
ጠቢብ ሰይፈ ሥላሴ መስተቀውም
ድኅረ ወድቀሂ ሞተ ገንጰለ
ጽድቀ ሐቅለ አቤሮን ሴም
ሞት ሠረገላ ዘተንሥኣ በሰላም
ለነሢኣ ብዙኅ ሕዝብ ለሰይፈ ሥላሴ ሥዩም
ኢያትረፈ ዘርዐ ሰብእ ወኢክፍልተ ዐፅም፡፡
ሀገረ ቴዎፍሎስ አብ መቃብረ ሥጋ
ሰይፈ ሥላሴ ነገደ በኀዲገ ብዙኅ ምሕረቱ
ወቅኔያቲሁ በዛኂት ሕፃናቲሁ እሙንቱ
እንዘ እንዘኀድግ በበክፍሉ
ቴውፍሎስ አምጣነ ጸውዖ ይትረከብ በቤቱ
ወቃለ ቴዎፍሎስ ዘያከብር ሰይፈ ሥላሴ ሰማዕት
ለቴዎፍሎስ አረፍቱ
ቴዎፍሎስሂ መሠረትነ
ወለክብረ ጳውሎስ ጥንቱ
ለሰይፈ ሥላሴ ከመ ንርአዮ
ፈንዎ በሕይወቱ
ድኅረ ነጸርኖሂ ኵልነ
ወጠየቅናሁ ለዝንቱ
ይትመየጥ መንገሌከ ወትገብር ዘትፈቱ፡፡

No comments:

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)