August 2, 2010

ውይይቱና ሽምግልናው በምን ዙሪያ?

(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 1/2010)፦ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአባቶች የሰላምና የዕርቅ ድርድር በነገው ዕለት ማለትም ሰኞ ኦገስት 2/2010 (ሐምሌ 26/2002 ዓ.ም) ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ከሁለቱም በኩል ያሉ ተወካይ “የሰላም ልዑካን” ዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ተሰባስበዋል። እንደተለመደው ውይይቱ እንደሚደረግ በደፈናው ከመታወቁ ውጪ በምን ዙሪያ፣ እንዴት የሚለው ጉዳይ “በምስጢር” ስለተያዘ ብዙም ለማለት አያስደፍርም። ቤተ ክህነቱን የብልሹ አሠራር ምንጭ ያደረገውና ለዚህ ሁሉ ውድቀት ያበቃን ዋነኛው ምክንያት ነገሮችን ከሚመለከተው አካልና ምእመን ደብቆ የመሥራት አባዜ ስለሆነ ይህ ብልሹ አመለካከት ይሰበር ዘንድ ዝምታው ይሰበር፣ መጋረጃው ይቀደድ እንላለን፤ ስለዚህም እንጽፋለን።
የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳ ወደሆነው ጉባዔ ስንመለስ፣ ይህ ጉባዔ ሊነጋገርባቸው/ ሊመለከታቸው ይገባል የምንላቸውን ነጥቦች ለማቅረብ እንወዳለን። እነዚህም፦
·    በነዚህ 18 የልዩነት ዓመታት ውስጥ የተፈጠሩ ስሕተቶች ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዴት ሊታረሙ ይችላሉ?
·    የሁለቱ ፓትርያርኮች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል፣
·    አሜሪካ ባሉት አባቶች ክፍሎች የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ዕጣ ፈንታና ጉዳይ እንዴት ይፈታል?
·    ከልዩነቱ በኋላ የተሠሩ ሥራዎች፣ የተደነገጉ ድንጋጌዎች ወዘተ እንዴት ይስተካከላሉ?
·    በሁለቱም በኩል የተላለፉ ውግዘቶች እንዴት ይታያሉ፣ ይፈታሉ?
·    ዕርቁ የጳጳሳት ብቻ እንዳይሆን፣ በእነርሱ ምክንያት የተለያዩት (በልዩነቱ ውስጥ ተዋናይ የነበሩ) የተለያዩ አካላት ዕጣ ፈንታስ?
·    ውይይቱና እርቁ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ምን ማድረግ ይገባል?
·    እርቁ ከተፈጸመም በኋላ ቢሆን ስምምነቱ ሊመጣበት ከሚችለው ተቃውሞ (ካለ) በተለይም ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ዘዋሪዎች (አሽከርካሪዎች) ከሆኑት (በሀገር ቤት ከኢህአዴግ፣ በውጪ ደግሞ ከተቃዋሚዎች) ተጽዕኖ እንዴት ነጻ ማድረግ ይቻላል?

 የሚሉት እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው። 

የአባቶች ሽምግልና እና እርቅ ከየት ይነሣ፣ የት ይድረስ?

(ደጀ ሰላም፣ ጁን 26/2010)፦ በግንቦቱ የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ እንደተገለፀው ከአምስተኛው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሲመት ማግስት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተነሣውን መከፋፈል ለማቆምና በአባቶች መካከልም የተፈጠረውን እስከ መወጋገዝ የሚያደርስ ልዩነት በእርቅ ለመጨረስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ይኸው ከአበው ካህናት፣ ከምእመናንና ከታዋቂ ግለሰቦች በአባልነት የተውጣጡ ሰዎች የሚሳተፉበት ነው የተባለው አንቀሳቃሽ ቡድን በግንቦት ወር ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት (አዲስ አበባ) እንዲሁም ወደ ኒውዮርክ ልዑካንን በመላክ እርቁ እንዲጀመር አግባብቷል።


በዚህም ከሁለቱም በኩል ቀና ምላሽ አግኝቷል። ቀጣዩ ሁለቱንም ወገኖች ፊት-ለፊት፣ መሳ-ለመሳ ማገናኘትና ማወያየት ይሆናል። ሁሉ ነገር ምሥጢር፣ ሁሉ ነገር ከመጋረጃ ጀርባ ተጀምሮ ከመጋረጃ ጀርባ በሚያልቅበት “የምሥጢር ማኅበረሰብ” መካከል ስለምንኖር ልናውቀው የሚገባንን ሳናውቅ፣ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣበት የሚገባው ነገር ላይ ምንም ሳናከናውን ጊዜው እንዳያልፍ ግን አስግቶናል። ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረጉ ቲያትሮች ታዲያ ጦሳቸው ጥንቡሳታቸው ዘግይቶ ይደርሰንና “ለምን የመጣ ለምን ይተርፋል” ይሆናል። በፖለቲካችንም፣ በቤተ ክህነታችንም፣ በሃይማኖታችንም ሁሉ ከጀርባ እያለቀ የሚመጣው ነገር አገሪቱንም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱንም ሲያምሳት እነሆ የአንድ ሰው ዕድሜ በላይ ሆኖናል። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና “የእርቁ ነገር” ላይ ለመወያየት እንሞክር።

ጥንተ ታሪክ

ኢሕአዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት “ከደርግ ጋር አብረዋል” ያላቸውን አራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን “እንደማንኛውም ደርግ/ ደርጌ” በመቁጠር አብሯቸው ሊሠራ እንደማይችል በወቅቱ አዛዥ ናዛዥ በነበሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ በኩል ግልጽ አደረገ። እርሳቸውን ከስልጣን ለማውረድ ከቤተ ክህነቱም ከቤተ መንግሥቱም ስምምነት ላይ ተደረሰ። እርሳቸው ፓትርያርኩም አልተቃወሙም። ጥያቄው ከወረዱ በኋላ ስለሚኖሩት የኑሮ ዓይነት ነበር። በምትካቸውም አፈር ይቅለላቸውና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ አቃቤ መንበር (መንበር/ ወንበር/ ዙፋን ጠባቂ) ሆነው ተሾሙ። ከዚያም ጊዜውን ጠብቆ አዲስ ፓትርያርክ እንዲመረጥ ተወሰነ። ለእጩነት የቀረቡት ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ተመረጡ እና አምስተኛው ፓትርያርክ ሆኑ። በወቅቱ “ብፌ እንኳን ለማንሳት ዕውቀት ያልነበራቸው አባቶች አልፈው እንግሊዝኛ ተናጋሪ፣ ዶክተር፣ ዓለምን ጠንቅቆ ያወቀ አባት ተገኘ” ተባለና ሁሉም አባት ደስ አለው። “ይደልዎ”!!! እያለ በቪዲዮ ተቀረፀ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ በኬንያም፣ በባሌም፣ በቦሌም ወደ አሜሪካ መጡ እና “ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ” ተመሠረተ ተባለ። አራተኛውም ፓትርያርክ ተቀላቀሏቸው”። ከዚያም “ስደተኞቹ አባቶች” የዚህኛው ቡድን ፖለቲካ አቀንቃኝ፣ አምስተኛው ፓትርያርክ ደግሞ አዲስ አበባ ተቀምጠው የሚኒሊክ ቤተ መንግሥትን የተቆጣጠረው ቡድን አቀንቃኝ ሆነው በሬዲዮም፣ በጋዜጣም፣ በእንቁላልም ሲደባበደቡ 20 ዓመት ሊሞላ አንድ ፈሪ (ማለትም 19 ዓመት) ሆነው።

ዛሬ አሜሪካ የተሰበሰቡት ስዱዳን አባቶች ቅ/ሲኖዶሱን ጥለው ከወጡ ጀምሮ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሰሞን አንገታቸውን ደፍተው በትህትና ሲመላለሱ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ አንገታቸው ቀና አደረጉና ሌሎችን አንገት አስደፉ። ስደተኞቹ ከአሜሪካ እንቁላላቸውን በወረወሩ መጠን አቡነ ጳውሎስም ከመንገዳቸው ወደ ኋላ ከመመለስ ይልቅ የበለጠ ገፉበት። ከዚያም በውጪ ያሉት አባቶች “ጳጳሳት ሾምን” ብለው የበለጠ ልዩነቱን አስፍተው ቀኖና እስከመጣስ ድረስ ሄዱ። ከዚያም ውግዘት ተከተለ እና አራተኛው ፓትርያርክ እና አብረዋቸው ያሉት አባቶች በሙሉ በየስማቸው ተወገዙ። እነርሱም በፈንታቸው ሌላውን አወገዙ። እንዲህ እንዲህ ቆይቶ አሁን የእርቅ ዜና ተሰማ። ተመስገን። ነገር ግን እርቁ በየትኛው ላይ ይሆን? ውይይቱና ሽምግልናውስ እስከምን ድረስ?

ለእርቅና ለሽምግልና የሚያስፈልጉ አራት ነጥቦች

 
ይህንን የመሰሉ አገራዊ አጀንዳዎችን ይዞ የሚነሣ አካል ሊያውቃቸው የሚገባ አራት ነጥቦች አሉ። የመጀመሪያው አብረውት የሚሠሩ የቴክኒክ እና የምክር ኮሚቴዎች ሊኖሩት እንደሚገባ ነው። አንድ ሰው ተሰሚነት ያለው ሰው በመሆኑ ብቻ ሽማግሌ ይሆናል፣ ለማስታረቅ የሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ፣ ታሪካዊ እና ንግግራዊ ክህሎቶች አሉት ማለት አይደለም። የሁለቱን ወገኖች ታሪካዊ ሽግግር፣ የልዩነት ምክንያቶች፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (ልምድ)፣ ከዚህ በፊት የነበሩ የእርቅ-ድርድሮች ሊከሽፉ/ሊሳኩ የቻሉበት ምክንያት፣ የታራቂዎቹ ጠባይ ወዘተ የሚለውን የሚያጠና፣ ስልት የሚጠቁም እና ሙያዊ እገዛ የሚያደርግ አካል ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ታራቂዎቹ የሃይማኖት ሰዎች ሆነው አስታራቂዎቹ ግን የሃይማኖቱን ቀኖና እና መሠረተ ሐሳብ ያልተረዱ አልያም ታራቂዎቹ ፖለቲከኞች ሆነው አስታራቂዎቹ የፖለቲካን አካሄድ ጭራሽ ያልተረዱ ከሆኑ እርቁ በደፈናው “አንተም ተው፣ አንተም ተው” ዓይነት ይሆናል። በዚህ ጊዜ አካሄዶችን አጥንተው መንገድ የሚያሳዩ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ።

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ የሕዝብ ይሁንታ ነው። አገራዊ የሆኑ እርቆች ሲደረጉ ሕዝቡ ስለጉዳዩ ሐሳብ እየሰጠ፣ አቅጣጫ እየጠቆመ. ከመነሻው ይሁንታውን እየሰጠ መሆን አለበት። የሕዝብ ጉዳይ ለሕዝብ ዱብ ዕዳ መሆን የለበትም። እንዲህ ዓይነቱ ዱብ ዕዳ ሲከሰት ሕዝቡ ስለ እርቁ የራሱን ምክንያት እና አንድምታ ይሰጥና ከእርቁ መንፈስ ይወጣል። የሰዎቹን እርቅ ቅቡልነት (ተቀባይ መሆን) ጥርጣሬ ላይ ይጥለዋል። በርግጥ በእርቁ ሒደት ምስጢራዊ ሊሆኑ የሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች ይኖራሉ። ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር ምስጢራዊ ይሆናል ማለት አይደለም። ልዑል እግዚአብሔር እንኳን ከሰዎች ልጆች ጋር እርቅን ሲመሰርት መንገዱን፣ አመጣጡን፣ አሠራሩን ከመጀመሪያው ጀምሮ ሱባዔ አስቆጥሮ እና በኦሪት እና በነቢያት አናግሮ ነው። መቼ ከዚ ምስጢር (ከምስጢረ ሥጋዌ) የበለጠ ምንም ምስጢር የለም።

ሦስተኛው ነጥብ ደግሞ የሽማግሌዎቹ ለእርቁ ተገቢ መሆን እና በሰዎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ነው። ሽምግልናው ተቀባይነት የሚኖረው ሕዝቡ ሲቀበለው፣ ሽምግልናው ውጤት ሲያመጣ እና ለሌሎችም ምሳሌ መሆን ሲችል ነውና ይህንን ለማድረግ አደራዳሪዎቹ ራሳቸው በሌላው ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፣ ወገንተኝነት ያላጠቃቸው መሆን አለባቸው። አሁን በተጀመረው ሽምግልና ማን ሽማግሌ እንደሆነ፣ ሽማግሌዎቹ በምን መመዘኛ እንደተመረጡ፣ ዓላማቸው ምን እንደሆነ በትክክል ለሕዝብ አልተገለጸም። ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ ጥያቄ ማስነሣቱ አይቀርም። ነገሩ የሃይማኖት መሆኑን ስናውቅ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

የተሸምጋዮቹ ሽምግልናውን እና የእርቅ ጥያቄውን መቀበላቸው ብቻ ጅምሩን የተሳካ አያደርገውም። ለምሳሌ የቀድሞ የቅንጅት አመራሮችን የተፈቱበትን ሒደት እንመልከት። በሽማግሌዎቹ አማካይነት የታሠሩት ተፈቱ ተባለ። ይህ መልካም ነው። የሽምግልናው ሒደት ግን ምስጢራዊነቱ እጅግ የበዛ እና ሽማግሌዎቹ እንዴት ሊሸመግሉ እንደበቁ ባለመገለጡ ውጤቱ እስካሁን በሕዝቡ ዘንድ ጥያቄ እንዳስነሣ ነው። እንኳን ሕዝቡ ራሳቸው ተሸምጋዮቹ ጥያቄ የሚያነሡበት ሒደት ሆኗል።

አራተኛው ነጥብ የሽምግልናው ግብ በግልጽ መቀመጥ መቻሉ ነው። ሽማግሌዎቹ ዓላማቸው ምንድርነው? የሚጠብቁት ውጤትስ ምንድርነው? ሽምግልናው ተሳካ/አልተሳካም የሚሉት የት ጋር ሲደርሱ ነው? እነዚህ እና እነዚህን መሰል ጥያቄዎች በግልጽ ተነሥተው በግልጽ መልስ ማግኘት አለባቸው። “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” እንደሚባለው እንዳይሆን።

ከዚህ አንጻር አሁን የተጀመረው መልካም የእርቅ እና የሽምግልና ሒደት ግቡን እንዲመታ የሽማግሌዎቹ ቡድን እነዚህን ጉዳዮች ለመፈተሽ ሃይማኖታዊም፣ ባህላዊም፣ ሞራላዊው ግዴታ አለበትና በዝርዝር ሊመለስበት፣ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠትም ሆነ ሕዝቡን ይወክላሉ የሚባሉ አካላትን በማማከር ገለልተኛነቱን እና ብቃቱን ማሳየት አለበት እንላለን። አለበለዚያ ግን እንደ አልጀርሱ የኢትዮ-ኤርትራ ሽምግልና “ተፈፀመ፣ ታረቁ” የሚለው ፊርማ ሳይደርቅ “አልታረቅንም” የሚል መግለጫ እንደማይወጣ ማስተማመኛ አይኖረንም።

በመጨረሻ
 

ይህንን ሁሉ ማለት የፈለግነው እንዲያው በደፈናው “ጨለምተኞች” (ፔሲሚስት) ስለሆንን፣ ወይም ይህ እርቅ እንዳይሳካ ስለምንፈልግ፣ ወይም እንዲያው ነገር ለማዳመቅ ከመሻት አለመሆኑን ማንም አስተዋይ ልቡና ያለው ሁሉ ይረዳዋል ብለን እንገምታለን። ሽማግሌዎች እና ተደራዳሪዎቹም ጭምር።

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

8 comments:

Anonymous said...

DS,
Good Analysis. Is there any way to deliver this message to the 'Shimagiles'? I think it could be a good input for both sides of 'Shimaglies'.

Chane

Anonymous said...

I don't think DS is ready for peace. You are not worried about theose bishops who are annointed by "gubo" in addis but worried only about those in the usa??????
Don't make laugh.
Don't take side. Peace and love come only when everybody gives up his side and tries to find a common side.

Dan said...

We know the church leaders, both those in Ethiopia and in America, and its administrative structure are dysfunctional and the root cause of the crisis/corruptions/problems.

"የሰላምና የዕርቅ ድርድር" will do no good for the church and the people of God.

Therefore, I suggest, the church should be reorganized if it is to serve the people as a true followers of Christ as:

The synod

The church national assembly

The church national council

The synod as the highest authority of the Ethiopian Orthodox Church made up of archbishops, bishops, and assistant bishops. A standing synod that functions between the sessions of the synod; it includes the patriarch, the archbishops, and the secretary of the synod.

We ought to have a representative central body of the Ethiopian Orthodox Church for all administrative issues as well as for matters that are not dealt with by the synod as the church national assembly.

This national assembly of church, formed by the synod members and three representatives of each diocese or archdiocese (a clergy and two or three lay persons), appointed or chosen by the respective diocesan assemblies.

The third body, The supreme administrative body, both of the synod and of the church national assembly is the church national council, composed of three clergy and six lay persons elected by the church national assembly, as well as of the administrative counselors as permanent members.

The Patriarch is/will be the chair of these bodies of the Church. (hopefully none of the current title "Patriarch" holders. Both should be sent to a monastery to a life of prayers and repentance)

As a starter, as I wrote here some times ago..

አማራጭ የሌለው መፍትሄ 
አሁን ካሉት ጳጳሳት አምስት ወይም አስር የሚሆኑ
በብቃታቸው:ወንጌላውያን 
ለማስተማር የበቁ፥ 
የማይነቀፉ፥ የማይጨቃጨቁ የማይከራከሩ 
ነገር ግን ገር የሆኑ፥፥


ገንዘብን የማይወዱ፥ 
በጭምትነት ሁሉ እየመከሩ በመልካም ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ፤

(ሰው ራሱን መቆጣጠር ማስተዳድር ሳያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያስተዳድራል እንዴት ይጠብቃታል?)

በትዕቢት ያልተነፉ (በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቁ)

በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቁ፥ በቤተ ክርስቲያን ሰዎች በመልካም የሚመሰከርላቸው ።እግዚአብሔርንም መምሰል ታላቅነት ያወቁ ፤ 

በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገውን ክርስቶስን የሚመሰክሩ

ለደሀ ወንጌልን የሚሰብኩ ይለዩልን::እንደነሱ ብቃት ያላቸውን በመልካም የሚመሰከርላቸው (በአሮጌ እርሾ ያልተበከሉትን ) ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጋር ሆነው እየመረጡ 
በየቦታው እየሾሙ ክርስቶስን እንዲመሰክሩ ለደሀ ወንጌልን እንዲሰብኩ ይላኩዋቸው::እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ያለ የበጎች አረኛ እነሱንም በቅድስና የሚመራ ከመካከላቸው በጸሎት ይምረጡ::የቀሩትን ግን ጠብቁ ተብለው የተሰጣቸውን በጎች ግልገሎች የሚበሉ 
ለአውሬ አሳልፈው የሰጡትን ቤተ ክርስቲያን ስብስባ በየገዳማቱ በጸሎት ተወስነው ይቀመጡ:: 
ጌታ አንድም ነፍስ እንድትጠፋ አይፈልግምና::

De. said...

When do we let God does his job?
We have seen that our wisdom did not work and it will never do! Only God can solve this problem.So let us leave it to Him,brothers and sisters.He is God of Truth and Justice and Peace.

Unknown said...

Besemeab wewold wemwnfesekiduse ahadu amlak amain;
Dear brothers and sisters
Yes let us wait and see what is coming from the owner of the church "GOD". Let us not rush to judgment. Let us not prepare a guideline or precondition for our church unity. Don’t you see this problem questioned the unity and oneness of our holy church? (AHATI KIDIST BETEKIRISTIAN) Let us first get a general and umbrella reconciliation among the top leaders and then the rest will follow according to the will of Holy Spirit. I don't see the need of preaching against this reconciliation especially using the name of the EOTC believers like a desperate politician.
As I see it any thing against this peace process is only from the enemy. Dear brothers and sisters in Christ let us pray for good result! Don’t forget that we have high possibility and good hope from God if in case the “Shemaglewochu” have undesired hidden objective (I said so because of some peoples’ negative comments and suspicions); the hope that we all Christians know. We know our God is Almighty. So let us say to Him “Let your will be accomplished”.
Otherwise, what we need to look forward now is to seek for peace through feeling and saying sorry about our previous wrong doing and get a possibility of holding hand in hand all over again throught the world for our common good.

May the owner of our church “GOD” give us his everlasting peace;
Fikeremariam

zekere said...

geta wtetun yasamrew

De. said...

ዘሚኔሶታ
ሰላም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው ጥበበኞች ስንመስል ደንቆሮዎች መሆናችን ታይቷል
ሁሉን ለእግዚአብሔር መተው ይጠበቅብናል እርሱ የሚሰጠው ሰላም እኛ እንደምናስበው ያለ በጠባብ
አእምሮ የተሰላ አይደለም ስለዚህ አንድነትና ሰላም ከፈለግን ዝም ብለን የእርሱን ማዳን እንጠባበቅ

Christian said...

ሁላችን ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች የአባቶች ውይይት ስምምነት ላይ እንዲደርስ በጸሎታችን ወደ እግዚአብሔር እናሳስብ። በመጀመሪያ ግን ይህ ውይይት መካሄዱ በራሱ በጣም ደስ እንዳሰኘኝ ሳልገልጽ አላልፍም። በጣም ጥሩ የሆነ መነሳሳት ነው።
የአባቶች መስማማት የቤተ ክርስቲያን ህልውና እንዲስፋፋ፤ ኢየሱስ እንዲሰበክ፤ አንድነትና ህብረታችን እንዲጠበቅ የሚያደርግ መሆን ይገባዋል። በሁለቱ ወገን ጽንፍ ይዘው የሚያሳድዱና የሚጨቃጨቁ ሰዎችም ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ቆም ብለው ሊያስበቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
በተለይ ወገንተኞች እና በግሩፕ መንቀሳቀስ በቤተ ክርስቲያን ሊቀሩ ከሚገባቸው ነገሮች ስለሆኑ እነዚህ ጉዳዮች ልናስብባቸው የሚገባ ነው። በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነሱ ሓይማኖታዊም ሆነ ቀኖናዊ እንዲሁም አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን በእየጊዜው እየፈታ እንዲሄድ መንፈሰ ጠንካሮች፤ ለክርስቶስ ወንጌል ቅድሚያ የሚሰጡ ፤ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ እንድትመራ ቁርጥ አቋም ያላቸው አባቶችን ወደ አስተዳደር ማምጣት አለባቸው።
ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ።

Blog Archive

የአቡነ ጳውሎስ "ሐውልተ ስምዕ"

ነጻ ፓትርያርክ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ማንን ይመርጡ ነበር? እንበልና ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ የተከናወነ የእጩዎች ምርጫ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የምናነሣቸው ጉድለቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆን የምትመርጡት ማንን ነበር? (ማሳሰቢያ፦ አሁን ያለው ክፍፍል እና የመንግሥት ተጽዕኖ ባይኖር ኖሮ ተብሎ የሚመለስ ጥያቄ ነው። የምን “ባይኖር ኖሮ ነው” የሚል አስተያየት ካለዎትም እናከብራለን።)