August 8, 2010

የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የቀብር ሥነ ሥርዐት ሰኞ ይፈጸማል


(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 8/2010)፦ በትላንት ዕለት በድንገተኛ ሕመም ሕይወታቸው ያለፈው የመጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የቀብር ሥነ ሥርዐት ሰኞ፣ ነሐሴ ሦስት ቀን 2002 ዓ.ም በስምንት ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡

በትላንትናው ዕለት ረፋድ ላይ ለእርቅ እና ድርድር ጉባኤ የሄዱበትን የአሜሪካ ተልእኮ አጠናቀው አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ እንደ ደረሱ ራሳቸውን የማቃጠል እና ልባቸውን የመውጋት ስሜት እንደተሰማቸው አብረዋቸው ለተጓዙት የልኡካን ቡድኑ አባላት የተናገሩት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ፣ አስቸኳይ ሕክምና ሊያገኙ ይችሉ ከነበረበት ስፍራ ርቆ እና ከጊዜው ዘግይቶ አራት ኪሎ አካባቢ ቀድሞ ‹‹ጉድሸፐርድ›› አሁን ‹‹አዲስ የሕፃናት እና እናቶች ሆስፒታል›› በሚባለው የሕክምና ተቋም ውስጥ የመጀመርያ ደረጃ ምርመራ እየተደረገላቸው ሳለ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ ወዲያኑ አስከሬናቸው በቅዱስ ገብርኤል እና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች ከፍተኛ ምርመራ ከተካሄደለት በኋላ ዛሬ ቀትር ላይ ሰበካቸው በሚገኝበት እና በአገልግሎት ብዙ በደከሙበት በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡

የመጋቤ ብሉይ ሰይፈን ድንገተኛ ሞት በመስማት ለሱባኤው እና ለግል ጤንነታቸው ካለው ወቅታዊ ተስማሚነት ጋራ በተያያዘ ከሄዱበት ድሬዳዋ በትላንትናው ዕለት የተመለሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ማምሻውን በመጋቤ ብሉይ መኖርያ ቤት ተገኝተው ቤተሰቡን በአባታዊ ቃል አጽናንተዋል፡፡ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ከቤተሰቡ አባላት ጋራ በተደረገ ምክክር የቀብር ሥነ ሥርዐቱ በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲፈጸም ፍላጎቱ የነበረ ቢኾንም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ቀርቧል በተባለው ሐሳብ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡

ዛሬ ከቀትር በኋላ አስከሬኑ ባረፈበት በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ጸሎተ ፍትሐት የተደረሰ ሲኾን በነገው ዕለት ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተጓጉዞ በዚያም ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ ቅዳሴ ከተደረሰ በኋላ ከስምንት ሰዓት ጀምሮ የቀብር ሥነ ሥርዐቱ እንደሚከናወን ተገልጧል፡፡

በተያያዘ ዜና መጋቤ ብሉይ ሰይፈ በእርቅ እና ድርድር ጉባኤው ላይ በሚሳተፈው የልኡካን ቡድን ውስጥ እንዳይካተቱ እና በቅድመ ጉባኤ ውይይቱ ወቅትም ከድርድሩ እንዲወጡ በስደት የሚገኘው ወገን ጫና ከመፍጠሩ አስቀድሞ የልኡካን ቡድኑ አባል ኾነው ለመሄድ ፍላጎቱ እንዳልነበራቸው ለቤተሰቦቻቸው እና ለፓትርያሪኩ ተናግረው እንደ ነበር ተሰምቷል፡፡ የልኡካን ቡድኑ ከአገር ቤት ከመነሣቱ አስቀድሞ የስደተኛው ወገን ዒላማ መኾናቸውን ያልወደዱት መጋቤ ብሉይ፣ ‹‹እኔ ባልሄድ፣ ቢቀርብኝ፤ ሌላ ሰው ይተካ›› በማለት በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም በአቡነ ጳውሎስ ጫና ለመሄድ እንደ ተገደዱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በድርድሩ ስፍራም በተለይ በስደት ከሚገኙት ተወያዮች አንዱ ከኾኑት አቡነ መልከ ጼዴቅ ጋራ ከፍተኛ አተካራ ውስጥ መግባታቸው ተገልጧል፡፡ ኹኔታው በመጋቤ ብሉይ ልቡና ላይ ከፍተኛ ኀዘኔታ እና ጭንቀት እንደፈጠረ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን ነው የጉዳዩ ታዛቢዎች የሚገልጹት፡፡ እኒሁ ታዛቢዎች አክለውም በርግጥም ውይይቱ እንዲሳካ ልባዊ ፍላጎቱ ከነበረ እንዲህ ያሉትን መለስተኛ ችግሮች ቀድሞ መቅረፍ ይቻል እንደ ነበር እና ይህ ዐይነቱ ውዝግብ አስቀድሞም ውይይቱ እንዳይሳካ ሥር የሰደደ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ሤራ ሊኾን እንደሚችል ሁለቱንም ወገኖች በመውቀስ ይናገራሉ፡፡

ለቀብር ሥነ ሥርዐቱ የተሰናዳውን የመጋቤ ብሉይ ሰይፈን ዜና ሕይወት እና ሥራ እንደደረሰን የምናቀርብ መኾኑን እየገለጽን አምላከ ቅዱሳን ለመጋቤ ብሉይ ዕረፍተ ነፍስን ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን፡፡

5 comments:

Anonymous said...

"Blessed are the peacemakers, for they shall be called sons of God." Matthew 5:9
Being the source of peace, Our Lord Jesus Christ found no price sufficient for peace other than shedding His own blood.
In doing so, Our Lord Jesus Christ reveals Himself to us as the reconciler, the Prince of Peace. Isaiah 9:6, Ephesians 2:14-19
The Holy Spirit gives peace to those who imitate Our Lord Jesus Christ.
Thus, peacemakers share God's peace with those around them, imitating Our Lord Jesus Christ sacrificial love and participating in His work. By God's grace, peacemakers become sons of God themselves.
May God rest the soul of our Father Seyfe Silasie, the real peacemaker.

ኢትዮጵያ said...

+++
እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸዉን በአብርሐም፣ በይስሐቅ፣ በያዕቆብ አጠገብ ያኑርልን አሜን።

ከብሪታኒያ

selamawi said...

ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል።
መዝ 144፥4

አይ የሰው ነገር በጣም ያሳዝናል አለ ሲሉት የለም

ነፍሳቸውን ይማር ሌላ ምን ማለት ይቻላል

Anonymous said...

yemigermew neger gin patriyarku leEgnih shinTachewun letekerakerulachew abat qebir keDiredewa dires simeTu le enie talaq PaPas Abune Melke tsedeq gin fitachewun mazorachew new::
Yigermal... patriarku bete krstianitun yemimerut beSinodos endalhone ena lela dibiq "sinodos" endalachew megemet ayikebdim::

Libuna yisTachew::

Anonymous said...

መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ አዋቂ እና የተማሩ ሲሆኑ
ራሳቸውን ትሑት አድርገው ታዛዥ ሆነው ከሰው ጋር ክፉ ነገር ሳይነጋገሩ
ሰው ሳያስቀይሙ ወደመጨረሻው ዓለም ሄዱ ምን ሊባል ይችላል ነፍሳቸውን
ከቅዱሳኑ ጎን ያሳርፍልን እንደሳቸው ያለ ሊቅ ቤተ ክርስቲያኗ ስታጣ ቀላል ጉዳት
አይደለም “የጨው ካብ ሲናድ ያወቀ አለቀሰ ያላወቀ ላሰ” እንደሚባለው ለሚገባው ጉዳቱ
ቀላል አይደለም እግዚአብሔር ሰው ይፍጠር ፡፡

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)