August 9, 2010

የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች:- የስውሩ ፀሐፊ “ስም አጥፊ” አዲስ መጽሐፍ


  • ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ድሮም ዘንድሮም ወደፊትም ያው ናቸው፡፡ ነገሮች ሁሉ ባልተለወጡበት እና ባሉበት ኹኔታ እየቀጠሉ በጋሻውን የለወጠው ኹኔታ ስታሰብ የጥቅሙን ስፍራ ከማዘዋወር በቀር የሚገባን ነገር የለም፡፡››
  • ወ/ሮ እጅጋየሁ ‹‹የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር አየር ባየር ትመራለች፡፡››           
  • ‹‹የአቡነ ጳውሎስን ሐውልት መቶ ሺሕ ብር አውጥቶ ያስገነባው በጋሻው ስርየት የሌለው ጥፋት ውስጥ የገባ የራሱን ጥቅም ማዕከል በማድረግ ነው፡፡››
  •  ስለ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒን ምንም አለመናገሩ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡  
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 8/2010)፦ የፓትርያርኩና የማፊያው ቡድን “ስውር ፀሐፊ” (Ghost Writer) ዘሪሁን ሙላቱ ስለ ፓትርያርኩ ሐውልትና ተያያዥ ጉዳዮች  ባለ 50 ገጽ መጽሐፍ አወጣ፤ እነ በጋሻው ደሳለኝና ኤልዛቤል የምትባለው ወ/ሮ እጅጋየሁ ተጠቅሰውበታል። ዲያቆን ሲባል ቆይቶ በቅርቡ ሊቀ ትጉሃን የሚል የማዕረግ ስም የደረበው Ghost Writer ዘሪሁን ሙላቱ ጊዜውን በቶሎ በማጥናት እና የፓትርያርኩ ሐውልት ብዙ ተቃውሞ እንደበዛበት ሲመለከት፣ የሐውልቱ ተቃዋሚዎች ያሉትን በመሰብሰብና መጽሐፍ አድርጎ በማሳተም ሲያሳዝነው የሰነበተውን ምእመን አሁን ደግሞ ገንዘቡን ሊበላው ይህንን ፓምፍሌት (መጽሐፍ ለማለት ይከብዳል) አሳትሟል። መታሰቢያነቱንም በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በማድረግ መጽሐፉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሞክሯል። ርእሱን ደግሞ በቅርቡ እኛም ካወጣነው (በአዲስ አበባ በጋዜጣ ከወጣ) አንድ ጽሑፍ ላይ የወሰደው ነው።
ቅጥረኛው ጸሐፊ(the Ghost Writer) ዘሪሁን ሙላቱ (የቅርብ ጓደኞቹ እንደሚጠሩት ‹ሁከት›) ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› በሚል ርእስ ያዘጋጀውን እና ያሳተመውን መጽሐፍ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ በገበያ ላይ አዋለ፡፡ መጽሐፉ ‹ፈታሒ በጽድቅ› በሚል የፈጠራ ደራሲ ስም የተሰየመ ሲኾን ሽፋኑን እና የመግቢያ ገጾቹን ጨምሮ 50 ገጾች አሉት፡፡ የአንዱ መጽሐፍ ዋጋ 15 ብር ሲኾን በቅርቡ ላረፉት የከምባታ፣ ሐዲያ እና ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለነበሩት ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ መታሰቢያ ተደርጓል፡፡

በመጽሐፉ የፊት ሽፋን ላይ - ሐምሌ አራት ቀን 2002 ዓ.ም የአቡነ ጳውሎስን 18ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ‹‹በልዩ ኹኔታ ለማክበር›› በሚል በበጋሻው ደሳለኝ አሳሳቢነት፣ በራሱ በዘሪሁን ሙላቱ (ሁከት) ሐሳብ አመንጪነት እና አቀናባሪነት፣ በሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ እና ተባባሪዎቹ የገንዘብ ድጋፍ፣ በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ(ኤልዛቤል) አስፈጻሚነት፣ በአቡነ ጳውሎስ እና ሌሎች ዐሥራ አንድ ጳጳሳት መራቂነት ይፋ የኾነው የአቡነ ጳውሎስ ‹‹የምስክርነት ሐውልት›› በጥቁር ሰማያዊ መደብ እና በክበብ ውስጥ ቆሞ ይታያል፡፡ ከሥሩ ደግሞ በሦስት የካርታ መጫዎቻዎች ላይ የሦስት ሰዎች ምስል ይታያል - በመጀመርያው እና ‹ሸሌ› እየተባለ በሚጠራው ካርታ ውስጥ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ በሁለተኛው ካርታ እና ‹ዳይመንድ› እየተባለ በሚጠራው ካርታ ውስጥ በጋሻው ደሳለኝ፣ በሦስተኛው እና ‹ጆከር› እየተባለ በሚጠራው ካርታ ውስጥ ደግሞ አወዛጋቢው - የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የኾኑት፣ ለአቡነ ጳውሎስ የተበረከተውን የ3.5 ሚልዮን መኪና ስጦታ በውድም በግድም እንዲሰጥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትን እና አድባራትን ያስተባበሩት እና በመጽሐፉ ውስጥ በሀገረ ስብከቱ በሚፈጽሙት ዐይን ያወጣ ሙሰኛነታቸው እና አመንዝራነታቸው ክፉኛ የተብጠለጠሉት የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ሥዕለ ገጽ ይታያል፡፡

ዘሪሁን ሙላቱ (ሁከት) ይህን መጽሐፍ ለማሳተም ይሻ እንደ ነበር ቀደም ብሎ ይታወቅ የነበረ ቢኾንም ምንደኛው ጸሐፊ በገጠመው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እስከ አሁን እንደዘገየ ይገመታል፡፡ ይኸው በአንዳንድ የቤተ ክህነቱ ሰዎች የጥቅም ተጋሪነት እገዛ ለኅትመት እንደበቃ የሚነገርለት መጽሐፍ፣ ቅጥረኛው ጸሐፊ ያለበትን ሥር የሰደደ የገንዘብ ሰቀቀን ለማስታገሥ እና ግለሰባዊ ቂም በቀሉን ለመወጣት እንደ ጻፈው የቅርብ ባልንጀሮቹ ይናገራሉ፡፡ መጽሐፉ ዛሬ ለኅትመት ከመብቃቱ በፊት በውስጡ በስም ለይቶ እየጠቀሰ የግል ገመናቸውን እና ኀጢአታቸውን ከዘከዘከባቸው ሰዎች መካከል ለከፊሎቹ የሚመለከታቸውን የረቂቁ ክፍል ከኅትመቱ አስቀድሞ እንዲደርሳቸው በማድረግ የጠየቀውን ገንዘብ እንዲሰጡት ማስፈራራቱን (Blackmailing) ለግለሰቦቹ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ከእኒህም መካከል እንደ መጽሐፉ አባባል ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጋራ ያላቸው የጠበቀ ግንኙነት መቼ እና ማን እንደጀመረው በ‹ሳይንሳዊ እና ፖለቲካዊ› የምርምር ዘዴ እና አካሄድ በ‹ስውር ጸሐፊዎች› እየተጠኑ ያሉት ወ/ሮ እጅጋየሁ ሽፈራው እና በጋሻው ደሳለኝ ይገኙበታል፡፡

በተለይም የመጽሐፉን ዝግጅት ዜና ቀደም ብለው የሰሙት ወ/ሮ እጅጋየሁ ምንደኛውን በመልእክተኛ ሳይደራደሩት እንዳልቀረ ነው ቀራቢዎቻቸው የሚመሰክሩት፡፡ እርሳቸውን የሚመለከታቸው ያልታተመውን የመጽሐፉን ገጾች እንደተመለከቱት በመጀመርያ ከት ብለው የኮረኮሯቸውን ያህል የሣቁት ወይዘሮዋ አፍታም ሳይቆዩ ምርር ብለው ማልቀሳቸውን እና ቅጥረኛውን ጸሐፊ ‹‹ልክ እንደሚያገቡት፣ ዋጋውን እንደሚሰጡት›› መዛታቸው ተሰምቷል፡፡ ሴትዮዋ የፓትርያሪኩ አጋፋሪ እና በረኛ፣ በራሱ አገላለጽ ‹‹የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር አየር ባየር የምትመራ›› ኾነው ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ የሚገቡትን እና የሚወጡትን ሰዎች ወሳኝ መኾናቸው(ገጽ 31) ያስከፋው ጸሐፊው ከሚሌኒየሙ በዓል አከባበር በኋላ ከሴትዮዋ ጋራ በጥቅም በፈጠሩት እያደር የሚያገረሽ እና የማያባራ ግጭት የተነሣ እርሱም ከፓትርያሪኩ ጋራ እንደ ልቡ የመገናኘቱ ዕድል በ‹‹እቴጌዋ›› የተወሰነበት በመኾኑ በቂም በቀል ተነሣስቶ እንዳደረገው ብዙዎች ሐሳባቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይህም ኾኖ ወይዘሮዋ ውስጥ ዐዋቂው ስውሩ ጸሐፊ ከዚህም ከዚያም የቃረመውን ጉዳቸውን እንዳያወጣባቸው እስከ 20‚000 ብር በሚደርስ አፍ ማበሻ ሊለጉሙት ቢሞክሩም ሳያሳካላቸው ቀርቷል፡፡

በዚህ መጽሐፍ ክፉኛ ከተሳጡት ከአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ እና ከማፊያ ቡድኑ አባል ያሬድ አደመ በላይ የብዙዎችን አንጀት የበላው እና በምጸት ከንፈር የተመጠጠለት የማፊያ ቡድኑ መሪ በጋሻው ደሳለኝ ነው፡፡ በጋሻው እና ወ/ሮ እጅጋየሁ ‹ስማቸውን ለማስጠራት› እንደተሳሰሩ የገለጸው ምንደኛው ጸሐፊ በጋሻው ሴትዮዋ ያቋቋመችው ‹‹ቀራንዮ›› የሚባል የጉዞ ማኅበር የኮሚሽን ሠራተኛ እንደ ነበር በመጥቀስ ይሳለቅበታል፡፡ የፓትርያሪኩ ሐውልትም የሁለቱ ‹‹የገንዘብ ማጋበሻ›› ስልት እንደ ነበር እና በጋሻው ‹‹ገንዘብን ያማከለ መናፍቅነት›› ወይዘሮዋ ‹‹ገንዘብን ያማከለ ዘማዊነት›› የዘወትር ቋንቋቸው እንደ ኾነ ገልጧል፡፡ በማያያዝም ‹‹እነዚህ ሰዎች የጎደፈውን ስማቸውን ለማስጠራት አዲሱን ስማቸውን ለማስተዋወቅ እና ኑፋቄያቸውን ለመሸፈን ሐውልቱ ሥር ተከልለው ይቆምራሉ፤›› ብሏል፡፡ የፓትርያሪኩን ሐውልት ማቆም የማን ውሳኔ ነው፣ ከየት የመጣ ትምህርት ነው፣ ይህ የሐውልት አሠራር የማን ውሳኔ ነው የሚሉትን ጥያቄዎች አንሥቶ ምላሽ ያልሰጠው ጸሐፊው፣ ‹‹...ሐውልቱ እንዲህ ያለ ውዝግብ የሚያስነሣ ከኾነ መፍትሔው መፍረስ ብቻ ነው፤ እንኳን የእጅጋየሁ እና የበጋሻው ሐውልት የሰሎሞን ቤተ መቅደስም ፈርሷል፤›› በማለት በሐውልቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ያፌዛል፤ ሐውልቱን በማሠራት ረገድ ሁነኛ ሚና እንደ ተጫወተ የሚነገርለትን ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒን ከተጠያቂነት በማውጣት በጋሻው 100,000 ብር መርዳቱን ጽፏል፡፡

‹‹ለምጻሙ ሰባኪ›› በማለት የገለጸው በጋሻው ደሳለኝ ቀደም ሲል ‹‹የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች›› በሚል ርእስ በጻፈው መጽሐፍ ያሰፈራቸውን ሐሳቦች እና በተቃራኒው የጎደፈ ስሙን ለማደስ እና ለቢዝነስ አሠርቶታል ባለው በአቡነ ጳውሎስ ሐውልት ምረቃ ላይ ያሳየውን ሰብእና በማነጻጸር በተለያዩ አገላለጾች ይወርፈዋል፤ ከእኒህም የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፤
.‹‹ትላንት ‹በመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች› - ‹በወንጌል አላፍርም› አለ፡፡ ዛሬ እርሱ ራሱ ‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኛ› ኾኖ ‹በሐውልቱ አላፍርም› አለ፡፡
ትላንት ‹የመስቀሉ ቁማርተኞች› ብሎ አባቶችን ዘለፈ፤ ዛሬ እርሱ ራሱ ‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኛ› ኾኖ ተገኘ፡፡››

.‹‹ትላንት ‹በመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች› ትላንት ‹ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ተሰበከ ይበቃል› አለ፤ ዛሬ እርሱ ራሱ የሐውልቱ ሥር ቁማርተኛ ኾኖ ዘማዊቷን ‹የአገልጋዮች እናት ወ/ሮ እጅጋየሁ ከሴቶች ሁሉ ትበልጣለች፣ እንስበካት አለ፤ ትላንት ‹በመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች› ‹አቡነ መርቆሬዎስ ከኢትዮጵያ ገዳማት ይልቅ አሜሪካን መርጠው ኮበለሉ፤› አለ፤ ዛሬ እርሱ ራሱ የሐውልቱ ሥር ቁማርተኛ ኾኖ ‹አሜሪካ ቅድስት አገር ናት› በሚል የራሱን ጉዞ አመቻችቷል፡፡....››

.‹‹ትላንት ‹በመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ብሎ የምን ደብረ ሊባኖስ መሄድ፣ የምንስ አክሱም መሄድ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት ማለትስ ለምን አስፈለገ› እንዳላለ ዛሬ ዛሬ እርሱ ራሱ የሐውልቱ ሥር ቁማርተኛ ኾኖ ሁሉንም የማዕርግ ስማቸውን ከጠራ በኋላ ትርጉሙን ሳያውቀው ‹ስምከ ሕያው ሰማዕት ዘእንበለ ደም› የሚለውም የማዕርግ ተጨማሪ ስም ይገባቸዋል› ብሎ ዐውደ ምሕረት ላይ አፉን ስትራፖ እስኪይዘው ድረስ ሙሉ ስማቸውን ጠራ፡፡ ይህ ደግሞ ሊቃውንቱ የግእዙ ተሸካሚ እርሱ ደግሞ ተጠቃሚ መኾኑን በእጅጉ ያሳየናል፡፡››

.‹‹የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች› የሚለውን መጽሐፍ አንብበው የሃማኖት አባቶች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ያሳደሩ ምእመናን፣ ድንጋይም የጨበጡ ምእመናን ሰዎች ዛሬም አሉ፡፡ እርሱ ግን የጨበጠውን ድንጋይ አቅልጦ የንግድ ምልክት ሐውልት አድርጎታል፡፡ እርሱን እንዲህ የለወጠው እውነተኛ ነገር ካለ ይንገራቸው እና ይለወጡ......‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኛ› እንዲህ እያለ ለገንዘብ ጥቅም በሚያምታታበት ኹኔታ የማስተማር ዕውቀትም ኾነ የመናገር ብቃት የለውም፡፡ ይህ ዘመን የሚያገለግልበት ሳይኾን የሚገለልበት የንስሐ ዘመኑ ነው፡፡››

.‹‹ወይ በጋሻው ገና የድንግል ማርያምን አማላጅነት ሳትሰብክ የወ/ሮ እጅጋየሁን አማላጅነት መስበክ ጀመርክ፡፡ እጅጋየሁን ‹አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ› አልካት፡፡ ይህን ከአንተ አልጠበቅንም ነበር፡፡ ዕውቀት እንደሌለህ ብናምንም እግዚአብሔር እንደ በለዓም አህያ ይጠቀምብሃል ብለን አስበን ነበር፡፡ በድምፅህ ብቻ አታለልከን፤ ተጠግተን ስናይህ ግን ከድምፅህ ጎርናናነት በስተጀርባ ውሸታምነት፣ አታላይነት፣ መናፍቅነት ተሸክመሃል፡፡››

.‹‹በመሠረቱ መምህር ዘመድኩን በቀለ አንዳንድ ምልክቶችን ‹ቤተ ክርስቲያን አደጋ ላይ ነች› በሚል ርእስ ማስጠንቀቂያ ምልክት አሳይቶን ነበር፡፡ እኛም ፍጻሜህን እንይ ብለን እስከ ቀራንዮ(ቦሌ መድኃኔዓለም) ተከተልንህ፡፡ አንተም በራስህ የገንዘብ ፍቅር እና ፍላጎት ራስህን ሰቅለህ ‹የሚያደርጉትን አያውቁም› በሚል ስላቅ እኛ ላይ ሙድ ያዝክብን፡፡ ለውሸት ብለው የውሸት ሣቅ የሚሥቁ ብለህ እንዳልነበርክ አንተም የእውነቱ ሣቅ ጠፍቶብህ የውሸት ሣቅ መሣቅህ ምስጢሩ ምን ይኾን?

የመጽሐፉ ርዕስ፦ የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች፣
ዋጋው፦ 15 ብር
የገጽ ብዛት፦ 50 ብቻ
ደራሲ፦ ፈታሒ በጽድቅ (የብዕር ስም)፣
መታሰቢያነቱ፦ ለአቡነ መልከ ጼዴቅ
ማተሚያ ቤት፦ አልተጠቀሰም፣
ምእመናን እንዲህ ዓይነቱን ርካሽ መጽሐፍ እየገዙ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን በተዘዋዋሪ እንዳይጠቅሙ እናስታውሳለን።

6 comments:

Anonymous said...

I 'appreciate', how these people are working the business, just they need money in any direction....Egziabher hoy libona sitatchew

Anonymous said...

ጉድ ነው። እባካችሁ ይእ አዲስ አበባና ታላላቅ ከተሞች ለሚኖሩ ምዕመናን እንዲደርስ ይደረግ። የዚህ አይነት ርካሽ ስራ ወደ ቤተክርስቲያናችን መግባቱ በጣም ያሳዝናል። የታተመበት ቦታ የማይጠቀስ መጽሐፍ በብዛት የሚውለው ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው።

Basha said...

selam Dejeselamoch

lemerejaw betam eyamesegenkugn yebelete yihe 'metsehaf' esti bihonm lemanbeb yakil gezten eniyew bilew memenan begeza genzebachew betekiristiyanen endaygodu manim yemichil Dejeselamawi 'metsehafun' be PDF dejeselam lay biletef ena benetsa biserach gexi ayinorewm biye aminalew.

Anonymous said...

God please please please save us from this game pls.

Anonymous said...

ይድረስ ለደጀ ሰላም አዘጋጆች ብዙ ግዜ የምታወጡትን መጣጥፍ አነባልሁ አሁን የሚወጡት ፁሁፎች ግን መንፈሳዊ ይዘት የጎደላቸው ስለግለሰብ የሚያወሩ ከግል ጋዜጦች ብዙም የማይልዩ ናቸው። አስተያየት ሰጮዎቹም ብዙዎቹ ስድብ የተሞሉ ክርስቲያናዊ ባህሪ የማይታይባቸው ሲሆኑ በጥቂቱ ደግሞ መልካም ሆኑ አስተያየቶች ለመመልክት ቸያልሁ።
የዚች ድህረ ግፅ ጥቅም ክርስቲያናዊ ባህሪን ማጎልበት ካልሆነ ዝም ብሎ የሰው ጉድፍ ማውራት ምን ጥቅም አለው? በራሳችን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ሳናውጣ ማን ፈራጅ አረግን? ክርስቶስ ፍቅር ነው ደቀ መዝሙሩ ክሆንን ፍቅርን መቻቻልን መከባበርን እንልመድ።
ስለክርስቶስ ወንጌል እናውራ በቃ ደፍረን እንግለጠው በዚህ ዓለም ስላለው ተረት ማውራት ይብቃን እውነት ካልን በፍቅር እንመክር። እኛ የተጠራነው የጳውሎስ ወይም የአጵሎስ ደቀመዝሙር እንድንሆን ነው?
ጌታ ማስተዋሉን ይስጠን።
ተባረኩ በ ጌታ አወዳችሁዋልሁ ውድማችሁ ነኝ

Unknown said...

thank u dejeselam

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)