August 7, 2010

መግለጫዎቹ መግጫ፣ መገጫ፣ መገጫጫ ባይሆኑ


(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 6/2010):- እነሆ አባቶችን ለማስታረቅ የተደረገው ሙከራ የተፈለገውን ያህል ሳይራመድ መቅረቱን ስንዘግብ ቆይተናል፤ አሁን ደግሞ አሸማጋዩ ክፍል “መግለጫ”ውን አውጥቶ የሄደበትን ሒደት እና የደረሰበትን፣ እንዲሁም ድርድሩ የፈረሰበትን ምክንያት ነግሮናል። ከዚህኛው ጋር በድምሩ ሦስት መግለጫ አንብበናል ማለት ነው። ነገ ደግሞ ሌላ መግለጫ ሊመጣ፣ ለዚያ መልስ የሚሰጥ ሌላ መግለጫ እንዳይወጣ፣ ያንን የሚያስተባብል ሌላ መግለጫ እንዳይከተል እና መግለጫዎቹ መግለጫነታቸው ተረስቶ “መግጫ፣ መገጫ እና መገጫጫ” እንዳይሆኑ ከወዲሁ ለመጠቆም ወደድን።

መግለጫ 1፦ የአሜሪካ አባቶች መግለጫ (http://eotcholysynod.org/synod/PressRelease082010.pdf)
በዚህ መግለጫ በዋነኝነት ድርድሩን ያፈረሱበትን ምክንያት ዘርዝረዋል። ለዚህም በምክንያትነት ያቀረቡት “አንድ ግለሰብ” መሆኑን ሲሆን ያ አንድ ግለሰብ “መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ” መሆናቸውን፤ “ጥፋታቸውም” በሬዲዮ የሰጡት ቃለ ምልልስ መሆኑን ተረድተናል። ይኸው የድምጽ ቅጂ ከዝግጅት ክፍላችን ስለደረሰ እንደ አስፈላጊነቱ እናቀርበዋለን። እዚህ ላይ ልንጠይቀው የምንፈልገው አንድ ጥያቄ ግን “መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ምንም ይበሉ ምን ቅ/ሲኖዶስን ወክለው እስከተገኙ ድረስ መቀበል አይገባም ነበር?” የሚል ይሆናል።

መግለጫ 2፦ ከአዲስ አበባ የመጣው ልዑክ መግለጫ (http://www.eotcdc.org/)
ይህ መግለጫ የአሁኑ ድርድር የፈረሰበትን ምክንያት ለማስረዳት ከመሞከሩም በላይ ቀድሞውኑ ይህ መለያየት የተፈጠረበት ታሪካዊ ዳራ እና ምክንያት ለማብራራት ጊዜ ወስዷል። 
  • አራተኛው ፓትርያርክ እንዴት እንደወረዱና በወቅቱም አሁን የተለዩት አባቶች እንደተስማሙ፤ 
  • አሁን የተለዩት አባቶች የተቆጩት በ4ኛው ፓትርያርክ መውረድ ሳይሆን እነርሱ ቦታውን ባለመያዛቸው እንደሆነ፤ 
  • ይህም ባለመሳካቱ ቀኖና ጥሰው አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን እንደሾሙ፤ 
  • እነዚህ አባቶች ሕዝቡን ለማቃቃር “በፖለቲካ ዓለም እየገቡ የተሸከሙትን የቤተ ክርስቲያን ክቡር ሥልጣን” ማዋረዳቸውን፤ 
  • ይህንን ልዩነት ለመፍታት ቤተ ክርስቲያን ብዙ እንደደከመች፤ 
  • አሁን የተጀመረው ጥረት በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ሞት ማግስት የተጀመረ እንደነበረ፤  
  • በሰሜን አሜሪካ የሚገኙት አባቶች የሚፈጥሩት የሰላም እንቅፋት ብዙ መሆኑን ወዘተ አትተዋል። 
በየመካከሉም መብራራት የሚገባቸው ሌሎች ጥያቄዎች አጭሮ አልፏል። ለምሳሌ በዚሁ መግለጫ ገጽ 3 ሁለተኛው አንቀጽ ላይ በውጪ የሚገኙት አባቶች ሕዝቡን ለማቃቃር “በፖለቲካ ዓለም እየገቡ የተሸከሙትን የቤተ ክርስቲያን ክቡር ሥልጣን” ማዋረዳቸውን አትተዋል። ትክክል ነው። ይሁን እንጂ በዚህ የፖለቲካ አባዜ ተጠምደው ቤተ ክርስቲያኒቱን በማስደፈር በኩል አዲስ አበባ ያሉት አባቶች እኩል ተጠያቂዎች ናቸው። ልዩነቱ ሰሜን አሜሪካ ያሉት የተቃዋሚዎች ፖለቲካ አራማጅ መሆናቸው፤ አገር ቤት ያሉት ደግሞ የኢሕአዴግ ፖለቲካ ደጋፊና አራማጆች መሆናቸው ብቻ ነው። ዋናው ቁም ነገር እርሱ አይደለም። ለዚህ ለዚህማ ሁለቱንም ክፍል የምንጠይቅበት ዘመን ይመጣ ይሆናል። ይህ መግለጫ በመጨረሻ የቤተ ክርስቲያን የሰላም በር አለመዘጋቱን በማስረዳት ይፈጽማል። ይህ ጥሩ ማጠቃለያ ነው። ለሰላም የሚዘጋ ምንም በር መኖር የለበትም። ለሰላም ምንም ቅድመ ሁኔታ እና ጊዜ ገደብ መኖርም የለበትም። ያውም ለቤተ ክርስቲያን ሰላም።

መግለጫ 3፦ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባዔ መግለጫ”
(http://www.dejeselam.org/2010/08/blog-post_06.html)
መግለጫው ባለ 3 ገጽ ሲሆን ጉባዔው የሄደበትን ሒደት በአጭሩ ከዘረዘረ በኋላ የአሁኑ ሙከራ ያልተሳካበትን ምክንያት ያብራራል። ሙከራ ያልተሳካበት ምክንያትንም ሲያትት በአሜሪካ አባቶች መግለጫ በተጠቀሰው ይስማማና የአዲስ አበባው ክፍል ይህንን ጉዳይ ቀድሞ ቢያውቅም መፍትሔ ፈልጎ አለመምጣቱን ያትታል። ልዑካኑን “ፊት ለፊት ቀርቦ ለማነጋገር ያላስቻለው ዕንቅፋት … ከአዲስ አበባ ከተመደቡት ልዑካን መካከል በአንዱ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ” መነሣቱ መሆኑን፣ “የሰላም ጉባኤውም ከልዑካኑ መካከል እንዳይሆኑ በደብዳቤም ሆነ በስልክ ያደረገው ጥረት" እንዳልተሳካ ይገልጻል። ይህ መግለጫ የአሸማጋዮችን ስምና ማንነት፣ አስታራቂዎቹ እነማን እንደነበሩ ሳያስረዳን አልፏል። አሁንም በደፈናው “ሽማግሌዎች” እንላቸዋለን እንጂ ማንነታቸውን አልገለፁም። ይህንን የሚያክል ታላቅ ተግባር አሁንም ተደብቀውና ደብቀው መሥራት የመረጡ ይመስላሉ። ወይም ስማቸው ቢታወቅ “እንዴ? እነርሱ ናቸው እንዴ?” እንዳይባሉ የፈሩ ይመስላሉ።

መግለጫዎቹ ሲገጫጩ
አሁን እንደሚባለው ሁሉም ቡድን በየትኛውም መግለጫ አልተደሰተም። ከተሠራው ሥራ ይልቅ ለመግለጫዎቹ ትልቅ ትኩረት የሰጠ ይመስላል። ሁሉም ጣቱን ለመጠቆምና ራሱን ለማዳን የሚሞክርም ይመስላል። እርቁ ተጀመረ እንጂ አልተፈጸመም። በአንድ ዙር ይፈጸማል ተብሎም አልተጠበቀም። ለሚቀጥለው ሥራ እንቅፋት ላለማስቀመጥ ግን ቢሞክር ጥሩ ነው። በመግለጫ ጋጋታ መገጫጨቱ ምንም አይፈይድም። ያለፈው አለፈ። እስቲ በተሻለ ጥራት ለመሥራት ቢሞክር። ለዚህም ከሽማግሌዎቹ ይጀመር። ከማጀት ወደ አደባባይ ውጡ። እንወቃችሁ። ሕዝብ የማይፈልጋቸው ካሉ መንገዱን ለሚታመኑ ሰዎች ይልቀቁ። ራሳቸው ሳይታረቁ ማስታረቅ የሚፈልጉም ካሉ በመጀመሪያ ይስተካከሉ። ሦስት ወይም አራት ወር ብዙ አይደለም። ትንሽም አይደለም። አስታራቂዎቹ አሁን በገጠማቸው ነገር ተስፋ ሳይቆርጡ ሥራውን ይቀጥሉ። ይህንንም ቢሆን ያደረጉት እነርሱ ናቸው። ሌላው ቁጭ ብሎ ድንጋይ ያቀብል የለ? እንደ እብድ ገላጋይ! ስለዚህ የተጀመረው ይጠናከር። የተበላሸው ይስተካከል። ሽማግሌዎቹ ሸምግለው ይሸምግሉ። ታርቀው ያስታርቁ።

የሰላም አምላክ ሰላሙን ይስጠን፣
አሜን

4 comments:

Anonymous said...

LEMEHONU SHMAGLEWOCH ENEMAN NACHW ??

Anonymous said...

የሽማግሌዎቹ መግለጫ የተላለፈው በምንድነው? እንደሁለቱ መግለጫዎች አግኝተን ብናነበው ጥሩ ስለሆነ ቢነገረን።

Anonymous said...

Last Anonym,
Here is the meglecha.
http://www.dejeselam.org/2010/08/blog-post_06.html

ኢትዮጵያ said...

ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንጸልይ! መልካም ሱባዔ።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)