August 2, 2010

የሐዋሳ ከተማ ምእመናን ተወካዮች ከፓትርያርኩ ጋራ ተወያዩ

  • የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ ተጠየቀ፤
  • ችግሩን አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወሰነ፤
  • ‹‹ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ኀበ ሐዋሳ ንሐውር፤. . . የሐዋሳን ሕዝብ  ከመውደዴ የተነሣ እኔ ራሴን የአጣሪ ኮሚቴው አባል ባደርግ ደስ ይለኝ ነበር፤›› (አቡነ ጳውሎስ)
  •  ‹‹ምእመኑ ቤተ ክርስቲያን ተሳልሞ ከመመለስ ውጭ የሚያገባው ጉዳይ የለም፤ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሕገጋት የማወጣም ኾነ የምሽር እኔ ነኝ፤›› (አቡነ ፋኑኤል) 
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 2/2010)፦ በሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ ያለአግባብ በመነሣታቸው እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ የሚፈጸመው አስተዳደራዊ በደል እና ሙስና እየተባባሰ በመሄዱ ሳቢያ አፋጣኝ ፍትሕ እንዲሰጣቸው አቤቱታ ያቀረቡት የሐዋሳ ከተማ ምእመናን ተወካዮች ከፓትርያርኩ ጋራ ባደረጉት ውይይት ችግሩን አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ስምምነት ላይ የተደረሰ መኾኑን የስብሰባው ምንጮች ገለጹ፡፡
ሐምሌ 22 ቀን 2002 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በተደረገው በዚሁ ውይይት የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሰበካ ጉባኤ እና ልማት ኮሚቴ አባላት የኾኑት የምእመናኑ ተወካዮች በጽሑፍ ያዘጋጁትን ባለ አምስት ገጽ አቤቱታ በንባብ እንዲሁም በጽሑፍ ያልተካተተውን በቃል አቅርበዋል፡፡ ፍትሕ ፈላጊ እና የልማት አጋር መኾናቸውን የገለጹት ተወካዮቹ በአቤቱታቸው፣ ላለፉት አራት ዓመታት እና ከዚያም በላይ ለኾነ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና በተባባሪዎቻቸው የሚፈጸመው ከፍተኛ የኾነ አስተዳደራዊ በደል እና የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ምዝበራ ሥር መስደዱን እና አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን በመግለጽ የምእመናኑን ልብ በኀዘን እያደሙ ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ፀሐይ መልአኩ ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ ጠይቀዋል፤ የተፈጠረውን ችግር በጥሞና መርምሮ እና አጢኖ ምእመኑን ከማረጋጋት ይልቅ፣ ‹‹ምእመኑ ቤተ ክርስቲያን ተሳልሞ ከመመለስ ውጭ የሚያገባው ጉዳይ የለም፤ የቅዱስ ሲኖዶሱን ሕገጋት የማወጣም ኾነ የምሽር እኔ ነኝ፤. . .ሦስት አውቶብስ ሙሉ ሕዝብ የአራት ኪሎን ዝናም እና ፀሐይ ጠጥቶ ሲመለስ እኔ እዚህ ከቅዱስነታቸው ጋራ በስልክ እነጋገር ነበር፤ ቅዱስነታቸው ከእኔ የሚነገራቸውን ተቀብለው ከመወሰን በቀር 300 ሰው የሚሰሙበት ጊዜ የላቸውም፤›› በማለት ለምእመኑ ያላቸውን ንቀት እና አነስተኛ አባታዊ ክብር በተደጋጋሚ ባሳዩት፣ ‹‹የልማት አባት›› በመባል የሚታወቁትን የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ ዋሕድ ወልደ ሳሙኤልን ያለጥፋታቸው ከሐላፊነታቸው እንዲነሡ ባደረጉት በአቡነ ፋኑኤል ላይም ተወካዮቹ የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል፡፡
በጽሑፍ ከቀረበው እና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ለልዩ ልዩ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታዊ አካላት ግልባጭ ከተደረገው የምእመናኑ አቤቱታ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በመኖርያ ቤት ውድነት በምትታወቀው ሐዋሳ ከአንድም ሁለት የመኖርያ ቤቶችን ሠርተዋል፤ ግልጽነት በጎደለው አኳኋን ልጆቻቸውን በሀገረ ስብከቱ የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ አስቀጥረዋል፤ የቅዱስ ሩፋኤልን ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን፣ ‹‹ስለ ገንዘብ እና ጉልበት አስተዋፅኦ እንጂ ስለ አስተዳደሩ አያገባችኹም፤›› በማለት የግለሰቦች መጠቀሚያ አድርገውታል፤ በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ያለሰበካ ጉባኤው ዕውቅና ንብረቱ እንዲሸጥ ወስነዋል፤ ከሰበካ ጉባኤው ዕውቅና ውጭ ቅጥር በመፈጸም ካህናቱን፣ ‹‹የቀጠርኳችኹ እኔ ነኝ፤ ላነሣችኹም ሥልጣን አለኝ፤›› እያሉ ተጽዕኖ ያደርጋሉ፤ የደብር አስተዳዳሪዎችን በሐሰተኛ መረጃ በመክሰስ ያስፈራራሉ፤ የሥራ ሞራላቸውን ይጎዳሉ፤ ግራ ያጋባሉ፤ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በቃለ ዐዋዲው መሠረት እና በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጡትን የሰንበት ት/ቤቱን አመራሮች በመበተን፣ ከዓላማ እና የጥቅም አጋሮቻቸው ጋራ የሰንበት ት/ቤቱን ቁልፍ በመሮ ሰርስሮ በመሥበር እና በሌላ ቁልፍ በመቀየር ቀደም ሲል ከሰንበት ት/ቤቱ የታገዱ ሰዎችን አስገብተው እንዲተኩ አድርገዋል፤ አቤቱታ ያቀረቡ የምእመናን ተወካዮችን ‹‹ፀረ ሰላም፣ የዐመፅ እና የሽብር ኀይሎች ናቸው፤›› በማለት በአደባባይ ወንጅለዋል፤ በአንጻሩ ቀደም ሲል በነበሩት ሊቀ ጳጳስ እና በራሳቸው በሥራ አስኪያጁ ፊርማ ከአገልግሎት የታገደውን፣ የሐዋሳ ቅድስት ሥላሴን ማኅተም እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ያሉ ግለሰቦችን እና ተቋማትን የሐሰት ማኅተም ተጠቅሞ ገንዘብ በመሰብሰብ ሕገ ወጥ ጉባኤ ለማካሄድ የተንቀሳቀሰውን ራሱን ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ፀረ - ኤድስ ማኅበር›› እያለ የሚጠራውን አካል ተመስጋኝ የልማት ተቋም አድርጎ በማቅረብ ምእመኑ ከእርሳቸው ጋራ እንዳለ ለማስመሰል እና ያደረሱትን አስተዳደራዊ በደል ለመሸፈን ተንቀሳቅሰዋል፡፡
የምእመናኑ ተወካዮች በአቤቱታቸው መጨረሻ የሀገረ ስብከቱን ችግር ለዘለቄታው የሚያስወግድ፣ ምእመኑን ከእርስ በርስ ግጭት የሚታደግ፣ የግለሰቦች ሳይኾን የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት፣ የልማት እና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚስፋፋበት የመፍትሔ ሐሳብ ቀደም ሲል የሀገረ ስብከቱን ችግር መርምሮ የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተቋቁሞ በተላከው አጣሪ ኮሚቴ አማካይነት በአስቸኳይ ተጥንቶ ለፓትርያርኩ እንዲያቀርብ ይታዘዝ ዘንድ፣ እስከዚያው ድረስ ከቃለ ዐዋዲው ውጭ በከተማው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አዲስ የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ለማካሄድ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና ሥራ አስኪያጅ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም፣ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ አባ ገብረ ዋሕድ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፣ ያጠፉት ነገር ካለም ጉዳዩ ተጣርቶ ውሳኔ እስኪሰጣቸው ድረስ በሐላፊነት እንዲቆዩ፣ የገዳሙን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አስመልክቶ ከመንበረ ጵጵስናው እና ከሀገረ ስብከቱ እየተላለፉ የሚገኙ ውሳኔዎች ለጊዜው በሙሉ እንዲታገዱ፣ ጉዳዩ ተጣርቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ችግሩን የሚያባብስ ማንኛውም ውሳኔ ከማስተላለፍ ይታቀቡ ዘንድ ጥብቅ መመርያ እንዲሰጥ፣ ማንኛውም የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ከገዳሙ ዐውደ ምሕረት ውጭ እንዳይካሄድ እና ሕዝበ ክርስቲያኑ የግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይኾን ጥብቅ መመርያ እንዲተላለፍላቸው ጠይቀዋል፡፡
የምእመናኑ ተወካዮች በጽሑፍ እና በቃል ያቀረቡትን አቤቱታ እና የመፍትሔ ሐሳብ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና ከጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ጋራ ኾነው ያዳመጡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ‹‹...እኔ የሁሉም አባት ነኝ፤ ለማንም አላዳላም፤ እዚህ የተቀመጥኹት የእግዚአብሔር እንደራሴ የሲኖዶሱ ሥራ አስፈጻሚ ኾኜ ነው፤ የሲኖዶሱ የበላይ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ እኔ ደግሞ የሲኖዶሱ ተላላኪ - ሥራ አስፈጻሚ ነኝ፤ እግዚአብሔር ለማንም አያዳላም፤ የእግዚአብሔር እንደራሴ ኾኜ እንደ መቀመጤ እኔም ለማንም አላዳላም፤ የአንድ ወገን ወሬ ብቻ ሰምቼ አልወስንም፤ አሁን የእናንተን ሰምቼ ብወስን ነገ ደግሞ የሌሎቹንም እንዲህ ነው የሚወስነው ብላችኹ ትታዘቡኛላችኹ፤...›› በማለት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሐሳብ እንዲሰጡበት ይጠይቋቸዋል፤ ብፁዕ ሥራ አስኪያጁም ወደ ሐዋሳ አለመሄዳቸውን በመግለጽ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ይታቀባሉ፤ ፓትርያርኩም መልሰው፣ ‹‹አዋሳ ሄደው ማየት ነበረብዎት፤ እንዴት ዐይነት እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ መሰልዎት፤...ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ኀበ ሐዋሳ ንሐውር እንዲሉ ነው፤...አንዳንድ ሰዎች ከተፈጠረው ስሜት አንጻር ‹ወደ አዋሳ እንዳትሄድ› ብለው አሳስበውኝ ነበር፤ እኔ አንድ መነኩሴ ነኝ፤ የመጣው ይምጣ ብዬ ነው የሄድኹት፤ እንግዲህ እናንተም ይህ ሁሉ በደል ደርሶባችኹ እያለ አባትነቴን አክብራችኹ ምንም ሳትሉ ችግር ሳይፈጠር በመመለሴ የምትመሰገኑ ጨዋዎች ናችኹ፤...›› ማለታቸውን የውውይቱ ደጀ ሰላማውያን አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጋራ ተመሳሳይ ሐሳብ የሰጡት ብፁዕ አቡነ ኤልያስም፣ ‹‹...የቤተ ክርስቲያንን ሰላም አናደፈርስም ብላችኹ ለውይይት መምጣታችኹ የሚያስመሰግናችኹ ነው፤ ልጆች በዚህ መልኩ ከአባት ጋራ መወያየታቸው የሚያስደስት ነው፤...›› ብለዋል፡፡

ከረፋዱ አራት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት በመግባባት መንፈስ እንደ ተካሄደ በተገለጸው በዚሁ ውይይት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በቀረበው አቤቱታ ላይ በአስቸኳይ እንደሚወያዩበት መናገራቸው ተገልጧል፡፡ በምእመናኑ ተወካዮች በኩል ቀድሞ የነበረው አጣሪ ኮሚቴ ተጠናክሮ ሥራውን እንዲቀጥል እና አስቸኳይ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በተሰጠው የመፍትሔ ሐሳብ ላይም ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲኾን አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ሥራ ባይበዛብኝ የአዋሳን ሕዝብ ከመውደዴ የተነሣ እኔ ራሴን የአጣሪው ኮሚቴ አባል ባደርግ ደስ ይለኝ ነበር፤ አትጨነቁ ካስፈለገ [ሥራ አስኪያጁን] ወደ ሌላ ቦታ መቀየር ነው፤›› ማለታቸው ተመልክቷል፡፡
Post a Comment

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)